Sunday, 17 June 2018 00:00

በሃዋሳና ወልቂጤ ግጭቶች አገረሹ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

በወልቂጤና በሃዋሳ አገርሽተው የሰነበቱ ግጭቶች ከሃሙስ ጀምሮ መረጋጋታቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ጠቁሞ፤ የግጭቶቹን መንስኤዎችና ጉዳት አጣርቶ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል፡፡
በሁለቱ ከተሞች በተከሠተው ግጭት፣ በሰዎች ላይ አካላዊ ጉዳት የደረሰ ሲሆን የንብረት ውድመት ማስከተሉንም የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ም/ኮሚሽነር አህመድ ላዲን ጀማል ጠቁመዋል፡፡
በሃዋሳ ከተማ ማክሰኞ ሰኔ 6 ቀን 2010 ዓ.ም የተፈጠረው ግጭት፣ ከሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ የፍቼ ጨንበላላ በዓል ጋር ተያያዥነት ያለው ሲሆን በወልቂጤ የተነሣው ግጭት መነሻ ደግሞ በሁለት የእግር ኳስ ቡድነወ ደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑ ታውቋል።
ማዕከሉን ወልቂጤ ከተማ ባደረገው የጉራጌ ዞን ውስጥ የጉራጌ፣ ቀቤናና ማረቆ ብሄረሰቦች የሚኖሩ ሲሆን በእግር ኳስ ሠበብ የተነሳው ግጭት፣ ወደ ብሄር ግጭት መዞሩ ታውቋል። በጉራጌና በቀቤና ብሔረሰቦች መካከልም “የወልቂጤ ከተማ ይገባኛል፤ ከተማችንን ለቃችሁ ውጡ” ወደሚል ግጭት ማምራቱን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በርካታ መኖሪያ ቤቶችና ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን እስከ ረቡዕ አመሻሽ ድረስም ከአዲስ አበባ ጅማ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት ተስተጓጉሎ መቆየቱ ተጠቁሟል፡፡
በእነዚህ ግጭቶች የደረሱ አጠቃላይ ጉዳቶች ተጣርተው ለህዝብ ይፋ እንደሚደረጉ የክልሉ መንግስት ያስታወቀ ሲሆን ግጭቶቹ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ መረጋጋታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ በኩል፤ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የ3ኛ ዓመት ተማሪዎች፤ “የሆልስቲክ ፈተና አንፈተንም” በሚል ተቃውሞ፣ ባለፈው ሐሙስ ግቢውን ለቀው መውጣታቸው ታውቋል።

Read 3604 times