Sunday, 17 June 2018 00:00

የለውጥ አስተማሪዎቼ!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ - (አተአ)
Rate this item
(7 votes)


      *… መንገደኛ ሆይ መንገደኛ
ትላንት አንጥፍና ዛሬን ደርብና ተኛ
ጧት በበርህ በምድራኳ
የነገ ዛሬ እስኪያንኳኳ!
(መንገደኛ፣ የብርሃን ፍቅር፣ ደበበ ሰይፉ)
*   *   *
የፍልስፍና አስተማሪዬን በጣም እወደው ነበር፡፡ ሙሉ ሰው ነው፡፡ ጣጣ የማያውቅ፣ ይሉኝታውን ያራገፈ፣ ምንም ነገር የማያስጨንቀውና ስለሰው ልጅ ሰላምና ፍትህ ተጨንቆ የሚያስብ ፣ በጣም የሚገርሙ የተለዩ ፀባዮች የነበሩት ሰው ነበር፡፡
ከምንማርበት ዩንቨርስቲ ውስጥ ከእርሱ ቢሮ እስከዋናው መንገድ የሚወስደውን መንገድ የሚያጸዱና አትክልቱን የሚንከባከቡ ሽማግሌ በራሱ ደምወዝ ቀጥሮ ያሰራ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ እኚህ ታታሪ ሽማግሌ ሁልጊዜ አትክልቱ ውስጥ ትንሽዬ መኮትኮቻቸውን ይዘው ሲዞሩ ሳይ እኔ ራሴ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ የዩንቨርሲቲው ሰራተኞች በወሩ መጨረሻ ደምወዝ ሲቀበሉ እርሳቸውም ከፋይዋ ጋር ይገቡና ለእርሳቸው ከተዘጋጀው ፔይሮል* ላይ ፈርመው ይወስዳሉ። (ያው ከአመታት በፊት ደምወዝ በባንክ አልነበረምና!) ታዲያ እርሱ ከኪሱ አውጥቶ በእጃቸው አይከፍላቸውም፣ እንደማንኛውም ሰራተኛ ከከፋይዋ ነው የሚቀበሉት፡፡
ከተማው ውስጥ  ትልቅ የመኖሪያ ቤት ነበረው … ዋናውን ቤት አከራይቶ እርሱ የሚኖረው ከአንዲት ክፍል ነበር፡፡ በወቅቱ ያናድደኝ የነበረው አለባበሱ ነበር፡፡  እንደ ህንድ አስተማሪ ተመርቄ እስክወጣ ድረስ ለአመታት ሲለብስ ያየሁት አንዲት ልብስ ብቻ ነበር፡፡ (ሁልጊዜ አንድ ልብስ ፣ ልብሱ ሲታጠብስ ምን ይለብስ ይሆን እያልኩ አስብ ነበር፡፡ ምናልባት ብርድ ልብስ እየለበሰ በግቢው ውስጥ ይውል ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይሆን ይሆናል!)
