Sunday, 17 June 2018 00:00

አይበገሬው ልበ-ባልጩት ሰብዕና!

Written by 
Rate this item
(0 votes)


    “በስራ በዕውቀት
ግሎ ለመነሳት፣
ቆስቋሽ ይፈልጋል
የሰው ልጅ እንደ’ሳት!”
(የክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል “አጭሬ”)
መነሾ ለነገር…     
በደቡብ መለስ አመራር አካዳሚ ለክልሉ ዓቃብያነ ህግ ተዘጋጅቶ በነበረ ስልጠና ላይ ለመሳተፍ ከሐይቋ ከተማ ሐዋሳ ተገኘሁ፡፡ የስልጠናው ማጠናቀቂያ ሰሞን ግቢው ውስጥ መጽሃፍ እያዞሩ የሚሸጡ ሰዎች ተከሰቱና “ለሙያ ባልደረባችን ድጋፍ እያሰባሰብን ስለሆነ፣ ይህቺን መጽሃፍ ግዙን” ብለው ከያዟቸው መጽሃፍት ውስጥ አንዱን ሰጡኝ፡፡ የመጽሃፉ ሽፋን ያምራል፣ ርዕሱም ቢሆን ሳቢ ነው፣ “አዲስ ሕይወት” የሚልና ከሽፋን ስዕሉ ጋር ስሙም ሆኖ ይህንኑ የሕይወት ጅማሬ በትክክል የሚወክል የችግኝ ምስል ትዕምርት ሆኖ አብሮት አለ፡፡ መጽሃፉ በ-137- ገጾች “ለምን እኔ?” ከሚለው ቀዳሚው ምዕራፍ ጀምሮ፣ “ቅድመ ታሪክ” እስከሚለው ፍጻሜ፣ በ-6- ምዕራፎች እጥር ምጥን ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡
ከመጽሑፉ መግቢያ ቀጥሎ፣ “አንባቢያን ሆይ” በሚል ርዕስ የተቀመጠውን የደራሲውን መልዕክት በጥሞና ስመለከት፣ ብዙ ነገሮች ውስጤ ተመላለሱ፡- “አሁን ይህንን መጽሃፍ በምታነብበት ሠዓት በተለያዩ ችግሮችና ሁኔታዎች ውስጥ ትሆናለህ… እስቲ ምንም ነገር ከመወሰንህ በፊት ወይም የማማረር ህይወትህን ከመቀጠልህ በፊት ስለ ራሴ ልንገርህ። ይህንን መጽሃፍ በምጽፍበት ሰዓት በደረሰብኝ ጉዳት ከአንገቴ በታች ያለውን ሙሉ የሰውነቴን ክፍል መቆጣጠርም ሆነ ማዘዝ አልችልም፡፡ እጆቼ መያዝም ሆነ መጨበጥ አይችሉም። እግሮቼ መቆምም ሆነ መራመድ አይችሉም፡፡ ሽንትም ሆነ ሰገራ አልቆጣጠርም። የተኛሁበትን ጎን መቀየርም ሆነ መገላበጥ አልችልም። ማንኛውንም እንቅስቃሴ ከሰው ዕርዳታ ውጪ የማድረግ አቅም የለኝም… እንግዲያው አንተ ያለህበትንና እኔ ያለሁበትን ሁኔታ አስተያይ፡፡ ከኔ በባሰ ሁኔታ ውስጥ ነህ? አይደለህም! ብትሆን እንኳን ይህ ባንተ የደረሰው በማንም ላይ ያልደረሰ አዲስ ጉዳይ ካለመሆኑም በላይ ምንም አይነት መውጫ መንገድ የሌለው አይደለም፡፡”
ጉዳቱ የደረሰበት የመጽሃፉ ደራሲ፣ ወጣት የህግ ባለሙያ ነው፡፡ ዳግማዊ አሰፋ ይባላል፡፡ በምን ምክንያት ጉዳቱ እንደደረሰበትና የደረሰበትን ጉዳት ምንነት ስጠይቅ፣ በአካባቢው የነበሩ የሙያ መሰሎቼና የመጽሃፉ አከፋፋዮች ተያይተው፤ “እንዴት እስካሁን…?” በሚል ግርምታ ዝምታን መረጡ፡፡
