Saturday, 09 June 2018 12:15

ዓለማችን በ2017 በግጭቶች ሳቢያ 14.8 ትሪሊዮን ዶላር አጥታለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በጦር ሜዳ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በ10 ዓመታት በ246 በመቶ ጨምሯል

    የዓለማችን ሰላም ባለፉት አስር ዓመታት እያሽቆለቆለ መምጣቱንና ባለፈው የፈረንጆች አመት 2017 ብቻ የአለማችን አገራት በግጭቶች ሳቢያ በድምሩ 14.8 ትሪሊዮን ዶላር ማጣታቸውን አይኢፒ የተባለው የጥናት ተቋም አመለከተ፡፡
ኢንስቲቲዩት ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፒስ የተባለው የጥናት ተቋም፣ ባለፈው ረቡዕ ለ12ኛ ጊዜ ይፋ ያደረገው አለማቀፍ የሰላም ሁኔታ አመላካች ሪፖርት እንደሚለው፤ በአለማችን በጦር ሜዳዎች ላይ ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር ባለፉት አስር አመታት በ246 በመቶ ያደገ ሲሆን ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በአንጻሩ በ203 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ባለፈው የፈረንጆች አመት 2017 በአለማችን 92 አገራት፣ የሰላም ሁኔታ ላይ ማሽቆልቆል የታየ ሲሆን ሶርያ፣ አፍጋኒስታንና ደቡብ ሱዳን በከፍተኛ ሁኔታ ሰላም የራቃቸው አገራት ናቸው ተብሏል፡፡
በአመቱ የ71 የአለማችን አገራት ሰላም መሻሻል ታይቶበታል ያለው የተቋሙ ሪፖርት፤ በ2017 የፈረንጆች አመት 104 የአለማችን አገራት፣ የመከላከያ ወጪያቸውን ከኢኮኖሚ ወጪዎች ያነሰ ማድረጋቸውንና 115 አገራት ደግሞ ወታደራዊ የሰው ሃይላቸውን መቀነሳቸው  በመልካም ተሞክሮነት ጠቅሶታል፡፡
በአለማችን በአመቱ ከፍተኛውን ሰላም ያስተናገዱት የአለማችን አገራት፤ አይስላንድ፣ ኦስትሪያና ፖርቹጋል መሆናቸውን የጠቆመው ተቋሙ፤ በአፍሪካ ሰላማቸውን በጥሩ ሁኔታ ያሻሻሉ አገራት፤ ጋምቢያ፣ ላይቤሪያና ብሩንዲ መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1527 times