Sunday, 17 June 2018 00:00

በጣሊያን ኤምባሲ የሚገኙት 2ቱ የደርግ ባለስልጣናት ከቤተሠቦቻቸው ሊቀላቀሉ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

      ላለፉት 26 አመታት አዲስ አበባ በሚገኘው የጣሊያን ኢምባሲ በቁም እስር  ላይ የቆዩት ሁለት ከፍተኛ የደርግ ባለስልጣናት ምህረት ተደርጎላቸው ከቤተሠቦቻቸው ጋር ሊቀላቀሉ መሆኑን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
የ82 አመቱ አዛውንት ሌተና ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህ እና የ74 አመቱ ሌተና ጄነራል አዲስ ተድላ በህዳር 2010 ዓ.ም ከተጠለሉበት የጣሊያን ኢምባሲ በምህረት ወጥተው ከቤተሠቦቻቸው እንዲቀላቀሉ የተለያዩ አካላት ለመንግስት ጥያቄ ማቅረባቸው የሚታወቅ ሲሆን በአሁኑ ወቅት መንግስት በምህረት ሊፈታቸው የህግ ሂደቶች መጀመራቸውን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
ጉዳያቸው ከሠሞኑ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ህግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ ቀርቦ፣ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ለፓርላማው ውሣኔ ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ለማወቅ ተችሏል፡፡
አዲስ አድማስ ጋዜጣ በህዳር 30 2010 እትሙ፣ ሁለቱ ከፍተኛ የደርግ ባለስልጣናት ያሉበትን ሁኔታ አስመልክቶ ባቀረበው ዘገባ፤ ምንም እንኳ ኢምባሲው ለረዥም ዓመታት ከለላ ቢሰጣቸውም ከቤተሠቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር የመገናኘት ዕድል ስለሌላቸው ለከፍተኛ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት መዳረጋቸውን ጠቁሟል፡
ሌተናል ኮለኔል ብርሃኑ ባየህ በመጨረሻዎቹ የደርግ የስልጣን ዘመናት፣ የመንግስት ም/ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩ ሲሆን ሌ/ጀነራል አዲስ ተድላ በበኩላቸው፣ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም እንደነበሩ ይታወቃል፡፡
ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው መንፈስ አነቃቂ ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ንግግር “በኤምባሲ ውስጥ ታስረው የሚገኙ የቀድሞ መንግስታት ከፍተኛ ባለስልጣናት ይቅርታ አድርገንላቸው ሊወጡ ይገባል” ማለታቸው ይታወሳል፡፡

Read 12478 times