Sunday, 17 June 2018 00:00

የዶ/ር አቢይ ዘመን

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(3 votes)

      ዶ/ር አቢይ አህመድ በአስቸጋሪ ወቅት ወደ ሥልጣን የመጡ ናቸው፡፡ እንደ ቀድሞው ጠ/ሚ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፤ እሳቸውም ሐገር የመምራት ኃላፊነትን የተቀበሉት በተደላደለ ጎዳና አልፈው አይደለም፡፡ ታዲያ ዶ/ር አቢይ አህመድ ሐገር የመምራት ከባድ ኃላፊነትን የተሸከሙት በድንገት ቢሆንም፤ ኃላፊነቱን በብቃት ለመወጣት የሚያስችል የህሊና ዝግጅት እንደ ነበራቸው በታሪካዊው የፓርላማ ንግግራቸው ከእናታቸው ጋር የተያዘዘ ፍንጭ ሰጥተውናል፡፡ እንዲሁም ለከፍተኛ ባለሥልጣናት በተዘጋጀው የገለጻ መድረክ፤ ራስን ለአንድ ዓላማ አጭቶ ለሥራ መሰለፍ ያለውን ጠቀሜታ ሲገልፁ፤ ዕድል - ዕድል የሚሆነው ተዘጋጅቶ ለጠበቀ ሰው ብቻ መሆኑን የራሳቸውን ህይወት በምሣሌ በማንሳት አብራርተዋል። ዶ/ር አቢይ አህመድ የነበራቸው የህሊና ዝግጅት፤ በድንገት የወደቀባቸውን ኃላፊነት በልበ ሙሉነት ለመቀበል ብቻ ሳይሆን፤ ኃላፊነቱ የሚጠይቀውን የመንፈስ ዝግጁነት፣ ዕውቀት፣ ክህሎትና አርአያነት ያለው የሥነ ምግባር ስንቅ እንዲይዙ ረድቷቸዋል፡፡
ዶ/ር አቢይ አህመድ ኃላፊነቱን በሙሉ ልብ መቀበል ብቻ ሳይሆን፤ ደፈር ያሉ እርምጃዎች ለመውሰድ የማያመነቱ ሰው መሆናቸውንም አሳይተውናል፡፡ ድርጅታቸው ኢህአዴግ ራሱን ሪፎርም ለማድረግ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በራሳቸው የአገላለጽ ዘዬ ለማብራራት የሚደፍሩ በመሆናቸው፤ ለአንዳንዶች ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ቢፈጥርባቸውም የእስካሁኑ ሂደት በግልጽ እንደሚያመለክተው፤ በአጭር ጊዜ ያን ጥቁር ደመና በመግፈፍ፣ ሐገሪቱ ወደ ተሟላ ሰላም እንድትመለስ በማድረግ፣ ህዝቡ ወደ ልማት ሥራ እንዲያተኩር በማድረግ ረገድ የተሳካ ሥራ ሰርተዋል፡፡
እንደምናስታውሰው፤ የምክር ቤቱ የሹመት ሥነ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ፤ ከአቶ ኃይለማርያም ጋር የጽ/ቤት ርክክብ ሲያደርጉ፤ ዶ/ር አቢይ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ቃለ ምልልስ የተናገሩት ቃል፣ ከአቶ ኃይለማርያም የተለየ ነበር፡፡ አቶ ኃይለማርያም፤ ‹‹እንደኔ በዚህ ኃላፊነት ከቆየ ሰው ካልሆነ በቀር የዚህን ኃላፊነት ክብደት ለመረዳት የሚችል ሰው አይኖርም›› ሲሉ፤ ዶ/ር አቢይ የተሰጣቸው ኃላፊነት ከባድ መሆኑን መረዳታቸው ባይቀርም፤ በንግግራቸው ጎልቶ የወጣው ቃል፣ የኃላፊነቱን ክብደት የሚጠቅስ ቃል ሳይሆን ሥራቸውን በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን የሚያሳይ ቃል ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ፤ ህዝቡ ምን መስማት እንደሚፈልግና ምንስ እንደሚያስከፋው ጠንቅቀው ከመረዳት ሳይሆን (ይህም አስፈላጊ ነው)፤ ሐገራቸው ወቅታዊና ዘላቂ ሁኔታ ምን እንደሚጠይቅ በውል በመረዳት የሚንቀሳቀሱ መሪ ይመስለኛል፡፡ ህዝባቸው ከሁሉም ነገር በላይ መስማት የሚፈልገውና የሚጠቅመው የልዩነትና የክፍፍል ድምጽን ሳይሆን፤ ኢትዮጵያዊ አንድነትን፣ ፍቅርንና የአብሮነት መንፈስን ነው፡፡ ስለዚህ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ተናግረው አይሰለቹም፡፡