የሆነ ቀን … ከሰዓት በኋላ .. ከግቢ ወጥቼ መዋል ፈለግሁና እየወጣሁ እያለ በሩ አካባቢ የጥበቃዎቹን በር አለፍ እንዳልኩ፣ በደመነፍስ ወደ ጥበቃዎቹ መቀመጫ ዞር ብል፣ አስተማሪዬ ከጥበቃዎቹና ከውጪ ለምግብ ከሚገቡት ጀብሎዎች ጋር፣ በትልቅ የፕላስቲክ መዘፍዘፊያ ከተሰጣቸው የተማሪ ትርፍራፊ ፍትፍት (ኡፋ!) ረዣዥም ጣቶቹን እየከተተ ይዘግናል፡፡ ያጣጥማል፡፡ እንዳየኝ … ፈገግ ብሎ ‹ና!› የሚል የእጅ ምልክት አሳየኝ! በመገረም አፌን ከፍቼ ለሰከንዶች ቆምኩ፡፡ ወዲያው ወደ ቀልቤ ስመልስ ደንግጬ ፈረጠጥኩ፡፡
በፍጥነት በሩን አልፌ ወደ ውጪ ወጣሁና ከአካባቢው ተሰወርኩ፡፡ (እኔ ሚስጥር አድርጌ ለአንድም ሰው አላወራሁትም ነበር፡፡ ለካ የሁልጊዜ ስራው ነውና አብዛኛው ተማሪ ያውቃል፡፡)
*   *   *
ሲያስተምር ድንቅ ነበር፡፡
ከፊት ለፊታችን መድረኩ ላይ ቆሞ እያነበነበ ያስደምመናል፣ ይሰድበናል፣ ይመክረናል፣ ያሳለፈውን አንድ የትዝታ ሰበዝ ይመዝና ያዝናናናል፡፡  በዚያ በነገረን ታሪክ ስቀን ጉዳዩን ከረሳነው ተበላን! ምክንያቱም በማንኛውም ፈተናው ላይ የሚመጡት ታሪኮች ከነዚያ የሚጨለፉ ነበሩ ፡፡ እንዲያው በአጠቃላይ ሰምተን አንጠግበውም ነበር፡፡ አፌን ገርበብ አድርጌ እያዳመጥኩ የወደፊት ህይወቴን ስተነብይ፣ አስተማሪ ብሆን እንደ እርሱ ለመሆን እመኝ ነበር፡፡ ድንገት ተናዶ ከተሳደበ፣ ስድቡ አንድና አንድ ብቻ ነበረች፣ የሆነ ነገር ስታደርግ ከያዘህ ‹አኒማል!›* ብሎ ይጮህብሃል፣ አበቃ፡፡
ድንገት የፍልስፍና ጥያቄ ይጠይቅህና ማብራራት ካቃተህ እንዲህ ሲል ይመክርሃል፡፡
(Don’t stick your ass on the wooden chair the whole day without a petit purpose, ask the direction of the library whenever it is necessary! Go and dig in to the shelves before you dig your lunch box!)
ወንድሜ …
ተቀምጠህ ከምትጠብቅ
የላይብረሪውን አቅጣጫ ጠይቅ፣
ምሳ ሳህንህን ሳትቆፍር
የላይብረሪ መደርደሪያ በርብር፡፡
(እንደማለት መሰለኝ …)
*   *   *
ከእለታት አንድ ቀን ከምሳ በኋላ ሊያስተምረን ከመምህራን መንጎራደጃ መድረክ ላይ ወጣና በፈገግታ ሽቅብ አስተዋለን፡፡ ከዚያም እንደተለመደው በአስገምጋሚ ድምፁ እንዲህ ሲል ጀመረ …
‹‹ለዚህ ለምነግራችሁ እንቆቅልሽ ነፃ ማብራሪያችሁን፣ ምልከታችሁንና አጠቃላይ ስለህይወት ያላችሁን ፍልስፍና ታሪኩ ላይ በመመርኮዝ ከአስር ገፅ በማይበልጥ ወረቀት አነስተኛ ፅሁፍ ሰርታችሁ ታመጣላችሁ፡፡ እንቆቅልሹ… የቲ-ሲየስ የመርከብ እንቆቅልሽ ይባላል! (Ship of Theseus Paradox) … እንቆቅልሹ እንዲህ ይቀጥላል፣ አነስተኛ ውይይት ልናደርግበትም እንችላለን …
የሆነ የምትወዱት ከእንጨት የተሰራ መርከብ አላችሁ!  እናም ሁሉንም አካሉን ቀስ እያላችሁ፣ አንድ በአንድ እየነቀላችሁ በሌላ ቀየራችሁት እንበል፡፡ ይህን ነገር እያንዳንዱ የመርከቡ አካል በአዲሱ እስኪለወጥ አደረጋችሁት፡፡ መጨረሻ ላይ ተሳካና እያዳንዱን አካል በሌላ ተቀየረ፡፡ ምንም ሳይቀር በአዲስ ነገር ለወጣችሁት፡፡ ታዲያ ያ መርከባችሁ የዱሮው መርከባችሁ ነው ወይስ ሌላ አዲስ ነው!፡፡ መርከቤ ራሱ ነው ትላላችሁ ወይስ ሌላ አዲስ መርከብ ነው፡፡ … (…ፀጥታ…)…››
ይቀጥልና ….
