Sunday, 10 June 2018 00:00

የመተርጐም ገጽታዎች፡- ንባብ፡ ኣንድምታ፡ ሒስ፡ ኣርትዖት

Written by  ደገፍ ግደይ
Rate this item
(1 Vote)


    (ክፍል-2)
ዓብደላ ጥበበኛ አንባቢ፡ ሓሳብ ኣፍላቂ
ኣኹንም ‘ንግባእከ…’፡ ሳንሸሽ ዞር ካልንበት እንመለስ። የመተርጕሙ  ኣእምሮ ላይ የሰፈረውን የኣቶ ጠያቂን ጕዳይ ኣንሥተን ነበር፤ የኣንድምታው ሊቅ ዘንድ ጥያቄም፡ መልስም ከራስ ነው ስንል ነው። ሊቁ ለራሱ ኣዳልቶ ምቹ ጥያቄ ኣይመርጥም፤ ያፍታታ፡ ያብራራዋል፡ ያፍረጠርጠዋል እንጂ ኣግበስብሶም ኣያልፍ። ላብዛኞቻችን የሚቀለው ግን እንደ ዓብደላ ራሱን ችሎ ከሚቀርብ ተሟጋች መጋፈጥ ነው። ያ ሞጋች፣ ያ ተከራካሪ (ነገረተኛ) የተሰወረ ለት ወዮልን! ኣንደበታችን እሱ ላነሣው ነገር መልስ ማቅረብ ነዋ የለመደው።
እንዲኽ ኾነላችዅ (-በጨረፍታም ቢመስል-) ባሻይ ብርሃነ ወላይና ባሻይ ወለገብሪአል ባላንጣዎች ነበሩ፤ ኣንዱ ሲያርፉ ቀሪውን ጨነቃቸው! ‘መልቀስ ሳንዳ’ በሚል ያደረሱን ወዮ እንሆ!
መልቀስ ሳንዳ
ወዲ ባሻይ ወላይ በላዒ መኒዑ፡
ወዲ ሓጐስ በላዒ መኒዑ፡
ገደፍኩምና ዶ ምስ ቈልዑ፡
እንተ ጸዋዕኻዮም ለይሰምዑ፡
እንተ ለኣኽካዮም ለየቕንዑ?
ዓርከይ፡ ወይ ጸጕዑና፡ ወይለ ንዑ፡፡
***
ወዮ
ሰሙ ወይ ኣባ ቡታ፡ ኣባ ቀማው፡
የባሻይ ወላይ ልጅ፡ የሓጐስ ቡችላ ነጥቆ በላው፡  
ከቶ ካይኾኑነ፡ ካሽከር እንጋፈጥ?
ወይ ባይ ከሌለዉ፡ ተልኮ ካያሰልጥ?
ወዳጄ፡ ይልቅ ኣንቱ ስሙ፡-
ወይ ጥሩነ፡ ኣለያም ኑ።
ዓብደላ ያንድምታ ሰው ወዝ ነበረው። የሞጋች ረዳት የሚሻን ሰው ኣጐደለ። ትክረት!
ሰውየው ፡- ኣቶ ኣገሬ፡ ኣቶ እገሌ፡ ዓጅሬ (ኣቶ ተዋጽኦ) ወዝ ኣልኩኝ፡ ከዓብደላ ጋራ ከዛ በላይ ማለት የሚያስችል ትውውቅ ባይኖረኝ። ሰውን መቼም ኣያውቁት፤ ባሕር ነው፡ ኣይደርሱበትም። ወዙን ግን፡ በቅርቤ ያለ ማሳያ ልጥቀስና፡ የጥበባት ተዋርሶን፡ ተዋስቦን የተቸበት መንገድ ላይ ኣገኘኹት ልበል፡- “ሥዕልና ድርሰት ሲቀሳቀሱ… በኣንድ ሥዕል በመጠበብ ግጥም ለመቀኘት መብቃት… ከኣንድ  የበቃ፡ የወጣለት የፈጠራ ውጤት በመነሣሣት፡ ዓዲስ እይታ በመንጠቅ መቀኘት…”።  ድር በድር ኾነ እንጂ ስመ ገናናው ተግባር ነጠቃም እኮ እሱ ነው፤ ኣንዱ ቅኔ ሲወጠን ወዲያው ቀጨም ኣርጎ ዓዲስ ቅኔን ሲያስቀኝ! ብሎም፡ ኣልቃሽ፡ የተቀጠፈ ኣበባ ኣይቶ ‘አረ እናንተው’ ሲል፡ ‘ክንብል ያርገኝ’ ሲል ልብ ማለት፤ ፈቅ ሲልም፡ ጕርምርሜው ሉዊ ኣርምስትሮንግ (ኣቍማዳፍ) ነብዩ ዮናስን ስለ ገጠመው መውጅ፡ ስለ ዋጠው ዓሣ ነባሪ ሲያንጐራጕር ማድመጥ ነው። ወለሎ በየፈርጁ!
የቃላት-ያገባብ-የቅርጽ ግንዛቤ
ዳግመኛም፡ የዓብደላ የቃላት ፍቅርና ግንዛቤ በኣንድምተኛው መጠንና ዓይነት ይመስላል። የሰዋስውን ጥበብ፡ የብትን ቃላትን ውበት ነቅሶ ሲያወጣና ሲያጣጥም ኣላስተዋልኩም፤ ከቃል ቃል ማማረጥ ስለ ደስ ደስም እኮ ነው። (ትንሽ ከፍ ብሎ፡ ‘ማጣጣምና መተንተን ምንና ምን ናቸው?’ የሚል ገራገር ጥያቄ ማስቀደሜ ከዚኽ በመነሣት ነበር።)
ቅርጽንም  ‘ሸንቃጣ’  በመሰለ ቃል ነው ነካ የሚያረገው… በጨረፍታ። ጕዳዩ ግን ነገረ ሰዋስውን ያያል፡- በስም ከነጓዙ፡ በግስ ከነጓዙ የሚፈጠረው ሓረግ፡ የኣገባቦቹ (ሙያ እንጂ ትርጕም የሌላቸው ሚጢጢ ቃላት) እና የሸካፊው ማሰሪያ ኣንቀጽ ቦታ፡ ወዘተ።
ኣንድምታም ወደ ምስጢሩ ለመዝለቅ  የሰዋስውን ጕዳይ ያነሣ እንደዅ እንጂ፡ ያዝ ኣርጎኣቸው ኣይቆይም፡ ኣገላብጦ ኣይመለከታቸውም፤ ከዘይቤ ወዲያ ያለ ምስጢርን እንጂ ነጠላ ቃላትንማ ኣይደነቅባቸውም። ባይደነቅባቸውም ግን፡ ስማቸውን ጠርቶ ኣይደመምባቸው እንጂ፡ ሊቁ፡ ለኣንድምታው ማኼጃ ቃል መርጦ ሲያነሣ ግጥሙን ያገኘዋል። ኣመቻችቶ ለማዋሉ ማ ብሎት? ለመመሰል ሲጠበብ ኣንጀት ዓርሶ ነው።
ውሰት ከነጓዙ-- የቆየ  ኣዝማሚያ
ዓብደላም ለሓሳቡ ቃላት መባያ ኣያጣም፤ ነገር ግን፡ ባንድ ቋንቋ ተጽፎ በሌላ ቋንቋ ፈሊጥ የሚሰሙት (‘እኔ ባማርኛ ልጻፈው፡ ኣንተ በእንግሊዝ ፈሊጥ ስማው፡ ተረዳው፡’) የሚመስል ነገር ኣለው። ኣንዳንዴ፡ ጽሑፉ የእንግሊዝኛ ግልባጭ እስኪመስል፡ የዘመኑን ኣዝማሚያ ተከትሎ፡ በዚያኛው ቋንቋ ኣሻራ ባሻራ ተሞልቷል።
