Sunday, 17 June 2018 00:00

“ተነስና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ”

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(6 votes)

       ኢሕአዴግ ገዥ ፓርቲ ነው፡፡ ከፍተኛ የኢትዮጵያ የመንግሥት አካል ማለትም፣ የተወካዮች ምክር ቤት ሙሉ በሙሉ የተያዘው በእሱ እጅ ነው፡፡ ምክር ቤቱ የሕዝብ ተወካዮች እየተባለ ቢጠራም፣ ሲወክል የኖረው ገዥውን ፓርቲ መሆኑ የሚጠረጠር አይደለም፡፡ እስከ ዛሬ ባለው ታሪኩም አስፈፃሚውን አካል “ከዚህ ልታልፍ አትችልም” ብሎ ሲገታው፣ ታይቶ አይታወቅም፡፡  ከአስፈፃሚው ጫማ ስር ነው ማለት ድፍረት አይሆንም፡፡
የፓርቲውና የመንግሥት ሚና ደብልቅልቁ የወጣበት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ ተሰብስቦ፣ ምክር ቤቱን ወደ ጎን በመግፋት፣ “ኢትዮጵያና ኤርትራ አልጀርስ ላይ በደረሱት ስምምነት መሠረት፣ የድንበር ኮሚሽኑ ያሳለፈውን ውሳኔ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ነን” ሲል መግለጫ ሰጠ፡፡ ይህ ማለት “የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ በመሠረተ ሀሳብ እንቀበላለን፣ ሆኖም ወደ ተግባር ለመሻገር ተጨማሪ ውይይትና ድርድር ያስፈልገናል” ሲል የኖረው ኢሕአዴግ፤ አቋሙን ቀየረ ማለት  ይሆናል፡፡
ነገር ከሥሩ እንጀምር፡፡ ኤርትራ በ1983 ዓ.ም እራሷን ነፃ አገር አድርጋ ስታውጅ፣ በምሥራቅ ከአፋር ክልል፣ በሰሜን ከትግራይ ክልል፣ በምዕራብ ከአማራ ጋር እየተዋሰነች የያዘቻቸው አካባቢዎች እንደ ነፃ ግዛቷ ሊቆጠሩላት ይችላሉ፡፡ በመሬት ላይ የተከለለና የድንበር ምልክት ያረፈበት መሬት ባይኖርም፣ የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባል አገር ሆና የተመዘገበችው በዚሁ ይዞታዋ ነው፡፡ የባድመ ወረራ ሽፋን እንጂ ዋናው ጉዳይ ሌላ እንደሆነ የሚያምኑ ብዙዎች እንዳሉ ባይዘነጋም፣ ኤርትራ ባድመን ወርራ እስከ ያዘችበት ጊዜ ድረስም፣ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ አቅርባ እንደማታውቅም መወሳት አለበት፡፡
ኤርትራ ብሔራዊ ውትድርና አውጃ ወጣቶችን ሳዋ ማሰልጠኛ እያስገባች እንደምታሰለጥን፣ ኢትዮጵያ ላይም ወረራ ልትፈጽም እንደምትችልም፣ ያላቸውን ጥርጣሬ እንደ “ጦቢያ” ያሉ የግል ጋዜጦች ደጋግመው ቢዘግቡም፣ መንግሥት ጆሮ ሊሰጣቸው አልፈለገም ነበር፡፡ በወቅቱ ከነበረው ወዳጅነታቸው አንጻር፣ “ኤርትራ አታደርገውም” ቢሉም እሷ ግን አደረገችው፡፡ “ዘመቻ ፀሐይ መውጣት” በሚል በሰየመችው፤ ወታደራዊ እንቅስቃሴ፣ ባልተጠበቀ ሰዓት፣ ያለ ምንም ተከላካይ ኃይል፣ ባድመንና ሌሎች ዋና ዋና ቦታዎችን ያዘች፡፡ ከየመን ጋር ለነበራት ግጭት ኢትዮጵያ  በሰጠቻት ልዩ ልዩ ከባድ የጦር መሳሪያም፣ ራሷን ኢትዮጵያን መልሳ ለመውጋት እንደተጠቀመችበት ይነገራል፡፡  
በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ አልተነሳም፤ የመረጠው ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማግኘት መጣር ነበር፡፡ ይህን ያደረገው ደግሞ ችግሩን በድርድር እፈታለሁ በሚል ሳይሆን  የጦር ኃይሉን ለማዘጋጀት፣ጊዜ መግዣ እንደነበር  ይታወሳል፡፡
