Sunday, 17 June 2018 00:00

ማንበብ ከጀመራችሁ የማታቋርጡት ፅሁፍii

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

         የስምንት መቶ ብር ጫማ አድርጌ፣ በስምንት መቶ ብር መነፅር ፍሬም፣ በመአት ሚሊዮን ብር የተሰሩ ፎቆችን ሳስተውላቸው፣ የስሙኒ ደስታ እንኳን አልሰጡኝም፡፡ ምንም ባልተከፈለበት፣ በነፃ በተሰጠኝ አይኔ፣ የማንም ያልነውን ሰማይ ፈለግሁት … አጣሁት። የቢራ ማስታወቂያ ሊለጥፉበት ወስደውት ይሆናል ብዬ አሰብኩ። የአስራ አምስት ብር ካርድ አጉርሼ፣ የሁለት ሺ ብር ስልኩን ቀሰቀስኩት፡፡ በነፃ ወሬ የሚለጥፉ ሰዎች የሚሉትን ለማየት፣ ፌስቡክን ጥርስ በሌለው የፓስወርድ ቁልፍ ከፈትኩት፡፡
እስክሪኑን ወደ ላይ ወደ ላይ፣ ወደ ታች አንፏቀቅኩት፡፡ የስምንት መቶ ብር ጫማዬን በአምስት ብር እያስጠረግሁ፣ የስሙኒ ደስታዬን ድፍን ለማድረግ፣ አይኔ ላይ ባለመስታወት እስክሪኑን አሰስኩት፡፡ በነፃ የተሰጠኝን አንጎል የሚከፍት አንድም መረጃ የለም፡፡ “የኢያሪኮ ግንብ በጩኸት ሳይሆን “ጃ ያስተሰርያል” በሚለው ዘፈን ነው የፈረሰው” የሚሉ አቆርቋዥ ሀሳቦች፤ ከፀሐዩዋ ጋር ተዳምረው ጨጓራዬን አጋሉት፡፡ በአስራ አምስት ብር ካርድ፣ አስራ አምስት ሰዎች መሞታቸውን ሰማሁኝ። የለመድኩት ነው፡፡ በሽንት ባህር ውስጥ ተዘፍዝፈህ፣ እንባ ብታፈስ፣ የባህሩን ቀለም አትለወጠውም። ውሃን ወደ ወይን ቀይሯል መሲሁ፡፡ እኛ ደግሞ ሽንትን ወደ እንባ፡፡ አዝማሪን ወደ መሲህ፡፡ … ዋጋ የሌላቸው ነገሮች፣ ዋጋ ያላቸው መስለው ገዝፈዋል፡፡ ዋጋ ያለው ሰው በፍርሀቱ ውስጥ ተዘፍዝፎ፣ እንደ ሽንብራ ቆዳው ተሸብሽቧል። …
መሬቱ አስፋልት ለብሷል፡፡ ሰማዩ በፎቅ ተጣቧል። በስምንት መቶ ብር ፍሬም ውስጥ አድርጌ ሳያቸው፣ የስሙኒ ዋጋ ያለው ደስታ አይሰጡኝም፡፡ ዓለምን በሁለቱ ሺ ብር ሞባይል፣ በአስራ አምስት ብር ካርድ አሰስኩት፤ ግን ሁሉም ከንቱ ነው፡፡ “አይንም ከማየት አይጠግብም፣ ጆሮም ከመስማት አይሞላም” አለ ብልጡ ሰለሞን … የአፈ ታሪኩ ንጉስ፡፡
የገዛሁዋቸው ቅራቅንቦዎች ጫማና መነፅር አሊያም በእየምክኒያቱ የሚንቀጠቀጥ ስልክ የእኔ አይደሉም፡፡ አልኮራባቸውም፣ አልደሰትባቸውም፡፡ ስስት አይሰማኝም፡፡ … በፊት ለሰዎች ስስት ነበረኝ፡፡ አሁን ግን የለኝም፡፡ ምናልባት ሰዎቹ በእቃዎች ውስጥ ሲያልፉ የእቃው ባህርይ ይላከክባቸዋል፡፡ በፊት ለፊት ስታገኘው ትግባባው የነበረ ሰው፣ በስልክ ውስጥ ስታገኘው ሌላ ይሆንብሃል፡፡ መንገድ ላይ ገላምጦ ያለፈህ ሰው፣ በፌስ ቡክ ኢንቦክስ መልካም ልደት ይልሀል፡፡ እቃውን ሆኗል፡፡ ውሸታም ያልነበሩ ሰዎች፣ በስልክ ምክኒያት ይዋሻሉ፡፡ በማያምኑበት ዘመቻ ውስጥ ተዘፍዝፈው፣ በፌስቡክ ገፅ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ሜዳ ላይ የማይሳደቡ ሰዎች ይሳደባሉ፡፡ የማያደርጉትን ይዝታሉ፡፡ እዝታለሁ፡፡
ቪትዝ መኪና ውስጥ ያለ እንቶኔ፣ ባህርይው እንቶኔ - ሲደመር - ቪትዝ ነው። ፎቅ ያለው ከሆነ ደግሞ ድምሩ ይብሳል፡፡ ያሉት እቃዎች ድምር ውስጥ ሰውዬው ተነጥሎ፣ ብዙውን ጊዜ መግዘፍ አይችልም፡፡ የሚገዝፍና በእቃዎቻቸው ድምር/ክምር ውስጥ “በሳር ውስጥ እንደወደቀ መርፌ” ሆነው የማይጠፉ ይኖራሉ፡፡ ግን በጣም ጥቂት ናቸው።