‹‹…በሚገርም ሁኔታ ከዚህኛው መርከብ ላይ የተነቀለውን እያንዳንዱን አካል ደግሞ ሌላ ቦታ ወስዳችሁ ሌላ ሙሉ ተመሳሳይ መርከብ ሰራችሁበት፡፡ ታዲያ የበፊቱ መርከባችሁ ያኛው ነው ወይስ አዲሱ እዚህ የተሰራው።  የመጀመሪያ መርከባችሁ በእርግጥ አሁን የቷ ናት! … (…ፀጥ…)…››
ክፍሉ ውስጥ ለደቂቃዎች ፀጥታ ይወድቅና ትንፋሻችን እንኳ የሚሰማበት ክፍል ይሆናል፡፡ በትንሹ የሚሰማው የመቀመጫ ወንበሮች ሲጥሲጥታ ብቻ ነው፡፡ ፀሃይ በጣም የከረረችበት ሰዓት ስለሆነ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች አይታዩም፡፡ በሙቀቱ የተነሳ የሚንጠራሩ በዝተዋል፣ በታሪኩ የተነሳ ግን እንቅልፋሞች ነቅተዋል፡፡ አተኩሬ በበሩ ክፍተት ስመለከታት መሬት የፀሃዩ ድብደባ ስለበዛባት መሸሽ ፈልጋ መደበቂያ እንዳጣች ምስኪን በተስፋ መቁረጥ ያሸለበች ትመስላለች። ውሃ ውሃ ብላ የምትጮህ ምስኪን ፡፡ አረንጓዴ ተክሎችና አበቦች አንገታቸውን ቀለስ እያደረጉ ቆመዋል፡፡ ቀትሩ ያንገበግባል፡፡
ከሰከንዶች ዝምታ በኋላ ጫጫታችን እንደሆነ ፍንዳታ በአዲስ ይፈጠራል፡፡ ሁሉም ተማሪ ማውራት ይጀምራል፡፡ ክፍላችን በኡኡታ ትናጣለች፡፡
ያንን እንቆቅልሽ እያሰብኩ፣ ፈገግ ብዬ ከጫጫታው በሃሳቤ እነጠልና፣ ከአያቴ ጋር የነበረና ያለፈ ታሪክ አስባለሁ። አያቴ የሆነ ጊዜ በትክክል ይህንን ታሪክ አስተምሮኝ ነበር። ጉዳዩን በሃሳቤ አስታውሰውና ፊቴ በፈገግታ ይሞላል፡፡ በርግጥ አያቴ የቲሲየስ እንቆቅልሽ ብሎ አላስተማረኝም፡፡ ቢሆንም ያው ነበር፡፡ ህይወት ደጋግማ የምታሳየን ነገር ነው፡፡
ድንገት አስተማሪዬ ስሜን ሲጠራው … ክፍሉ ፀጥ አለ፡፡ ደንግጬ ቀና ስል እንዲህ አለኝ …
‹‹…አልዓዛር የሆነ ሀሳብ አለው እስኪ እናዳምጠው … ›› … ዝም አልኩ፡፡ ግራ ገባኝ …
‹‹…እስኪ ያስፈገገህን ነገር አጫውተን  … መልሳችን የሚኖረው ከእንዲያ አይነት ታሪኮች ውስጥ ተሸሽጎ ነው። ለብቻ የሚያስቅና የሚያስፈግግ፣ ወይም የሚያስተክዝና የሚያስለቅስ ነገር ምርጥ ታሪክና ፍልስፍና ነው፡፡ ለብዙዎች መፍትሔ የሚሆነውም ያ ታሪክ ነው ፡፡ … ›› ሲል አበረታታኝ። ለደቂቃ አንገራገርኩና ታሪኩን እንዲህ ስል አጫወትኳቸው …
*   *   *
