Sunday, 17 June 2018 00:00

ህውሓት፤ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚን መግለጫ አብጠለጠለ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 “መግለጫው እርስበርሱ የሚጣረስና ግራ የተጋባ ነው” - አረና

   የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ በኢትዮ - ኤርትራ የድንበር ግጭትና በኢኮኖሚ የማሻሻያ እርምጃ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ፣ ስብሰባ የተቀመጠው የህውሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ፤ ኢህአዴግ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ የጠየቀ ሲሆን የግንባሩንም መግለጫ አብጠልጥሏል፡፡
የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫም፤ “ኢህአዴግ የአመራር ብልሹነት አጋጥሞታል፤ የድርጅቱ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር አደጋ ላይ ወድቋል” ሲል በስጋት የታጀበ ትችት ሰንዝሯል፡፡
የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በስብሰባው፣ በመጋቢት 2010 የም/ቤት ስብሰባ ላይ የተላለፉ ውሣኔዎች የደረሡበትን ደረጃ ሊመለከት ይገባው ነበር ያለው ህውሓት፣ ምክር ቤቱ በወቅቱ ያስቀመጣቸው ድርጅቱን ከአደጋ የማዳኛ መንገዶችና አቅጣጫዎች አሁንም በጥብቅ ዲሲፒሊንና ተጠያቂነት ሊተገበሩ ይገባል ብሏል፡፡
የኢትዮጵያና የኤርትራ የ18 አመታት ግጭት በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ እንዲሁም የመንግስት የልማት ድርጅቶችን አስመልክቶ የወጣው መግለጫ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፖሊሲ ጋር የሚቃረን አለመሆኑን የጠቆመው የህወኃት ማዕከላዊ ኮሚቴ፤ አፈፃፀሙ ግን በጥንቃቄ መከናወን እንዳለበት አሳስቧል፡፡
በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ላይ የተሠጠው ውሣኔ ለህዝብ ይፋ መደረግ አልነበረበትም ያለው ድርጅቱ፤ በመጀመሪያ ህዝቡ ሊውያይበት ይገባ ነበር ብሏል፡፡ በጉዳዩ ላይ አጋር ድርጅቶችም መወያየት እንደነበረባቸው በመጠቆም፡፡
በዚሁ የአቋም መግለጫ በዴሞክራሲ ሃይሎችና በጥገኝነት መካከል ቀጣይ ትግል ይደረጋል ያለው ህወሓት፤ “ህገ መንግስቱ በሚገባ መልስ የሰጠባቸውን የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች፣ ፌደራላዊ ስርአቱን በመፃረርና የህዝቡን ክብር በሚነካ መልኩ በሃይልና በተፅዕኖ፣ የትግራይ ህዝብን አንድነትና ሠላም ለመረበሽ እየተደረጉ ያሉ ፀረ ዲሞክራሲ እንቅስቃሴዎችን ከህዝቡ ጋር በመሆን በፅናት እታገላለሁ ብሏል፡፡
ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመራችን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አደጋ ውስጥ ወድቋል የሚለው ድርጅቱ፤ የኢህአዴግ አመራር አብዮታዊ ዲሞክራሲ ባህሪው እየተሸረሸረ በከፋ የጥገኛ ዝቅጠት አረንቋ ውስጥ መዘፈቁን አስታውቋል። ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር ወድቀትም አመራሩ ተጠያቂ ነው ብሏል- ህወኃት በመግለጫው፡፡
አንዳንድ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ውሳኔዎችን በመግለጫው ያብጠለጠለው ህወሓት፤ በድርጅቱ ውስጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በግልፅ እየታየ የመጣውን የአመራር ብልሹነት መመልከት ይገባው ነበር ብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢህአዴግ ደረጃ እየተደረጉ ያሉ የአመራር ምደባዎች የኢህአዴግን ህገ-ደንብና ተቋማዊ አሠራር ያልተከተሉ ናቸው ሲል በመተቸትም፤ የአመራር ምደባዎቹ እንዲታረሙ ጠይቋል፡፡ ለድርጅቱ ነባር አመራሮች እውቅና እንዲሠጥም ህወሓት ጠይቋል፡፡
የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወኃት፤ እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመራችን አስተማማኝ ደጀን በመሆን፣ ትግሉን ያጠናከራል ብሏል በመግለጫው፡፡
ሠላማዊ ህጋዊ መንገድ ተከትለው አማራጭ ሃሣብ ከሚያቀረቡ ሃይሎች ጋር አብሮ እንደሚሠራ የጠቆመው ድርጅቱ፤ ህውሓትንና የትግራይን ህዝብ ለማዳከምና ለመምታት በተለያዩ መንገዶች፣ ፀረ-ትግራይ ህዝብና ፀረ-ህወኃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ የውስጥም የውጭም ሃይሎችን ህዝቡ አምርሮ እንዲታገላቸው ጥሪ አቅርቧል፡፡
የህወሓትን መግለጫ አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለአዲስ አድማስ የሰጡት የአረና ትግራይ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጎይቶም ፀጋዬ፤ መግለጫው እርስ በእርሡ የሚጣረስና ግራ የተጋባ ነው ብለዋል፡፡
“ህወኃት የተቃወመው አንድ ነገር ቢኖር፣ የህዝብ ድጋፍ ያለው የባለስልጣናት በጡረታ መሰናበትን ነው” የሚሉት አቶ ጎይቶኦም፤ መግለጫው በኤርትራ ጉዳይና በልማት ድርጅቶች ላይ ህወኃት ከኢህአዴግ የተለየ አቋም እንዳላንፀባረቀ ያመላክታል ብለዋል፡፡

Read 10324 times