ኤርትራ የያዘቸውን መሬት እንደያዘች ተደራድራ፣ የግዞት ወሰኗን ለማስከለል ስትፈልግ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ለወሰን ጉዳይ፣ ድርድር ውስጥ የምትገባው ኤርትራ፣ ጦሯን ከኢትዮጵያ ግዛት ካወጣችና ነገሩ ወደ ነበረበት ከተመለሰ በኋላ ነው በማለት በአቋሟ ፀናች፡፡ ጦርነት የመጨረሻ ምርጫ ሆነ፡፡ “ዘመቻ ፀሐይ ግባት” ተከፈተ። ኢትዮጵያ ከሰማኒያ ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎቿን ህይወት ሰውታ፣ በብዙ ቢሊዮን ብር የሚገመት ሃብቷን ከስክሳ፣ ጦርነቱን ባሸናፊነት ተወጣች፡፡ የጦርነቱ መጠሪያ የሆነችውን ባድመንም በራሷ በእጇ አስገባች፡፡ ኢትዮጵያ ድል አድራጊ ሆነች፡፡
በወታደራዊ ኃይል የተገኘው ድል የነገሩ መጨረሻ ሆኖ አልተወሰደም፡፡ በአልጀሪያ አግባቢነት ሁለቱ አገሮች በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው፣ ለችግራቸው “ዘላቂ መፍትሔ” ለማምጣት ተስማሙ፡፡ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት በአደራዳሪነት፣ የአፍሪካ አንድነት በታዛቢነት ተሰለፉ፡፡ ጦርነቱን ማን እንደጀመረው መለየት፣ የጦር ጉዳት ካሣና የሁለቱ አገሮች ድንበር የቱ ነው ብሎ መወሰን፣ የድርድሩ ዋና ዋና ጉዳዮች ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያና ኢጣሊያ በ1903 እና በ1908 የተዋዋሏቸው ውሎች፣ የሁለቱን አገሮች ድንበር ለመወሰን እንዲያገለግሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ሀሳብ ከማቅረቡ በላይ የድንበር ኮሚሽኑ የሚሰጠው ውሳኔ ይግባኝ የሌለውም እንዲሆን ተስማማ፡፡ አቶ መለስና መንግሥታቸው፤ እነዚህን ውሎች ከመቃብር አንስተው ለመጠቀም ያስገደዳቸው ምክንያት ምን እንደሆነ የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡  
በመስከረም 1993 ዓ.ም አቶ መለስ ዜናዊ፣ ወደ ዋሺንግተን ብቅ ብለው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጠራው ስብስባ ላይ ተገኝተውም ለተሰብሳቢው፤ የአሰብንም ሆነ የሌላውን የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ፣ በሕግ ክርክር ኢትዮጵያ የተቻለውን ሁሉ እንደምትሠራ ቃል ከመግባታቸውም በላይ የውጭ አገር ባለሙያዎች መቀጠራቸውን አስታውቀው ነበር፡፡ በዚያው ጊዜ አካባቢ ላይ የአሰብ ጉዳይ በጥያቄነት የተነሳላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍን፤ “ምን አልባት በሌላ ምዕራፍ ይነሳ ይሆናል፤ አሁን ግን አይነሳም” በማለት መልስ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡  
ከሮም፣ ከለንደን ከፓሪስ ተሰባሰበ የተባለ አምስት ሺህ ሰነድ ለድንበር ኮሚሽኑ ያቀረበው መንግሥት፤ የድንበር ጉዳይ ዋና ተከራካሪ፡- የወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መሥፍንን፣ ተባባሪ ተከራካሪ፡- አምባሳደር ፍስሐ ይመርን፣ ረዳት ተከራካሪ፡- አቶ ሰይፈ ስላሴ ለማን  አድርጎ ከርክሩ ቀጠለ፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከዩኒቨርሲቲው ውጪ አቶ ክፍሌ ወዳጆ፣ ፕሮፌሰር መርእድ ወልደ አረጋይ፣ ዶ/ር አዳነ ኃይሌ፣ አቶ ሺፈራው በቀለ፣ አቶ ፀጋዬ በርሄና አቶ ሐድጉ ገብረመድህን በሰነድ ማሰባሰብ ተግባር ላይ እንዲሳተፉ ተደረገ፡፡ ዜግነታቸው የውጭ አገር የሆኑ አምስት ጠበቆችና ስድስት አማካሪዎች መቀጠራቸውን ሪፖተር ጋዜጣ በሚያዚያ 5 ቀን 1994 ዓ.