Sunday, 17 June 2018 00:00

“የልማታዊ መንግስት አስተሳሰብ “ሸሸ ወይስ አፈገፈገ”??”

Written by  ታምራት መርጊያ
Rate this item
(2 votes)

 በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1994 ዓ.ም ነበር፥ ኢህአዴግ መራሹ መንግሥት፥ ከእንግዲህ ሀገሪቱን የማስተዳድርበት የፖለቲካ - ኢኮኖሚ ስልት፣ “የልማታዊ መንግሥት መስመር” (Developmental State path) ነው፥ ሲል በይፋ ያስታወቀው። ይሁን እንጂ፥ መንግስቱ ይህን አስተሳሰብ በህዝብ አገልጋዩ የቢሮክራሲው ክፍልም ሆነ (Civil service system)፥ በፖለቲካ መዋቅሩ ውስጥ እንዲወርድ ሲያደርግ፤ በአግባቡ ተብላልቶ፣ ዳብሮና በቂ ቅድመ ትግበራ ዝግጅት (pre-adoption preparation) ተደርጎበት ባለመሆኑ ምክንያት፤ የንድፈ ሐሳቡን ፍሬ ነገር፤ ከራሳቸው የሐሳቡ ወጣኒ ከበሩት የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊና ምናልባት በጣት ከሚቆጠሩ የአገዛዙ ሹማምንቶች ውጭ፥ ከቃላት በዘለለ ይህ ነው በሚባል ደረጃ ንድፈ ሐሳቡን  በዉል የተረዱ የአገዛዙ ባለሰልጣናትም ሆኑ የቢሮክራሲው አካላት ነበሩ ብሎ መናገር እጅግ አዳጋች ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ፥ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፥ “ዳንዲ” ብለው በሰየሙት መጽሐፋቸው ላይ፥ ቃል በቃልም ባይሆን እንደገለፁት፤ በእርሳቸው ርዕሰ ብሔርነት ዘመን “የልማታዊ መንግስት”ን ንድፈ ሐሳብን፣ እንደ አቶ መለስ ዜናዊ በአግባቡ የተረዳና መልሶ ማስረዳት የሚችል የአገዛዙ ሰው እንዳልገጠማቸው የገለጹበት አውድ፥ ለዚህ ሃቅ ተጠቃሽ ሆኖ በአስረጂነት ሊቀርብ የሚችል ነው።  “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ፡ የሐሳቡ አመንጪና ቀያሽ መሀንዲስ፤ የነበሩትን አቶ መለስ ዜናዊን ህልፈት ተከትሎ፥ ኢሕአዴግ፣ በሚመራው መንግስትና በጠቅላላው ህብረተሰብ ዘንድ ንድፈ ሐሳቡ አሻሚ ጎናጅ (Term) እና  ለትግበራ አስቸጋሪ ከመሆን አልፎ፣ የመደናገርና የብዥታ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።
በዚህ እረገድ፥ እንደ ተቃርኖናችሁ እንቆቅልሽ ሆኖ የሚነሳው ጉዳይ፥ ሐሳቡን  በቅጡ እንኳ ያልተረዱ ከቀበሌ እስከ ከፍተኛ የሓላፊነት ደረጃ..፥ ከካድሬ እስከ ተራ  የፓርቲ አባላት ድረስ የሚገኙ የአገዛዙ፥ ዘዋሪና አፋሽ አከንፋሽ ወገኖች፥ “ልማታዊ መንግስታችን” እንዲ አርጎ፥ እንዲህ ሰርቶ……፣ “በልማታዊ መንግስት መስመር” ተጉዘን፣ ይህን አግኝተን፥ ያን እንዲህ አድርገን……... እና ወዘተ.. እያሉ እምብዛም ባልተረዱትና ጭብጡን በውል ባልተገነዘቡት ጽንሰ ሐሳብ፥ በየተሰየሙበት መድረኮችና የመገናኛ አውታሮች ሁሉ፥ “ልማታዊ መንግስት” የሚለውን ንድፈ ሐሳባዊ ስያሜ፥ እንደ ወሬ ማጣፈጫነት እየተገለገሉበትና እንደ ዳዊት እየደጋገሙት፤ ተደናግረው፥ ህብረተሰቡን ሲያደናግሩት ተደጋግሞ የመታየትታቸው ነገር ነው።
ወደ ፍሬ ነገራችን ስንመለስ፥ ለመሆኑ “ልማታዊ መንግሥት” ወይም በፈረንጆቹ አጠራር “Developmental state” ማለት ምንድነው??? የሚለውን በጥቂቱ ለመመልከት እንሞክር።
በአጭሩ “ልማታዊ መንግሥት” (Developmental state) ወይም “ጠንካራ መንግስት” (hard stat) በግርድፉ ሲተረጎም፤ መንግሥት መራሽ አገር አቀፍ የምጣኔ ሃብት እቅድ (state-led macroeconomic planning) እንደ ማለት ነው። የዚህ ጽንሰ ሃሣብ ቅድመ ወጣኒና አማጭ “ቻልመርስ ጆንሰን” የተሰኘ አሜሪካዊ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና ቀድሞ የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ወይም በምህጻረ ቃል ሲ.አይ.ኤ ተብሎ የሚጠራው ተቋም አማካሪ የነበረ ሰው እንደሆነ በተለያዩ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሰነዶች ላይ ተገልጾ ይገኛል።
የልማታዊ መንግስት ጽንሰ ሐሣብ፥ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት አንስቶ እስከ 1970ዎቹ የዘለቀ፣ “የ20ኛው ክፍለ ዘመን የልማታዊ መንግስት ሞዴል” እና በምዕራቡ ዓለም ውስጥ ባለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ገፊ ምክንያት መሰረት፥ ከዛ ቀጥሎ ካሉት ጊዜያት ማለትም 1970ዎቹ፥ አንስቶ ደግሞ በተወሰነ ደረጃ የስልትና የአቀራረብ ለውጥ ተደርጎበት፥ “የ21ኛው ክፍለ ዘመን የልማታዊ መንግስት ሞዴል” በመባል በሚታወቅ ማሻሻያ  ሁለት ዓይነት መልክና ምዕራፎች ኖሮት የቀረበ ሲሆን፥ ጽንሰ ሐሳቡን በመጀመሪያ የተገበሩት ደግሞ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፣ ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ የምስራቅ ኤዥያ ሃገራት፡ ደቡብ ኮርያ፥ ጃፖን፥ ታይዋን እና ሆንግ ኮንግ... እንደሆኑ በስፋት ይገለጻል።
በርግጥም እነዚህ መንግስታት በልማታዊ መንግሥት ፍልስፍና እና መርህ በመመራት፥ ለሚመሩት ሕዝብና ሐገር እጅግ ከፍተኛ የሚባል እድገትና ብልፅግናን ማስመዝገብ ችለዋል። በተጨማሪም ከሠላሣ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ደሐና ጎስቋላ የነበረውን ሕዝባቸውን ኑሮ ቀይረው፣ ከፍተኛ ምጣኔ ሐብታዊና ማሕበረሰባዊ እምርታን በማምጣት፥ ዛሬ በዓለም በኢኮኖሚያቸው፣ ቁንጮ ከሚባሉት ሐገራት ተርታ በኩራት መሰልፈ ችለዋል።     
በልማታዊ መንግሥት ፍልስፍና እሳቤ መሰረት፥ በካፒታሊስቱና በኒዮሊበራሉ ዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ጠንካራ ኪዳኖች በመሆን የሚመለክባቸው መንግስት በገበያ ውስጥ ምንም አይነት ሚናን እንዳይኖረው በማድረግ፥ የገበያ ሀይሎች (the market forces) በመባል የሚታወቁት “የፍላጎት እና የአቅርቦት” (demand and supply) መጣጣም፤ ገበያውን ፍትሐዊ ለማድረግ የሚያስችል አቅም አላቸው (The invisible hand)፤ የሚለውን ሐሳብ “የገበያ አክራሪነት” (Market extremism) ብሎ ከመፈረጅና ከማጣጣል መነሻ በመነሳት፤ ይልቁንም “የገበያ ሐይሎች” ማለትም “ፍላጎት እና አቅርቦት” ያለ መንግስት ጣልቃ ገብነት እራሳቸውን ችለው፥ የአንድን ሀገር ሐብት ፍትሀዊና ለሁሉም ዜጎች እኩል ተደራሽ በሆነ መልኩ ማዳረስም ሆነ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ፍትሀዊና እኩል (Equitable) በሆነ መልኩ የሐገራዊ እድገቱና ልማቱ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲሁም ገበያውን ማረጋጋት አይችሉም፤ በሚል አመክንዮአዊ መሰረት (logical reasoning)፤ ይህንን ክፍት ለመሙላትና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም ሆነ የልማት ተቋዳሽነትን ለማምጣት፥ መንግሥት የግድ በልማታዊ መንግሥት መርህ መሰረት በገበያ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ በመንቀሣቀስና ጣልቃ ገብ በመሆን (Interventionist Government)፤ ዋና ዋና በሆኑና በተመረጡ የንግድ ተግባራት ውስጥ እራሱ ገብቶ የንግድ ስራዎችን በማካሄድ፣ ለህብረተሰቡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን መስጠት አንደሚገባው ይመክራል።