ገንዘቡን የሰራውን ሰውዬ መሆንና በገንዘቡ አማካኝነት የተሰራው ሰውዬን መሆን ለየቅል ናቸው። ስልክን የመስራት አቅም ኖሮት የማያውቅ ባህል ያለውን ህዝብ፣ ስልክ ስትሰጠው፣ የተሰጠው ገፀ በረከት ውስጥ ይጠፋል፡፡ የለበሱትን ልብስ ለመምሰል የሚሞክሩ፣ በልብሳቸው ጭቆና የተጠቁ ብዙ አሉ። … ጥቃቱ አልፎ አልፎ ራስን በመጥላት መልክ ብቅ ብሎ ይሰወራል፡፡ ከቁሶች ውስጥ አልፎ የሰውን ሰብዕና ይቆጣጠራል፡፡ “የኢያሪኮ ግንብ” በህልውና በሌለበት፣ በሀይማኖት መልክ ተቆጣጥሯቸው የፈረሰውን ግንብ (የበለጠ እንዳይፈርስ፣) የሚጠብቁ የትውፊት ባሮች አሉ፡፡ እኔም ባሪያ ነኝ፡፡ ግን የእኔ ትንሽ የሚለየው ባርነቱ የት ጋ እንዳለ አውቃለሁኝ። በፃፍኩት መፅሐፍ መልሼ መፃፍና በጠባብ ሳጥን መቆለፍን አልፈልግም። … የራሴን ድምፅ መልሼ የመስማት ሰመመን ሱሰኛ እንዳልሆን እታገላለሁኝ። ቀላል አይደለም፡፡
…ለመፅሐፍ ስስት አለኝ፡፡ መጽሐፍ እቃ አይደለም፤ ሀሳብ ነው፡፡ መፅሐፍ በመሰረቱ፤ በአንድ ጊዜ ሁሉንም ዋጋ እና ምንም ዋጋ የሌለው ነገር ነው። መጽሐፍ ውስጥ ያለው ሀሳብ ሁሉ የሚቆጣጠርህ ከሆነ የሀሳብ እቃ ሆነሃል፡፡ ሀሳቡ የራስህን ጠንካራ ሰብዕና ለማነፅ ከጠቀመህ ግን አንተም ለመፅሐፉ፣ መፅሐፉም ደግሞ ላንተ እቃ አይደሉም፡፡ ሁሉም መፅሐፍ ሀሳብ አይደለም፡፡ ምንም የማይጨምር፣ የወረቀት እቃን በሀሳብ ስም መሸከም አያስፈልግም። መነፅር የተሻለ ለማየት ካላገለገለ፣ ስምንት መቶ ብር ገዝቶ፣ መሸከም የባርነት አይነተኛ መገለጫ ነው፡፡
በመሰረቱማ እቃም ተብሎ በአንድ ቅርፅና ይዘት የተጠራቀመ ነገር የሀሳብ ክምችት ነው፡፡ የበር - የመስኮት - የጓማ - የሞተርና የመቀመጫ ወንበር ጥርቅም ነው፤ “መኪና” ብለን የምንጠራው እቃ፡፡ እያንዳንዱ ቁስ በተናጠል ከጀርባው ሀሳብና አገልግሎት አለው፡፡
… አገልግሎቱን ከመፈለግ … እና “ይጠቅማል” ከሚል ምርጫ ነው እቃውን ወደ መግዛት የሚያስኬደን፡፡ የማንነት ማወዳደሪያ የሚሆነው፣ በውድነቱና በተፈላጊነቱ መጠን ነው፡፡
በሚፈለጉ ነገሮች ሽኩቻ ሌጣው የሰው ዋጋ ተራና አልባሌ ወደመሆን የሚሄድ ከሆነ ግን መሰረታዊው ነገር ተረስቷል፡፡ ሰው መሆንና ህይወት በነፃ ብዙ ሳይከፈልበት የሚገኝና በቀላሉ የሚጠፋ መሆኑ ተራ አያደርገውም፡፡ ይድበሰበስ ይሆናል እንጂ መሰረታዊው ነገር ሰው ነው፡፡ ስለ ሰው የማይገደው … ስለ ልማትም ሆነ ስለ ቁስ ፈፅሞ ቢያወራ ከሰውነት መውደቅ ነው፡፡
ሰውነት አንጡራ እውነት ነው፡፡ ሰውነት ከእቃዎችና በተለያዩ ሀሳቦች ወይም እሴቶች ውስጥ ከማለፉ በፊት በተፈጥሮ የሆነው ነገር ሀብት ነው። እውነት ነው፡፡ ያንን እውነት ሳይረሱ፣ ሳይሸራረፍ ይዞ መቀጠል ነው ትግሉ፡፡ ትግሉ ሰው ከተፈጥሮ ጋር የሚያደርገው አይደለም፡፡ ተፈጥሮን በአእምሮው አማካኝነት ገና ባይቆጣጠርም፣ መሳ ለመሳ ሆኖ መቀጠል ችሎበታል፡፡
አሁን ያቃተው ራሱን ከራሱ ነፃ ማውጣት ነው፡፡ ራሱን … ራሱ ከሰራቸውና ሊያጠፉት ከሚሞክሩ ሀሳቦች፣ ባህሎች፣ እሴቶች፣ … በአጠቃላይ በእኔ ቋንቋ፣ “እቃዎች” ነፃ ማውጣት ነው ትልቁ የወደፊት ፈተናው።   

Read 1767 times