ይበልጥ ግራ መጋባቴን ሲያስተውሉ ግን ታሪኩን ቀንጭበው ተረኩልኝ፡፡ ፊልም እንጂ እውነት የማይመስል መሳጭ ታሪክ ነው፡፡ ከአይረቤ የመንደር መሸታ ቤት ትርክቶች ያልወጡት ፊልመኞቻችን፣ ሊሰሩት የማይፈልጉት አይነት ፊልም፡፡
“እኔ የማውቀው ሰውዬው መሞቱን ነው” አልኩ፡፡
“አልሞተም በህይወት አለ!” ተባልኩ፡፡
እናም ራሴን እንዲህ አልኩት፤ “አንተ ሰው ሆይ! የምታውቀው የታሪኩን ከፊል ገጽታ ብቻ ነውና፣ ለሌላው የከፊል ገጽ ዕውቀት ይህ መጽሃፍ ያስፈልግሃል!” የአራተኛ አመት ተማሪ እያለሁ፣ አንድ መምህራችን ይህንኑ ጉዳይ አንስቶ፣ የህግ ባለሙያ መሆንን ከባድነት ማሳያ አድርጎ ሲናገር አስታውሳለሁ። ትኩረት ነፍጌው’ንጂ በወቅቱ ብዙ መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበርም ይታወሰኛል… እነሆ የታሪካችን ተራኪ፣ ትርክቱን እንዲነግረኝ ጉጉቴና ሙሉ ፈቃዴ ሆነ፡፡
ህይወት ብርቅርቅታ!
የሰው ልጅ ህይወት ሁለት ገጽታዎች አሏት። በህይወት የመጀመሪያው ምዕራፍ ውስጥ ሰው፤ ከልደት እስከ ሞቱ በፈተና የተከበበና አንድም ለድልና ሽልማት፣ አንድም ለሌላ ዙር ፈተና የሚታጭበት ሲሆን የህይወት “ምዕራፍ ሁለት” ደግሞ የማሸነፍ ትግል የሚካሄድበትና ብቁ ሆኖ የተገኘው በህይወት “The fittest will survive (የጸና ይኖራል!)” መርህ መሰረት፣ ኑረቱን የሚቀጥልበት ነው፡፡
እንደ ስሙ “ዳግማዊ” ህይወትን ያገኘው ዳግማዊ አሰፋ፤ የመጽሃፉን ምዕራፍ አንድ የሚጀምረው ከመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ያለ አንድ ሃይለ ቃል በመጥቀስና “ህይወት ብርቱ ሰልፍ ናት” በማለት ነው። ይህ የቅዱስ መጽሃፍ ቃል ደግሞ ህይወት በትግል የመሞላቷን እውነታ ተናጋሪ ነው፡፡ ሊያውም በህይወት ፈተና የጸኑቱ ብቻ የሚያሸንፉበት ብርቱ ትግል፡፡፡
ደራሲው የአስረኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ነበር፣ በህግ የትምህርት ዘርፍ ለመዝለቅ ከቁርጥ ውሳኔ ላይ የደረሰው፡፡ ይህን ከመሰለ አይቀለበሴ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ያደረገውም፣ ከመኖሪያ ቤታቸው ከማይርቀው የሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንድ ቀን እግር ጥሎት ሲገኝ የታዘበው የችሎት ሥነ-ሥርዓትና ድባብ ነበር፡፡ ያኔ እርሱ ለዚች ሃገር ጎበዝ ዳኛ ወይም ጎበዝ ጠበቃ መሆንን ሲያልም፣ ብዙዎች “ህግ በሌለበት ሃገር ለምን ህግ ትማራለህ? ቢቀርብህ ይሻላል!” ይሉት እንደነበርም ጽፏል፡፡
