Sunday, 17 June 2018 00:00

ኃይሌ ፊዳ በዶክተር አማረ ተግባሩ ዓይን!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

 የስድሳዎቹ የታሪክ መጽሐፍት ደም ያጠቀሱና ፀፀት ያረገዙ ስለሆኑ፣ ለማንበብ በእጅጉ ደንደን ያለ ልብ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ በተለይ ለዓመታት በጨለማ ውስጥ ከማሳለፋችን አንጻር፣ ያንን የወገን ሰቆቃና የስሜት ነበልባል ሙቀት መታከክ በእጅጉ ያምማል። ያ ሕመም ደግሞ ያስቆዝማል፡፡ ያኔ ድልድያችን ባይሰበር፣ ያኔ መንገዳችን ባይፈርስ፣ ዛሬ የገባንበት ማጥ ውስጥ ላንገባ እንችል ነበር የሚል እምነት ይሁን ግምት አለኝ፡፡
ሰሞኑን “ኃይሌ ፊዳ እና የግሌ ትዝታ” የሚለውን መጽሐፍ ለማንበብ ስነሳ፣ ሕመሙንና ቁጭቱን የምችልበት ጎን እንደሚኖረኝ እርግጠኛ ባልሆንም፣ ሰሞኑን ዶክተር ዐቢይ ባስታጠቁኝ ተስፋና መጽናናት ብርሃን ውስጥ ሆኜ አልፈዋለሁ ብዬ ማንበቤን ጀምሬ አጠናቀቅሁኝ፡፡
መግቢያው በፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ መጻፉም በግሌ ደስ ብሎኛል፡፡ ምክንያቱም ለኒህ ምሁር ያለኝ ግምት፤ “ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስ አበባ” የሚለውን ግለ ታሪካቸውን ካነበብኩ በኋላ ከፍ ብሏል። እርሳቸውም ስለ ኃይሌ ፊዳ እንዲህ የሚል ሀሳብ አስፍረዋል፡- “ኃይሉ ፊዳ ለዘመናት ለሰው ልጆች የኑሮ መሻሻል ይመኝ፣ ያስብና ያሰላስል የነበረ፣ ያንን ምኞቱን ግብ ለማስመታት ያስችላል ብሎ ያመነበትን የፖለቲካ ፍልስፍና በተግባር ለመተርጎም የሚጥር ግለሰብ ነው፡፡”
እንግዲህ የነገሩንን ይህንን ኃይሌን ፍለጋ ማንበብ የግድ ይላል፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ ዶክተር በአማረ ተግባሩ በየነ፤ ከኃይሉ ፊዳ ጋር የቅርብ ጓደኛ፣ አብሮ ሰራተኛ፣ ምስጢረኛም ጭምር ስለነበሩ፣ መጽሐፉን ለመፃፍ በቂ መነሻ አላቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ የመጀመሪያ መረጃ ያለው፣ በታሪኩ የተሳተፈ፣ ቅርበት ያለውና በተለይ በአንድ ዐላማ፣ ለአንድ ግብ አብሮ የሰራ ሰው፤ ብዙ ነገር ማወቅ ስለሚችል፤ ስለሚፃፍለት ሰው፣ የተሻለ ግንዛቤ ሊሰጥ ይችላልና ደግ ነው፡፡
ስለ ኃይሌ ፊዳ ከመግቢያው ጀምሮ በተደጋጋሚ የሚታየው ነገር፣ ኃይሌ እኔ አዋቂ ነኝ የማይል፣ የተረጋጋ፣ የሌሎችን ሃሳብ የሚቀበልና የሚያከብር፣ ከፍተኛ የፖለቲካ እውቀት የነበረው ቅን ሰው መሆኑ ነው፡፡ አንዳንዴም ኃይሌ ፊዳ፤ ቀልድ የሚያውቅ፣ በራሱም ሳይቀር የሚቀልድ፣ ምናልባትም እንደ ነቢይ የተናገረው የሚይዝለት ሰው ነበር፤ ለዚህም ነው ኮሌኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም፤ “ለምሳ ያሰቡንን ለቁርስ አደረግናቸው” ያሉትን እየጠቀሰ፤ “እኔንም አንድ ቀን እንዲሁ ያደርጉኛል” እንዳለው የተበላው፡፡