ዶ/ር አቢይ የፖለቲካ ሥራቸው ቀዳሚ ትኩረት ያደረጉት፣ በህዝቡ ዘንድ ያለውን ስሜት መረዳትና ብሔራዊ የአንድነት ስሜት እንዲጠናከር የማድረግ ሥራን ነው፡፡ ጠ/ሚ አቢይ በዚህ ረገድ የፈጠሩት መንፈስ አስራሚ ነው፡፡ ህዝቡ ከልብ የተቀበላቸው መሪ መሆናቸውን ለመረዳት ብዙ ጊዜ አልፈጀብንም። የተፎካካሪ ፓርቲ አመራርና አባላትን ጨምሮ ኢህአዴግን በዓይናቸው ለማየት የማይፈልጉ ሰዎች ጭምር የእርሳቸውን መመረጥ በደስታ መቀበላቸውን ሲገልፁ መስማት አስገራሚ ነበር፡፡
ዶ/ር አቢይ አህመድ ጽ/ቤታቸውን ከአቶ ኃይለማርያም በተረከቡ ጊዜ፤ ‹‹እኔ ይህን ታላቅ ህዝብና ሐገር ያለ ምንም አድሎ ሁሉንም በእኩል በማየት፣ የሁሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኜ ኃላፊነቴን ለመወጣት ጥረት አደርጋለሁ›› ማለታቸው አይዘነጋም። በርግጥ የሁሉም ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ስሜት ለመፍጠር ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ (ምናልባትም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ) በሁለት ተቃራኒ አምባዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከልብ የተቀበሏቸውና ድጋፍ የቸሯቸው መሪ ሆነው መውጣት ችለዋል፡፡ እውነት ለመናር በዚህች ሐገር የዶ/ር አቢይን ያህል በሁሉም የሐገሪቱ ዜጎች ፊት በአንድ ጊዜ እኩል ተቀባይነትና አክብሮትን ያገኘ መሪ መኖሩ አጠራጣሪ ነው፡፡ ልብ አድርጉ፤ እንዲህ ዓይነት ተቀባይነት ያገኙት፤ ቢያንስ ባለፉት ሁለት ዓመታት ክህዝብ ጋር ሲጋጭ የከረመው የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሊቀ መንበር የሆኑ ሰው ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ እንቆቅልሹን ያጠናክረዋል፡፡
ዶ/ር አቢይ አህመድ የሚያስፈጽሙት የድርጅታቸውን ፖሊሲ ነው፡፡ በተለይም በተሐድሶ የተለዩ ችግሮችን ለመቅረፍና በድርጅቱ ውሳኔ የተቀመጡ የአሰራር ማሻሻያዎችን የሚያስፈጽሙ ቢሆኑም፤  የሚከተሉት የአመራር ዘዬ፤ በአዲስ ጎዳና የሚሄዱ እንዲመስለን ማድረግ የቻለና ህዝቡ ተስፋ በቆረጠ ስሜት ይመለከተው የነበረውን ድርጅት በአዲስ ተስፋ እንዲመለከተው ያደረገ ዘዬ መሆኑን በተጨባጭ አይተናል፡፡  በአጭሩ፤ በአንድ የፖሊሲ መስመር በሚመሩና ተመሳሳይ ፖሊሲን ለማስፈጸም ጥረት የሚያደርጉ ሁለት ሰዎች በሚከተሉት የአመራር ዘይቤ የተነሳ ሰፊ ልዩነት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ የሚያመለክት ተጨባጭ ልምድ አግኝተናል፡፡