በእርግጥ ይህን አባባል ሳይሰማና ምናልባትም ራሱ ለራሱ ሳይለው የቀረ የህግ ተማሪ የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ዳግማዊ ከህግ ትምህርት ቤት ከተመረቀ በኋላ በዚሁ በሚወደው የጥብቅና ሙያ ተሰማርቶ፣ ገና በያኔው የተማሪነትና የወጣትነት ዘመኑ ከሚያውቀው፣ ገና ያኔ ህግ የመማር ውሳኔውን ያጠነክርለት ከነበረው፣ “ይህ መጽሃፍ መታሰቢያነቱ ዓይኔ እያየ በግፍ ለተገደለው ለዳንኤል ዋለልኝ ይሁን” ላለለት የህይወት ዘመን ጓደኛው፣ ዳንኤል ዋለልኝ ጋር የጥብቅናን ስራ ጀመረ፡፡
በዚሁ የጥብቅና ስራ ላይ እያለ ነበር አገልግሎታቸውን የፈለገ አንድ ደንበኛ እነሱ ቢሮ የመጣው፡፡ ይህ ሰው ከአንድ ሌላ ሰው ላይ በሐዋሳ ከተማ የሚገኘውን “ብሉ ናይል” የተሰኘ ዕውቅ ሆቴል፣ በ35 ሚሊዮን ብር የገዛ ሰው ሲሆን የሚፈልገው የጥብቅና አገልግሎት ደግሞ ሆቴሉን የሸጠለት ግለሰብ፣ የመንግስትና የህዝብ ድርሻ የሆነውን 3 ሚሊዮን ብር ግብር አልከፍልም በማለቱ፣ ገዢው ከራሱ ከፍሎ ስለነበር፣ ይህንን በትርፍ የከፈለውን እላፊ ገንዘብ ሆቴሉን ከሸጠለት ሰው ማስመለስን ወይም መቀበልን የሚመለከት ነበር፡፡
ሆቴሉን የሸጠው ግለሰብ በአንጻሩ የመንግስትን ድርሻ ላለመክፈል ይደራደራቸው፣ ሆን ብለው እንዲሸነፉና ያቀረበላቸውን የ600 ሺህ ብር እጅ መንሻ እንዲወስዱ ያስፈራራቸውም ነበር፡፡ ሰውዬው ታምራት ሙሉ ይባላል፡፡ የመንግስትን ግብር በማጭበርበር ወንጀል ተከሶ በሌለበት የ12 ዓመት እስር የተፈረደበትና በፖሊስ እየተፈለገ ያለ ሰውም ነበር፡፡ ዳግማዊ መስከረም 27 ቀን 2007 ይህንን ሰው ቢሯቸው በር ላይ መኪና ሲያቆም አየው፡፡ “ትኩር ብሎ ላየው ሰው ግርማ ሞገሱ እንኳን ወንጀል የሚፈጽም ክፋት የሚያውቅም አይመስልም፡፡” ይለናል በትረካው-(ገጽ-103) ሰውዬው ግን የልቡን በልቡ የያዘ ነበር፡፡
በዚህ ዕለት ጠበቃውን ዳንኤልንና ረዳቱን ዳግማዊን ቢሮ ሳያገኝ የተመለሰው ይህ ሰው፤ በማግስቱ መስከረም 28 ንጋት ላይ መጣ፡፡ ዳንኤልና ዳግማዊ እየተነጋገሩ ነበር፤ ሰውየው ኮፍያ አድርጎና በጃኬት ተጀቡኖ ከቢሯቸው የተከሰተው፡፡ ሁሉም ነገር በፍጥነትና ቅጽበታዊ ሆኖ ተከናወነ… ክፍሉ በጥይት ባሩድ ሽታ ተሞላ፡፡ ሰውዬውም ከመጣበት ፍጥነት በፈጠነ ሁኔታ ከቢሮው ሮጦ ወጣ፡፡ ድንጋጤ፣ ደም፣ ስቃይ ያዘለ የጣር ጩኸት…. ከዚህ ዝብርቅርቅ መልስ የዳግማዊ አይኖች የዳንኤልን ጣርና ደም ተመለከቱ….. “ያዙት!.. ያዙት!” እያለ ሰውዬውን መከተል ሲጀምርም፣ ተባራሪው መውጫ በር ላይ ደርሶ ነበር፡፡ ወደ ዳግማዊ ዞረ፡፡ አነጣጠረና አንዲት ጥይት ተኮሰ፡፡ ዳግም በዚያች ቅጽበት የሆነውን እንዲህ ይተርከዋል፡-