 የቅድመ አያቶቻችንን መቃብር ቤትና ውስጡ ያሉ ሶስት ሃውልቶችን … እኔና ታላላቅ ወንድሞቼ ሆነን በእምነበረድ አሰርተን በጨርስንበት ማታ፣ ከአያቴ ጋር ቁጭ ብለን እናወራለን፡፡ የወትሮው ፈገግታው ከፊቱ ላይ የለም፣ ጭፍግግ ብሎና በብርቱካንማ ቀለም ከምትታየው የምትጠልቅ ፀሃይ ላይ ቅዝዝ ብሎ ሳየው ፣ ቀኑን ሙሉ ደስታ ያስጨፈራት ነፍሴ ድንግጥ አለች ፡፡
‹‹ምነው አባበይ!* … ›› አልኩት ደከም ባለ ድምፅ ‹‹  … ምንም ጌታመሳይ! … እህህህ … ›› ሲል ጉሮሮውን አፀዳዳና መለስ ብሎ አስተዋለኝ ‹‹ … ትክዝ አልክኮ፡፡ የሆነ ያሳሰበህ ነገርማ እንዳለ አያለሁ፣ ነገሩን አላወኩትም እንጂ! … ››
በፈገግታ አየኝና … ‹‹ .. ጌታመሳይ … ምን መሰለህ … የቀኝ ጌታ መቃብር ቤት ነገር ነው ያሳሰበኝ…››
ቀኝ ጌታ የእርሱ አባት ናቸው፣ ለእኔ ደግሞ ቅድመ አያቴ፡፡  መቃብራቸው ከታዋቂው የስላሴ ደብር ጓሮ ያለውና ተባብረን ያሳደስነው ነው፡፡ ምን ሆነ ብዬ ደነገጥኩ … ‹‹ መቃብሩ ምን ሆነ! … ››
‹‹…እሱስ ምንም አልሆነ፣ ያው አሳመራችሁት አደል! … እንዲያው ግን የአባቴ መቃብር አልመስልህ እያለኝ ተቸገርኩ። ሊቁ ቀኝ ጌታ ያረፉበት መቃብር ቤት አይመስለኝም! … ሌላ ይመስለኛል!…››
‹‹ለምን አባበይ!... እንዴት!››
‹‹…አየህ ጌታመሳይ … ያቺ መቃብር ቤት ድሮ አባቴ ራሳቸው በሳር ክፍክፍ አድርገው፣ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ማረፊያ ትሆን ዘንድ ያሰሯት ቆንጆ ጎጆ ነበረች፡፡ ታዲያ ሲሞቱ ያሳረፍናቸው ከዚያው ነበር፡፡ እንዴት ያለች ግሩም ጎጆ ነበረች መሰለህ ልጄ፡፡ ታዲያ አባትህ ስራ እንደያዘ ሰሞን መጀመሪያ ጎጆው ይፍረስ አለና ወደ ቆርቆሮ ቀይሮ ቢያሰራው፡፡ የቀድሞ ሞገሷ ጠፍቶ ሌላ ቤት መሰለች…››
በዝግታ የሚጎትተውን ነጭ ጢሙን እያሻሸ አይኖቹን አርገበገበ፡፡ እንባው የመጣ መሰለኝ፡፡ ትንንሽ አይኖቹ በምትጠልቀው ጀንበር ታጅበው ያንጸባርቃሉ …
‹‹…ውስጡን በባህር ዛፍና በጥድ ቅጠል እንጎዘጉዘው ነበር፡፡ ሽታውና ስትረግጠው ወደ መሬት የሚሰርገው የቅጠላ ቅጠል ክምር አሁን ድረስ ትዝ ይለኛል፡፡ በየወሩ ሰንበቴ ይጠጣበት ነበር፡፡ ባሰብሁት ቁጥር ያስደስተኛል፡፡ ቀኝ ጌታን ያስታውሰኛልም፡፡ …. ኋላ ደግሞ አባትህ ወለሉን ወደ ድንጋይ ንጣፍ ቀየረውና ፍጹም ተቀየረብኝ፡፡ የወትሮው  የቤተሰቦቼ ማረፊያ አይመስለኝም፡፡ ትዝታዬና የቤተሰቦቼ መንፈስ ሁሉ ያረፈው ከሳር ጎጆዋና ከቤትዋ ላይ ይመስል ሁሉም አብረው ሸሹ፡፡ እንዲያውም ይገርምሃል ትቼው ቀረሁ፡፡ በአመት አንዴ እንኳ ስገባበት የሌላ ሰው ይመስለኝ ጀመር … ››