ኣዝማሚያውን ያብራራልኝ እንደዅ ባለፈ ዘመን ምሳሌ ልደገፍና የገብስ ገብሱን እየተጫወትን ወዳስተያየቴ ልዝለቅ። በግእዝ ይነበብና ባማርኛ እንዲረዱት የሚፈለግ ያጻጻፍ ዓይነት ነበረ (የቸከችዋን ምሳሌ ላንሣ፡- በካፋ ኢትርሳዕ ዘተዋነይነ ክልኤነ/ እንዘ ኣበ ኣብረሃም ኣንተ ወብእሲተ ኣብረሃም ኣነ=  በካፋ ሆይ፡ የተጫወትነውን ዓደራ። ያውም፡ ሰዓቱ ትዝ ይበልኽና፡ ኣንተ ታራ ነበር፡ እኔም ሳራ ። (ግእዝ) ሥላሴ  ጥብሑ በግዐክሙ ጸዓዳ/ እንዘ ሠርጸ ኵሉ ይረግጽ ኣምጣነ ያመጽእ ዕዳ። (ነጠላ ትርጕም) ሥላሴዎች ሆይ፡ ነጭ በጋችኹን ዕረዱ/ የዅሉን ቡቃያ እየረገጠ ዕዳ ያመጣልና። ቅኔው እንዲሳካ፡ የ’መጫወት’ ተቀዳሚ ፍቺ ሳይኾን ሰፋ ኣርጎ ‘መባባል፡ መመካከር’ መኾኑን የሚገነዘብ፡ ‘የናንተን በግ’ የሚለውን ትቶ ‘በጋችኹን’ ብሎ የሚረዳ (ሰሚ) ተርጓሚ ይፈልጋል።)
እንደ ኣወራረዱ ኣይቶ የመፍታትን መንገድ ለማስረዳት ይኽ ንባብ ይጠቀሳል፡- ‘መኑ ዘይክል ነቢበ ዕበየኪ ወኣልቦ ዘይመስል ኪያኪ’። ‘ኣልቦ’ንና ‘መኑ’ን ኣወራርሶ መፍታት፡ ለዚኽ ለምንለው ሓሳብ ተጨማሪ ማንጸሪያ ይኾን ይኾናል።  
ለጠጥከው እንዳልባል እንጂ፡ ወደ ኋላ ተመልሶ ኣንድምታውንም እንዴት እንደሚነካ ኣንድ ምስክር ልጥራ። የቃል ትምህርቱ ውዳሴ ማርያም ላይ ‘ሰኣሊ ለነ ቅድስት’ የሚል ንባብ ኣለ። ዓማርኛ የ3ቱን ቃላት ሰዐለ- ሰአለ- ሠዐለ ኣደማመጥ ኣዋሕዶታል፡ ያፈታት እንጂ የንባብ ልዩነት ጠፍቷል፤ ጸሓፊም ለፊደላቱ እምብዛ ኣይጠነቀቅም። ይኽ መደባለቅ  […] ክብሩንና ጸጋውን እንዳይነሣን ለምኝልን ይልና፡ የኣንድም ያኽል፡ ‘ኣእምሮውን፡ ለብዎን፡ በልቡናችን ሣይልን፡ ኣሳድሪልን‘’  ማለትን ያስከትላል።
በተመሳሳይም መንፈስ፡ የግእዙን ቃል የሚመስል ያማርኛ ወይም የትግርኛ ጥሬ ቃል ካለና ጸያፍ ከኾነ፡ የግእዙን ቃል ቅሉን ከጸያፍ ያስቆጥረዋል። ባምርኛ፡ በትግርኛ እያሰቡ በግእዝ መቀኘት፡ መጻፍ መኾኑ ነው። ባንዱ እየተናገሩ በሌላው ሲመሰጠር፡ በተጻፈበት ቋንቋ የሌለ ነገር እንድናነብና እንድንረዳ ይጠበቅብናል ማለት ነው። ዓብደላ፡ በሒሶቹ ማኸል ይኽ ዓይነት ውሰት ሰርስሮ የገባበት ያጻጻፍ ስልት፡ የኣጠይቆ፡  ያረዳድ መንፈስ ነበረው።  ኣስረጅ፡-
[…] አያ ሳቅ እሳቱ፣ ፍሙን አክስሞታል
ኮሜዲው አርጅቶ ትራጀዲ ሆኗል።  […]
The late Mr Laugh has faded the embers;
 Comedy has aged into tragedy.
ፈረንሳ ከሩቅ ሩቅ ዘመዱ ‘እሳት’ ማለትን፡ ካያቱ ‘ነፍስ ኄር’ ማለትን ባንድ ቃል ‘feu’ ኣስተባብሮ ይገኛል። ትንሽ ግሪክ፡ ያን ያኽል ላቲን ከተማሩ፡ የ’እሳት’ መዳረሻ  እነእቶን፡ ምድጃ፡ ነበልባል ወዘተ እንደኾኑ፡ የ’ነፍስ ኄር’ ደሞ እነ ዕጣ ፈንታ፡ ዕድል፡ ‘ግደ’፡ ግድ  መኾናቸውን ኣያጡትም።   
[…] ድንገት ዞር ስትዪ፡ ዞር ብል በድንገት
 በዓይን ንጥቀት ፍጥነት
 የቆጠርናቸውም፣ ያልቆጠርናቸውም
 ትንሹ... ትልቁ
ከዋክብቱ ሁሉ ተደበላለቁ፤
 ከንፈሮቻችን ላይ፣ እሳት አፈለቁ።
 ከዚያ የሆነውን፡
 እኛም አላወቅን፡ እነሱም ኣልነቁ […]
When you suddenly turned your head, and I mine,
Quick as an eye snatch,
Those we counted and those we missed,
The small … the big ones
All the stars mixed up.
They set our lips on fire.
Whatever happened henceforth
Neither did we realize, nor were they aware.
snatch በእንግሊዝ ወያልኛ ፍቺ ኣላት። ኣዝማሚያዉን ኣይቶ የ’ዓይን ንጥቀት’  ቢጤቷ ከግእዙ ‘ቅጽበተ ዓይን ’ ይልቅ ወደ እንግሊዙ ወያልኛ snatch ያደላል ይሏል።  
 […]ህይወት መልኳ ሁለት ነው
አንድ ፊቷ ሙቀት ውበት፡ ላንጨብጠው የምናየው፡
 እንደ ምድጃ ዳር ተረት በፈገግታ የምንለውጠው፤
 ሌላ ፊቷ ፈጣን ቀለም፡ ከሩቅ ከቅርብ የምንወደው
 በርረን-ለፍተን፡ ጨንቆን-ጠቦን፡ ተሯሩጠን የምንይዘው […]
Life has two looks:
 A face of warmth and beauty only to behold,
 Just like a fireside tale we turn into a smile;
The other, fast color we love at a distance or close at hand That we take in our stride or laboriously, in anguish or in haste.  