እንደ መጽሐፉ ደራሲ፤ ከኃይሌ ፊዳ ጋር የጠበቀ ግንኙነትና በቂ መረጃ እንዲኖራቸው ያደረጋቸው፤ “አዲስ ፋና” በሚል የምትታወቀውን፣ የድርጅታቸውን መጽሔት አብረው ያዘጋጁ ስለነበር ነው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ እንደምናየው፣ ቀደም ሲል፣ በኢትዮጵያ አብዮት ወላፈን ውስጥ በትግል ያለፉ ትልልቅ ፖለቲከኞችም ታሪክ ብቅ ጥልቅ ይላል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ዶክተር ነገደ ጎበዜ፣ ብርሃነ መስቀል ረዳና ሌሎቹም ይጠቀሳሉ። ጌታቸው ማሩም በመጠኑ ብቅ ጥልቅ ብሏል፡፡ የደርጉ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርም በታሪኩ ውስጥ ሰፊ ድርሻ አላቸው፡፡
በደራሲው መነሻነት ስናየው፤ ኃይሌ ፊዳ ጠንካራ አብዮተኛና የህዝብ ተቆርቋሪ ነው፡፡ የሊቀመንበር ማኦ ዜቱንግና የቻይና አብዮት ደጋፊም ነው፡፡ ምናልባት ያልተዋጠለት የሶቪየት ኅብረቱ አብዮት ይመስላል። ይህንም የምናየው ሶማሊያን እስከ አፍንጫዋ አስታጥቆ፣ እዚህ ሌላ አብዮት እየደገፈ፣ ወደ ራስ የማሰለፍ፣ ሸፍጥ ነው ብሎ በመጠርጠር፣ ኮሎኔል መንግሥቱ ከሚሰጡት ፍንጭ በመነሳት ነው፡፡
ኃይሌ ፊዳ በእጅጉ ሥነ ጽሑፍ ወዳድ፣ አንባቢና አሰላሳይ እንደሆነ ደራሲው በብዙ ማስረጃዎች አሳይተዋል፡፡ በሀገራችን የተተረጎሙ እንዲሁም የሌሎች ሀገራትን ቋንቋ በማጥናት አንዳንዴም በመተርጎም የጥበብ ሥራዎችን  ይጋሩ ነበር፡፡ የሚያደንቁትን ማኦ ሴቱንግንና የቻይናን መዝሙር እንዲህ ይዘምሩ ነበር፡-
ቀይ ኮከብ ወጥቶ በምስራቅ፣
ቻይናን አጥለቀለቃት፣
ከብዙ ሺህ ጨለማ ዓመታት፣
የማኦ ሴቱንግ አገር ታየች ሆና እጅግ ደማቅ፣
ማኦ ስቱንግ ይኖራል ዘላም በወዛደሩ ልብ፡፡
አብዮት ነውና ረጅም መራራ ትግል
እንታጠቅ
አሁኑን በማኦ ሴቱንግ ትምህርት
ማኦ ሴቱንግ ይኖራል ዘላለም በሁላችንም ልብ፡፡
ኃይሌ ከላይ እንደተጠቀሰው አውቃለሁ ባይ ሳይሆን፣ የሚያውቀውንና ለህዝብ ይጠቅማል ያለውን ነገር በቀላል መንገድ ማስተላለፍ የሚፈልግ ሰው ነው። ደራሲው ዶክተር በአማረ፤ ለዚህ ማሳያ ያደረጉት ራሳቸውን ነው፡፡ እንዲህ በማለት፤ …. “አልፎ አልፎ በእንግሊዝኛ መግለጫዎች ማውጣት ይኖርብንና እኔ ረቂቁን እንዳዘጋጅ ይወሰንና እኔም የተባለውን ረቂቅ ይዤ ስቀርብ፣ ኃይሌ ይመለከትና በሳቅና ፈገግታ፤ ‹መቼ ይሆን ያ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቦምባስቲክ የሆነ የአፃፃፍ ባህል የሚለቅሽ?› በማለት አንዲቱን ቃል፣ አንድ ክንድ ያክል መርዘሟን በማመልከት፣ ሰው አንብቦ ለመረዳት መዝገበ ቃላት መያዝ  ይኖርበታል፤ ማለቱን ያስታውሳሉ፡፡
ይህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ኃይሌ ፊዳን ለማወቅ፣ በየመጽሔቶቹ የፃፋቸውን መጣጥፎች ሀሳብ ማየት መፈተሽ ያስፈልገናል፡፡ ያኔ ሚዛናዊነቱን፣ ሀገር ወዳድነቱን፣ ነገሮችን በኃይል ሳይሆን በንግግር ለመፍታት ያለውን ፍላጎት--- ሁሉ እናጤናለን። ከመገዳደል ይልቅ፣ ወደ መነጋገርና አደጋ ወደ መቀነስ እንደሚያደላ ለማየት፣ ከደርግ ጋር በነበራቸው ግንኙነት፣ በጥንቃቄ የሄደባቸውን መንገዶች  ማጤን ይበቃል፡፡
