Saturday, 09 June 2018 12:09

መካንነት… ከወንድ ወይንስ ከሴት…ወይንስ ከሁለቱም?

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 በአለም አቀፍ ደረጃ መካንነት 15% በጥቅሉም ሲታይ ወደ 48.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ጥንዶችን ያስቸግራል፡፡ ከዚህ ውስጥ ወንዶች ከ20-30% የሚሆነውን የመካንነት ችግር ድርሻ የሚጋሩ ሲሆን በአጠቃላይም ወደ 50% ለሚሆነው መካንነት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ በእርግጥ ይህ ቁጥር በትክክል በአለም አቀፍ ስላለው ሁኔታ መረጃ ይሆናል ማለት አይደለም እንደ ባዮ ሜድ ሴንትራል መረጃነት፡፡
በአለማችን ቢያንስ ቢያንስ 30/ሚሊዮን የሚሆኑ ወንዶች የመካንነት ችግር ያለባቸው ሲሆን በአፍሪካ፤ በመካከለኛው እና ምስራቅ አውሮፓ ግን የበለጠ እንደሆነ መረጃው ይጠቁማል፡፡
በአፍሪካም ይሁን በአንዳንድ አገራት የሴቶች መካንነት እንጂ የወንዶች መካንነት እንደ ጉዳይ ተነስቶ ለውይይት አይቀርብም፡፡ በተለይም በወንዶች የበላይነት በሚያምኑና በሚተዳደሩ የህብ ረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ትክክለኛውን መረጃ ማግኘት እንኩዋን በጣም ይከብዳል፡፡ ለምሳሌም በሰሜናዊ አፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ሴቶች መካን ናቸው ተብለው ወደሐኪም ቀርበው የተለያየ የጤና ምርመራ ሲያደርጉ ወንዶቹ ግን ያሉበትን የጤና ሁኔታ ለማወቅ የህክምና ምርመራ ለማድረግ ፈቃደኛ አይሆኑም። ከዚህም በተጨማሪ ከአንድ በላይ ሚስት ስለሚያገቡ ምናልባትም አንዱዋ ልጅ ባትወልድ ከሌላዋ ልጅ ይገኛል የሚለውን እምነታቸውን ስለሚያጠ ናክርላቸው ብዙም ግድ እንደማይሰጣቸው እና በዚህም ምክንያት የትኛው ወንድ መካን ነው የሚለውን ለማወቅ አስቸጋሪ ይሆናል። በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በሚተገበረው ባህል ባልየው ልጅ መውለድ ካቃተው ወንድሙን ወይንም የቅርብ ዘመድ የሆነውን ሰው ከሚስቱ ጋር እንዲገናኝ በመፍቀድ ልጅ እንዲረገዝና እሱ ወለደ እንዲባል እንዲሁም በህብረተሰቡ ዘንድ ወላድ ነው እንዲባል የሚጠቀሙበት ዘዴም እንዳለ መረጃው ይጠቁማል፡፡ የወንድ መካንነት እንደ ስነ ተዋልዶ ጤና ችግር የማይቆጠርበት አጋጣሚም ይስተዋላል፡፡
የወንዶች መካንነት በሰሜን አፍሪካ፤ ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት እና በምስራቅ አው ሮፓ በተመሳሳይ ሁኔታ መጠኑ ከአለምአቀፉ ከፍ ያለ እንደሆነ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በአፍሪካ የመካንነት ችግር በሚያይልባቸው አገራት ወንዶች የተለያዩ የስነ ተዋልዶ ጤና አክል ይገጥማቸዋል፡፡ እነርሱም ጨብጥ፤ ከርክር፤ እና የመሳሰሉት ሲሆኑ እነዚህ የጤና እውክ ታዎች ወንዶቹን ለመካንነት ከሚያጋልጡ መካከል ናቸው ተብሎ ይገመታል፡፡
