Sunday, 17 June 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

 (የኢድ ስጦታ)
 “ሁሴን አውቶሞቢል መኪና፣ ለኢድ በዓል በስጦታ አገኘ፡፡” - ይለናል፤ ከዘመናዊ፣ እስላማዊ ታሪኮች አንዱ ---- “A brother like that” በሚል ርዕስ የተፃፈው፡፡ … የሁሴን ጓደኞችና የአካባቢው ልጆች መኪናዋን እያዩ ‹ጉድ› አሉ፡፡ ከነሱ መሃል አንደኛው አሊ፤
“በጣም የምታምር መኪና ናት” አለው፤ ለሁሴን፡፡
ሁሴንም፤ “አመሰግናለሁ፣ ወንድሜ ነው የገዛልኝ” ሲል ነገረው፡፡
አሊ በመገረም፤ “አንተ ምንም ገንዘብ አላወጣህበትም?” በማለት ጠየቀው
“ምንም” አለ ሁሴን፡፡
“በጣም ዕድለኛ ነህ፡፡ እኔም እንደዛ ዓይነት ወንድም…”  ጣልቃ በገባ ነገር ምክንያት፣ አሊ ሀሳቡን ለሁሴን ተናግሮ ሳይጨርስ ተናጠበ፡፡
ሁሴን ግን፤ “እኔም እንዳንተ ዓይነት ወንድም ቢኖረኝ ይገዛልኝ ነበር” ማለት እንደፈለገ ገባው፡፡ ግን ተሳሳተ፡፡
የአሊ ሁኔታ ስላሳዘነውና ልቡ ስለተነካም …. “ግባና ዞር ዞር እንበልባት” ብሎት መንሸራሸር ጀመሩ። በእነ አሊ ቤት በኩል ሲያልፉ …. አሊ፤ “አንድ ጊዜ አቁምልኝ” አለውና ከመኪናው ወርዶ እየሮጠ ወደ ቤቱ ገባ፡፡ ሁሴንም፤ አሊ በዘመናዊ መኪና ከጓደኛው ጋር እየተንሸራሸረ መሆኑን ለቤተሰቦቹ ማሳየት እንደፈለገ ገባውና ዘና አለ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ተሳሳተ፡፡ … ስህተቶቹ ምን ነበሩ? … እንመለስበታለን፡፡
***
ወዳጄ፡- “መስጠት ማለት፤ የተረፈህን ሳይሆን ለራስህ ከሚያስፈልግህ ላይ ስታካፍል ነው” ይላሉ ሊቃውንቶች፡፡ ስጦታ ግብር አይደለም፣ ህግ አያስፈልገውም፡፡ ስጦታ የፍቅርና የመውደድ መገለጫ ነው፡፡ ስጦታ ከሰደቃና ከዘካ የዘለለ፣ የደግነትና የርህራሄ ማሳያ ነው፡፡ “ወገኖችህ እየተራቡ ለነገ የምታስተርፍ አንተ ማን ነህ?.... ነገን ላንተ ማን ሰጠህ? … ትናንት አጠገብህ የነበሩት ሁሉ ዛሬ አጠገብህ አሉን? … እንዲያ ከሆነ፣ ስለ ምን “ኢንሻ አላህ!” ማለት አስፈለገ?” በማለት ይጠይቁናል … ሊቃውንቶቹ ኡላማዎች፡፡ ስትሰጥ በምትኩ “ይኼን አገኛለሁ፣ ይኸ ይደረግልኛል ብለህ ካሰብክ ከስረሃል፡፡ ስጦታ ንግድ ወይም Transaction አይደለም፡፡ ለራስህ ከሚያስፈልግህ ላይ ቀንሰህ እንዳንተው ለሚያስፈልጋቸው ስትሰጥ ነው … ስጦታ፣ ‹ስጦታ› የሚባለው፡፡” ይላሉ!! … ባይኖርህ፣ ባይመችህና ባታደርግ ለራስህ የምትመኘውን፣ እንዲሆንልህ የምትፈልገውን ለነሱ ከተመኘህላቸው በቂ ነው፡፡ ከልብህ ከሆነ፣ የስሜትህ ትኩሳት፣ የፍቅርህ ግለት ባሉበት ይደርሳቸዋል፡፡