ጸንተኽ (ቁም፡ ኑር) ሲልም፡ የማይገስ፡ የማይለቅ (ቀለም) ሲልም fast ይላል እንግሊዙ። ዓማርኛው ደሞ ቀልጣፋውን ሰው ፎጠና፡ ሳተና ይሏል። ተቀላጥፈን ኣፈፍ የምናረገው ዘላቂውን: ረግቶ የሚኖረውን ሳይኾን ይቀራል? እሱ ይኾን የታሰበው? ያ ከኾነ የእንግሊዙን  ፍቺ ሳያክሉ  በ’ፈጣን ቀለም’ የትም ኣይደረስ። ስንኞቹ  በጠረጠርነው መንገድ፡ በግልባጭ ስልት ተደርሰው ከኾነ፡ ዓብደላም የሚገነዘባቸው  በሌሎች ቋንቋዎች ስለሚቀበላቸው ይኾን?
‘ተናዳፊ ግጥም’-- ኣሻሚነት፡ ግልጽነት፡ ደብዛዛነት፡ ዘገባ፡ ፋታ… በዚኽም ላይ የዓብደላ ኣተያዮቹ  ዓዳዲስ ከመኾናቸው የተነሣ፡ የሚሰነዝራቸው ኣረፍተ ነገሮች እንግዳነት ይሰማባቸዋል።
ኣንድን ቋንቋ የገነባ ያስተሳሰብ ሰዋስው ኣለናም፡ የዚያ ሰዋስው ባለቤት ካልኾኑ፡ ቃል ሲለጠጥ፡ ኣለወትሮው ዘይቤ ሲላበስ፡ ኣልተለመደበት ቦታ ሲውል ግር ይላል። እንግሊዝኛና መሰል ቋንቋ  ለማያውቅ ዳገት ነው። እንደዚኹም፡ ቀዳማይ ኣንቀጽን ሲያዘወትር፡ በዚያኛው ቋንቋ እየተረጐሙ ካላነበቡት ለዛውን ኣይገነዘቡም።
ከዚኽ ቀደም ኣበው ያስተዋሉት ነገር ዓይነት ነው። ፍካሬ ዘጻድቃን ወዘኃጥኣን በተሠኘው የዳዊት መቅድም (ታሪክ) ላይ እንዲኽ የሚል ቋንቋ ነክ ቃል ይገኛል፡-
**[…] ይኽን ሰምቶ፡‘ እንቢክሙ ደቂቅየ፡ እንቢክሙ ደቂቅየ። ኣኮ ሠናይ ዘእሰምዕ ብክሙ፡’ ይላል።
## ‘ይኽ በናንተ የምሰማው ነገር  መልካም ኣይደለም። ‘እንቢላችዅ  ልጆቼ፡ እንቢላችዅ፡’ ኣላቸው።  በሃገራቸው ቋንቋ የተመለሰ ዓማርኛ። በሃገራችን ‘ኣይኾንም፡ ኣይኾንም!’ ማለት ነው።
[…] በትግርኛ በ3ቱም መደብ ዘምቶ ‘እምብልኹም፡ እምብልኩም’ን ጭምር የሚያሰኘው ‘እንቢ’፡ ባማርኛ  የተለመደው ተዘርዝሮ  ‘እንቢዮ’፡ ‘እንቢኝ’፡ ‘እንቢልኝ’  ሲል ነው።
ዓብደላ፡ የዘመናይ ነክ ቄንጡ በሚከነክኑት የኹኔታችን ጭብጦች ላይም ያጠላል፡- ‘የዕድር መሠነጣጠቅ፡ ያባል መነጠል፡ ብቸኝነት፡ ባይተዋርነት’ …ወቦ ዘ የተባሉ ሕመሞች ደጋግሞ ይጽፍባቸዋል። ኣልሞትንላቸውም እንጂ ገድለውናል እኮ፡ ኣሊያማ ምኑን ዘመናይ ኾነው? የሚል ይመስላል። እንግዲኽ ይኽ መስፈንጠርና ውሰት (በግእዝና ባማርኛ/ በትግርኛ) እስ በስ በኾነው ጕዳይ ጣዕሙ እንጂ ምረሩ እምብዛም ኣይታይ ይኾናል፤ በምኑም በምኑም ራቅ ባሉ ባዳዎች (ለምሳሌ እንግሊዝና ዓማርኛ) መካከል ሲከናወን ግን፡ ብሎም ሲንሰራፋ ፡ የሰፊ ሕመም ሰበብም መገለጫም መኾኑ ኣይቀርም። ምሁራዊው ሒስ ይኽን ዓይነቱ የሓሳቦች ታሪክ መመርመር  ተቀዳሚ ተግባሩ ነው።
በተራው ኗሪና ባገር ላይ የሚያመጣው መዘዝ ግን ምርምር ኣይሻም። ሰው ምስጢር ኣነባብሮ፡ መስሎና ኣሽሞንሙኖ መናገር በሚችልበት ቋንቋ የተጻፈ ጽሑፍ ተነቦለት ግር ይለዋል፤ በየስብሰባው ሲናገር ኣፉን እንዳልፈታ ሕፃን መኰላተፍ፡ ገልቱ መስሎ  መታየት ኣለ። የንግግሩ ወርቁን ካጣው ጥንትኑ ሰሙን በማያውቀው ሰዋስው ቢጋግሩት፡ ቢቀርጹት ነው። ኣምሳል መርገፉ ባዳ ቢኾን ነው። በመገናኛ ብዙኃን፡ በሥነ ጽሑፋችን (ዝርው ኾነ፡ ግጥም ኾነ) ያለውን ቋንቋ መመልከቱ ያስጠነቅቀን ይኾናል።
ካላቻ መጠጋት ካለ መለቃቱ ኣይቀሬ ነው። ነገር ግን ኣጋር ያሉት ባላጋራ ሲኾንም እናስተውል። ጕዳቱ መግዘፍ መለወጡ ላይ ኣይደለም፡ መገታቱ ላይ እንጂ። የማናውቅ የማንችለውን፡ በቅርባችን የማይበቅል የማይገኘውን ነገር ያስገብረናልና መናወዙ ይጠናወታል።  ፊደልን ያኽል ሃብት በጅ እያለ  እንዲኽ  በቋጥሮ የሚነገር የሥነ ጽሑፍ ክምችት ይዞ መገኘትን ያስከትላል። ይኽን ኹኔታ መናገር በራስ ፍቅር መታወር ኣይደለም፤ ይኽ በሽታ የለብንም… የጠናብንስ ሌላ።
ይኽ በኛ ቋንቋ ጽፌው በነእንቶኔ  ፊሊጥ ተረዳው መባባሉ፡ዅሉም ላይ ከለማበት፡ ፈጽሞ የሠለጠነብን ለት፡ ንግግሩ በልሳን፡ ገበያው ተያይዞ  ዘረባና ጨረባ፡ እርምጃው ቅጥ ዓጥ ዘጭ እንዘጭ ይኾኗታል! በያምባችን መኖር ከቀረ ወዲኽ፡ ባስኳላው ሥርዓት ፊደል መቍጠር ተጨምሮበት፡ ወግና ጌጡ በባዕድኛ ማሰብ ኹኗል፤ ለባዕድ እንትን ማደር ደሞ ምሱ ይኸው ነው። ‘ጦሱን ጥንብሳሱን ለማርከስ፡  ወደ ኣማናዊው ራስና ልብ መገሥገሥ፡’ ይላሉ ፊተኛውን መንገድ የመረመሩቱ! ተስፈኛ ተጓዥ ደሞ ለመዘመኑ ልብቃና እንዳሻው ያርገኝ እያለ ነው!