(CDC) center for disease control and prevention እንደሚያስነብበው፤
1/3ኛ ለሚሆነው የመካንነት ችግር ምክንያቱ ወንዶች ናቸው፡፡
1/3ኛው ለሚሆነው የመካንነት ችግር ምክንያቱ በግልጽ የማይታወቅ ሲሆን ከወንዱ ወይንም ከሴትዋ ሊሆን ስለሚችል የሁለቱም ችግር ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
1/3ኛው የሚሆነው ልጅ ያለመውለድ ችግር ምክንያቱ ከሴትዋ ይሆናል፡፡
የመካንነት ሁኔታ በሴቶች እስከ 50% ሲሆን በወንዶች ደግሞ ከ20-30% ድረስ ይሆናል፡፡ የተቀረው ከ20-30% የሚሆነው መካንነት ከወንዱ እና ከሴትዋ ከሁለቱም ተፈጥሮ በተቀላቀለ ሁኔታ የሚከሰት ነው፡፡  
ልጅ የመውለድ እድል ለወንዱም ሆነ ለሴትዋ እንደ እድሜ ሁኔታው ይወሰናል፡፡ በእርግጥ እድሜ በተለይም በሴቶች በኩል ልጅ ላለመውለድ ከወንዶች በበለጠ ምክንያት ይሆናል፡፡ ሴቶች በ30/ዎቹ አመት እድሜያቸው ልጅ የመውለድ ተፈጥሮአዊ ብቃታቸው በ20ዎቹ እድሜያቸው ከነበረው በግማሽ ያህል ይቀንሳል። ሴቶች በእድሜያቸው 35/አመት ሲደርሱ ልጅ የማርገዝ እድላቸው በፍጥነት እየቀነሰ የሚሄድ ሲሆን የወንዶች ልጅ የማስረገዝ ብቃት ግን እየቀነሰ የሚሄድ ቢሆንም በዝግታ ነው፡፡
ወንዶች ለመካንነት ከሚዳረጉባቸው ምክንያቶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
የመጀመሪያው testes የተባለው በብልት አካባቢ የሚገኘው የስነተዋልዶ አካል ነው፡፡ ይህ አካል ሁለት ስራ አለው፡፡ አንደኛው የወንድ ዘር ፍሬ እና ሁለተኛው ደግሞ ቴስቴስትሮን የተባለውን ሆርሞን ማምረት ነው፡፡ አንድ ወንድ ይህ የሰውነት ክፍሉ በትክክል ካልሰራ የሴትየዋን እንቁላል መስበርና ልጅ እንዲረገዝ ማስቻል ያቅተዋል፡፡
ሌላው የሆርሞን መዛባት ወይንም ተፈጥሮው ማቆም እንዲሁም የቲዩብ ወይንም መስመር መዘጋት ነው፡፡
የአኑዋኑዋር ሁኔታ እና ከእድሜ ጋር በተያያዘ የሚፈጠር የመካንት ችግር ያጋጥማል፡፡
የመካንነት ችግር ካለባቸው ወንዶች ወደ 15% የሚሆኑት የዘር ፍሬ ጭርሱኑ የሌላቸው ናቸው፡፡
ከትክክለኛው መጠን እንዲሁም አቅም በታች የሆነ የዘር ፍሬ የሚያመርቱ ወንዶችም ለመካንነት ችግር ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡  
ባጠቃላይም አንዳንድ የጤና እና ተፈጥሮአዊ እውክታዎችን ጨምሮ የሚከተሉት ምክንያቶች የወንዶችን የዘር ፍሬ በትክክለኛው መንገድ እንዳይመረት ያደርጋሉ፡፡
የክሮሞዞም ችግር
የስኩዋር ሕመም
የtesticle የተባለው የዘር ፍሬና የሆርሞን አምራች የሰውነት ክፍል መጎዳት
