Sunday, 10 June 2018 00:00

“ብክነት” እንደ “እድገት” የሚቆጠርበት፣… ጥፋትና ልማትን የሚያምታታ አገር!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)

የመንግስት ፕሮጀክቶች ብክነት፣ የመንግስት ድርጅቶች ኪሳራና የመንግስት እዳ፣… ከ”ደብል ዲጂት” በላይ ጨምሯል። “አድጓል”። በ10 ዓመት ውስጥ ከ10 እጥፍ በላይ ሆኗል።
ልዩ የኢትዮጵያ ገናና ምልክት ቁ.1 - ከእውነት የመሸሽና ነገርን የማድበስበስ አባዜ - የጭፍንነት አመል!
በአስፈሪ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ የውድቀትና የትርምስ አፋፍ ላይ እንደደረስን፣ ያን ያህልም በግልፅ ለማወቅ ፍላጎት አይታይብንም።
መንግስትም፣ በከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱና መፈናፈኛ ማጣቱን በግልፅ ሲናገር አልሰማንም።
ልዩ የኢትዮጵያ ገናና ምልክት ቁ.2 - ችግሮች፣ ያለመፍትሄ፣ በምትሃት እንዲጠፉለት የመመኘት ሱስ!
በቅጡ ማሰብ የተመናመነበት፣… ጭፍን ስሜት ከእውቀት በላይ፣ ድፍን ምኞት ከመፍትሄ በላይ የመውደድ ልማት ባይፀናወተን ኖሮ፣… አገሬውን በብክነትና በእዳ ያብረከረኩ አክሳሪ የመንግስት ፕሮጀክቶችንና ድርጅቶችን፣ እንደ ጣኦት እያመለክን የሙጢኝ እንይዝ ነበር?
ገና ለገና፣… በግልፅ ያልተዘረዘረ “የመፍትሄ ጅምር” ከመንግስት ስለተሰማ፣ ለዚያውም፣ “አነስተኛ የአክሲዮን ድርሻ እሸጣለሁ” በሚል ተደጋጋሚ አባባል እጅጉን ተበርዞ የሳሳ “የመፍትሄ ጭላንጭል” መጣ የሚል ግርግር ይፈጠር ነበር?
እንደወትሮው፣ ዛሬም… አገራችን ምን ያህል ፈተና እንደሚጠብቃት የሚመሰክሩ ውዝግቦችንና የሃሳብ ትርምሶችን ሲራገቡ ሰንብተዋል። በጥንቃቄ ማስተዋልና ጠንቅቆ ማገናዘብ፣… በስርዓት ማሰብና ማወቅ፣… ብዙም ያልተለመደበት አገር፣… “ብክነት” እንደ “እድገት” የሚቆጠርበት፣… ጥፋትና ልማትን የሚያምታታ አገር፣… ምንኛ አስቸጋሪ እንደሆነ፣ ይሄውና አሁንም በተግባር አየን።
“በልማት ላይ ልማት” እየተባለ፣ ለዓመታት የተዘመረላቸውን የመንግስት ፕሮጀክቶችና ድርጅቶች፣… ያስከተሉት ኪሳራ፣ ብክነትና እዳ፣… ያን ያህልም ሚስጥር አይደለም። የውጭ እዳ፣ በአስር ዓመት ውስጥ 10 እጥፍ ሆኗል። “አድጓል” እንበል? እዳና ብክነት “አድጓል” የምንል ካልሆነ በቀር፣ እንዴት ነው የመንግስት ፕሮጀክቶችንና ድርጅቶችን እንደ ልማት የምንቆጥራቸው?
ዋና ዋናዎቹን እናስታውስ። የባቡር ፕሮጀክቶች፣… የስኳር ፕሮጀክቶች፣… የማዳበሪያና የኮንዶሚኒዬም ፕሮጀክቶች፣… የነፋስ ተርባይ ፕሮጀክቶች… እነዚህ ናቸው አብዛኛውን ሃብት ያባከኑ፣ አገሪቱ ላይ የእዳ መዓት የከመሩ።

በ1983 ዓ.ም ማግስት የፈረሰው የስኳር ኮርፖሬሽን በ2003 ዓ.ም መጣ!
የስኳር ፕሮጀክቶች፣… በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር እዳ ያስከተሉና  ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ የፈሰሰባቸው፣… ያፈሰሱ፣ በእልልታና በጭብጨባ የተጀመሩ፣ ከተቃዋሚዎች እንኳ ድጋፍ እንጂ ከቁጥር የሚገባ የትችት ሃሳብ ያልቀረበባቸው፣ ገናና የመንግስት ፕሮጀክቶችና ድርጅቶች ናቸው።
ከዚያስ? በርካታ ገልባጭ መኪኖች፣… ገና መንፈቅ ሳይሞላቸው ተበላሽተው ከአገልግሎት ውጭ ሆኑ። የተሰራው መስኖ ጎርፍ ወሰደው። እንደገና የተሰራው፣… ደለል ደፈነው። አዳዲስ ግሬደሮች፣ አንድ ወር ሳይሞላቸው በብልሽት ቆሙ።… በችግር ላይ ችግር፣ በጥፋት ላይ ጥፋት፣ በኪሳራና በብክነት ላይ፣… በየዓመቱ ተጨማሪ ኪሳራና ብክነት።
ግን ችግር የለውም። በየዓመቱ ተጨማሪ በጀት ይመደብላቸዋል፣ ብድር ይቀርብላቸዋል። ነገር ግን፣ ከስኳር እጥረት፣ ከወረፋና ከራሽን የሚገላግል ይቅርና፣… ትንሽ እፎይታ የሚሰጥና ችግርን የሚያቃልል፣… በተግባር የሚቀመስ፣ ተጨማሪ የስኳር ምርት የለም።