የዶ/ር አቢይ አህመድ የአመራር ዘይቤ ‹‹ማካበድ›› የሌለበት ነው፡፡ ‹‹ማካበድ›› የሚል ቃል የተጠቀምኩት Simplicity የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ለመተርጎም ነው፡፡ Simplicity በሚለው ቃል ሊገለፁ ከሚችሉ በርካታ ነገሮች መካከል፤ ታሪካዊ ባልኩት የመጀመሪያው የፓርላማ ንግግራቸው፤ ከዚህ ቀደም ከተለመደው የድርጅታቸው ባህል ወጣ ባለ መንገድ እናታቸውን መጥቀሳቸው አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹ገና የሰባት ዓመት ልጅ እያለሁ…..›› እያሉ ሲናገሩ፤ ከአድማጫቸው ጋር በቀላሉ ያቀራርባቸዋል፡፡ የታመመ ሲጠይቁ፤ ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ፤ ከፕሬዚዳንት አልሲሲ ጋር ተነጋግረው ከወህኒ እንዲወጡ ያደረጓቸውን ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ቻርተርድ አውሮፕላን ይዘው ከመምጣት በተጨማሪ አብረዋቸው ፎቶግራፍ ሲነሱ ማየትም በSimplicity ሊተረጎም የሚችል ድርጊት ነው፡፡ ከግብጽ እስር ቤት የተፈቱት ዜጎቻችንና ለዓመታት በተቃውሞ ጎራ ተሰልፈው የቆዩ ፖለቲከኞች ስለ ዶ/ር አቢይ ሲናገሩ፤ ከአንደበታቸው የሚደመጠው የፍቅርና የወዳጅነት ስሜት Simplicity የፈጠረው በረከት ነው፡፡ ዶ/ር አቢይ ለከፍተኛ ባለሥልጣናት ባዘጋጁት የገለጻ መድረክ እንደተናገሩት Simplicity የላቀ ጥበብ ነው፡፡ በራስ የመተማመን ውጤት ነው፡፡
ዶ/ር አቢይ በፓርላማ ያደረጉት ንግግር፤ የአመራር ቅኝታቸውን የመሠረቱበት ወይም በእርሳቸው ቃል ‹‹ቶን ሴት›› ያደረጉበት ንግግር ነበር፡፡ እስከ አሁን የምናየው ክንውናቸው፣ ትኩረታቸው፤ የአመራር ዘይቤያቸው ከዚያ ንግግር የሚቀዳ ነው፡፡ ስለዚህ የተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸውን ባጸደቀበት ዕለት፣ በም/ቤቱ አዳራሽ ያደረጉት ንግግር፣ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ውብ ንግግር ብቻ አልነበረም፡፡ ‹‹ቶን ሴት›› ያደረጉበት ንግግርም ነበር፡፡ ዶ/ር በዚያ ንግግራቸው፣ ከድርጅቱ የታወቀ ባህል ወጣ ያለ ሁኔታ ለማንጸባረቅ ፈራ ተባ የማይሉ ሰው መሆናቸውን አመላክተውናል። በዚህም በግለሰባዊ የአመራር ዘዬ፣ ስልት፣ የአጀንዳ የቅደም ተከተላዊ አሰዳደር፣ አቅራረብና የዝንባሌ መለያየት ምን ያህል ከፍተኛ ልዩነት ሊፈጥር እንደሚችል ለመረዳት የሚያስችል አጋጣሚ አግኝተናል፡፡
ብዙዎቻችን እንደምናስታውሰው፤ ዶ/ር አቢይ በጽ/ቤታቸው ለከፍተኛ ባለስልጣናት በሰጡት መግለጫ፤ ባለሥልጣኖቻቸውን ሲመክሩ፤ ‹‹በተሰማራችሁበት መስሪያ ቤት ቶን ሴት አድርጉ›› ብለው ነበር፡፡ በወቅቱ እርሳቸው ከሰጡት ማብራሪያ መረዳት እንደሚቻለው፤ ‹‹ቶን ሴት አድርጉ›› ሲሉ ‹‹የአመራር ቅኝታችሁን መስርቱ›› ማለታቸው ነው። ሠራተኞቻችሁ እንዲያደርጉ የምትፈልጉትን ነገር በግልጽ የሚያመለክት ወይም ስታንዳርድ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል የአሰራር ስርዓት አጽኑ ማለታቸው ነው፡፡