ኃይሌ ትውልዱ በቀድሞው አጠራር ወለጋ ጠቅላይ ግዛት፣ አርጆ አውራጃ፣ አርጆ ከተማ ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን እስከ 5ኛ ክፍል አርጆ ቢትወደድ መኮንን ደምሰው ትምህርት ቤት ተምሮ፣ በኋላም አክስቱ ጋ ነቀምቴ በመሄድ፣ እስከ ሰባተኛ ክፍል ተምሯል፡፡ በጊዜው ከሰባተኛ ክፍል አንደኛ በመውጣቱና ለትምህርት ያለው ፍላጎትና ጥረት ከፍ ያለ ስለነበር፣ የስምንተኛን ክፍል መልቀቂያ ፈተና (ሚኒስትሪ) እንዲወስድ ተፈቅዶለት፣ በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ውጤት ካመጡት አንዱ ስለነበር፣ ወደ ጄኔራል ዊንጌት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከመጡት አንዱ ሆኗል። በጄኔራል ዊንጌት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነፃ ትምህርት ዕድል አግኝቶም፣ አዲስ አበባ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብቷል፡፡ ታዲያ ከሁሉ ይልቅ ፊዚክስ፣ ሂሳብና ኬሚስትሪ ላይ ችሎታው የላቀ ነበር፡፡ በተጨማሪም ሙዚቃ፣ ሥዕል በአጠቃላይ ጥበባት ላይ ያለው ፍቅር እጅግ ከፍ ያለ ነበር፡፡
በመጨረሻም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጂኦሎጂና በፊዚክስ ተመርቋል፡፡ በኋላም የፖለቲካ ዝንባሌውን ተከትሎ፣ ከፓሪስ ስርቦን ዩኒቨርሲቲ በሶሽዮሎጂ ተመርቋል፡፡ ያው ጥሪው ነውና በአውሮፓ የተማሪዎች ንቅናቄን፣ በኋላም የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስታዊ ንቅናቄ (መኢሶን) መሪ በመሆን ፣ እስከ ሕይወቱ መጨረሻ  አገልግሏል፡፡
ኃይሌ፤ የፖለቲካ ጥሪ፣ የሀገርና የወገን ዕዳ እንደሆነ ተረድቶ፣ የውስጡን ሀሳብ የገለጠበትን ደራሲው፣ ገፅ 59 ላይ፣ እንዲህ አስፍረውታል፡-
“እኔ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ነፃነትና በሶሻሊዝም ላይ ለቆመ የዕኩልነት ሥርዐት መመስረት የገባሁበት ትግል ከሁሉም በላይ ትርጉም ያለውና ከራሴም ህይወት ጭምር የሚበልጥ በመሆኑ እንጂ ማንኛውም ፈረንሳይ አገር የሚኖር የውጭ ሰው ያለ ውዴታው የሚሰራውን ዝቅተኛና የተናቀ ሥራ ሰርቼ፣ ለልጆቼ የዕለት ቀለብ ማቅረብ አቅቶኝ አይደለም፡፡”
ይህን ያለው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ መሪ በመሆኑ የተነሳ፣ መንግስት ስኮላርሺፑን በማገዱና ፓስፖርቱንም በመንጠቁ እንደሆነ የህይወት ታሪኩ ጸሐፊ  ይነግሩናል፡፡ ይህ ፈተና፣ ትዳሩና ቤቱ ገብቶ፣ ህይወቱንም ማመሳቀሉን ጭምር እናያለን፡፡
የኃይሌ ፊዳን ሰዋዊ ርኅራኄ ከሚያሳዩት ነገሮች አንዱ፣ የመጽሐፉ ደራሲ ዶክተር በአማረ ተግባሩ፣ በህመም ምክንያት ሆስፒታል በነበሩ ጊዜ ያደርግላቸው የነበረው እንክብካቤና ጥያቃ ነው፡፡ ደራሲው እንዲህ ገልፀውታል፡- “ከሳምንት በላይ ሆስፒታል ተኝቼ፣ ህክምና በምከታተልበት ወቅት አንድም ቀን ከሆስፒታሉ ተለይቶ አያውቅም ነበር፡፡ በየቀኑም የሚያምረኝን የምግብ አይነት ራሱ ሰርቶ በማምጣት፣ ያደረገልኝ እንክብካቤ የማይረሳ ነው፡፡  
በፖለቲካዊ አካሄዱም የመቻቻልና ግጭት የመቀነስ መርህ ተከታይ መሆኑን የሚያሳዩ ሀሳቦች መጽሐፉ ውስጥ ተካትተዋል፡፡ ለምሳሌ ገፅ 134፡-
