Sunday, 17 June 2018 00:00

ብህትውናና ዘመናዊነት

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(1 Vote)

(ክፍል - 1 የብህትውና ምንጭና ትርጓሜ)
           
    በአሁኑ ወቅት ‹‹የሀገራችንን የብህትውና ጉዞ፣ ምንጩንና አሻራውን›› በማጥናት ላይ እገኛለሁ። የሰሜኑን የሀገራችንን ክፍል የታሪክ ጉዞ፣ ባህል፣ ሃይማኖትና ማህበረሰብ በአንድነት የሚያስተሳስር ፅንሰ ሐሳብ ቢኖር ‹‹ብህትውና›› ነው፡፡ ይህ ፅንሰ ሐሳብ የሀገራችን ታሪክ፣ ፍልስፍና፣ ፖለቲካ፣ ኪነጥበብና ሥነ ፅሁፍ እንደገና የሚታይበትን አዲስ መነፅር የሚያቀብል በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በመሆኑም፣ በተከታታይ በማስነብባችሁ ፅሁፎች ላይ የብህትውናችን አሻራው እንዴት አሁን ድረስ ኪነጥበባችን፣ ሥነ ፅሁፋችንና ፖለቲካችን ላይ ሳይቀር ሰፍሮ እንደሚገኝና ይሄም እንዴት የዘመናዊነት ጉዟችን ላይ እንቅፋት እንደፈጠረ አብረን እንመለከታለን፡፡
ብህትውና የእንግሊዝኛ ተዛማጅ ቃሉ Ascetic ሲሆን፣ እንግሊዝኛውም ይሄንን ቃል መጠቀም የጀመረው Askesis ከሚለው የግሪክ ቃል በመዋስ ነው፤ ትርጉሙም ‹‹ልምምድ ወይም ስልጠና›› ማለት ነው፡፡ የጥንት ግሪኮች Askesis የሚለውን ቃል የሚጠቀሙት አካላቸውን ለስፖርት ወይም ለውትድርና ለማብቃት ነው፡፡ በመሆኑም፣ የቃሉ ጥንታዊ መነሻና ጥቅም ሃይማኖታዊ አይደለም። ቆየት ብሎ ግን Askesis የሚለውን ቃል ፈላስፎችም አእምሯዊ የሆነውን ‹‹ልምምድ ወይም ስልጠና›› ለመግለፅ ይጠቀሙበት ጀመር፡፡ ካህናት ደግሞ ቃሉን ከፈላስፎች ተቀበሉት። ፅንሰ ሐሳቡ ወደ ፍልስፍናና ሃይማኖት ውስጥ ሲገባ ግን ብህትውና (Asceticism) የሚል ፍቺ ተሰጠው፡፡
በመሆኑም በፍልስፍናዊና በሃይማኖታዊ ትርጓሜው ብህትውና ማለት ራስን ማቀብ፣ ራስን መከልከል፣ ብቻን መሆን፣ ሥጋዊና ዓለማዊ ህይወትን መተው የሚል ፍቺ አለው፡፡ ‹‹ተባሕተወ›› የሚለው የግዕዝ ቃልም የሚገልፀው ይሄንኑ ‹‹ብቸኝነትን፣ ከዓለም መለየትንና ከስጋዊ ፍላጎት ራስን ማቀብን›› ነው፡፡ በመሆኑም፣ ከዚህ በኋላ ብህትውና ስንል በዚህ ትርጓሜው ነው የምንሄደው፡፡
ብህትውና በዘመናዊው ዓለም ውስጥ በአብዛኛው በአሉታዊ ጎን ቢታይም፣ አዎንታዊ ጎኖቹን ግን ልንክድ አንችልም፡፡ ምሁራን በማንኛውም ዓይነት ጥናትና ምርምሮች ላይ ከፍ ያሉ ሐሳቦችን ለማፍለቅ በጊዜ የተገደበ ብህትውናዊ ህይወትን (የጥሞናና የማሰላሰያ የብቸኝነት ጊዜን) ይመርጣሉ፡፡ በኪነጥበቡና በሥነ ፅሁፍ ዘርፎች ውስጥም የላቁ ሥራዎችን የምናገኘው ብህትውናዊ በሆነው መንገድ የተሰሩትን ነው። በሃይማኖት ውስጥ ደግሞ ከፍ ያለው መንፈሳዊ ህይወት የሚገኘው በብህትውና እንደሆነ ይታመናል፡፡ በመሆኑም፣ ብህትውና በእኛም ሀገር የላቁ ምሁራዊና መንፈሳዊ ሥራዎችን ለመስራት በምሁራንና በመንፈሳዊ ሰዎች በብዛት የሚተገበር አስተሳሰብ ነው፡፡
