Print this page
Sunday, 17 June 2018 00:00

“ጄሚናይ” በደራሲ መንግስቱ ለማ ውስጥ (ዝክረ አብዬ መንግሥቱ)

Written by  በኃይሌ ሲሳይ ገበየሁ
Rate this item
(2 votes)

     ራስ ተፈሪ በነበራቸው የአውሮፓ ቀመስ ትምህርትና በተራማጅነታቸው፣ ልዑል አልጋ ወራሽ ተብለው ተሾሙ፡፡ ዘውዲቱ ደግሞ የኢትዮጵያዊያን ወግ አጥባቂ የመኳንንት ቡድን ምርጫ በመሆናቸው፣ ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ተብለው በተሾሙ ስድሰተኛ ዓመታቸውን የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ትያትር በቴራስ ሆቴል ታየ፡፡ ወዲያው ግን ስርዓቱን ጎንትሏል በመባሉ እንዳይታይ ታገደ፡፡ በታገደ ሁለተኛ አመቱ ሰኔ 1 ቀን 1916 ዓ.ም በሐረር፣ አደሬ ጢቆ፣ በኮከብ ቆጣሪዎች (አስትሮሎጂዎች) የኮከብ ምድብ “ንፋስ”፣ የኮከብ ገዥ ፕላኔት “ሜርኩሪ”፣ ዋና ኮከቡ “ጄሚናይ” የሆነ ህፃን ተወለደ፡፡ ጄሚናዮች ደግሞ ነገር ሥራቸው ሁሉ የልጅ ነው፡፡ ተግባቢና ድንጋይም ቢሆን ማናገር የሚችሉ ሲሆኑ ብዙዎቹ ደግሞ ዲፕሎማቶች ናቸው። የውስጣቸውን ሀሳብ ለቀሪው ዓለም አውጥተው የማካፍል ሁኔታ አላቸው፡፡ ንግግር፣ ቋንቋ፣ የንግድ ሥራ፣ ማቲማቲክስና በዛ ያሉ የአእምሮ ስራዎች መክሊታቸው ነው፡፡
ይሁንና ይህ ህፃን፣ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ፣ በመጀመሪያ ጥንታዊውን የቤተክርስቲያን ትምህርት፣ በመቀጠልም ከኢትዮጵያ እስከ ሎንዶን ዘመናዊ ትምህርቱን ተማረ፡፡ በዚህ ትምህርቱም ከጅምሩ ጥንታዊውንና ዘመናዊውን የኢትዮጵያ ትውልድ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያንና የሌላውን ዓለም ባህልና ወግ እርስ በእርስ ለማስተዋወቅ፣ ማያያዣ ሰንሰለትና መገናኛ ድልድይ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። ከአንተ ወደ አንቱታ ያሸጋገረው፡- ሥራ ደግሞ ጥንታዊውንና ዘመናዊውን ትውልድ ለማስተዋወቅ  ከሠራቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ የሆነው “መፅሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ” ነው፡፡ ውድ አንባቢያን፡- ከዚህ በታች ላሉት ማጣቀሻዎች ምስክርነታቸውን የሰጡት ጎደኞቻቸው፣ የስራ ባልደረቦቻቸው፣ ተማሪዎቻቸውና በተለያዩ ሁኔታ የሚያውቋቸው ሰዎች ናቸው፡፡
መንግስቱ ለማ የኮከብ ምድባቸው “ንፋስ” ነው ብለናል፡፡ ንፋሶች ደግሞ አፍ የማያስከድኑ፣ ተጫዋችና አንደበተ ርእቱ ተናጋሪዎች ናቸው፡፡ በዚህ ገፅ መንግስቱ ለማን ስናያቸው፣ ንፋስ ከስብዕናቸው ጋር የተዋሀደ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አርቲስት ተፈሪ ዓለሙ ይህን ሲያበረታ፤ “ስለ ምንም ጉዳይ ቢያወሩ አፍ ያስከፍታሉ። በሚያስከፋም ነገር አዝነውና ተቆጥተው ሲናገሩ እንኳን በሳቅ ያፈርሳሉ፡፡ ካፋቸው ማር ጠብ ይላል የሚባሉ አይነት ጨዋታ አዋቂ ነበሩ። ቀልዶቻቸው እጅግ ጥልቅ ናቸው፡፡ ጨዋታዎቻቸው የማይሰለቹ ብቻ ሳይሆኑ እስከ መቼም አይረሱም” ብሏል፡፡