በኢሕአፓ ጥይት መጀመሪያ የወደቀው የፍቅሬ መርዕድ ቀብር ሥነ ስርዓት ላይ የመኢሶን አመራርና ደጋፊዎች በቁጣ ተሞልተው፣ የአንድ አብዮታዊ ታጋይን ሞት፣ በብዙ እጥፍ በቀል እንደሚከፈል ሲገልፁ፤ ኃይሉ ፊዳ ግን ይህን ሀሳብ አልደገፈም ነበር፡፡ ይልቁኑም ነገሩን እንዲህ በሚል የሰከነ መንፈስ አይቶታል፡-
“ውድ ጓዶች፣ ልብ ብለን ብናስተውልና የአናርኪስቱ ቡድን ይህንን የመሰለ ጥቃት ሊፈፅምብን የቻለው ለምን እንደሆነ ራሳችንን ብንጠይቅ፣ መልሱ እንደምናስበው ድርጅታችን ጠንካራ፣ አቋማችን ትክክል ስለሆነ ብቻ እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡ ይህ ጥቃት ሊፈፀምብን የቻለው በእርግጥም ድርጅታችን ደካማና ገና ብዙ ያልተሰራ ሥራ በመኖሩ እንደሆነ ማመን ይኖርብናል። ከአናርኪስቱ ኢሕአፓ ጉያ ወጣቱን ለመሳብና ወደ ድርጅታችን አቋም ለማምጣት አለመቻላችን በራሱ ይህንን ለመሳሰሉ ጥቃቶች ሊያጋልጠን ችሏል፡፡ ለኢሕአፓ ምላሹ በቀል አይደለም፡፡ ይህማ ኢሕአፓን ራሱን መሆን ነው፤ ጓዶች። ኧረ ተዉ ጓዶች! እንዲህማ ሊሆን አይችልም ጓዶች!”
ሰውየው ከኃይል ይልቅ በእውቀት ያምናል፡፡ ሰዎች አእምሮ ላይ መስራት ላይ ያተኩራል፡፡ ሀገርና ትውልድ እንዳትጎዳ ያምጣል፡፡ ምናልባትም እስከ ዛሬ የምንቸገርበትን ነገር፣ እርሱ በጊዜ ደርሶበት ነበር፡፡ ግን ግጥሚያው ከወታደራዊ አምባገነኖች ጋር ነበርና፣ ያለ ጥይት መልስ አላገኘም፡፡
ኃይሌ ፊዳ ሀገራዊ ክብርን በተመለከተ ያለው አመለካከት፣ የሚደንቅና ፍፁም ኢትዮጵያዊ ክብርን የጠበቀ ነው፡፡ ማንም ሕዝብ በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ኩሩና ባለታሪክ ህዝብ ከሆነ ለገዛ ነፃነቱ፣ ለገዛ አብዮቱና ለገዛ ክብሩ፣ ከሁሉም በፊት መተማመን ያለበት በራሱ መሆኑ መታወቅ አለበት። ስለሆነም የውጭ እርዳታን በሚመለከት ረገድ ብሔራዊ ክብርና ነፃነት እንደዚሁም ከሁሉ በፊት በራስ መተማመን የሚለው ዋናው መመሪያችን ይሆናል፡፡
ኃይሉ ፊዳ ከሞላ ጎደል ይህን ይመስላል፡፡ በተቻለ መጠን ከጠመንጃ ይልቅ በሀሳብ ፍጭት የሚያምን፣ ሀገሩን የሚወድድ፣ ለህዝቦች ነፃነት ግድ የሚለው እንደሆነ የመጽሐፉ ደራሲ አሳይተውናል፡፡
ምናልባት ቅር ሊያሰኙን የሚችሉት ኃይሌ ፊዳ እንደ ሰው ችግሮቹ ምን ነበሩ? የሚለው ያለመጠቀሱ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ አንዳንድ ቦታ ኢሕአፓ በአንድ ምንባብ ውስጥ ከአውድ ውጭ እየጠቀሰ ይጠቀም እንደነበረና ጥራዝ ነጠቅ መሆኑ የተገለፀበት ቦታ ምን ያህል አሳማኝ ነው የሚለው ነው፡፡ “ለራስ ሲቆርሱ፣ አያሳንሱ” እንዳይሆን ስጋት አለኝ፡፡ ሌላው ምናልባት በድጋሚ ሲታተም መታረም ያለበት፣ “በወለጋ ክፍለ ሀገር” የሚለውና ስለ ኃይሌ የትውልድ አካባቢ የሚናገረው ሀሳብ ነው፡፡ ክፍለ ሀገር የሚለው ጥቅም ላይ የዋለው ከ1966 ዓ.ም አብዮት በኋላ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ የተዘነጋ ይመስለኛልና ቢታረም፡፡ በተረፈ ይህንን የመሰለ ታላቅ፣ ድንቅ ሰው፣ ከህይወቱ ገፆች ብዙ መማር የምንችልበትን የሀገር ታሪክ ጽፈው በማቅረብዎ፣ በእጅጉ ሊመሰገኑና ሊከበሩ ይገባል ባይ ነኝ!

Read 1240 times