በዚህም የተነሳ የዘርፉ ምሁራን ብህትውናን በሁለት ይከፍሉታል፡፡ ለምሳሌ ጀርመናዊው ሶሲዮሎጂስት ማክስ ቬበር (Max Weber) ብህትውናን ‹‹በዓለም ውስጥ የሚኖር ብህትውና›› (Inner-worldly or Secular Asceticism) እና ‹‹ከዓለም የሚነጠል ብህትውና›› (Other-worldly Asceticism) በማለት በሁለት ይከፍለዋል፡፡ ‹‹ዓለማዊው ብህትውና›› በዓለም ውስጥ የሚኖር፣ ሐብት ማፍራትን የማይቃወም ሲሆን በአኗኗሩ ግን ከብዙ ነገሮች (ለምሳሌ - ከሙዚቃ፣ ከጭፈራ፣ ከአልኮል፣ ከፖለቲካዊ ተሳትፎ፣) የሚታቀብ ነው። ከዓለም የሚነጠለው ብህትውና ግን ዓለምን ሙሉ በሙሉ ትቶ የሚመንን ነው፡፡ ቬበር ‹‹ዓለማዊ ብህትውናን ለጠንካራ የሥራ ባህል፣ ለሃብት መከማቸትና ለካፒታሊዝም ዕድገት ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጓል›› ይላል፡፡
በሌላ በኩል Cuthbert Butler የተባለው እንግሊዛዊ መነኩሴ ደግሞ ብህትውናን፤ ‹‹ተፈጥሯዊና ተፈጥሯዊ ያልሆነ›› በማለት ለሁለት ይከፍለዋል። በመጠኑ መኖር (ቅንጦትን አለመፈለግ)፣ ውድ ልብሶችን አለመልበስ፣ ስጋዊ ፍላጎቶችን መገደብ፣ አለማግባት፣ ከወሲብ መታቀብ፣ በዋሻ ውስጥ ለብቻ መኖር የመሳሰሉት ‹‹ተፈጥሯዊ ብህትውና›› ውስጥ የሚመደቡ ሲሆን፤ ራስን መግረፍ፣ ማኮላሸትና እንደ ስምዖን ዘአምድ በዓምድ ላይ ቁጢጥ ብሎ መኖር ደግሞ ‹‹ተፈጥሯዊ ያልሆነ ብህትውና›› ነው፡፡
በእኛ ሀገር ‹‹ከዓለማዊው ብህትውና›› በስተቀር ሌሎቹ የብህትውና ዓይነቶች በስፋት ሲተገበሩ ኖረዋል፡፡ ሆኖም ግን፣ ይህ የብህትውና እሳቤ በሀገራችን ሊቃውንት ተጠንስሶ የጎለመሰ አስተሳሰብ አይደለም፤ ምንጩም ክርስትና አይደለም፡፡ እሳቤው በጥንት ግሪካውያንና አይሁዳውያን፣ የቡድሂዝምና የሂንዱይዝም እምነቶች ውስጥ ሲተገበር የነበረ በጣም የቆየ አስተሳሰብ ነው፡፡ እንደ ፕሌቶኒዝም፣ ስቶይሲዝምና ማኒኬይዝም ባሉ የጥንት የግሪክና የመካከለኛው ምስራቅ ፍልስፍናዎች ውስጥ ሳይቀር ብህትውና ትልቅ የስነ መለኮትና የስነ ምግባር አስተምህሮ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
የብህትውና አስተምህሮ እንዴት ወደ ክርስትና ገባ?