‹‹እህ ..›› አልኩ በድካም መልክ … የሚለው ነገር ጥቂት የገባኝ መሰለኝ …
‹‹…አሁን ደግሞ እናንተ የልጅ ልጆች መጣችሁና እንዲህ ሙሉውን በእምነበረድ ለብጣችሁ ቀየራችሁት፡፡ እና በርግጥ እሱ ራሱ ነው ወይ! በጭራሽ የቤቶቼ* ማረፊያ መስሎም አይታየኝ፡፡ ሌላ ነው … መልኩም፣ ጠረኑም፣ መንፈሱም ተቀይሯል ጌታመሳይ….››
‹‹ታዲያ … ጥሩ አይደለም አባበይ!  … የሰራነው ልክ አይደለም ማለት ነዋ! ...››
‹‹…እናንተማ ጥሩ ነው ያላችሁትን ሰራችሁ፡፡ እኔ ግን ልቤ አልቀበለው አለኝ፡፡ ይህ ቤት የድሮው ነው ወይስ ታድሶ ነው፣ ወይስ አዲስ ነው! እሱን ማወቅ አቃተኝ፡፡ የድሮው እንዳልል የለም፣ የታደሰው ሌላ ነው ምኑም የድሮውን አይመስልም፡፡ ከድሮው ያልተለወጠው ነገር የቆመበት ቦታ ብቻ ነው፡፡  እርሱም እንደድሮው ለምለም አይደለም … እግር ስለሚበዛበት ደርቋል… ››
‹‹…ታዲያ እኛ አሳመርነውና ቆንጆ አደረግነው ብለን ነበር፡፡ አንተ ደግሞ ጠላኸው ምን ተሻለ….››
በምሽቱ ለመጀመሪያ ግዜ ፊቱ ላይ ፈገግታ አየሁ … ‹‹…አየህ ጌትዬ ሁሉን ነገር አንድ ግዜ መቀየር ይከብዳል! አንድ ክፉ አመል ያለው ሰው ነገውኑ ተቀይሮ ብታየው አታምነውምኮ!  በአንዴ የተቀየረ ነገር ሌላ ይሆናል፡፡ አሁን አንተ ነገ ማለዳ ስትነሳ አርጅተህ ብትገኝ ማን ያምንሃል!  ለውጥ የሚመጣ ቢሆንም ብዙ ግዜ አዝጋሚ ሲሆን ጥሩ ነው፤ አንድ ቢራቢሮ ውቢቱን ቢራቢሮ ሆኖ ለመብረር ከዕንቁላል ጀምሮ የሚቀየረው በአንዲት ጀምበር እንዳይደለ! … እንዲሁ ሁሉን ነገር በአንድ ጀምበር ለመለወጥ መሞከር ከንቱ ነው፡፡ ድንገቴ ለውጥ የሚመጣ ቢሆንም ቅቡል ለመሆን የሚከብደው ለዚያ ነው ፤ ድንገቴ ለውጥ የሚሰራው ለፈውስና ለተዓምራት ብቻ ነው ፣ በተረፈ ህይወታችን ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡ ግና ሁሉን የጣለ ሳይሆን ያለፈበትን ምልክትና መነሻ ያደረገ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ የአገራችንን መንግስታት አታይም፣ አይበረክቱም፡፡ ለምን ብትል ከአንድ መንግስት መውደቅ በኋላ እንዳለ ገርስሰው ከአቧራ ስለሚሰሩ ነውኮ። አየህ የነበረውን ለመገንባት የደከሙና በበጎ የለፉ ሰዎች አዲሱ የነሱ አይመስላቸውም፡፡ እነሱ የለፉበት ትዝታውና የላባቸው ሽታ ከበፊቱ ጋር አብሮት ይጠፋልና፡፡
… የአባቴን መቃብር ቤት የተውኩት ለዚያ ነው፤ ለውጡ ድንገቴና የነበረንን ትዝታ ወዲያ አሽቀንጥሮ የሚጥል ነው፣ እናም የቀኝ ጌታ መቃብር ቤት ቀድሞ የማውቀው አልሆን ቢለኝ፣ እንዲያ እንደማውቀው አይነት ጠረን አልሸት ቢለኝ፣ ጭንቅላቴ ውስጥ ያለው የአባቴ ማረፊያ ትዝታ እያለ ከዚህ ከተገነባ ቤት ላይ ምን አለፋኝ ብዬ ተውኩት፡፡
ጌትዬ አዝማሪ እንዲህ ሲል አልሰማህም ወይ … ሰውየው ሚስቱን ይጠረጥራታል፣ እናም የጫጉላ ጊዜያቸው አለፍ እንዳለ አረገዝኩ ብትለው … እንዲህ አለ አሉ …
ጥርስሽን ተወቀርሽ … ዝም አልኩሽ ዝም አልኩሽ
አንገትሽ ተነቀስሽ … ዝም አልኩሽ ዝም አልኩሽ
እንደ እንጨት ሰባሪ … በየጥሻ ወደቅሽ
እንደ አልጋ አሳሪ … ስንቱን መደብ ዳበስሽ! … ዝም አልኩሽ! ዝም አልኩሽ!
ይህን ሁሉ አይቼ
ከሰው አፍ ገብቼ …. ከሰው ልኖር ብዬ … ዝም አልኩሽ ዝም አልኩሽ!
ከሁሉ የከፋ
ዘጠኝ ወሬ ገባ … ብትይኝ በአንድ አዳር
ይህን ተቀብዬ እንዴት ልዋል ልደር! …››
የአባበይ ትምህርት በዝምታና በዝግታ በልቤ ሲሰርግ ይታወቀኝ ነበር፡፡ ለውጥ አዝጋሚ ሲሆን ሰላማዊ መሆኑን፣ ነውጥ  ደግሞ ድንገቴ ሆኖ ሃይለኛ መሆኑን የተማርኩ መሰለኝ፡፡
*   *   *
የፍልስፍና ትምህርቴን የአያቴን ታሪክ በማውራት ብ። በጽሁፍ ሰርቼ ማስገባት ሳያስፈልገኝ … የዚያኑ ቀን ሙሉ ማርክ ተሰጠኝ፡፡ ልክ ታሪኩን አውርቼ ስጨርስ አስተማሪዬ መዳፎቹ እስኪቃጠሉ አጨበጨበ፡፡ እንባ ባጤዙ አይኖች በፍቅር እያስተዋለኝ … ‹‹ እውነትም ጌታመሳይ! … በሉ አጨብጭቡለት፣ በአሳይመንቱ ሙሉ ማርክ ሰጥቼዋለሁ! ..›› ቢል … ክፍላችን በጭብጨባ ተናወጠች፡፡
ላቤን ከግንባሬ በሹራቦቼ እየጠረግሁ ተገረምኩ…፡፡
እስከ ዛሬው የህይወት ጉዞዬ የሁለቱ አስተማሪዎቼ የበጎ ምግባርና የጥሩ አመለካከት ዳና በልቤ ላይ እንዳይጠፋ ሆኖ አለ፡፡

Read 3380 times