***
ነገሮች በቀደዱት ቦይ ነጐድኩና ከወንድም ዓብደላ ዓይነቱ ኣንድምታ ተቀላቀልኵ ልበል? ዓብደላ፡ ኣንድ ምንባብ በግለ ሰውነቱ ያሳደረበትን ስሜት ሲያካፍለን ካንድምታው ትውፊት ያፈነግጣል። ጥንቁቁ ባለ ኣንድምታ፡ ዅላችን ልናየው ወደምንችል ምስጢር እንኼድ ዘንድ  መንገዱን ከፍቶልን ካንባቢዎቹ  ይደባለቃል፤ ከኛው ኣንዱ የኾነ ያክል  ይሰወራል፤ ስሙንም ኣናውቀው። ስምም ካነሣ  ያባቶቹን ነው፡ እየተቀባበሉ፡ እያዳበሩ ዕውቀት ያደረሱትን ኣመስግኖ ለማስመስገን፤ትውፊቱ ትሕትናን ከጥልቅ ዕውቀት ያገናዝባልና። የተገናዝቦው ደንብ ምስጢሩን በማስረጃ ኣስደግፎ ማብራራት እንጂ፡ የነፍሱን ሓሤትና መቧጠጥ፡ የልቡን መጓጐጥ ኣይነግረንም፤ ስሜቱ ሞልቶ ኣይፈስበትም። ይኽ ‘ኣሠኘኝ’ የሒስ ጥራት ላይ ኣንዳች እንከን ያመጣበት ይኾን?
ይልቅ፡ ኣንድምታን ያነሣ፡ ትጋትን ኣነሣ፤ ካልተጉ ኣይተቡምና፡ ምስጢር ኣይገኝምና። ዓብደላ ትጉ ነበር፤ ትጋቱ ምንኛ ጠቃሚ እንደ ነበር በሚያውቁት ዘንድ በጣም ምስጉን ኣርጎታል። ለሥነ ጽሑፋችን ካንጀቱ የሚቆረቆር ሰው እንደ መኾኑ ላቅ ያለ የድርሰት ደረጃ ለማዋለድ ግጥሞችን በትጋት ኣንቧል፡ የጥበብ ሥራዎችን ፈትሿል። ያንዳንድ ደራሲዎች ሙሉ ሥራ መመርመር ኣንዱ መንገድ ነበር፤ ዘለግ ያለ ጊዜ ይበላል፤ ውጤቱም ኑሮ ኑሮ ብቅ የሚል (የሚደርስ) ነው።  ኣንዳንድ  ድርስ ጽሑፎችን እየመረጡ መተንተን ሌላው ኣማራጭ ነበረለት። ካለንበቱ የጥበብ ዓለማችን የሚገጥም ይኽ ኋለኛው መንገድ ቢመስለው፡ ‘ተናዳፊ ግጥም’ በሚል፡ ረገድና መንፈስን በተመረኰዘ ርእሰ ኣንቀጽ ማዕቀፍ፡ ተስፋ ያስቋጠረ ጥረት ኣካኺዷል። መሬት ላይ  ባይተከልም ተቋም ኣከል ኹኔታ ፈጥሮ ነበር፤ በተቀረጸለት መልክና የተመደበለትን ጊዜ ሳያዛንፍ፡ ያስለመደውን ብቃት ሳያጓድል መገኘት መቻሉ፡ ተቋም ያሠኘዋል። ዕድሜው ቢያጥርም በ’ዓዲስ ኣድማስ’ ላይ ያከናወነው ተግባር ወንበር ዘርግቶ ጕባኤ የመትከል ያኽል ነበር።
ወንበር ዘርግቶ ጕባኤ መትከል ደሞ ማስጨበጥ የሚሹትን ይዘው ሲገኙ ነው።  ማሥረጽ የፈለጓቸውን ጽንሰ ሓሳቦች ደጋግመው ያነሣሉ።
ዓብደላ ከሚያዘወትራቸው ቃላት፡ ኣንዳንዶቹ ጽንሰ ሓሳቦች ኣሻሚነት፡ ደብዘዛነት፡ ግልጽነት ናቸው።  ደብዘዛነት ሲል መላ ቅጡ የጠፋ፡ እጅ እግር የለው፡ ኣይያዝ፡ ኣይጨበጥ፡ ያልተብራራ ለማለት ይመስላል።
ኣሻሚነት የገጸ ንባቡ ባሕርይ ሲኾን የንባብ ዓጸፋው ኣንድምታ ነው። ምልኣትን ሲሹ ምንተ ራሱ  ደብለቅ የሚል ዕዝል ኣለ፤ የሰመረ ኣሻሚነት ነው።  ይኹነኝ ተብሎ የተጐነጐነው ግን ስንቅር ከመኾን ኣያመልጥም።  ያብደላ ወትዋችነት ደራሲው ይኹነኝ ብሎ ኣሻሚነቱን እንዲፈጥረው እስከ ማበረታታት ይኼድ ነበር ይኾን?
ግልጽነት ሲባል ለወትሮው ውሽልሽልና ድብስብስ ያላለ፡ የተብራራ፡ ብርሃን የዋለበት፡ ወለል ያለና የሚያምር ነገርን  ወደ ዓይነ ኅሊና ይስባል። ግልጽነት ቢቻልማ ኑሮ በተመቸ! እቅጩን ማለት ባለመቻሉ ግን የመምሰል፡ መመሰል፡ ማስመሰል ጥበብ  ተፈጠረ። በማን ወጣ መንገዱ? በግዱ!  እንዲባል። የጥበብ መሠረቱ የዚኽ የቋንቋ ዓቅመ ቢስነት ይመስላል፡ ጕዳዩን በጥበብ መወጣት። በዚኽ በገባኝ መንገድ ሳየው፡ የግልጽነት ሰሓው ማጠጡ ነው፡ የልብ አለሞምላቱ፡ ኣለማድረሱ። እንጂማ ለተፈለገው ጕዳይ ልክክ የሚል ቃል ቢገኝ ዕሰየው ነበረ። ምስልና ምሳሌ ከዋናው እንደሚያንስ (“ምሳሌ ዘየሓጽጽ እምኣማናዊ”፡ “ምሳሌ ይውኅድ  እምኣማን”)  በሰውም በዝንጀሮም ዘንድ  ይታወቃል።
 ---(ምስል)ጐፍላ(እንቡጣ)
ኣባቴ ጌታ ነው፡ እናቴ እመቤት ነች እያሉ ጨዋታ፡
 በጐፍላ ማለብ ነው ላም ጥጃዋ ሞታ።
-- የማሳ ዝንጀሮና ሰው--(ምስል፡ማስፈራርቾ)
ተው እንዲኽ ኣይኾንም፡ ኑሮ በተዳሎ፤
 ዓጣንና ነው ወይ ሰውና ደበሎ?