እርሳቸውም ‹‹የአመራር ቅኝት የመሠረቱት›› ወይም ቶን ሴት ያደረጉት፤ ቃለ መሃላ በፈጸሙ ዕለት በፓርላማው ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግራቸው ነበር። በዚያ ንግግራቸው የተነሱ ሐሳቦችን በመመርመርና ባለፉት ሁለት ወራት ያከናወኗቸውን ዋና ዋና ተግባራት በመመልከት፤ የመሠረቱት ‹‹የአመራር ቅኝት›› ምን እንደሆነ ለመገንዘብ አንችላለን፡፡ በመጀመሪያው የፓርላማ ንግግራቸው ተደጋግሞ የተሰማውን ቃል፤ በአጽንዖት የገለጹትን ጉዳይ ወይም ‹‹ዲስኮርሳቸውን›› (ሐቲታቸውን ወይም የቃላት ምርጫቸውን) በመመልከት ‹‹ሴት›› ሊያደርጉት የፈለጉትን ‹‹ቶን›› መረዳት አንችላለን፡፡
ታዲያ ከዚህ አንጻር፤ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት የሚሉ ቃላትን ማንሳት እንችላለን፡፡ እንዲሁም ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሐገራቸው አማራጭ ፖሊሲ ይዘው የቀረቡ የዜጎች ስብስብ እንጂ ጠላቶች አይደሉም›› የሚለው ንግግራቸው፣ የአመራር ቅኝታቸውን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡
ዶ/ር አቢይ ቃለ መሃላ ከፈጸሙበት ዕለት ጀምሮ ግልጽ ያደረጉትና በተግባርም ያረጋገጡት ነገር፤ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን እንደ ጠላት የመቁጠር ልማዳዊ አተያይ እንዲሻር ማድረግ ነው። ‹‹ተቃዋሚዎችን›› እንደ ‹‹ተፎካካሪ›› የሚመለከትና በወንድማዊ መንፈስ የሚቀበል ዝንባሌአቸውን ግልጽ አድርገዋል፡፡ ያለ እነሱ ተሳትፎ ዴሞክራሲ ትርጉም የለሽ መሆኑን ከመግለጽ ጀምሮ፤ አብሮ ለመስራት ያላቸውን ዝግጁነት በማሳወቅ፤ በሐገር ቤትም ሆነ በውጭ ለሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች ጥሪ በማድረግ ‹‹ቶናቸውን ሴት›› አድርገዋል፡፡ በዚህም ከመንግስት ጋር በተለያዩ ምክንያቶች ባለመስማማት ያኮረፉና በተቃውሞ ጎራ ለተሰለፉ ኢትዮጵያውያን ‹‹የአብረን እንስራ!›› ጥሪያቸውን አብስረዋል፡፡
ይህ የጠ/ሚኒስትሩ አቋም መላ የሐገሪቱን ዜጎች ያሰደሰተ ብቻ ሳይሆን ለሐገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታም ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡ በርግጥ፤ ይህን እርምጃ በበጎ መመልክት የተሳናቸው አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ በተለይ በውጭ ሐገር ለሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ኃይሎች፣ የሰላም ጥሪ ማድረግን፣ ለሽብር ኃይሎች እውቅና እንደ መስጠት ቆጥረው ነቀፋ ይሰነዝራሉ፡፡ ትናንት ስርዓቱን በኃይል ለመናድ ጥረት ሲያደርግ ከነበረ ቡድን ጋር ለእርቅ መቀመጥ ለሐገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት መጠናከር የሚሰጠውን ጥቅም ከመመልከት ይልቅ፤ ነገሩን እንደ ሽንፈት በመቁጠር፣ የሰላም ጥሪውን በደፈናው ሲቃወሙና እርምጃውን በጥርጣሬ ሲመለከቱ አይተናል፡፡
