Print this page
Saturday, 16 June 2018 13:19

አየርላንዳዊው ደራሲ በ1 አረፍተ ነገር ልቦለድ፣ 100 ሺህ ፓውንድ ተሸለሙ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አየርላንዳዊው ደራሲ ማይክ ማኮርማክ በአይነቱ ባልተለመደውና አንድ አረፍተ ነገር ብቻ ባለው የልቦለድ ስራቸው የዘንድሮው የደብሊን አለማቀፍ የስነጽሁፍ ሽልማት 100 ሺህ ፓውንድ ተሸላሚ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡
ደራሲው በአለማችን እጅግ ከፍተኛውን የስነጽሁፍ የገንዘብ ሽልማት ለሚያስገኘው የደብሊን አለማቀፍ የስነጽሁፍ ሽልማት የበቁት፣ ሶላር ቦንስ የሚል ርዕስ በሰጡትና 270 ገጾች ባሉት የረጅም ልቦለድ መጽሃፋቸው ሲሆን የልቦለዱ ታሪክ ተጀምሮ የሚያበቃው በአንድ እጅግ እጅግ እጅግ እጅግ ረጅም አረፍተ ነገር ብቻ መሆኑንም አይሪሽ ታይምስ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ ይህ የረጅም ልቦለድ መጽሃፍ ከዚህ ቀደምም ጎልድስሚዝ ፕራይዝን ጨምሮ የተለያዩ አገራዊና አለማቀፍ የስነጽሁፍ ሽልማቶችን ማግኘቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ መጽሃፉ በአንባብያንና በሃያሲያን ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን እንዳገኘና መነጋገሪያ ሆኖ መዝለቁን ገልጧል፡፡
ባለፈው ረቡዕ ለተካሄደው የ2018 የደብሊን አለማቀፍ የስነጽሁፍ ሽልማት፣ ከ37 የአለማችን አገራት በድምሩ 150 መጽሃፍት በዕጩነት መቅረባቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ አየርላንዳዊው ደራሲ ማይክ ማክሮማክ ከዚህ በፊትም አምስት ልቦለድ መጽሃፍትን ለንባብ ማብቃታቸውን አስታውሷል፡፡

Read 2363 times
Administrator

Latest from Administrator