ዓብደላ ግን ግልጽነትን  ከድክመት ወደ መቍጠር ያጋድላል።  ይኽ ነገር የሚያስኬደው ግልጽነትን ፊት ለፊት መጠንቆል፡ መደንቀር ብለን ካሰብነው ነው። የዓብደላ ኣጠቃቀምና  ላይ የተጠቆመው የተለመደው ዘይቤ በማኛና መናኛ ያለውን ልዩነት ያኽላል። መነሻው ምን ይኹን ምን፡ ዓብደላ ግልጽነትን ባሉታ ያየው ለተዋሰው እንግሊዝኛ ቃል ኣቻ ትርጕም ሌላ ቃል ኣጣዅ በሚል እንደዅ? መፍጠጡን እንደዅ የጠላው?
ከኣሻሚነት በተጓዳኝ ‘ፋታ’ ሌላው ሓሳብ ነው። በንባብ ጊዜ  ላፍታ ቆም ብሎ የመጡበትን መንገድ ማጤን ኣለ፤ ጐዳናዉን ትቶ በስላቹ ጭልጥ ማለት ኣለ፤ ከቀናው ወጥቶ ዘወርወር እያሉ መናፈስም ኣለ። ድርሰቱ  በጐደለው ሙላ፡ የጠመመውን ኣቅናልኝ የማለት ያኽል በሰዋስዉም በሥርዓተ ነጥቡም ኣንባቢውን ይጋብዘዋል። ለምሳሌ ‘ነገሩ ገባኝ’ የሚለውን (የነብዩ?) ግጥም በመንቶ በመንቶ የተደረደረ ግጥም ሰተት ብሎ መዝለቅ ኣቅቶት መንገጫገጩ ኣይደለም፤ እያስተዋልክ፡ እየቋጠርክ ቀጥል ማለትም ይኾናል። ባራት ነጥብ መግታት፡ በማይሰድ ኣንቀጽ ማሰር እርጋታን ያመጣል።
ነጠብጣብን ዘርቶ በቸልታ ማፈግፈግ ኣንባቢዉን ለውጥን ጨራሽነት ሚና መጋበዝ ነው። ዓይን፡ ማረፊያ ኣገኘች ሲሏት ብር ብላ ሌላዉን መልከት፡ የወዲያኛውን ገረፍ ታረግ የለ?  ኣንባቢው ወለል ብሎ የሚታየው ኣቅጣጫ ኣለ፡ ገጸ ንባቡ ግን ሳይመስልበት ወደ ሌላ ያመራል፤ ለምን? ያመራምራል! ላንባቢው ፍቅርና ክብርም ማሳየት የደራሲው ጨዋነት ነው፤ ምንተ ጭውውቱ፡ ምንተ ዓብሮነት መጻፍም ኣለበታ… የመድረስ ነገር! ከዛ ካንባቢውም ቤት ኣእምሮ ኣለና ንግግሩ፡ ተዋሥኦው ነዋ የተሻው። ፋታው ዓረፍ ለማለት ሳይኾን ያንባቢውን፡ የታዳሚዉን ተሳትፎ ኣግኝቶ ትርጉም ለማዝመር ነው።
ኣማናዊው ኣካል (በተገኘበት)-- መልክ (በልባይምሮ)---ኪነ ጥበብ (ውጤት)
‘ዘገባ’ የሚለው ነቀፌታም ነበረው። ማንኛውም ነገር ራሱን ችሎ ይኖር በቦታው ኣለ እንበል፤ ኣማናዊ ኣካል (ምንጭም) እንበለው። ነገሩን ስናይ ስንሰማው፡ ተቀራርበን ስንነካካ፡  መዓዛ ጣዕሙን ስንቃመስ  ከሱው ልክ በመለስ ኣንድ መልክ (ቅጂ፡ ትርጕም)  - እንዲኽ እንበለውና- በውስጣችን ይፈጠራል። ከኾድ ኣንጀታችን፡ ከልብ ኣእምሮኣችን፡ ከኅሊናችን ይሰፍራል፤ ስሙ ካፌ፡ መልኩ ካይኔ ኣይጠፋም የምንለውም ኣለ። ነገሩ ነክቶ፡ ከንክኖ ላሳረፈብን የመልክ ኣሻራ  ቅጥ እናበጅለትና ኪነ ጥበብ ኹኖ ይሰናዳል።
ባብዛኛው ግን፡ ምን፡ መቼና የት እንዴት ኣሻራውን እንዳሳረፈብን ኣይታወቀንምና፡ ወጥ ነገር ከምናባችን ፈለቀ ስንል እንውተረተራለን። ኣበውም ያቆዩን ጕደኛንና ዋሾን የሚያይ ኣንዱ ተረት ይኽ እንዲቻል የሚያጠይቅ ይመስላል፡- ‘ወሲኹ ጸዋዪ፡ ሓሻዊ፤ ምሂዙ ጸዋዪ፡ ጕድ ኣናቢ፤’ (ቆርጦ ቀጥል፡ ዋሽቶ፤  ጕድ ኣናሚ፡ ፈጥሮ )።    
ነገር ግን፡ እንደኔ እምነትና “መቼም ኣለው ፈር ፈር፡ ለነገር መነሻ፡ ለመነሻ ነገር” እንዲል ደራሲ፡ ለነገር ጥንት ኣለው፡ ምክን ኣለው፤  እነሱም ምንጭና ኣሻራ፡ ልክና መሳይ መልክ(ምስል፡ ቅጂ፡ ትርጉም) ይኳዃናሉ።  እናም፡ ላረፈብን ኣሻራ ቅጥ ስናበጅለት፡ ኣንድም፡ ከራሳችን ኣውጥተን ኣገላብጠን እናስተውለው፡ እንገነዘበው ዘንድ ነው፤ ኣንድም፡ እዩልን፡ ስሙልን ስንል፤ ኣንድም ስለ ደስ ደስ፡ ወዘተ። ይኽም ኪነ ጥበብ፡ የመልክ መልክ (የቅጂ ቅጂ፡ የትርጉም ትርጉም) መኾኑ ነው… ከልክ ወደ መሳይ መልክ፡ ከመሳይ መልክ ወደ ጭገሬታ የመዝለቅ ያኽል ተኺዷል። ሰይፉ መታፈሪያ ይኽን ኺደት  ኣድቀው ኣልምተው ያወጉታል።
እንግዲኽ ኪነ ጥበቡ ጠበቅ ተደርጎ ከተመረመረ የመሳይ መልክ መሳይ መልክ ነው። በምን ማመልከቻ? በቀለም፡ ቃል፡ ቃና፡ ቅርጽ። ምን ቁስ ላይ?  ወረቀት፡ ብራና፡ ሸራ፡ ጨርቅ፡  ዕንጨት፡ ድንጋይ ላይ።  
