Sunday, 10 June 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)


              “መታዘዝን የቻለ፣ ጥሩ አዛዥ ይሆናል”


    “መጣር እፈልጋለሁ፤ ማወቅን እሻለሁ” አለው። ጠቢቡም “የምትፈልገውን እንድታገኝ ለኔም ለሌሎችም የምታበረክተው አገልግሎት አለህ? ፈቃደኛ ነህን?” ሲል ብላቴናውን ጠየቀ፡፡
ብላቴናውም፤ “ደስ ይለኛል” በማለት ተስማማና ማገልገል ጀመረ፡፡… ሩቅ ቦታ ይላላካል፣ ምግብ ያበስላል፣ ታላላቆቹ ሲወያዩ እያዳመጠ፣ በሌላ ጊዜ ሲጠይቁት እያስታወሰ ይነግራቸዋል፡፡ በምሽት መጽሐፍት ሲያነቡ ጧፍ ያበራላቸዋል፡፡ እንደነዚህና የመሳሰሉትን ነገሮች እያከናወነ አንድ ዓመት ቆየ፡፡ ወደ ጠቢቡም ሂዶ፡-
“እነሆ አንድ ዓመት ሞላኝ፤ ትምህርቱን መቼ ነው የምጀምረው?” ብሎ ጠየቀው፡፡
“ገና ነው” ተባለ፡፡
ሁለት ዓመት ሲሞላው እንዲሁ አስታወሰው፡፡ አሁንም፡-
“ገና ነው” አለው መምህሩ፡፡…በሶስተኛውም፤ በአራተኛውም ዓመት እየቀረበ ቢያስታውሰውም የመምህሩ መልስ… “ገና ነው” የሚል ነበር፡፡
ዘመን እየሄደ፤ ዘመን ሲተካ የብላቴናውም አገልግሎት እየበዛና እየጨመረ መጣ፡፡ የሚነጋገሩትን ሁሉ ሳይቀር ባሳዩት መልዕክቶችና ፊደሎች እየከተበ እንዲያስቀምጥ ያደርጉታል፡፡ በስራው ከመጠመዱ ብዛት ወደ መምህሩ እየሄደ ማስታወሱን እየዘነጋው መጣ፡፡ በሁዋላም ከነአካቴው ረሳው፡፡ ሃያ ዓመታት ያህል አለፉ፡፡ አንድ ቀን ከመምህሩ ጋር በአጋጣሚ ለብቻቸው ተገናኙ፡፡ ብላቴናው ሰላምታ ሰጥቶት አለፈ፡፡ ጠቢቡ ግን ቆም አለና ጠራው፡፡
“አቤት” ብሎ ቀረበ፡፡
መምህሩም፤ “ስለ ሞን አላስታወስከኝም?” ብሎ ቢጠይቀው፣ ምን ብሎ እንደመለሰ ታውቃለህ?... “በሁዋላ እነግርሃለሁ፡፡”
* * *
ወዳጄ፡- የሚያስፈልግህን፤ የምትመኘውን ከረሳህ ወይም ካላስታወስክ ‹ራስህን› ረስተኸዋል ማለት ነው፡፡ አለበለዚያ የምትመኘውን አግኝተሃል፤ የምትፈልገውን ሆነሃል፡፡ ህልምህ ተፈታ፤ ነቃህ፤ በራህ እንዲሉ!! ይህ ካልሆነ ግን መጀመሪያውንም የምፈልገው ነገር አልነበረም፡፡ ወይም የምትፈልገውን አታውቅም። ወይም ራስህን አልተረዳኸውም፡፡ ምናልባት ደግሞ በፍለጋ ላይ ትሆናለህ? ወይስ…?... ወይስ ሩቅ ሆኖብህ ተስፋ ቆርጠሃል?... አጋጣሚ አልተመቻቸልህም? ወይስ ኑሮና የገበያ ዋጋ አሸንፎህ ተሸጠሃል? ወዳጄ፡- ምክንያትህ ምንም ይሁን ምንም፣ ራስህን ፈልገህ እስካላገኘኸው ድረስ የነፍስህ ጥሪ ይጮሃል አያቋርጥም፡፡ አንተ ‹አንተነትክን› አይረሳውም፡፡ ለዚህ ነው ራስህ ራስህን የሚጠይቀው፡፡ “ማነኝ?፣ የምፈልገውን አግኝቻአለሁ?፣ የምመኘውን ሆኛለሁ?፣ ለነፍሴ ጥሪ መልስ ሰጥቻለሁ?” እያለ ይወተውትሃል፡፡ ባትነግረውም የሚያውቀውን ዕውነት እንድትነግረው ይጨቀጭቅሃል፡፡
ወዳጄ፡- አንተና ውስጥህ ማለት አንተና አንተ ከሆናችሁ፤ ፍላጎትህና ምኞትህ አንተ ውስጥህ የተቀበረ ማንነትህ ነው፡፡ አብሮህ ኖሮ አብሮህ ያረጃል፡፡ በደንብ ግን ላትተዋወቁ ትችላላችሁ፡፡ እንዳትተዋወቁ ያደረጋችሁ እንግዳ ነገር መሃላችሁ ገብቷል፡፡ ይህን ከፋፋይ እንግዳ ተፈጥሮአችን አይፈልገውም፡፡ እኛ ግን ሁሌም ወደ ራሳችን እንጋብዘዋለን፡፡ መሆን የፈለኩትን አልሆንኩም ወይም መሆን የምፈልገው ‹እንትን› ነበር የምንለው ወይም ሌሎች ወዳጆቻችን “አንተ መሆን የነበረብህ እንትን ነበር” የሚሉን በሱ የተነሳ ነው፡፡…በማስመሰል!!