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ደግሞ “መንግስቱን ፈገግተኛ ተጫዋች፣ ተግባቢ፣ ውይይት የሚወድ፣ ሰው ነበር” ይላሉ፡፡ ወንድወሰን በየነ በመመረቂያ ጽሁፍ ይህንኑ ሲያደምቅ እንዲህ ብሏል፤ “ቢከፋቸውም ቢደሰቱም ከፊታቸው የፈገግታ ፀዳል አጥቶ የሚመለስ አልነበረም፡፡ እንደ መስከረም አደይ ፍኩ ገፅታን ታድለውታል” ይላል፤ ምንም እንኳን የኮከብ ምድባቸው “ንፋስ” የሆኑ ሰዎች የታደሉት በረከት ቢሆንም፡፡
የመንግስቱ ለማ ገዥ ፕላኔት “ሜርኩሪ” ነው ብለን የለ፡፡ ሜርኩሪ ደግሞ የአእምሮና የተግባቦት ፕላኔት ነው፡፡ በዚህም ገዥ ፕላኔት አማካኝነት የማሰብ፣ የመፃፍ፣ የመናገርና የማስተዋል ክሂሎችን እናዳብራለን፡፡ በዙሪያችን ያለውን ሰፊውን ዓለም በንቃት እንድናስተውልም ይረዳናል፤ ርዕዮተ ዓለማችንን ይቀርፀዋል፡፡ ወሬና ክርክር፣ ሙግትና ጭቅጭቅም ነብሱ ነው፡፡
ገና ከጅምሩ በለንደን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበርን ከመመሥረት ጀምሮ በዋና ፀሃፊነትና በፕሬዝዳንትነት ማኅበሩን መርተዋል፡፡ በዚህ ወቅት “Lion cub” (ደቦል አንበሳ) እየተባለ ይጠራ በነበረው የማህበሩ ልሳን “ኢትዮፒስ” በሚል የብእር ስም፣ የኢትዮጵያን ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገቶችን የተመለከቱ ጽሁፎችን በአማርኛና በእንግሊዝኛ በተከታታይ ያወጡ ነበር፡፡ ፕሮፌሴር ሪቻርድ ፓንክረስት እንደሚሉት፤ “መንግስቱ ለንደን ስኩል ኦቭ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት በነበሩበት ጊዜ ከሚማሩበት የትምህርት ዘርፍ ይልቅ ወደ ፖለቲካ ሳይንስና የልብ ወለድ (የፈጠራ ስነ ጽሁፍ) ስራዎች አዘንብለው ነበር፡፡ በተለይም imperialism, the highest stage of capitalism እና  the state and revolution የተሰኙትን የሌኒንን መጻሕፍትና የሩሲያ ጸሐፍት ተውኔት ለምሳሌ፡- የጎጎል፣ የዶስቶየቭስኪን፣ የቶልስቶይን፣ የቼኾቭን፣ የጎርኪንና ከምእራባወውያን ጸሐፍት ውስጥ የጆርጅ በርናርዶ ሾውን ተውኔቶች በስሜትና ተመስጦ ያነቡ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡”
ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ ደግሞ ‹ያኔ ይግረመው ሸዋ› ብሎ የሰየማት ላምበሬታ ኢጣሊያን ሀገር የምትመረት አነስተኛ ሞተር ብስክሌት) ነበረችው። በዚያች ሲንዶቆዶቅ ሲመጣ እምብዛም ፍሬ ነገር ከሱ አልጠበቅንም ነበር፡፡ ነገር ግን ጥቂት ስለ ቅኔ፣ ስለ ግጥም ገለጻ ካደረገልን በኋላ ለቅምሻ ያህል ከግጥሞቹ ጥቂቶቹን በቃሉና በንባብ ሲወጣልን አፋችንን ከፍተን ቀረን፡፡ በወል ቤት ግጥሞች ብቻ ተጠምቀን ያደግን ወጣቶች፤ ለአማርኛ ግጥም የነበረንን አድማስ በሰፊው ዘረጋልን፡፡ በኢትዮጵያ ስነ-ግጥም ሰማይ ላይ የአዲስ ኮከብ ጮራ መፈንጠቁ ታየ፡፡ በመቀጠልም፤ መጽሐፉን በራሱ ወጭ ሲያሣትምና ምንባቡንም በየስብሰባው ሲያሰማ፣ ለታዳጊ ብዕረኞች ምናብ ታላቅ መስህብ ሆነ” ሲሉ ይገልፃሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከአርባ አመታት በላይ በሆነው የምሁር ሕይወታቸው፤ አያሌ የሥነ ፅሁፍ ጥናታዊ መጣጥፎችን አሳትመዋል፡፡ በስነ ፅሁፍ ዙሪያ በአደባባይ ተከራክረዋል፣ በጋዜጣ ላይ ጽፈዋል፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ቀርበው ሃሳባቸውን አስረድተዋል፡፡ መንግሥቱ ለማ ዘመናዊ ኮሜዲን ለሀገራችን በማስተዋወቅ ረገድም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በተለይም “ጠልፎ በኪሴ”፣ “ያላቻ ጋብቻ” እና “ባለካባና ባለዳባ” ለሕዝብ ቀርበው ከፍተኛ አድናቆትን አትርፈውላቸዋል፡፡ በተለይም “ያላቻ ጋብቻ” በ1960 ዓ.ም የቀ.ኃ.ሥ ሽልማት፣ “ጠልፎ በኪሴ” ደግሞ የእንግሊዘኛው ትርጉም የካሊፎርንያ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ሥነ ጽሁፍ ሽልማትን አስገኝተውላቸዋል፡፡ የሆነው ሆኖ የመንግስቱ ለማ ዋና ኮከብ “ጄሚናይ” ነው ብለን የለ፡፡ ጄሚናይ ደግሞ ግልጽ፣ ተግባቢና ድንጋይም ቢሆን ማናገር የሚችሉ ናቸው፡፡ አንድ ቦታ ግን ሰክነው አይቀመጡም፡፡ ለዚህም ይመስላል መንግስቱ ለማ እየተዘዋወሩ፣ በሲቪል አቪየሽን መ/ቤት፣ በመገናኛ ሚኒስቴር፣ በብሔራዊ ሸንጎ መማክርት አባልነት፣ በኋላም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋዎችና ጥናት ተቋም በልዩ የመምህርነት (ሌክቸር) ማእረግ ተቀጥረው አገልግለዋል፡፡ በጽሁፋቸው ውስጥ ስለ ሕይወት፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ሞት፣ ስለ ትዝታና ስለ ሌሎችም ዘላቂ ቁም ነገሮች፣ በጥልቅ ስሜት አንስተዋል። በጥቅሉ የመንግስቱ ጄሚናይ ባህሪ በሃሳብ እየጎለበተ፣ በጽሁፍ እየተከተበ፣በክርክር እየዳበረ፣ ቀስ በቀስ ብርድና ቁሩን ተቋቁሞ እንደሚፈካው አደይ አበባ በመፍካት፤ ከአበባው የተገኘው ማር የጥበብ ፈውስ ሆኗል። በአደባባይም እንደ መስቀል ደመራ አብርቷል። የአደይ አበባው መዓዛና የመስቀል ደመራው ብርሃን የጠራቸው ንቦችም አበባውን ለመቅሰም እንደሚሹ ሁሉ፣ የመንግስቱን የጥበብ ብርሃን የሻቱ ሁሉ፣ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ለመቅሰም ታድለዋል። ያላቸውን የማካፈል፣ የማሰብ፣ የመፃፍ፣ የመናገርና የማስተዋል ኪሂል ደሞ በጄሚናይ መንግስቱ ለማ ዓይተናል ለማለት ያስደፍራል፡፡
(ለታላቁ ባለቅኔ፣ ፀሐፌ ተውኔት፣ ተርጓሚ፣ ደራሲና መምህር መንግሥቱ ለማ በህይወት ባይኖሩም በመንፈስ አሉና፣ ሰኔ 1 ቀን 2010 ዓ.ም 94 ዓመት ስለሞላቸው ለመታወሻነት የተዘጋጀ፡፡)

Read 3475 times