ጥበቡ ከነዚኽና መሰል ዓላባዎች ይገኛል፤ የጥበባት ዘርፍ ይወለዳል። መጻፍ መሸለም፡ መሣል መኳል፡ መቅረጽ ማንጠጥ፡ መሸመንና ማሽሞንሞን፡ መቃኘት፡ ወዘተ። እዚኽ የምንወያይበት ጕዳይ፡ ታይቶ፡ ተሰምቶ በሩቁ ስሜት/ዕውቀት ማሳደር ዓይነቱን  ነው፤ መነካት ቢኖር እንኳ መተሻሸት ኣይኖርም። (ላኹን የሚሸተተው መዓዛ፡ የሚቀመሰው ጣዕም ይቆየን። እነትወና፡ የሃይማኖት ክዋኔዎች ሌላ፡ ሌላ ጥበብ እየተጨመረባቸው ምንጭ ካልነው እየራቁ፡ እየራቁ የሚኼዱ (የቅጂ፡ ቅጂ፡ ቅጂ… የትርጉም፡ ትርጉም፡ትርጉም…) የውልድ ውልድ ውልድ… ጥበባትንም እንደዚኹ።) ከግዙፍ ወደ ረቂቅ ቢሰደሩ ቅርጽ፡ ሥዕል፡ ጥበበ ቃላት(ድርሰት)፡ ሙዚቃ (ቃና) እንል ይኾናል። እነዚኽ ጥበባት ዓለማት ናቸው፤ የየራሳቸው ‘ቋንቋ’ ኣላቸው።  ለጊዜውና ለመነጋገሩ፡ እኒኽን ‘ቋንቋዎች’፡ ቅርጽኛ፡ ሥዕልኛ፡ ቋንቍኛ (ኣንደበትኛ)፡ ሙዚቅኛ እንበላቸው።
በመደበኛው ቋንቋ፤ የኣንድን ቃል ፍቺ ለመንገር የግድ ሌላ ቃል ያስፈልጋል፤ ኣቻው እንዳልኾነ ግን እናውቃለን፡  የቋንቋ ሥሪት ላንድ ሓሳብ ኹለት የሚተካከሉ ቃላት ኣያባክንም። እንዲሁም ኣንዱን ጥበብ በራሱ ‘ቋንቋ’ ለመግለጽ ኣይቻልም። ለዚኽ ጕዳይ ሙያ የሚኾነን ለወትሮው ቋንቋ የምንለው፡ ቃላት እያሰካካን የምንገለገልበትን መገናኛ ነው። ሥዕልን በቋንቋ፡ ሙዚቃን በቋንቋ እንወያይባቸዋለን። ቋንቋ ላይ ስንመጣ ገላጭም ተገላጭም ራሱ መኾኑ ግር ይላል፤ እንጂማ ጥበበ ቃላትም ቋንቍኛ ብለን ስም ያወጣልነት የራሱ ‘ቋንቋ’ ኣለው። ‘ዘገባ’ እየተባለ ከሚጣጣለው ጀምሮ ‘ወለሎ’ እስከሚባለው ኣፋፍ  የተሰጡት ድርሰቶች  ኣንዱ መለያያቸው የጥበበ ቃላትን ‘ቋንቋ’፡ቋንቍኛዉን የመገንዘብ ጕዳይ ይመስላል።
***
የዓብደላ ጽሑፎች ‘ኹኔታችንን’ ለመገንዘብ የሚረዳ ፍንጭ ኣላቸው። ይበልጥ ቢፈለቀቅ ኣሳሳቢ ነገሮች ይገኙበታል፡- ሥነ ጽሑፉ ሳይኖር የሚተከል የሒስ ሙያ  ተስፈኛነቱ ኣጕል ነው፤ ካልበቀለበት ሃገረ ጥበብ የሚውል ሒስ ገልቱነት- ኣንዳንዴማ የሌለን እስከ ማግኘት የሚዘልቅ- ኣያጣውም፤ የጥበብ ነክ ትምህርት ሥርዓቶቻችን ወልደው የሚኰተኵቱበት ኣዝማሚያ … የማታ ማታ መክኖ በሚያመክን ግንጥል ልፋት እንዳንጠመድ  ያሠጋል።  ጕዳዩን  ግን፡ የዓብደላ ሥራ መነጋገሪያ ኹኖን እንጂ፡ ባገር የመጣ፡ ቀደም ብሎ የጀመረ መኾኑንም በተለያየ ገጽታው ኣነሣሥተነዋል። ጠንካራ ኣጋር ዘንድ ሲጠጉ ለመለቃት ነው። የራስን ሳይለቁ መለቃት ይሉት ጥበብ እምብዛም  ኣይሳካ፤ ዘመን ኣመጣው፡ ሰው ወደደው እያሉ መንሸራተት  ይቀላል።  
***
ሒስ ነቀፌታ፡ ትችትና ማሻሻል ከመኾኑ በፊት መረዳት ነው፤ የኣእምሮ ቋንቋ ነው፤ መተርጐም ነው። በዚኽ ረገድ የዓብደላ የነገሮች ማተራጐሚያ ስልት ወደ ይዘት ያጋደለ፡ ግምገማውም ሰው ተኰር መስሎ ይቀርባል። ሰው ከሰውና ከራሱ ያለውን ውስብስብ ዝምድና ወዳንድ ፈሊጥ ቀንሶና ኣቃሎ መተንተን ወትሮም ይፈታተነናል፤ ጭብጥ ኣርጎ በርግጠኝነት ዓለምን የምታስቃኝና የምትዘውር ኣንዲት ፍሬ (ሓባ) ጭብጥ እንሻለን። ለምሳሌ የመደብ ትግል ያንድ ያብደላ ዘመን መለያ ነበረች፤ በጨበጡ መፍረጥረጥ፡ በረገጡ መፍረክረክ እንዳለ፡ ሊጥነት ኣያጣው ዓለም በጣቶች መኻል ሳይሸሽ እንደሚያፈተልክ  ኣስረስታን ነበር። እንዲኹም ሥር ነቀል መኾንና ወግ መግሰስ ሰሞነኞች ነበሩ።
የኤፍሬም ስዩምን ኣንዲት ግጥም ያነበበበት መንገድ ማሳያ ትኹነኝ። ግጥሟ ነዳይና ከበርቴን በቤተ ክርስትያን ዓጸድ ታያለች።  በነዳይ መከራ መብሰልሰል የተከበረ ኣስተውሎትና የነፍስ ኣዝማሚያ ኹኖ ሳለ፡ የወሉን ቤተ እምነት ለመገንባት የሚነሣሣውን ስሜት በተቃርኖ ማንጸሪያነት ማስቀመጥ ግንዛቤዉን ወደ ተራ ውግዘት ይጐትተዋል (ወዲኽ ማዶ ርኅራኄና ብጽዓት-ጭካኔና ግብዝነት ወዲያ ማዶ)። ንባቡ የሰውን ዅለመናዊ ባሕርይና የወል ፈቃድን ዝቅ ያረግ መሰለ፤  የሰውን ልብ ሥርጓጕጥ ወለል ብሎ ወደሚታይና ለመወገን ወደሚመች ልሙጥነት ያድቦለቡለዋል። ሰውኮ ‘ሰው መኾኑ ጋራ ኣይደለም እንደ ሰው….’ ተብሎ ስንኝ ተቋጥሮለታል፤ ‘ትድረት የተባለ ይተወዋል ንቆ፡ ዠንበር ተመዲና እየታየው ዘልቆ’ ተብሎ ተቀኝቶለታል! ጥበብ ምልኣትን ለመላበስ ካላሻ ምን ሊኾን? ንባብኮ ቀርቦ ዝርዝርን፡ ፈቅ ብሎ ተዛምዶን ሲያቀዳጅ ነው ደስ የሚል።
ኣጕራ ሲዘለልስ የት ድረስ ነው? እሳተ መለኮት የመሰለን ባዋጅ የታወቀ፡ በትውፊት የጸደቀ መግባቢያ ምሳሌ ወደ ፍትወት ጣጣ መዶል ምን ጥልቅ ግንዛቤ ይገበይበታል? ዓውዱ የታወቀ ቢኾንም ምን ዓይነት ቅኔና ግጥም ሊቀሰቅስ  እንደሚችል ለቅምሻ ያኽል ከኣበው ክትትል ግጥም (ሰፋ ያለ ዘረፋ እንበለው?) ከግርጌ ጠቅሻለዅ፡፡   