እንደነዚህ ዓይነት ውስጥን የሚያኩ ስሜቶች (Feelings) ወደ ውጭ በሚጮኹ ቃላት መግለፅ ያስቸግራል፡፡ ለምሳሌ፡- አንዳንድ ሰዎች ትምህርታቸውን መርጠው ሳይሆን በተመደቡበት ፋኩሊቲ እንዲያጠኑ ይደረጋሉ፡፡ ወይም ቤተሰቦቻቸው “ልጄ ሲያድግ እንዲህ ይሆናል” እያሉ ያስጠኗቸውን ይሆናሉ፡፡ ሃኪም፤ መሃንዲስ፣ ኢኮኖሚስት፣ መምህር፣ እግሪካልቸርስ፣ ቴክኒሺያን፣ ወታደር ይሆኑና ይቀጠራሉ፡፡ ጥሩ ባለሙያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡… እንደ ጎበዝ ተዋናይ!!... ስራቸው በሚያስገኝላቸው ጥቅም፣ በመኖሪያ አካባቢ ወይም በሌሎች ሁኔታዎች ካልተደሰቱ ግን ወደ ተሻለና ወደሚመቻቸው አካባቢ ጥለው ይሄዳሉ፡፡ የተሻለ ጥቅም፣ ዝና ወይም ምቾት ያለው ሌላ ስራ ከቀናቸውም የተማሩትንንና የሰለጠኑበትን ሙያ እርግፍ አድርገው ይተዋሉ፡፡ ወደ ንግድ፤ ወደ ስፖርታዊ ጉዳዮች፣ ወደ አስተዳደር፣ ወደ ሃይማኖታዊ ተልዕኮ፤ ወደ ጥበብና ፖለቲካ ወይም የተገላቢጦሽ ሊያዘነብሉ ይችላሉ፡፡ አብሯቸው የሚቆየው የበፊቱ ትምህርት ሳይሆን የበፊቱ ማዕረግ ብቻ ይሆናል፡፡
ከውስጥ የመነጨ ፍላጎታቸውን የመሙላት ዕድል ያገኙት ወይም የነፍስ ጥሪአቸውን ያዳመጡት ግን ምንም ዓይነት ምቾት፤ ጥቅምና ዝና ሳያታልላቸው፤ በተማሩበትና በሰለጠኑበት ሙያ፤ ጦርነትን ጨምሮ እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ስራቸውን በፍቅር ይሰራሉ፡፡ ድንበር ተሻግረው “ሰው” በመሆናቸው ብቻ የሚያውቃቸውን ወገኖች በትምህርት፤ በህክምና፣ በልማትና በሌሎች ጉዳዮች ይረዳሉ፡፡ የቤትና የዱር እንስሳት፣ የባህር ፍጥረታትንና አዕዋፋትን እንዲሁም ደኖችና ሌሎች የተፈጥሮ ፀጋዎች በተገቢው መንገድ እንዲጠበቁና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው በሙያቸውና በፍላጎታቸው ያግዛሉ። ይህን በማድረጋቸው መንፈሳቸው ከአጠቃላይ ሁለንተናው ጋር ያጣመራል፡፡ ሁሉንም በነሱ፤ እነሱም በሁሉ ውስጥ ይኖራሉ!!
ወዳጄ፡- ለነፍስህ ጥሪ “አቤት!” ስትል፣ አንተና ውስጥህ አንድ ናችሁ፤ አንተና አንተ አትለያዩም፤ ፍላጎትህን በትክክል ታውቀዋለህ ማለት ነው፡፡ ለማስመሰል እጅ አትሰጥም፡፡
… የነፍስ ጥሪ ማለት
    የለሰለሰ ስብ፤
የተከፈተ ዓይን፤
“ማየት” ሚታይለት፤
“መደመጥ” ሚሰማበት፤
ከላይ- እንደ ሰማይ፣
ከታች እንደ መሬት፣
የነፍስ ጥሪ ማለት፡- ሁሉን ሚችሉበት!!
ማስተዋል ነው…ሩቅ፣
እየመረመሩ
ወደጥልቁ መዝለቅ!!
የነፍስ ጥሪ ማለት፡-
ሃሳብ ነው… አእምሮ፣
አጥር ያፈረሰ
ድንበር ኬላ ሰብሮ!!
የነፍስ ጥሪ ማለት፡-
“መሆንን የቻለ፣
ኢምንት የሚመስል
ትልቅ የገነነ፣
ለራሱ ሰው ሆኖ
ለሰው ሰው የሆነ!!
ወደ ተማሪያችን ስንመለስ፡- መምህሩ፡-
“ሰለሞን አላስታወስከኝም?” ብሎ ሲጠይቀው፡፡
“ምኑን?” በማለት ነበር መልሶ የጠየቀው፡፡ ጠቢቡ ይሄ ቀን እንደሚመጣ ያውቅ ነበር፡፡ ውስጡን ደስ አለው፡፡ ቀኑ የመጀመሪያው ትምህርት መጨረሻ ነው። ተማሪው ጠቢቡን ከአገኘበት ደቂቃ ጀምሮ እየተማረ መሆኑን የተረዳው፣ መታዘዝ መማር መሆኑን የገባው --- እያወቀ፣ እየበሰለ ሲመጣ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ወዳጄ፡- “መታዘዝን የቻለ ጥሩ አዛዥ ይወጣዋል” ያለንን ታስታውሳለህ? በኔና ባንተ ይቅርና፣ ያ ወዳጃችን ነው - ቮልቴር!!
ሠላም!!
ከአዘጋጁ፡- ባለፈው ሳምንት በዚህ ዓምድ ላይ በስህተት ለተዘለለው አንቀፅና የቃላት ግድፈቶች አንባቢን ልባዊ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡  

Read 1137 times