የባቡር ፕሮጀክቶችስ?
በትክክል የሚሰራ የባቡር መስመር ከመዘርጋትና በትክክል የሚሰሩ ባቡሮችን ከመጠቀም ይልቅ፣… የመንግስት ነገር፣… በአላዋቂነት፣ በወገኛነት፣ አልያም በክፋት የድሃ አገር ሃብትን የሚያባክን ነገር አመጡ - “በኤሌክትሪክ የሚሰራ የባቡር ፕሮጀክት ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ” ተባለልን። ግንባታው በመንግስት ሳይሆን፣ በኮንትራት ለኩባንያ ስለተሰጠ፣… የባቡር መስመር ተዘርግቷል። ግን ምን ዋጋ አለው? ይሄው እንደምታዩት ነው - የተልከሰከሰ ነገር። እዳው ግን የገነነ!

ኤሌክትሪክስ?
እንደ ሳሊኒ በመሳሰሉ የግል ኩባንያዎች አማካኝነት፣ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች ደህና ተገንብተዋል። ግን፣ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያና ማሰራጫ መስመርስ? መንግስት፣ የኤሌክትሪክ መስመሮችን እዘረጋለሁ ብሎ ብዙ ገንዘው አውጥቷል። ግን… ያው እንደተለመደው ብዙም አልተሳካም።
በዚያ ላይ፣ የሃብት ብክነት ፕሮጀክቶችን መፈልፈል ጀመረ። በፀሃይ ሃይል ቻርጅ የሚደረጉ ባለባትሪ የኤሌክትሪክ መብራት አስፋፋለሁ በሚል ፈሊጥ፣ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ብድር?  የተገዙት ቁሳቁስ ለዓመት የማይዘልቁ ሲሆኑ ምን ይደረግ? እንደገና ብድር እያመጣ፣ እዳው ይጨምራል።
በዚያ ላይ፣… ሰሞኑን ለአዲስ የነፋስ ተርባይን ፕሮጀክት ከዴንማርክ የመጣውን 210 ሚሊዮን ዶላርን ጨምሮ፣ እስከዛሬ 1 ቢሊዮን ዶላር የፈጁና፣… ከዚህ ውስጥም እስከ 700 ሚሊዮን የሚደርሰውን ገንዘብ በከንቱ ለብክነት የዳረጉ የነፋስ ተርባይን ጣቢያዎችን አስታውሱ። የነፋስ ተርባይኖቹ ሁሉ ተደምረው፣… በ300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ከተገነባ ግድብና ከሃይል ማመንጫ ጣቢያ ጋር የሚስተካከል አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት አይችሉም። በዚያ ላይ፣ የሚያመነጩት ኤሌክትሪክ፣ ለአገልግሎት ይውላል ማለት አይደለም። ለቁጥጥር እጅግ አስቸጋሪ ናቸው፤ የኤሌክትሪክ ሲስተምን ያዛባሉ። ነፋስ እንደውሃ ማጠራቀምና ፍስሰቱን መቆጣጠር አይቻል ነገር!
ግን ችግር የለውም። በነፋስ ተርባይኖች አማካኝነት በከንቱ የሚባክነው የድሃ አገር ሃብት፣ አሁን ባለው ምንዛሬ ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር ቢጠጋም ችግር የለውም። ለምን?
ተጨማሪ ብድር ይቀርብለታል? ተጨማሪ እዳ ጎትቶ ያመጣል።
ይህም ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ፣ አክሳሪ የኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶችን ለሚያቋቁሙ የውጭ ኩባንያዎች፣ “ድጎማ” ለመስጠት እየተስማማ ነው።
እንግዲህ አስቡት።
መንግስት፣… ወደ ኬንያ፣ ጂቡቲና ሱዳን የኤሌክትሪክ መስመሮች ለመዘርጋት፣… ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተበድሯል።
ባለፉት በርካታ ዓመታት እንደታየው፣… ለ1000 “ጊጋዋትአወር” በአማካይ፣ በ60 ሚሊዮን ዶላር ሂሳብ ነው የሽያጭ ገቢ የሚያገኘው።
ነገር ግን፣ ኢትዮጵያ የሃይል ማመንጫ የሚያቋቁሙ የውጭ ኩባንያዎች፣ በዚህ ባነሰ ዋጋ የሚሸጡ ቢሆን ኖሮ፣… “ከነሱ በአነስተኛ ዋጋ እየገዛሁ፣ ለጎረቤት አገራት መሸጥና ማትረፍ እችላለሁ” የማለት እድል ይኖረው ነበር። ግን፣ በአነስተኛ ዋጋ አይሸጡም። አያዋጣንም ብለዋል። ግን ችግር የለውም። በዶላር፣… “ድጎማ” ይከፈላቸዋል።
ኢትዮጵያ፣ ለውጭ ኩባንያዎች፣ በዶላር ድጎማ ለመክፈል ተፈራርማለች።
ለ1000 ጊጋዋትአወር፣ በ75 ሚሊዮን ዶላር ሂሳብ፣ ለውጭ ኩባንያዎች ለመክፈል ውል ተፈርሟል።
በዓመት 7000 ጊጋዋትአወር አመነጫለሁ ለሚል የውጭ ኩባንያ፣ 500 ሚሊዮን ዶላር ይከፍላል ማለት ነው መንግስት።
ከዚያስ?
ለጎረቤት አገራት ይሸጣል። በስንት፣… በ400 ሚሊዮን ዶላር ገደማ።
ለውጭ ኩባንያዎች፣ የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ ማለት ነው።
ለኢትዮጵያ ደግሞ፣… የ100 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ - ከንቱ ብክነት።
ይሄ ከንቱ የኪሳራና የብክነት ውል የተፈረመው፣ በየዓመቱ የሚደገም፣ በየዓመቱ የ100 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ለመሸከም እንደሆነ አትርሱ። የሃያ ዓመት ውሉ ሲጠናቀቅስ? የእንፋሎት ማመንጫ ጣቢያዎቹ በእርጅና ወላልቀው፣ በዝገት ተበልተው፣… የቅሪት ክምር ታቅሞ መቅረት ነው። የእንፋሎት ማመንጫዎችና የነፋስ ተርባይኖች፣ ከሃያ ዓመት በላይ ዋጋ እንደሌላቸው በደንብ ይታወቃል።    
ለዚህ ኪሳራ ነው፣ ወደ ጎረቤት አገራት መስመር ለመዘርጋት ያ ሁሉ ብድርና እዳ የገባነው።      