የChromosome መዛባት የመሳሰሉት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ሴቶች ለመካንነት የሚዳረጉባቸው ምክንያቶች፤-
ሴቶች የሚወለዱት በሕይወት ዘመናቸው የሚጠቀሙባቸውን እና እያደርም የማይተኩዋቸውን እንቁላሎች ይዘው ነው፡፡ ጥናት አድራጊዎች እንደሚያምኑት አንዲት ሴት ከ1-2ሚሊዮን እን ቁላሎችን ይዛ የምትወለድ ሲሆን የዚህ እንቁላል ቁጥር የሴትየዋ እድሜ እየጨመረ ሲሄድ እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ ከዚህም የተነሳ የሆርሞን መጠን እየቀነሰ ስለሚሄድ ልጅ የማፍራት እድል ዋም እያደር እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ የወር አበባ ሲቋረጥ እስከጭርሱኑ ስለ እርግዝና ማሰብም ይቀራል፡፡
በማህጸን አካባቢ እንዲሁም የሴት እንቁላልና የወንድ የዘር ፍሬ በሚገናኙበት fallopian ቲዩብ ላይ ኢንፌክሽን ካለ እንዲሁም በእንቁላሎቹ ላይ ተፈጥሮአዊ ችግር ካለ የመካንነት ችግር ሴቶችን ሊገጥማቸው ይችላል፡፡  
ከዚህም በተጨማሪ የአኑዋኑዋር ሁኔታ እና የእድሜ ጉዳይ ከሴትዋ እንቁላል ጋር የሚገና ኙበት ምክንያት ስለሚኖር ልጅ የመውለድን እድል እንደሚቀንሰው ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ የእነዚህ ተፈጥሮአዊ ሁኔታዎች ትክክለኛ አለመሆን ልጅ ማርገዝ አለመቻል ብቻ ሳይሆን  የተረገዘ ውም ሞቶ እንዲወለድ ወይንም ተፈጥሮአዊ ችግር ያለበት ልጅ እንዲወለድ ሊያደርግ ይችላል፡፡
በወንዶች በኩል እድሜ የዘር ፍሬን ጥራት እና መጠን እንደሚቀንስ የታወቀ ሲሆን ይህም እንቁላል እንዲሰብርና ልጅ እንዲረገዝ የማስቻል ብቃት እንዳይኖረው አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡
በዘመናችን ሳይንስ ብዙ አዳዲስ ፈጠራዎችን ወደ ተግባር እያሸጋገረ ሲሆን ከዚህም አንዱ ልጅ ለመውለድ እንዲቻል እንቁላልን ወይንም የዘርፍሬን በላቦራቶሪ ማስቀመጥ እና ልጅ መውለድ በሚያስፈ ልጋቸው ጊዜ መጠቀም እንዲችሉ የማድረጊያ ዘዴ አለ፡፡ ለምሳሌም ሰዎች በተለያዩ ሕመሞች ከተያዙ ወይንም የጤና መዛባት ከገጠማቸው እና ወደፊት ልጅ የመውለድ እድላቸ ውን የሚያሰ ናክለው ከሆነ በጊዜ እርምጃ ወስደው ልጅ እንዳያጡ ይረዳቸዋል፡፡ ይህንን የሳይንስ ውጤት ሊጠቀሙ የሚችሉት ሰዎች፡-
ለመርዛማ ንጥረ ነገሮች ተጋላጭ በሆነ ቦታ የሚሰሩ ከሆነ፤
በካንሰር ሕመም ከተያዙ፤
በአለርጂክ ሕመም የሚሰቃዩ፤
ልጅ የመውለድን እድል የሚያጨናግፉ በቤተሰብ የሚወረሱ ሕመሞች፤
ልጅ ከመውለድ ከዘገዩ…ወዘተ፤
የመካንነት ችግር አለም አቀፍ ችግር በመሆኑ ይህንን ለመፍታት የሚያስችሉ ሳይንሳዊ አገልግሎቶች በአገራችንም በስፋት ቢገኙ ብዙዎች መካንነት አያሳስባቸውም እንደ (CDC) እማኝነት፡፡

Read 390 times