“አንድ ነገር በቀጥታ አንገቴ ላይ መጥቶ ሲሰነቀርና መላው ሰውነቴን የመደንዘዝ ይሁን የመጎተት ስሜት ሲወረኝና ሲነዝረኝ ተሰማኝ፡፡ ራሴን መቆጣጠርም ሆነ ሚዛኔን መጠበቅ አልቻልኩም፡፡ ከአምስተኛው ደረጃ በቀጥታ ቁልቁል ወደ ታች በግንባሬ ወደቅኩ… አንድ ከውሃ ወፈር ያለ ጣዕሙን አሁን በቃል ለመግለጽ የሚከብደኝ ፈሳሽ ነገር ከግንባሬ ወርዶ አፌ ውስጥ ሲገባ ታወቀኝ፡፡ ደም፡፡ ደም ነው፡፡ በግንባሬ ስወድቅ የደረጃው ጠርዝ መሃል አናቴን ተርትሮት ስለነበር፣ ከዚያ የሚፈስ ደም ነው፡፡” (ገጽ-101)
ዳግም ሲቀጥል፤ የሁላችንንም ሃሳባዊ እውነት ነው የሚነግረን፡፡ “እንዲህ አይነት ነገር በእኔ ሕይወት ይሆናል ብዬ አስቤም አላውቅም፡፡ ጉዳት ስለደረሰባቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ የሰማሁ ቢሆንም፣ ጉዳቶች በሌሎች እንጂ በእኔ የሚደርስ ክስተት ይሆናል ብዬ ገምቼ አላውቅም። ለካ ሰው የሚችለው ማለምና ማቀድ ብቻ ነው፡፡ ለካ ሰው ከቤቱ የሚወጣው ምን እንደሚገጥመው አንኳን ሳያውቅ ነው፡፡ ለካ ለስራ ብሎ ለሞት የሚወጣ ብዙ ሰው አለ፡፡” ይለናል፡፡
የዳግማዊ ፈተና በዚህ ብቻ አልተገደበም፡፡ ከዚህ ክስተት በኋላም ህይወቱ ከተደጋጋሚ አደጋዎች ተርፋለች፡፡ ሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል እሱ የተኛበት ክፍል ውስጥ ያለው ኦክስጂን ፈንድቶ ለጥቂት ተርፏል። (ገጽ-107)
ስለ አምቡላንስ ጉዞ ፈታኝነት የነገረን ቁምነገር እንዳለ ሆኖ፣ ለተሻለ ህክምና በሚል በአምቡላንስ ከሐዋሳ ወደ አዲስ አበባ ኮሪያ ሆስፒታል ሲመጣ፣ “ኦክስጂን አለቀ!” መባልን የሰማበትን ቅጽበት ሲተርክልን፣ እኛ ከቁምነገር የማንጥፋቸውን የፈጣሪ ጸጋዎች እርሱ እንዲህ እያስተዋላቸው ነበር፡- “ሁሉም ሰው ደነገጠ፡፡ እኔ ደግሞ የበለጠ ደነገጥኩ፡፡… ሀገሩን ሁሉ የሞላው አየር ሆኖ፣ አብረውኝ ያሉትና ሌሎችም ሰዎች ሁሉ የማያሳስባቸው አየር ለእኔ ግን አለቀ፡፡ ምግብ አይደል እየተራብኩ አልጓዝም፡፡ መጠጥ አይደለ እየተጠማሁ መንገዱን አልቀጥልም፡፡ ያለቀው አየር ነው፡፡ ለካ ቀን ሲከፋ አየርም ያልቃል… የምንተነፍሰው አየር በክፍያ የሚገኝ ቢሆን ለአንድ ደቂቃ የምንከፍለው ክፍያ ስንት ይሆን?” (ገጽ-109)
ለምን?… ለምን አኔ ላይ?