ኣንዳንዴም የዓብደላ ሒስ ፈር ለቆ ዅለ ገብ ኣስተያየት ይኾንብኛል፤ የሚያስተዋውቀን ደራሲ ደሞ እሱ ራሱ ከመኾን ዓልፎ ሓያሲው  ከጸሓፊዎች ተራ  ብድግ ያረገው፡ ኣሊያም የፈጠረው ገጸ ባሕርይ ይመስለኛል። ያ ተደከመበት እንጂ እምብዛም ረብ የለው፤ ይኽ ከወረቱ ስንቁ፡ ከታምሩ መቅድሙ ማስባል ይዳዳዋል። የዅሉን መሰል ሰውና የዅለ ገብ ነገር እንዲያ ነውና።
***
እግረ መንገድ
“ዅሉን መሰሉ ሰው ምነው ቅር ያሰኝ? ኣለስ ወይ? ካለስ፡ ወዴት ነው?” በእግረ መንገድ ቢያነሡ፡ መልሱ ኣያወላዳም፤
ካለበት ኣለ! ላብነት፡ የተሰፋ ልብስ ነጋዴ ኣቶ ኣገሬን ጠንቅቆ ያቀዋል፡- ዓንገቱ፡ ወገቡ ይኽን ያኽል፡ የደረቱ ስፋት፡ የቁመቱ፡ የትከሻው ኹኔታ፡ የእጁ ርዝመት እንዲኽ፡ እንዲኽ  ተብሎ ይታወቃል። ይቺ ይቺን ሳይመራመር  ሰው በላው ገበያ ኣድጎ ነው? ኣቶ ኣገሬ ማተቡ እንዲኽ የላላና የከረረ፡ ሓሞቱ እንዲያ የቀጠነና ኰስተር ያለ ነው እያለ ሲሰፍረው፡ ሲመዝነው የሚውል ፖለቲከኛም ኣለ። ድሮስ ያንን ኣምኖ ኣይደል ካልነዳኹኽ የሚለው?  ኣቶ ኣገሬ ቤተኛ  ተብዬ ሰው ነው፤ ብዙ ያገር ሰው የሚጋራቸው ነገሮች ባለቤት ተደርጎ፡ የወል ልክና መልክ ይዞ  ይቀመራል፤  ነጠላችንን ዜጋ፡ በጥቅል መንጋ እየተሰኝን የምንዘልቀው እኛ ማለት ነው።    
ገጸ ባሕርይ ደሞ ዅሌም ዓጅሬ ኣቶ ተዋጽኦ ይሰኛል፤ ራሱን ነዋ እሚመስል። እንድናውቀው ኹኖ ይሣላል፤ ማወቅም መለየት ነውና እንድንለየው ተደርጎ። መለያው  ያልተነገረለትና በቃሉ፡ በግብሩ፡ ባዝማሚያው፡ በጭገሬታው የማይለይ ከኾነ ጥፍጥፍ ፍጥረት ነው። ‘ኣይ፡ የሱ ነገር እንዳመሉ ደሞ ተመቸ!’ የሚባልለት እገሌ፡ ‘ይቺ ተንኰል የሱ ሥራ ናት’ ተብሎ የሚማልለት ዓጅር፡ ‘ይቺ ቃል የራሱ ያንደበቱ ናት፡ ከሱ ሌላ ማንም ኣይላት!’ ተብሎ የሚመሰከርለት ገዛ ራስ፡ ከዃላ  ዓይነ ኅሊናችንን ጨፍኖ ‘ማን ነኝ?’ ቢል እዝነ ኅሊናችን በቃሉ ለይቶት በስሙ የምንጠራው ነው ገጸ ባሕርይ ማለት።
ፍጥርጥሩ፡ ግለ ሰቦች የገዛቸው ከኾነው ያዋጡት፡ ካንዱ፡ ካንዱ የተቃረመ የጠባይ፡ የመልክ ድብልቅ ነው። ቅይጡ ግን የለማኝ እኽል ይመስል ውጥን ቅጥ ሳይኾን፡ ለማሙዬ ተብሎ ባልትና የጐበኘው የ10ር እኽል ምጥን ዓይነቱ ነው። ምጥን ወይዘሮው በደራሲው ምናብ ይሰናዳል። ልቦለዱ ከነባሩ ይልቃል የመባሉ ምስጢር ይኽ የምንጭ ብዛት መስሎኝ። ያም ኹኖ፡ ካላችኹስ ለሕያዉ፡ ለቋሚው ሰው ለኣቶ እገሌ የሚቀርብ፡ ከኣቶ ኣገሬ ይልቅ ይኸዉ ገጸ ባሕርይ ዓጅሬ ኣቶ ተዋጽኦ ነው። ዓብደላ ያቀረበልኝ ኣንዳንድ ገጸ ባሕርያት ከደራሲዎቹ ኣልገጥም እያሉ ቅር ተሰኝቻለዅ። ዓብደላ ራሱ ግን ኣንድ ውድ ገጸ ባሕርይ ኹኖልኛል።
‘…ሰውነቱ ታውቆ’ የኖረን ሰው ከሰውነት ኣወጣኹት? ያተያይ ልዩነት ጣጠኛ ነው። ሰው ማንነቱን፡ ምንነቱን ሲፈልግ ሌላውን ሰው ዓይና ዓኑን ያያል። ይችን ሓቅ ኣስተውሎ፡ ኣንድ ደራሲ ‘እንዳዩሽ’ የተሰኘ ድንቅ መስታየት ፈጠረ፤ ሰዉም ምን እመስላለዅ ባለ ቍጥር መልኩ ኣልረጋ፡ ኣልጸና ኣለው …  መልክ በያይነቱ እንደ ተመልካቹ እየኾነ። ታዲያ፡ ኣንዱ ኣንባቢ፡ “ባገሩ ውዥንብር ነዛበት፡” ኣለ፤ ሌላው፡ “መልክ ባገሩ ናኘበት፡ ፈሰሰ ሃም ማይ ነሓሰ።” ለኔ፡ ገጸ ባሕሪው ዓብደላ ልበ ገብ ነበረ።   
ሒሶቹ ብዙ ሥራዎች ጋራ ኣላምደውኛል። እግረ መንገዳቸውም  የዓብደላ  ሓያሲው ሰው ኣንዳንድ ጠባዮች ጠቁመውኛል፡- በግልቢያና በዘልማድ ንባብ ጊዜ፡ እያሉ የማይታዩትን ገጽታዎች በኣስተዋይነቱ ኣስገነዘበ። የተዋጣላቸው ጽሑፎች እየደጋገመ በማቅረቡ፡ ሙያ ብለው የያዙትን ጕዳይ ሊካኑበት እንደሚገባ ኣሳየበት። የጥበብ ወዳጅ ነበርና ባካል ያልተዋወቃቸው እኔን የመሰሉ ብዙ ወዳጆች እንዳፈራ ዓውቃለዅ። ሒሶቹ ነብስ ይማር እያለ የሚቆዝምባቸው ብዙ ኣንባቢ- ገና ያልተወለደም- ይኖራቸዋል።   
የኅዳግ ማስታወሻ--  ከሰው ኣፍ፡ ከመጽሓፍ።
ሀ)- […] “ድንግል ወለት ትመስለነ ዕቤርተ፤// አኮኑ ትውዕል እንዘ ተሐቅፍ እሳተ” = ባልቴት መሰለችን  ድንግል ገና እያለች፤// ትውል የለም ወይ እሳት እንዳቀፈች?!”     
