Sunday, 17 June 2018 00:00

ኢትዮጵያዊነት ምንድነው?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ለመሆኑ ኢትዮጵያዊነት ምንድነው? እኔ እንደተረዳሁት፣ ኢትዮጵያዊነት ከአስራ ሶስት አምዶች የተሰራ የጥበብ ቤት ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት ማስተዋልና አርቆ አሳቢነት ነው
ብልሀተኛ ምርጫ ከማድረግ አንስቶ ለምንንና እንዴትን እስከ ማወቅ ይሄዳል፡፡ ሀበሻ ያለውን የትክክለኛነት ፍቅር፣ ልበ ሰፊነት፤ ለመለኛነትና ነገር አዋቂነት ያለው አድናቆት፣ ለትኩረትና አንክሮ ተዘክሮ ያለው ግዴታ እና የነግ በኔ ፍቅሩ ይህን አስተዋይነቱንና አርቆ አሳቢነቱን የሚመሰክሩለት ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊነት በትዕግስት የታሸ ጀግንነት ነው
ጨዋነቱ ወይም ያልነኩትን አለመንካቱ፣ አገር ወዳድነቱ፣ ለነፃነት ያለው ፍቅርና ታሪክ በደማቁ የፃፈለት የጀግንነት ገድሉ፣ የሞት ፍርሀትን መፀየፉና ታሪክ ሰሪነቱ የዚህ ምስክሮች ናቸው - ለሀበሻ።    
ኢትዮጵያዊነት ከግላዊነት የራቀ ማህበራዊ ፍቅር ወይም ከራስ ወዳድነት የተለየ የወገን ተቆርቋሪነት ነው
በህብረተሰቡ፣ መብትን ሳያጣጥሉ /በፈቃድ/ መብትን ሰውቶ ማገልገል ይበረታታል፣ የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ግብዝነት የሌለበት ወንድማማችነቱ፣ የማስተዋል ደግነቱና እንግዳ ተቀባይነቱ፣ የመቻቻል ትብብሩና አስታራቂነቱ፣ በሰው አክባሪነትና በጓደኛ መካሪነት ጭምር የሚገለጡት ብፅዕናዎቹ ለማህበራዊ ፍቅሩ ምስክሮች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊነት ርኩሰት የሌለበት ቅድስና ነው
ቁጥብነትና ትዕምርትን /ጨዋነትና ግብረገብነትን/ መከተሉ፣ ለቃል መታመንንና አደራ ጠባቂነትን ማንገሱ፣ ቀናነትንና የልብ ንጽህናን ማክበሩ፣ ቁምነገረኛነትን ማበረታታቱ ለዚህ ማስረጃ ሆነው የሚቀርቡ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊነት ትህትና ያልተለየው፤ የክብር መንፈስ ወይም የክብር ፀጋ ያልተለየው የትህትና መንፈስ ነው
ክብርን መጠበቅና ሰው አክባሪነት አብረው ያሉበት፤ ኩሩነትና ጭምትነት የተዳበሉበት፣ ትምክህተ እግዚአብሔርና ፈሪሀ እግዚአብሔር ያልተነጣጠሉበት ህይወት ነው፣ በህብረተሰቡ የሚንፀባረቀው፡፡ ይህን ኖሎታዊ የህሊና አያያዝ ልንለው እንችላለን፡፡ ይህም በከፍታ ጊዜ ዝቅታን፣ በዝቅታ ጊዜ ከፍታን እያሰቡ ሚዛን መጠበቅ ማለት ነው፡፡  
ኢትዮጵያዊነት የሰከነ ስሜት፣ የነቃ ህሊና ነው
ስሜቱ የሰከነ፣ የሰከነ እርጎ ተብሎ ይመሰገናል። መረጋጋት ይወደዳል፡፡ ራስን በማወቅ መደላደል፣ ደግሞም ለጉዳይ መንቃት ይደገፋል፡፡
ኢትዮጵያዊነት እንደ እባብ ልባምነት፣ እንደ ርግብ የዋህነት ነው
ልባምነት፤ ጠንቃቃነትና ራስን መጠበቅ ማለት ነው። የሚፈለገው አጉል ብልጣብልጥነትና ሞኛሞኝነት ሳይሆን ለብልጦች ብልጥ፣ ለገሮች ገር መሆን ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት የምንዳቤ ታጋይነትና የእድገት ርዕዮት ነው
እድገትን መመኘትና እድልን የማስፋት መሻት፣ መንፈስ ብርቱ መሆን ነው፡፡ የሚያስመሰግነው ከችግር ጋር መታገል፣ ትጋትና ስራ ወዳድነት፣ ባለጉዳይነትና ባለሙያነት ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት ሥርዓታዊነትና አግባባዊነት ነው
ደንቡ ምንድነው? የሚለውን ሀበሻ አስቀድሞ ማወቅ የሚሻው ነገር ነው፡፡ ጋጠ ወጥነትና ህገ - ወጥነት ውጉዝ ነው፡፡ ሁሉን እንደ አግባቡ እንደ ደንቡ መሥራትና ባህልና ወግ አክባሪነት የተመሰገነ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት ተራዳይነት ያልተለየው የእናት አባት ፍቅር ነው
እናትና አባትህን አክብር የሚለው ቃል በሰፊው የሚነገር ምክር ነው፡፡ ለእናት ያለ ልዩ ፍቅር፣ አባትን የመምሰል አኩሪነት፣ ጧሪ ቀባሪነት፣ አደራ ጠባቂነት ተፈላጊና የሚያስመሰግን ነገር ሆኖ እናገኘዋለን - በሀበሻ፡፡
ኢትዮጵያዊነት የግብረ ገብ ሥነ - ልቦና አንድነትና የአፋዊ ሥርዓት ህብር ነው
የጋራ ባህላችን በአንድ ቃል ከተነገረ ግብረ ገባዊ የጋራ ባህል ነው /ነገር ግን ብቸኛው አይደለም/ ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች እንደ ጭፈራ ባሉት አፋዊ ስርአቶችና ስነ - ስርዓቶች ሊለያዩ ቢችሉም፣ በግብረ ገብ ስነ ልቦና አንድ ናቸው፡፡ ወይም ደራሲ አያልነህ ሙላት እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ ህዝብና ማህበረሰቦች በአንድ መደብ የበቀሉ አበቦች ናቸው፡፡
 ኢትዮጵያዊነት ችኮ ድርቅና የራቀው የለምለም ጽናት ነው
ትልቅ የሚያስብለው መጀመር ሳይሆን መፈጸምና በጽናት ማስቀጠል መቻል ነው፡፡ ምክር ሰሚነትም የልባምነትና የቁም ነገረኛነት ምልክት ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት ሃይማኖተኛነትና እጅን ወደ እግዚአብሔር መዘርጋት ነው
ይህም ግልጽ ሆኖ የሚታይ ነው፡፡ ህዝቡ ሃይማኖተኛ ነው፡፡ “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፡፡” ሌሎችንም ማስረጃዎች ከምሳሌያዊና ፈሊጣዊ ንግግሮች አውጥተን ማየት እንችላለን፡፡

Read 2008 times