ብርቱው ሰው፤ “ለምን እኔ?” በሚል ርዕስ ለመጽሃፉ የመጀመሪያ ምዕራፍ መግቢያነት የተጠቀመበትን ፈረንጃዊ ብሂል እዚህ ልድገመው፡- “When life puts you in tough situations, don’t say “Why me?” Just say “try me!” (ሕይወት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስታስቀምጥህ፣ ‹ለምን እኔን?› ብለህ አትልፈስፈስ፡፡ ይልቁንም ‘እስኪ እንሞካከር!’ ብለህ ለትግል ተዘጋጅ‘ንጂ! እንደ ማለት”
ሃዘንና ደስታ እንደ ሌትና ቀን ተፈራራቂ  የህይወት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ዳግማዊም አደጋው ከተከሰተበትና ህይወቱ እሱ ካሰበው በሌላ አቅጣጫ መቀጠሏን ሲያስተውል፣ ይህንኑ ጥያቄ መጠየቁ አልቀረም፡፡ “ብዙዎቻችን መልካም በሆንንና መልካም ባሰብን፣ ያላሰብነው መከራ ወደ ሕይወታችን ሲመጣና ሕይወታችን ላይ በጎ ያልሆነ ለውጥ ሲከሰት የምንጠይቀው የመጀመሪያው ጥያቄ ‘ለምን?’ ‘ለምን እኔ?’… የሚል ነው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ “ለምን?” ብለን የምንጠይቅባቸው ነገር ግን በቂ ምላሽ የማናገኝባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ ሞት፣ ህመም፣ ማጣት፣ መራብ፣ የተፈጥሮ አደጋና የመሳሰሉት ችግሮች ፈልገንም ይሁን ሳንፈልግ ፣ለምን፣ እንድንል ያደርጉናል፡፡ የምንኖርባት ዓለም እንቆቅልሽዋ ብዙ ነው፡፡” ይለናል፡፡ የዚህን ጥያቄ ተፈጥሯዊነትና ምክንያታዊነት በመግለጽም ከፈጣሪ ጋር የተሟገተባቸው ቀናት በርካታ እንደነበሩ እንዲህ ጽፎልናል፡-
“ከ12 ዓመቴ ጀምሮ በእግዚአብሄር ቤት ሳገለግል አድጊያለሁ፡፡ ይህንን አደጋ እስካስተናገድኩበት ጊዜ ድረስም አገልጋይ ነበርኩ፡፡ በዚህም ምክንያት ጤነኝነትና ከአደጋ የጸዳ ነጻ ሕይወትን እንደ መብት ይገባኛል ብዬ እቆጥር ነበር… እግዚአብሔር እንዴት እኔን አገልጋዩን ለዚህ አደጋ አሳልፎ ይሰጣል…? ብያለሁ፡፡  “አይገባኝምም” ብያለሁ፡፡  “አይገባህምም” ተብያለሁ፡፡ ይህንኑ ጥያቄ ደጋግሜ እያነሳሁም ለወራት ቆይቻለሁ፡፡” ይለናል፡፡
የዳግም የህይወት ፍልስፍና በጊዜ ሂደት ስለመቀየሩና ይህ የምሬት አመለካከት የተሳሳተ መሆኑን በመረዳት “ለምን እኔ እንዲህ ሆንኩ?” እያለ ባጉረመረመ ልክ “ለምን ሌላው እንዲህ አልሆነም?” እያለ እንደሆነ ተረድቷልና፣ ይህም የጠነነ ራስ ወዳድነት ሆኖበታል፡፡ እርሱ በሌሎች ላይ ሊፈርድ ተገቢ እንዳይደለ “ለምን እኔ?” ብሎ እንደተማረረና ችግርን ለሌሎች እንደተፈጠረ አድርጎ ማሰቡን ሁሉ በመተው “ለምን ሌላውስ?” ይሉትን መልካም ትምህርት ፈጣሪው ከልቦናው አሳደረለት፡፡ የትናንት ፈተናውም እነሆ ለዛሬ የከፍታው መተረኪያ ሆነ፡፡
“አምኖ መቀበል” ከባዱ ነገር!