እንደሚታወቀው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ በሚከተሉ በተለይም ኒዮሊበራል በሚባሉት የምዕራቡ ዓለም ሐገራት፣ መንግስት በገበያ እንቅስቃሴ ውስጥ ምንም አይነት ሚና አይኖረውም፡፡ ከዚህም ባሻገርም መንግሥት ፈፅሞ በገበያ እንቅስቃሴ ውስጥ ጣልቃ አይገባም። በነዚህ ሐገራት ውስጥ በዋናነት የመንግሥት ሚና የሚሆነው፥ እንደ ቀረጥ መሠብሠብ፣ የሐገርን ሉአላዊነት ማስጠበቅ፣ ህግ የማስከበርና ፖሊሲ የማውጣት ወዘተ.... ተግባራት ሲሆኑ፤ ገበያው የሚመራው እራሱን ችሎ፣ በፍላጎት እና አቅርቦት መጣጣም ምክንያት (demand and supply factors) ብቻ ነው።
ያም ሆነ ይህ፥ የልማታዊ መንግስት መስመርና አስተሳሰብ የማረከው፥ በቀድሞው ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት፥ ይህን አስተሳሰብ በመላው መንግስታዊና የፖርቲ መዋቅሮቹ ውስጥ ገዢ ሐሳብ ሆኖ እንዲሠርጽ ለማስቻል ለበርካታ ዓመታት በብርቱ ሲጥርና ሲሰራ ቢቆይም፥ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው፥ ይህን አስተሳሰብ በውል የተረዱትን የአቶ መለስ ዜናዊን ህልፈት ተከትሎ፤ ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት፥ አስተሳሰቡን ለመተግበርም ሆነ ለማስቀጠል፥ ድህረ መለስ ዜናዊ የነበሩት ጊዜያት ብርቱ ፈተና ተጋርጦበትና እጅጉን አዳጋች ሆኖበት መቆየቱ በገሃድ የተስተዋለ ጉዳይ ነው።
 ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ ሰሞኑን ስብሰባ ያካሄደው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፥ ከዚህ አስተሳሰብ ወጣ ያለ በሚመስል መልኩ፥ ቀድሞ በአቶ መለስ የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ መሰረት “የምትታለብ ላም ማን ይሸጣል???” ተብለው የተገለጸላቸውን በመንግስት ይዞታ ሥር ያሉ፥ በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትም ሆነ በግንባታ ላይ ያሉ እንደ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴልና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ (privatization) እንዲተላለፉ፤ እንዲሁም ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ መንግስት ይዞ፣ ቀሪው አክሲዮን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፍ መወሰኑን ማሳወቁ፣ በከፍተኛ ደረጃ መነጋገሪያና ትኩረትን የሳበ ጉዳይ ሆኗል። በርግጥ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ የዚህ
አፈፃፀም የልማታዊ መንግስት ባህሪያትን በሚያስጠበቅና በጥብቅ ዲሲፒሊን ተግባራዊ እንዲደረግ ቢገልጽም፤ ብዙዎችም ግን ይህ ውሳኔ ያለተለመደና ያልተጠበቀ መሆኑን በመጠቆም፤ ጉዳዩን ከፖሊሲና ከርዮተ ዓለማዊ ለውጥ (paradigm shift) ጋር እያያዙ ሲገልጹት በስፋት ተደምጠዋል። በመሆኑም የዚህ አንድምታ የሚያመለክተው በቅርቡ የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ልሳን በሆነው አዲስ ራዕይ መጽሔት ላይ ሰፋ ባለ ሐተታ ታትሞ የወጣውና በመላው የድርጅቱ ካድሬ ዘንድ የውይይት አጀንዳና መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው “ኒዮሊበራሊዝም ሸሸ ወይስ አፈገፈገ” የሚለው ርእስ ተቀይሮ፤ በተቃራኒው አሁን ላይ “ልማታዊ መንግስት ሸሸ ወይስ አፈገፈገ?” ብለን የምንጠይቅበት ጊዜ ላይ መድረሳችን ማሳያ ሊሆን የሚችል ነው።