በሌላ በኩል፤ ዶክተር አቢይ ቃለ መሃላ ከፈጸሙበት ዕለት አንስቶ ባገኙት አጋጣሚዎች ሁሉ ያለ መታከት የሚሰብኩት አጀንዳ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን አጀንዳን ነው፡፡ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን በክብር በሚያነሳሳው ንግግራቸው፤ ስሜታቸው የተነካ ዜጎች በደስታ አንብተዋል፡፡ ሴቱ - ወንዱ፤ ህጻን - አዛውንቱ በደስታ እንባ ተራጭቷል። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንን በማወደስ ለህዝብ በሚያደርጉት እጅግ ውብ ንግግሮቻቸው የተነሳ፤ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያሉት መላው የሐገራችን ዜጎች ያለ ልዩነት ለእርሳቸዉ ያላቸውን አድናቆትና አክብሮት በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልፁ ተመልክተናል፡፡
ይህ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንን የማወደስና የማክበር ጉዳይ፣ የውብ ንግግር ማድመቂያ ሳይሆን፤ የዶ/ር አቢይ አህመድ መንግስት ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን፤ እስከ አሁን ባደረጓቸው የውጭ ጉብኝቶች፣ በባዕድ ሐገራት፣ በእስር ይማቅቁ የነበሩ ዜጎችን ከወህኒ እያወጡ ወደ ሐገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ፣ ተከታታይ ጥረታቸው የተለጠ እምነታቸው መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይተዋል፡፡
ለዘመናት በመቻቻልና በፍቅር አብሮ የኖረውና በጠንካራ አንድነቱ የሚታወቀው፤ ዓለምን የሚያስደንቅ የሐይማኖት መቻቻል እሴት ገንብቶ ለዘመናት አብሮ የኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ በቋንቋና በጎጥ ተለያይቶ ሲናቆር መመልከት፤ ይህ አኩሪ የአብሮነት ባህሉና እሴቱ ክፉኛ ተሸርሽሮ፣ እርስ በእርስ በጎሪጥ የሚተያይበት ሁኔታ ተፈጥሮ ማየት፤ አልፎ - አልፎም ብሔርን መሰረት ያደረገ የጥላቻ ስሜት ነግሶ፤ ዜጎች በህገ መንግስቱ የተረጋገጠላቸውን መብት ተጠቅመው ባሻቸው ቦታ መንቀሳቀስ፤ መስራትና መኖር ሲያቅታቸው፣ ማስተዋልና ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ፣ በመቶ ሺዎች የሚፈናቀሉበት ሲፈጠር ማየት፣ እጅግ የሚያሳዝን ክስተት ነው፡፡
የኢትዮጵያውያን የጋራ ሐገራዊ ራዕይ ተዳክሞ፤ በምትኩ በጎጥ የተወሰነ ጠባብ አጀንዳ ማራመድ ተበራክቶ፤ የእርስ በእርስ ጥላቻ ወይም መናቆር እየተሰበከ፤ ዜጎች የብሔር ማንነታቸው እየተጠቀሰ ለጥቃት የሚጋለጡበት፤ ለሞትና ለንብረት ውድመት የሚዳረጉበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ሲከሰት፤ የተዳከመውን የአብሮነት፤ የአንድነትና የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንደገና በመቀስቀስ ለጋራ ራዕይ እንዲሰለፉ ከማድረግ በላይ ትልቅ ሐገራዊ አጀንዳ ሊኖር አይችልም፡፡ በእስካሁኑ ጥረትም ትልቅ ስኬት ተመዝቧል፡፡
የልማት ሥራ በመሠረቱ ፖለቲካዊ ነው። ከዚያ ቀጥሎ ነው፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ የሚሆነው። በመሆኑም፤ ጠ/ሚኒስትሩ ዶ/ር አቢይ አህመድ የተበላሸውን ፖለቲካዊ ሁኔታ ለማስተካከል በየደረሱበት ሁሉ አንድነትን በመስበክ፣ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ዳግም እንዲለመልም ብርቱ ጥረት አድርገዋል። በዚህም በዕድሜ፣ በቋንቋ፣ በብሔር፣ በማህበራዊ አቋም፣ ሌላው ቀርቶ በርዕዮተ ዓለም ልዩነት ያልተገደበ የዜጎችን ፍቅር አትርፈዋል፡፡ ገዥዉ ፓርቲ ጋር የሚያቀርብላቸው ማር እንኳን ይመራቸው የነበሩት  የተቃዋሚ (ተፎካካሪ) ፓርቲ አመራሮች ጭምር ከተለመደው ባህርያቸው ወጥተው፣ በዶ/ር አቢይ ወደ ስልጣን መምጣት ደስተኞች መሆናቸውን በይፋ ገልፀዋል፡፡