ታዋቂው ኮሜዲያንና የሾው አዘጋጅ ቢል ኮዝቢ “changes; becoming the best you can be” በሚል ርዕስና dedicated with love to all በሚል የእንካችሁ ስጦታ ካሳተማት ቆየት ያለች አነስተኛ መጽሃፍ መግቢያ ላይ ያነበብኩት ምክር አዘል ጸሎት “Grant me the courage to change those things I can change; Grant me the patience to accept those things I can’t change; Grant me the wisdom to the difference!” ይላል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ነገሮችን መቀበል ፈታኝና ጊዜን የሚወስድ ቢሆንም አምኖ አለመቀበሉ ለውጥ የማያመጣልን ከሆነ ግን ሲያማርሩ መኖር ለሌላ የከፋ ምሬት ይዳርጋል፡፡
ዳግማዊም በተደጋጋሚ የሚነግረን ነገር መቀበሉ፣ የመናገርን ያህል ቀላል እንዳልሆነ ነው፡፡ “ነገሩ ሁሉ ግን በህልሜ ይመስለኛል፡፡ በመሃል ከእንቅልፌ የምነቃ እየመሰለኝ እጠብቃለሁ፡፡ አዎ እነቃለሁ! .... ህልም መሆን አለበት፡፡ አስቀያሚና መጥፎ ህልም። ነገር ግን ሁሉም ነገር እውነት ነው፡፡ ለመቀበል የሚከብድ እውነት፡፡ እስከዚህ ሰዓት ድረስ ጉዳት እንደደረሰብኝ ባውቅም የዚህን ያህል ይሆናል ብዬ ግን አልጠበቅኩም።” (ገጽ-108)
ዳግም ሁለት አይነት መቀበልን ተቀበሉ ይለናል። የመጀመሪያው አይነት “መቀበል” ለእኛው የተሻለ ጥንካሬ ሲባል ፈጣሪ በተለያየ የፈተና ትግል ውስጥ እንደሚፈትነንና እንደሚያሳልፈን አምኖ መቀበል ሲሆን ይህም ጭቃ ውስጥ እያለ ማንም ሊረግጠው እንኳ ይጸየፈው የነበረው ወርቅ በእሳት ተፈትኖ ያለፈ ቀን የሚኖረውን ልዩ የክብር ጌጥነት አይነት ነው፡፡ ሁለተኛው አይነት “መቀበል” ደግሞ “የምትወደውን ካላገኘህ ያገኘኸውን ውደድ!” ብለን ልንጠቀልለው የምንችለው አይነት መቀበል ነው፡፡ ችግርን መቀበል አለመቻል በዚያው ልክ ለችግሩ መፍትሄ መሻቱንም ይሰውርብናልና… ይህ ማለት ችግሩን አሜን ብሎ ተቀብሎ መቀመጥን ሳይሆን ለምን እኔ ላይ እያሉ ሲያማርሩ ከመኖር ይልቅ ችግሩ አብሮን እያለም ቢሆን እንዴት በደስታ ልንኖር እንደምንችል በማሰብ፣ ቀለል ያለ ህይወት የመኖር ጥበቡን መቀበል ነው፡፡ ከተጨማሪ ጉዳት ራሳችንን መጠበቁን መቀበል፡፡
ዳግም በህይወት አለ፡፡ መኖር ብቻም አይደለም፤ ለእኛም የተረፈ ሆነ ጥንካሬው፡፡ በየጽሁፎቹ መካከል እንዲህ ይለናል፤ “ሁሉም ሰው እንዲረዳልኝ የምፈልገው እውነት ግን ነገሮች ሁሉ ቀላል ነበሩ ማለቴ አይደለም፡፡
ሰው ጠያቂ ፍጥረት ነውና “ለምን!” ብለን የምናማረርባቸው፣ ለቅሶ የምናበዛባቸውና መፈጠራችንን የምንጠላባቸው ጊዜያቶች ይኖራሉ…..።” ለምን ተረፍኩ ብሎ ራሱን ሲጠይቅ፤ ነብሱ የምትነግረው ጻድቅ መሆኑን አይደለም፡፡ ድጋሚ ዕድል የተሰጠው የተፈጠረበትን ዓላማ ፈልጎ እንዲያገኝና ለዚያም እንዲተጋ ስለመሆኑ እንጂ፡፡ “መሞትን ሁሉም ሰው ይሞታል፡፡ እገሌ ይህን አድርጓል ተብሎ መሞት ግን መልካም ነው፡፡ ያለሁበት ሁኔታ እንዳለ ሆኖ እንደ ማንኛውም ሰው ስራ እሰራለሁ… የመከራን ቀን ጎንበስ ብሎ ማሳለፍ መልካም ነውና በዝምታ የአምላኬን ቀን እጠብቃለሁ፡፡” (ገጽ-92)
ትናንት ዛሬ እና ነገ!