የማዳበሪያ ፋብሪካ፣… የኮንዶምኒዬም ግንባታ፣… ውጤት የራቀው እዳ!
የማዳበሪያ ማምረቻ ፕሮጀክት 9 ቢሊዮን ብር ይፈጃል የተባለ ጊዜ፣… የደነገጡ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ግን፣… በ20 ቢሊዮን ብርም ሊጠናቀቅ አይችልም።
የአዲስ አበባ መስተዳድር፣ በ10 ዓመት ሚሊዮን ኮንዶሚኒዬም ቤቶች እሰራለሁ ብሎ ነው፣… ከነዋሪዎች ገንዘብ መሰብሰብ የጀመረው። 40 ቢሊዮን ብር የባንክ እዳም አናቱ ላይ ተሸክሟል። ግን፣… ባለፉት አስር አመታት፣… ሁለት መቶ ሺ መኖሪያ ቤቶችን እንኳ ማስረከብ አልቻለም።

የ1.3 ትሪሊዮን ብር ባለዕዳ መንግስት!
በአጠቃላይ የመንግስትና የፕሮጀክቶቹ እዳ፣… ዛሬ ከ1300 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል። ማለትም፣ 1.3 ትሪሊዮን ብር!
የውጭ እዳ 25 ቢ. ዶላር ነው። በዛሬ ምንዛሬ ስናሰላው፣ 700 ቢ. ብር። የአገር ውስጥ እዳ፣ ከ600 ቢ. ብር በላይ ነው።

እስቲ፣ በደንብ እናስተውለው። እንዴት ነው ነገሩ? አገሪቱ፣ የገደል አፋፍ ላይ እንደደረሰች፣ በቅጡ ብንገነዘብ ነው የሚሻለው።  የውጭ እዳዎችን ብቻ ተመልከቱ። በአስር አመት ውስጥ አስር እጥፍ ሆኗልኮ ሰዎች።
በ2000 ዓ.ም …… 2.5 ቢሊዮን ዶላር ነበር።
በ2010 ዓ.ም ……. 25 ቢሊዮን ዶላር (አስር እጥፍ)!

የወለድ ክፍያስ?
በ2000 ዓ.ም …… 45 ሚሊዮን ዶላር ነበር።
በ2010 ዓ.ም ……. 550 ሚሊዮን ዶላር (ከአስር እጥፍ በላይ)!

የብድር እዳ ክፍያ ከነወለዱስ?
በ2000 ዓ.ም …… 130 ሚሊዮን ዶላር ነበር።
በ2010 ዓ.ም ……. 1500 ሚሊዮን (1.5 ቢሊዮን ዶላር - ከአስር እጥፍ በላይ)!

ይህንን እያየን፣ አባካኝና አክሳሪ የመንግስት ፕሮጀክቶችን የሙጢኝ ይዞ የመቀጠል ምኞት የሚያሰክረን ከሆነ፣… የአገሪቱ መጨረሻ እንዳያምር ፈርደናል እንደማለት ነው - ትርጉሙ።


Read 2287 times