Print this page
Monday, 11 June 2018 00:00

የብሩንዲው መሪ ከ2 አመት በኋላ ስልጣን እለቃለሁ አሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  እስከ 2034 በስልጣን ላይ የመቆየት ዕቅድ አላቸው በሚል ሲተቹ ነበር

    በቅርቡ በተካሄደ ህዝበ ውሳኔ ለተጨማሪ 14 አመታት በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚስችላቸውን የህገ-መንግስት ማሻሻያ አስጸድቀዋል በሚል ከተቃዋሚዎችና ከአለማቀፍ ተንታኞች ውግዘት ሲወርድባቸውና በስልጣን ጥመኝነት ሲታሙ የከረሙት የብሩንዲው ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ፣ በ2020 ስልጣን እንደሚለቁ አስታውቀዋል፡፡
በ2020 የስልጣን ዘመናቸውን የሚያጠናቅቁት ፔሪ ንኩሩንዚዛ፣ በቅርቡ በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ፣ የህዝብ ድጋፍ አግኝቶ በህግነት በጸደቀው ማሻሻያ ለተጨማሪ ሁለት የስልጣን ዘመናት ወይም 14 አመታት በመንበራቸው ላይ እንደሚቆዩ ብዙዎች በእርግጠኝነት ሲናገሩ መቆየታቸውን ያስታወሰው ቢቢሲ፤ፕሬዚዳንቱ ግን በስልጣን ላይ የመቆየት ፍላጎት እንደሌላቸውና በቀጣዩ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ እንደማይወዳደሩ፣ ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸውን ዘግቧል፡፡
በብሩንዲ የፕሬዚዳንቱን የስልጣን ዘመን ለማራዘም በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ በቅርቡ በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ድምጽ ከሰጡት 4.7 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ ከ73 በመቶ በላይ ድጋፍ ማግኘቱንና ህግ ሆኖ መጽደቁን ያስታወሰው ቢቢሲ፤ ፕሬዚዳንቱ ግን ማሻሻያው በህግነት በጸደቀበት ስነስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የስልጣን ጥም እንደሌለባቸው መግለጻቸውን አመልክቷል፡፡
አብላጫ የድጋፍ ድምጽ ያገኘውና በህገ-መንግስቱ ውስጥ የተካተተው ማሻሻያ፣ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት አንድ የስልጣን ዘመን ከአምስት አመት ወደ ሰባት አመት ከፍ የሚያድርግ ሲሆን የስልጣን ዘመናቸው ከሁለት አመታት በኋላ የሚያበቃው የአገሪቱን መሪ ፔሪ ንኩሩንዚዛን ለተጨማሪ ሁለት የስልጣን ዘመናት በገዢነታቸው የሚያስቀጥል በመሆኑ ሲተች መቆየቱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
የህገመንግስት ማሻሻያው የፕሬዚዳንቱን የስልጣን ዘመን ከማራዘም በተጨማሪ፣ የበለጠ ስልጣን እንዲያገኙና ከፍተኛ ባለስልጣናትን ዘርን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲሾሙ ፍጹም ስልጣን የሚሰጥ በመሆኑ በአገሪቱ የእርስ በእርስ ግጭት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩንም ገልጧል፡፡
በ2005 ስልጣን የያዙት ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ፣ ህገመንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ውጭ ለ3ኛ የስልጣን ዘመን ተወዳድረው በስልጣን ላይ መቀጠላቸውን ተከትሎ፣ በአገሪቱ የእርስ በእርስ ግጭት መቀስቀሱን ያስታወሰው ዘገባው፤ በዚህም 1 ሺህ ያህል ሰዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውንና 400 ያህል ዜጎችም አገራቸውን ጥለው መሰደዳቸውን ገልጧል፡፡

Read 2725 times
Administrator

Latest from Administrator