ዳግም በመጽሃፉ ብርሃንን እንጂ ጨለማን አይሰብክም፣ ስለ ማበብና መለምለም እንጂ ስለ መጠውለግና መድረቅ አያወራም፡፡ የሰው ልጆችን በህይወት እስትንፋስ ዛሬ ላይ የሚያኖረን የትናንቱ ትዝታና የነገው ተስፋ ነውና ዳግምም በትውስታና በተስፋ የዛሬን እያንዳንዷን ቅጽበት እየኖራት ነውና እንዲህ ይለናል፡- “በአዲሱ ሕይወት ይህንን ተርኬያለሁ፡፡ ቀን አልፎ ይህ ጨለማ ሲገፈፍ ደግሞ የምተርከው ይኖረኛል፡፡” (ገጽ-92)
“ከትላንት ተማር፣ ዛሬን ኑር፣ ለነገ ደግሞ ተስፋ አድርግ” እንዲል አልበርት አንስታይን፤ ነገ የሚባል አዲስ ቀን እስካለ ድረስ አዲስ ተስፋ ሁሌም አለ። አዲስ ተስፋ እስካለ ደግሞ አዲስ ሕይወት መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ ዳግማዊም የትናንቱን ነገር በጸጋ እንድንቀበለውና የዛሬውን ችግርም በጽናት በመቆም እንድንጋፈጠው፣ ይህንንም አሳልፈን በእምነትና በተስፋ ነገን የተሻለ ይሆናል ብለን እንጠብቀው ይለናል፡፡ (ገጽ-87) በየጽሁፉ መካከልም “ሁሉም ሰው እንዲረዳልኝ የምፈልገው እውነት ግን ሁሉም ነገር ቀላል ነው እያልኩ እንዳልሆነ ነው፡፡ አምርሬ ያለቀስኩባቸው፣ መፈጠሬን የጠላሁባቸውና አንገቴን የደፋሁባቸው ቀናት ብዙ ናቸው፡፡… ከሞት አፋፍ ላመለጠ ሰው፤ ሌላው የህይወት ትግል አይከብደውም። በከባዱ የተማረ ሰው በቀላሉ አይሸነፍም፡፡” የሚል ነው ምክሩ፡፡
ስለ “አዲስ ሕይወት”
ኤርነስት ሄሚንግዌይ “ስለ ህይወት ለመጻፍ በቅድሚያ ያንን የምትጽፈውን ህይወት ልትኖረው ይገባል፡፡” ይላል፡፡ ዳግማዊ በመጽሃፉ መግቢያ ስር ይህንን መልዕክት ሲያስቀምጥ፣ ኖሮ ያለፈውን ህይወት እንደጻፈልን እየነገረን ነው፡፡ “ብዙዎቹ ለዓለም ጠቃሚ የሆኑ መጽሃፎች ተጽፈው የተገኙት ከስደተኞች፣ ከእስረኞችና ከችግረኞች በጠቅላላው ሕይወት በብርቱ ከፈተነቻቸውና ካስተማረቻቸው ሰዎች ነው። እነዚህን መጽሐፍት እጅግ ጠቃሚና ሕይወት ለዋጭ ያደረጋቸው ከዕውቀት ሳይሆን ከልብ መጻፋቸው ነው።”
እነማን ያንብቡት?!
የዚህ ጠያቂ ንዑስ ርዕስ መልስ፤ በመጽሐፏ መግቢያ ላይ እንዲህ ተመልሷል፡- “ከአዕምሮ የተጻፉ ጽሁፎች ዕውቀትን መሰረት ያደረጉ ሲሆኑ፣ ከልብ የተጻፉ ጽሁፎች እውነተኛ የሕይወት ልምድን ተመርኩዘው የሚጻፉ በመሆናቸው፣ በጎ ለውጥና ተጽዕኖ ይፈጥራሉ… ከዚህ ቀጥሎ ያለው ጽሁፍም በተለይ በተለይ በፈተና ሸለቆ ውስጥ ላሉ ሰዎች መንገድ የሚመራና አቅጣጫ የሚጠቁም ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡”
በተስፋ መቁረጥ ድባብ ውስጥ ላሉና ለቀቢጸ-ተስፋ ፍጡን ተጠቂዎች ብቻ ሳይሆን ማንበብን የሚችሉ ሁሉ ቢያነብቡት ችግርን ለመጋፈጥ ይበረታሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ በየትኛውም የህግ ሙያ ዘርፍ የተሰማሩ የህግ ባለሙያዎች ደግሞ ይህንን መጽሃፍ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ደጋግመው ማንበብ አለባቸው ብዬም አምናለሁ፡፡ አምኜም ጋብዤአችኋለሁ፡፡
ሠላም

Read 964 times