እስልምና እንደ ሌሎቹ ባህላዊ እምነቶች (Traditional beliefs) ከእምነቱ ባሻገር ወደ ኑሮ ዘይቤነት (way of life) እየተቀየረ ከመጣ ቆይቷል። ቤተሰባዊ ወንድማማችነት ሆኗል፡፡ “ለራስህ እንዲደረግልህ የምትፈልገውን ለወንድምህ አድርግለት፣ በራስህ እንዲደርስ የማትፈልገውን ክፉ ነገር በወንድምህ ላይ አታድርግ፣ ይልቁንም ውደደው” የሚለው፣ ሌሎች ወርቃማው ህግ (The Golden Rule) የሚሉት የተቀደሰ ቃል፤ ለእስልምና አዲስ አይደለም፡፡ … ራሱል አላህ (ሳል አላሁ አላይሂ ዋ ሰላም!) ተብሎ ተፅፏልና!! … “አሃምድልላሂ ታቦታችን ገባ! … ፈጣሪ ይመስገን መስጂዳችን ተጠናቀቀ” ማለታችን የዚሁ ፍቅር መግለጫ ነው፡፡
ወዳጄ፡- የሆነው ሆኖ ዘመኑ መቀየሩን ልብ ብለሃል? … ዘርህ ከየት ነው? … ሃይማኖትህ ምንድነው? የሚባሉ ጥያቄዎች አርጅተዋል፡፡ የፖለቲካ አስተሳሰብህና አመለካከትህም ሌሎች የጫኑብህ ሳይሆን አንተ ፈልገህ፣ ፈቅደህና አምነህበት የመረጥከው ቢሆን ችግር የለውም፡፡ … ዘመኑ የሚጠይቅህ፣ በዋናነት እንድትመልስለት የሚፈልገው ጉዳይ አንድና አንድ ብቻ ነው፡- … “መልካምና ቅን ሰው ነህ፣ አይደለህም??” የሚል!! … ይህን ጥያቄ ከመለስክ፣ ያልተጠየቅሃቸውን ሌሎች ጥያቄዎች ሁሉ አብረህ መልሰሃቸዋል፡፡
 … ምክንያቱም፡-
መልካምና ቅን ሰው፤ ፍትህ አያጎድልም፣ አያደላም። መልካምና ቅን ሰው፤ ካልተቸገረና የሚበላው ካላጣ አይሰርቅም፣ አያታልልም፣ አይዋሽም። መልካምና ቅን ሰው የሌሎችን አስተሳሰብ፣ እምነት፣ መብትና ነፃነት አይጋፋም፡፡ መልካምና ቅን ሰው፤ በራሱ ይተማመናል፣ የሚፈራበትና የሚሰጋበት ጉዳይ የለም፡፡ መልካምና ቅን ሰው፤ ሃይማኖተኛ፣ ሳይንቲስት፣ አርቲስት፣ አትሌት፣ ወታደር ወዘተ ቢሆንም ከማንም ጋር ፀብ የለውም፡፡ መልካምና ቅን ሰው፤ ምድራችን፣ ህዝቦቿ በሰላምና በፍቅር ተቻችለውና ተጋግዘው የሚኖሩባት ቦታ እንድትሆን ይፈልጋል፡፡
ወዳጄ፡- መልካምና ቅን እያልን ስንጨዋወት፤ “መልካምና ቅን ያልሆነም” አለ ማለታችን ይመስላል። … አንድ ነገር ልብ በልልኝ፡- ሰው በተፈጥሮው መጥፎ አይደለም፡፡ መልካምና ቅን መባልን የማይፈልግ የለም፡፡ ልዩነቱ የሚመጣው ህይወትን በተገቢው መንገድ ከመረዳትና ካለመረዳት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ አስተዳደጋችንና አካባቢያችን እንዲሁም ሌሎች ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎች ተደማምረው፣ እኛነታችን ወይም ተፈጥሯችን ላይ ተፅዕኖ ስለሚያደርጉ፣ መንገዳችን ለአንዳንዶቻችን ጨርቅ፣ ለአንዳንዶቻችን አስፓልት፣ ለአንዳንዶቻችን ኮረኮንች፣ ለአንዳንዶቻችን እሾሃማ ሊሆን ይችላል። በዚህም የተነሳ ስሪታችን ይለያያል፡፡ እንደ ምሳሌ፣ ከተለያየ ቦታና ቤተሰብ የተገኘን ሰዎች፤ በአንድ ክፍል ውስጥ እንማራለን እንበል፡፡ … የምንማረውን ፈጥነን የተረዳነው ጎበዝ ተማሪዎች ስንባል፣ አንዳንዶቻችን ጎበዝ፣ አንዳንዶቻችን መካከለኛ፣ አንዳንዶቻችን ደካማ፣ ሌሎቻችን ሰነፍ ልንባል እንችላለን፡፡ ውጤታችንም … እጅግ በጣም ጥሩ፣ በጣም ጥሩ፣ ጥሩ፣ በቂ፣ ውዳቂ (A, B, C, D,E) እየተባለ ደረጃ ይወጣለታል፡፡ ይኸ ግን ቋሚ ዕውነት አይሆንም፡፡ ተግቶ በመስራት ሊለወጥ የሚችል ነገር ነው፡፡ ባህሪያችንም ሁኔታዎች የጫኑብን እንጂ አብሮን የተፈጠረ ነገር አይደለም፡፡ ሲገባንና ስንረዳ እንሻሻላለን፡፡ ባለማወቅ ላጠፋነው እየተፀፀትን፣ እየታረምን፣ ስህተታችን እንዳይደገም እየተጠነቀቅን፣ ራሳችንን ማቃናት እንችላለን፡፡ የማይሳሳት የሞተ ብቻ ነው፡፡ “Failure is the mother of success” ይላሉ አውሮፓውያን፡፡ የፆምና የፀሎት ግቡም ይኸው ነው፡፡ … መልካምና ቅን መሆን!!
***
ወደ ሁሴንና አሊ ስንመለስ፡- ዓሊ የሁሴንን መኪና አይቶ እየተደነቀ፣ “በጣም ታምራለች እኔም እንዳንተ ዓይነት ወንድም...” ብሎ የጀመረውን ዓረፍተ ነገር አልጨረሰውም!! ሁሴንም፡- “… እንዳንተ ዓይነት ወንድም ቢኖረኝ ይገዛልኝ ነበር---” ማለት የፈለገ ነበር የመሰለው፡፡ ሁሴን ተሳስቷል ብለናል፡፡ በርግጥም ተሳስቷል፡፡ አሊ ያሰበው፡- “እንደ አንተ ዓይነት ወንድም መሆን እፈልጋለሁ” ለማለት ነበር፡፡ አሊ የፈለገው መቀበል ሳይሆን መስጠትን ነው፡፡ ሁለተኛው የሁሴን ስህተት፤ አሊ መኪናውን አስቁሞ፣ ወደ ቤቱ እየሮጠ ሲገባ፣ በቆንጆ መኪና እየተንሸራሸረ መሆኑን ለቤተሰቦቹ ለማሳየት ነው ብሎ ማሰቡ ነው፡፡ ዓሊ ከቤቱ ሲመለስ መራመድ የማይችለውን (Cripple) ታናሽ ወንድሙን ታቅፎ  ነበር የመጣው፡፡ በዚህ አጋጣሚ እንደሱ እንዲንሸራሸር፡፡ መኪናዋን እያሳየው፤ “አየሃት እንደምታምር? ወንድምየው ለሁሴን የሰጠው የኢድ በረከት ናት፡፡ እኔም አንድ ቀን እንደዚች ዓይነት ቆንጆ መኪና ገዝቼ እሰጥሃለሁ፡፡ ማታ ማታ የማጫውትህን ሁሉ አንተ ራስህ በመኪናህ እየዞርክ ታያቸዋለህ” ነበር ያለው፡፡ አላሁ አክበር! አያሰኝም? !
“ራሱል አላህ - ሳልአላሁ አላይሂ ዋ ሰላም!” የእንግሊዝኛው ትርጉም “Love for your brother what you have for yourself!!” የሚል ነው፡፡
ኢድ ሙባረክ!!

Read 752 times