Sunday, 17 June 2018 00:00

የአሰብን ጉዳይ ያካተተ አዲስ ስምምነት ያስፈልጋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

 “አረና” የአልጀርሱ ስምምነት እንዲሠረዝ የሚጠይቅ ሠላማዊ ሰልፍ ዛሬ በመቐሌ ያካሂዳል

    አረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉአላዊነት (አረና) የአልጀርሡ ስምምነት ተሰርዞ አዲስ ድርድር እንዲካሄድ የሚጠይቅ ሠላማዊ ሠልፍ ዛሬ በመቐሌ ከተማ ሮማናት አደባባይ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጎይቶም ፀጋዬ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ አረና በመቐሌ ከተማ በሮማናት አደባባይ ለሚያደርገው ሠላማዊ ሠልፍ፣ የእውቅና ጥያቄ፣ ከስድስት ቀናት በፊት ለከተማ አስተዳደሩ አስገብቷል፡፡
በዚህ ሠላማዊ ሠልፍ ላይ የአልጀርሱን ስምምነት አስመልክቶ፤ ፓርቲው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ያሣለፈው ውሣኔ የሃገሪቱን ሉአላዊነትና ጥቅም የማያስከብር በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ እንዲሠረዝ እንደሚጠየቅ አስታውቀዋል - አቶ ጎይቶም፡፡
“የአልጀርሡ ስምምነት አስቀድሞ በኤርትራ መንግስት ፈርሷል” ያለው ፓርቲው፤ “በኢትዮጵያ በኩል ይህን የፈረሠ ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ ተገቢነት የለውም ብሏል፡፡
በባድመ አካባቢ የሚኖሩ የኢሮብ ማህበረሰቦች፣ በኢህአዴግ ውሣኔ ከፍተኛ ቅሬታ እያቀረቡ መሆኑን የገለፁት አቶ ጎይቶም፤ ሕዝቡ አስቀድሞ አዲግራትን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ሠላማዊ ሠልፍ እያደረገ መሠንበቱን አስታውሰዋል፡፡
የአልጀርሡ ስምምነት ፈርሶ የአሠብን ጉዳይና ሌሎች የኢትዮጵያን ሉአላዊ ጥቅሞች ያካተቱ አዲስ ስምምነት መደረግ አለበት ብሎ እንደሚያምንም አረና አስገንዝቧል፡፡
ከሠሞኑ በባድመና አካባቢዋ በሚገኙ ከተሞች፣ ህዝባዊ ሠላማዊ ሠልፎች ሲካሄድ የሠነበቱ ሲሆን በሠልፎቹ ላይም “እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፤ ኤርትራዊ መሆን አንችልም፤ ‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኤርትራዊ መሆን የለብንም›፤ “እቃ እንጂ ሰውና አገር አይሸጥም” የሚሉና ሌሎች መፈክሮች ተሰምተዋል፡፡ በተመሳሳይ ዜና በአዲስ አበባ የሚገኙ የኢሮብ ማህበረሰብ ተወላጅ ባለሀብቶች፣ ምሁራንና ግለሰቦች የአልጀርሱን ስምምነት በመቃወም በነገው ዕለት ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርጉ ታውቋል፡፡

Read 8957 times