ዞሮ ዞሮ፥ ማንም ይሽሸ ወይም ያፈግፍግ፤ እንደ ዜጋ እኛን የሚያሳስበንም ሆነ የሚያስጨንቅ፤ ከሐገራችን ተጨባጭና ነባራዊ ሁኔታ አኳያ የሚጠቅመንና ለሁላችንም የሚበጀን የትኛው ንድፈ ሐሳብ ወይም ርዕዮተ ዓለማዊ መሰረት ነው? የሚለው ጉዳይ ነው። ይህንን ለመረዳት ደግሞ ከልማታዊ መንግሥት አስተስተሳሰብ ምን አተረፍን?  ምንስ አጎደለን?  ጉድለታችንስ ለምን ተከሰተና በምን ምክንያት ተፈጠረ?  ኒዮሊበራሊዝም ለኛ ይጠቅመናል ወይስ ይጎዳናል?  ለምን ይጎዳናልና እንዴትስ ይጠቅመናል? የሚሉ አንኳርና አስፈላጊ ጥያቄዎችን አንስተን፣ በቅጡ መጠየቅ፣ መፈተሽና ተንትኖ መረዳት ተገቢ ጉዳይ ይሆናል። ለዚህ ተግባራዊነት ደግሞ የምሁራኖቻችን ሚናና ሐገራዊ ሐላፊነት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ ይሆናል።
በዚህ ረገድ፥ ምሁራኖቻችን፥ ከልማታዊ መንግሥት የሚጠበቁ ባህሪያትና በጎ እሴቶች መካከል ለሐገር የሚበጁ እሳቤዎች፥ እንደ ብቃት ያለውና ነፃ የሆነ የቢሮክራሲ ስርዓት መገንባት (capable and autonomous beurocratic system)፥ ቁርጠኛ የፖለቲካ አመራር( Commitment among political leadership)፤ ብቃትን መሠረት ባደረገ ቅጥር የሚሾም የህዝብ አገልጋይ ስርዓት መዘርጋት ( Merit based civil service system)፤ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር (creating nation wide consensus )፤ የመንግሥትና የንግድ ግንኙነት (state-business relation) ወዘተ… የመሳሰሉ የልማታዊ መንግስት በጎ እሴቶችና ምሰሶዎች፥ በኢትዮጵያ ለምን እውን መሆን ሳይችሉ እንደቀሩና፥ የቱ ጋ ከነዚህ በጎ የልማታዊ መንግሥት እሴቶትች ጋር ተለያየን፤ የሚሉትን ጥያቄዎች፣ በጥናት በተደገፈ ትንንተና ታግዘው ያቀርቡልን ዘንድ፥ የሞራልና  ሐገራዊ ሐላፊነት እንዳለባቸው እሙን ነው።
መቼም ሌማቷ አልሞላ ብሎ ወይ የፖለቲካና ማህበራዊ አውዷ አልመችልሽ ብሏት ውድ ልጆቿን ለባዕዳን መጠቀሚያነት አሳልፋ ትሰጥ እንደሆን  እንጂ፤ ማህጸነ ለምለሟ ኢትዮጵያችን፤ የምሁር ደሃ ሆና አታውቅምና፥ ፍሬዎቿ በተለይም ውድ እናት ሐገሩ እንዲህ እጇን ዘርግታ ታደጉኝ በምትልበት ወቅት፥ ይንን ለማድረግና ችግሮቿን ነቅሶ ለማውጣትም ሆነ በቻለው መጠን የመፍትሔ አቅጣጫ ለማመላከት  ዳተኝነት የሚያሳይ፣ አቅሙ ያለው ከሷ የሆነ፣ ምሁር ይኖራል ተብል ከቶም አይታሰብም።
ለማጠቃለል፥ በዚች አጭር ጽሁፍ የተፈለገው ሐገራዊ የምርምር ጥያቄን ለማጫር እንጂ፥ የተነሳውን ጉዳይ መርምሮ መፍትሔ ለማመላከት፥ የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ አቅምም ሆነ የእውቀት ደረጃ አይፈቅድምና፤ በየትኛውም የዓለም ጫፍ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ የበለጠው  ማብራሪያና የመፍትሔ አቅጣጫ ይጠበቃል። አለበለዚያ ዳር ቆሞ መተቸት ለማንም አይበጅም፡፡
ቸር እንሰንብት!!!
ከአዘጋጁ፡- (ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻቸው፡-
feedback: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል)

Read 432 times