ም ዕትሙ ዘግቧል። ኢትዮጵያዊያኑ ምሁራን ሰነድ ከማቅረብ ያለፈ ቦታ እንዳልተሰጣቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ለምን ሆነ የሚለውን፣ በህይወት ያሉት ሊያስረዱን ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያዊ ጠፍቶ ነው ጠበቆችም ሆኑ አማካሪዎች፣ ሙሉ በሙሉ የውጭ አገር ሰዎች የተደረጉት? ለሚለው የዛሬ ጥያቄያችንም፣ በህወኃት ውስጥ ያሉት አቶ ሥዩም መሥፍን ቢያስረዱን ጥሩ ይሆናል፡፡
“በዳኝነት ላይ የሚገኝ ጉዳይ ነው” በሚል ምክንያት፣ በድንበር ኮሚሽኑ ዳኝነት የተደረገው የድንበር ክርክር፣ ከምን ተነስቶ ምን እንደደረሰ፣ ለባለ ጉዳዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይገለጥ እንዲቆይ ሆነ፡፡ ሚያዚያ 5 ቀን 1994 ዓ.ም የድንበር ኮሚሽኑ፣ ከሔግ ይፋ ባደረገው ጊዜ ግን ከእነ መርዶው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተገለጠ፡፡
የአቶ መለስ ዜናዊ መንግሥት፣ ለዚህ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ ያሳየው አቀባበል ተአምር የሚያሰኝ ነበር፡፡ ኮሚሽኑ ሚያዚያ 5 ቀን 1994 ጠዋት 4፡00 ላይ ውሳኔውን ይፋ አደረገ፡፡ በዚሁ ቅፅበት ውሳኔው በአልጀርሱ ስምምነት መሠረት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በአፍሪካ ህብረት ዘንድ እንዲታወቅ አደረገ፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተሰብስቦ ውሳኔውን ተቀበለው ተባለ፡፡ ባድመና ዛላንበሳ፣ ኢሮብ፣ አሊቴና፣ ባዳ፣ አደምሩግ የኢትዮጵያ አካል ሆነው ተከለሉ ተብሎ ታወጀ። ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ የወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ  ሚኒስትርና ዋናው ተጠሪ አቶ ሥዩም መሥፍን፤ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ብቅ ብለው “ድል በድል ሆነናል” ብለው፤ የምሥራቹን አሟሟቁት፡፡ የክልል መንግሥታት ለውሳኔው ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጥም ተሽቀዳደሙ፡፡
በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ኢትዮጵያን በብዙ የጎዳት መሆኑን ማጋለጡን ተያያዙት፡፡ ውሳኔው ተቀባይነት እንዳያገኝ የኩናማ፣ የኢሮብና የአፋር ሕዝብ መብት ተከራካሪ ድርጅትና የትግራይ ተወላጆች አለም አቀፍ ትብብር፣ ለጸጥታው ምክር ቤት አቤት አሉ። መልሱም፤ “በቅኝ ግዛት ውሎች መሠረት ድንበር እንዲከለል የፈለጉት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት መሪዎች ናቸው” የሚል ሆነ፡፡
 አቶ መለስ፤ “ፎርቶ፣ ጉናጉና፣ ሞኖክሰይቶ፣ ፆረና የኤርትራ ናቸው” ብለው ስለ መሰከሩ፣ ለኤርትራ መሰጠታቸው ይፋ ተደረገ፡፡ “ጦቢያ” ጋዜጣና መጽሔት፣ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ በባለሙያ አስጠንቶ ከነበራቸው ጥያቄ ኤርትራ 73 ከመቶ፣ ኢትዮጵያ 27 ከመቶ የተሳካላቸው መሆኑን አስታወቀ፡፡ በአጭር አገላለጥ፤ በጦር ሜዳ ባለ ድል የነበረችው ኢትዮጵያ፤ በድንበር ክርክሩ ፍጹም ተሸናፊ መሆኗ ቅልጥጥ ብሎ ወጣ።