(ገና ልጃገረድ፡ ልጂት፡ ሙጪት፡ ኣንዲት ፍሬ ሳለች) ይኽ ቅኔ ዓብደላን እንዲኽ ኣስብሎታል፡- “[…] ከትዳር ቀለበት ሾልከው፣ ሌላውንም በወሲብ መቅመስ ሳይደፍሩ የቀሩት፤ በስተርጅና ለመቆጨትም በትዝታም ለመፍለቅለቅ እንደ ሥንቅ ነው፤ ዕድሜ መች መክሰም ብቻ ኾነ? ዘዋሸራ ተክሌ ከነገረ መለኮት ሱባዔ ስሜታቸውን ጐትተው ግራ ቀኝ ገላምጠው ድንግል ልጃገረድ ያቀፈችው እሳት እንዴት አባበላቸው? እንዴት ለመቀኘት እርሾ ኾናቸው? ቢያሰኝም በሔዋን ውበትና ዕጣ ፈንታ መመሰጥ ለባለ ቅኔ አንድ የሕይወት ሰበዝ ነው፡፡ … ዘዋሸራ የተቀኘላት ልጃገረድ የታቀፈችውን እሳት ከሰብለ ወንጌል ጀምሮ በአያሌ ልብወለድ ተቀርጻለች […]”  
ተክሌ ዘዋሸራን  ሰውሰውኛዉን ንቆ ልመጻደቅ ሲል መስፍን ወዳስተዋለው ዓሳረኛ ( “[… ]የገዛ ራስ እስረኛ ሲኮን ደሞ ኣለዕድሜ መንኵሶ ካዩዋት ጋራ ዅሉ ዓይንን እያንከራተቱ መሰቃየት ይኖራል።[…]” ፍቅርና ፍቅረኞች። መስፍን ሃብተ ማርያም--እፍታ። ) ያወርድና፡ በስውር ሕሊናው የተቀበረው በቅኔው ወጣ ይለናል። ይኽ ኣፈታት በተለያዩ መንገዶች ሲቀርብ ይገኛል፡- ኣንዳንዶች ፊቱን ጸፍቶ  እውነቱን ኣናገረው/ የጎርጊስን የበላ ኣሰቀድሞ ያስለፈልፈዋል/ ዳኅፀ ልሳን/ በሳይኮ ኣናሊስስ ትንታኔ …ወዘተ
ቅኔ የሚፈታው፡ የተመሰጠረው ፍሬ ነገር የሚደረስበት ታሪክን ችላ ሳይሉ ነው፡ የቅኔዉንም ኾነ የቅኔን ኣካኼድ ታሪክ። (ያም ኾኖ የሌሎች ዓለባዎች ኣስፈላጊነት ኣይሳትም።) ባለቅኔው የመለኮትን ረቂቅ ባሕርይ፡ መርዕድ መልክ  በእሳት መስሎ ኣጠየቀ። የቀደሙት ኣበው የተከሉትን ምሳሌ ባንደበቱ ኣለው። ድንግሏን ጠቅሶ ልቡን ወደሞላው ዋናው ኣድናቆት ዘለቀ።
ፈጽማ ያረጠች፡ ሙቀት ልምላሜ የተለያትን ባልቴት ከመሰለችው ወዲያ፡ ደራሲው በነገረ ፍትወት ተብሰለሰለ ማለት ኣይሰድም። ዓብደላ ገጸ ንባቡን ተጋፋው። ትውፊቱን መደብና ገንዘብ ማረግ ግድ ነው፤ ይኽ ቅኔ በዓውዱ፡ በቤቱ ተቀዳሚም ተከታይም ኣለው። ካስረጅነታቸው ሌላ ስለ ደስ ደሱም፡ ስላሰኛኘታቸውም እኒኽ ተዛማጅ ግጥሞች ቀርቧል።
ሁ)- ኣቶ ቢረሳው ቢሻው (ቢቢ) እና ኣለቃ ተገኝ ታምሩ(ተታ)
በድንግል ማርያም ስም ማኅበር ይጠጣሉ። ባለድግሱን ባማርኛ ማሕሌት ካመሰገኑ በኋላ እንዲኽ ገጠሙ፡-
[ቢቢ-ነበልባለ እሳት በላይዋ ሰፍሮባት// ከልምላሜ ኾና ጫፍዋ ሳትቃጠል/ ድንግል ማርያም ናት ሙሴ ያያት ቅጠል
ኣለቃ ተገኝ ታምሩ ክትትል ኣድርገው እንዲኽ ገጠሙ፡-
ተታ- ንግባእኬ ብለን፡ ክብሯን ተመራምረን/// ድንግል እመቤቴን እስቲ እናሞግሳት፡/ እንዴት ፀነሰችው ዅለንተናው እሳት?
ቢቢ- ድንግል ኾኖ መውለድ፡ እሳትና በረድ/// ኹለት መስተፃርር ኣስማምታለችና/ ቤዛዊተ ዓለም ናት የግብፅ ደመና።
ተታ- ለጋ ወጣት ኹነሽ፡ በጠባቡ ጐንሽ/// እስኪ ልጠይቅሽ ማርያም ወዳጄ/ እሳታዊ ዙፋን ወዴት ተዘጋጀ?
ቢቢ- ዓራሽ ያልቀረባት፡ ዘር ያልወደቀባት/// ፍሬ ሕይወት ጌታን ያስገኘች ኣብቅላ/ የነኣብርሃም ገነት ድንግል ናት ወለላ።
ተታ- ወልዶ ድንግልና፡ እመቤት ግርድና/// ይኽ ዓይነት ዕድል የያዘች ኣፃምራ/ ካውራው ድምፅ ሰምቶ ንብ ዕጭ እንዲሠራ/ በብሥራት ወለደች የእግዚኣብሔር ሙሽራ።]
ሁ)-ዮፍታሔ ንጉሤ
ነበልባለ እሳት ከሓመልማል ጋራ፡/ ውዕየትና ርጥበት ኹለቱ በተራ፡/ እሳቱ ሳይጠፋ ሓመልማል ዓይሎ፡/ ሓመልማል እሳቱን ሳያጠፋ ውሎ፡/ ከግንብ ኣስገብቶ በጎቹን ቀላቅሎ፡/ ይኽንን ድንቅ ኣየ ሙሴ ተከታትሎ።---- (‘ለማስታወስ ያኽል’--ዮሓንስ ኣድማሱ--  መነን፡ ሰኔ 1961።)

Read 738 times