ክርስትና ብህትውናን የተቀበለው ከአይሁዳውያን ሳይሆን ከግሪክ የፍልስፍና ሊቃውንት ነው፡፡ ታሪኩ እንደዚህ ነው፤ ክርስትና በአንደኛው ክ/ዘ በተወለደበት ወቅት በመካከለኛው ምስራቅ ላይ ሦስት እጅግ የዳበሩ የፍልስፍና አስተምህሮዎች ነበሩ - ፕሌቶኒዝም፣ ስቶይሲዝምና ኢፒኩሪያኒዝም የተባሉ፡፡ ይሄንን ደግሞ መፅሐፍ ቅዱስም ይመሰክራል- እንዲህ በማለት፤ ‹‹ጳውሎስም በየቀኑ በገብያ ከሚያገኛቸው የአቴና ሰዎች ጋር ይነጋገር ነበር፤ ከኤፒኩረስ ወገንና ስቶይኮች ከተባሉ ፈላስፎች ጋርም ተገናኘ” (ሐዋ 17፡ 18)፡፡
ይሄ የሚያመላክተን፣ ክርስትና በግሪኩ ዓለም የተዘራው በፍልስፍና የዳበረ መሬት ላይ መሆኑን ነው። ይሄም ለክርስትናው ትልቅ ፈተና ነበር፡፡ የሐሳብ ገበያው በተለያዩ ፍልስፍናዎች አየተጫረተ ባለበት ወቅት ላይ ነበር ክርስትና በቅዱስ ጳውሎስ አማካኝነት ይሄንን የሐሳብ ገበያ የተቀላቀለው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ፣ በወቅቱ ክርስትና አዲስ የተወለደ ጨቅላ በመሆኑ ገና የራሱን ሊቃውንት አልፈጠረም ነበር፡፡ የክርስቶስ ሐዋርያትም በእርጅና ምክንያት ብዙዎቹ አልፈዋል። በመሆኑም፣ በወቅቱ የክርስትናው ትልቁ ፈተና የሐሳብ ገበያው ላይ በብቃት የሚጫረት ልሂቃንን ማግኘት ነበር፡፡ ለምሳሌ፣ የግሪክ ፈላስፎች ለክርስትያን መምህራን ካቀረቡት የመፈተኛ ጥያቄዎች ውስጥ አንደኛው፤ ‹‹የእናንተ እግዚአብሔር ዓለሙን ከመፍጠሩ በፊት ምን ይሰራ ነበር?›› የሚል ነበር፡፡ ይሄ የሥነ ፍጥረትን፣ የሥነ መለኮትንና የጊዜን ፅንሰ ሐሳቦችን በአንድነት የያዘ ፍልስፍናዊ ጥያቄ ነው። በመሆኑም፣ ይሄንን ጥያቄ ሃይማኖታዊ በሆነው መንገድ ብቻ መመለስ አይቻልም፡፡ መፅሐፍ ቅዱስን ከጫፍ እስከ ጫፍ ብናነብም ለዚህ ጥያቄ ቃል በቃል የተቀመጠ መልስ ማግኘት አንችልም፡፡
ክርስትና እንደዚህ ዓይነት ፈታኝ የሆኑ ፍልስፍናዊ ጥያቄዎች የሚጠየቁበት ዓለምና ወቅት ላይ ነበር የተወለደው፡፡ በመሆኑም፣ ክርስትና እነዚህን ፈታኝ ጥያቄዎች በብቃት የሚመክት ልሂቃን የግድ ከግሪክ የፍልስፍና ት/ቤቶች ማስኮብለል ነበረበት፡፡ ክርስትና የራሱን ልሂቃን ሐይማኖታዊ በሆነው ትምህርት ብቻ አስተምሮ የሐሳብ ገበያውን ማሸነፍ ስለማይችል፣ የግድ የፍልስፍና ሊቃውንትን ወደ ራሱ ማምጣት ነበረበት፡፡ በተለይም ደግሞ የፕሌቶኒዝም ፍልስፍና አራማጆችን። ምክንያቱም፣ ስለ ዓለምና የሰው ልጅ አፈጣጠር፣ ስለ ነፍስና ዘላለማዊ ህይወት … በተመለከተ የፕሌቶኒዝም ፍልስፍና ከክርስትና አስተምህሮ ጋር በጣም ተቀራራቢ ስለነበር፡፡