ለዘመናት ተቻችሎ፣ ተከባብሮና በደም ውል ተሳሰስሮ የኖረው ህዝብ፤ በዘረኝነት ወረርሽኝ እየታመሰ ግጭት ውስጥ ሲገባና፤  በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ ሲፈናቀሉ እየታየ፣ ችግር እንደ ሌለ ዝም ብሎ መጓዝ አይቻልም፡፡ ዛሬ ዘረኝነት የሃይማኖት ተቋማትን ጭምር ሲያውከ እያየን ነው። የእግር ኳስ ሜዳዎችና የትምህርት ተቋማት ዘርን መነሻ ያደረገ ጠብ እያስተናገዱ ነው፡፡ ስለዚህ ጠ/ሚኒስትራችን ነባሩን የህዝቦች ፍቅር፤ ወዳጅነትና አብሮነት ለመመለስ ደፋ ቀና ማለታቸው ተገቢ ነው። ዶ/ር አቢይ፤ በአጭር ጊዜ የሁሉንም ህዝብ ፍቅርና ከበሬታ ያተረፉትም በዚሁ ነው፡፡
አንዳንዶች፤ ዶ/ር አቢይ በተለመደው መንገድ፤ ጧት - ማታ፤ ‹‹ብሄር - ብሄረሰብ›› እያሉ ደጋግመው የሚናገሩ ባለመሆናቸው፤ የህዝቦች እኩልነትና የመብታቸው መከበር ደንታ የማይሰጣቸው አድርገው ይመለከቷቸዋል፡፡ ይህ የተሳሳተ አመለካከት ነው። በዚህ ወቅት አሳሳቢ ሆኖ ከፊታችን የተደቀነውን ችግር ከመከላከል በቀር ሌላ ትርጉም ሊሰጠው የሚገባ ባይሆንም፤ ለኢትዮጵያዊነት ስሜት ትልቅ ትኩረት ሰጥተው መሥራታቸውን የሚተቹና እርምጃቸውን በጥርጣሬ የሚያዩ ሰዎች አሉ፡፡
እውነት ለመናገር፤ በአርቆ አስተዋዩ የሐገራችን ህዝብ ታጋሽነትና ለዘመናት በተገነባው የህዝቦች የመቻቻል ባህል ብርታት ከአደጋ ተጠበቅን እንጂ፤ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በየቦታው ይታይ እንደ ነበረው የዘረኝነትና የጥላቻ ዘመቻ ብዛት ቢሆን ኖሮ፤ ሊቀለበስ የማይችል የሐገራዊ ህልውና ችግር ሊገጥመን ይችል ነበር፡፡
በመጨረሻም አንድ ነጥብ አክዬ ጽሑፌን ላጠቃል።
ከአቶ መለስ ወደ አቶ ኃይለማርያም የተደረገው ሽግግርም ሆነ፤ ከአቶ ኃይለማርያም ወደ ዶ/ር አቢይ ሽግግር ሲደረግ፤ በሁለቱም ጊዜ ሐገራዊ ድባቡ ጫን የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን ሁለቱን በሚዛን ቢቀመጡ የአስቸጋሪ ሁኔታው ጎልቶ የሚታየው በኋለኛው ነው። ቀደም ሲል፤ ምን ይመጣ ይሆን የሚል የሥጋት ድባብ መኖሩ የማይካድ ቢሆንም፤ የመሪ ድርጅቱ ውስጣዊ ሁኔታ ሰላማዊ የነበረ እና ከህዝቡ በኩልም የተለየ ጫና አልነበረም፡፡ በተቃራኒው፤ ሁለተኛው የሥልጣን ሽግግር የተከናወነው፤ በመሪ ድርጅቱ አባል ድርጅቶች መካከል መጠራጠር በሰፈነበት፤ ከሁለት ዓመታት በላይ የዘለቀ የህዝብ አመጽ ወይም አለመረጋጋት በተከሰተበት ሁኔታ ነው፡፡ ከዚህ አስከፊ ሁኔታ በማውጣት የተስፋ ፀሐይ ደምቆ የሚታይበት ሐገር መፍጠር የቻሉት ዶ/ር አቢይ፤ በኢኮኖሚውና በማህበራዊው መስክ የገጠሙንን አጣዳፊ ፈተናዎች በማስታገስ፤ በልማት የምትገሰግስ ሐገር እንደሚፈጥሩ ያለፉት ሁለት ወራት እንቅስቃሴዎች ጠቋሚ ይመስሉኛል፡፡  

Read 1492 times