ሚያዚያ 6 ቀን 1994 የአዲስ አበባና የአከባቢው ሕዝብ፣ መስቀል አደባባይ ወጥቶ፣ ለሄግ ውሳኔ ያለውን ድጋፍ በሰላማዊ ሰልፍ እንዲገልጥ ኢሕአዴግ ጥሪ አቀረበ፡፡ ግን ዝር የሚል ሰው ጠፋ፡፡ ኢሕአዴግ አፈረ፡፡ “የድንበር ኮሚሽኑ ያለ ጥያቄዋ፣ ለኤርትራ ስለሰጠው መሬት ማብራሪያ እንፈልጋለን” ሲል ለድንበር ኮሚሽኑ ፃፈ፡፡ “በማብራሪያ ስም ውሳኔ ማስቀየር አይቻልም” የሚል ቁርጥ ያለ መልስ ከኮሚሽኑ ተሰጠው፡፡ “የሄጉን ውሳኔ በመሠረተ ሀሳብ እንቀበላለን፤ ተግባራዊ ለማድረግ ግን በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ውይይት (ድርድር) እንዲኖር እንፈልጋለን” የሚል አቋም ይዞ እስከ ትናንት ድረስ እንደተገተረ ቀረ፡፡ ባለ ድሏ ኤርትራ፣ ይህን ጥሪ የሚሰማ ጆሮ አልነበራትም፡፡ አሁንም ያላት አትመስልም፡፡ “ወይ ፍንክች” ብላለች፡፡
የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፣ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም ያልተጠበቀ ውሳኔ አሳለፈ። የቀደመውን አቋም በመሻር፣ የኢትዮጵያ መንግስት፣ የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ለሕዝቡ አሳወቀ፡፡ ያንቀላፋው እሳት ተቀስቅሶ ተቀጣጠለ፡፡ በሀገር ውስጥም በውጪም ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ልዩ ልዩ ሀሳቦችና ተቋውሞዎች ተሰነዘሩ፡፡
የባድመ ጉዳይ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት እንጂ የፌደራሉ መንግሥት አይደለም ከሚሉት ጀምሮ፤ በድንበር አካባቢ የሚገኘው ሕዝብ ሀሳቡ ሊጠየቅ ይገባል፤ የአገር ድንበር ጉዳይን በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ብቻውን መወሰን አይችልም፤ የአልጀርሱን ስምምነት መቀበል ምንጊዜም ኤርትራዊ ነኝ ብሎ አስቦ ለማያውቀው የኢሮብ ሕዝብ መጥፋት ነው፤ ጀግኖች የሕዝብ ልጆችን የቀበርንባቸው የኢሮብ ተራራዎችን ወደ ኤርትራ መሄድ አንቀበልም፤ ወዘተ-- የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በባድመ ምክንያት የተቀሰቀሰው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፣ ኢትዮጵያዊያን ባለሃብቶችን አንድ ቢሊዮን ሁለት መቶ ሚሊየን ብር አሳጥቷቸዋል፡፡ እንደነ ያኮና ኢንጂነሪንግ ያሉ ድርጅቶች ከሥረው እንዲዘጉ ከማድረግም በላይ፣ ሕወሓቶችንም ለሁለት እንዲከፈሉ ሰበብ መሆኑ ይነገራል፡፡
ዛሬ “የትግራይ ሕዝብን ጥቅም አሳልፎ በሚሰጥ ጉዳይ ላይ እጄን አላስገባም” የሚለው ሕወሓት፤ የአልጀርስ ስምምነቱን የማያፈናፍን ቅሬታ እንኳ ማሰማትና ማስመዝገብ በማይቻልበት መንገድ ሲታሰር፣ አሳሪና አሳሳሪ እንደነበር እንዴት ሊረሳው ይችላል? ሌላ ጦርነት ከፍቶ ወይም አንድ ዓይነት ተዓምር ተፈጥሮ ውሉ እስካልፈረሰ ድረስ ምን ጊዜም ስልጣን ላይ የሚቀመጥ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ይህን በሽተኛ ውል፤ “ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” ከማለት ሌላስ ምን ምርጫ ይኖረዋል?

Read 3979 times