ይሄም ስትራቴጂ ውጤታማ ሆኖ በርካታ የፕሌቶኒዝም የፍልስፍና ሊቃውንት ክርስትናን ለመቀላቀል ቻሉ፡፡ በቤተ ክርስትያን ታሪክ ውስጥ አንደኛውና ሁለተኛው ክ/ዘ ‹‹ዘመነ ሊቃውንት›› ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህ ዘመን ውስጥ ክርስትናን በፅኑ መሰረት ላይ ካነፁ አባቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ ከፕሌቶኒዝም ፍልስፍና ወደ ክርስትና የገቡ ልሂቃን ናቸው - ለምሳሌ፣ ቅሌመንጦስ፣ ኦሪገን፣ ተርቱሊያን፣ አትናቲዎስ፣ ባሲል፣ ኦገስቲን … የመሳሰሉት፡፡
ችግሩ ግን ፕሌቶኒዝም በጣም ጠንካራ የሆነ (ከላይ Cuthbert Butler ‹‹ተፈጥሯዊ›› ብሎ የገለፀው) የብህትውና አስተምህሮ ያለበት ፍልስፍና መሆኑ ነው። በፕሌቶ ፍልስፍና ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዙት ሥነ መለኮት፣ ሥነ ዕውቀት፣ ሥነ ምግባርና ፖለቲካ ናቸው። በእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሁሉ ፕሌቶ የፈጠረው አስተምህሮ ዓለምን የሚያንቋሽሽ፣ የስሜት ህዋሳትን ታማኝነት የሚጠራጠር፣ ስሜትን የሚጠየፍና ስጋን የሚበድል ነው፡፡ የፕሌቶኒዝም የፍልስፍና ሊቃውንት ወደ ክርስትና ሲገቡ እነዚህን የብህትውና አስተሳሰቦች ተሸክመው ነው የገቡት፡፡ ለምሳሌ ኦሪገን ብልቱን እስከ መቁረጥ ደርሷል፡፡
ምንም እንኳ እነዚህ ሊቃውንት በብህትውና አስተሳሰብ አስፈላጊነት በፅኑ ቢያምኑም፣ ብህትውና ዋነኛ ክርስትያናዊ ንቅናቄ ሆኖ እንዳይወጣ ግን የወቅቱ አስቸጋሪ ፖለቲካዊ ሁኔታ እንቅፋት ሆኖ ነበር፡፡ በወቅቱ ክርስትያኖች በብዛት የሚገደሉበትና የሚሰደዱበት ጊዜ ስለነበር፣ ከፍተኛውን ክርስትና ከብህትውና ይልቅ ከሰማዕትነት ያገኙ ነበር። በመሆኑም በዘመነ ሊቃውንት ጊዜ ብህትውና በክርስትና ውስጥ እምብዛም አይተገበርም ነበር፡፡ በክፍል ሁለት ፅሁፌ፣ የታሪክ ተመራማሪውን ፕ/ር ስርግው ሐብለ ሥላሴን እየጠቀስን፣ ብህትውና እንዴት ወደ ጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔ እንደገባና በነገስታቱ የተደረገለትን አቀባበል እንመለከታለን።
ከአዘጋጁ፡- (ጸሃፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህርና ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› መፅሐፍ ደራሲ ሲሆን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል)

Read 1107 times