Sunday, 10 June 2018 00:00

ሜሪስቶፕስ - የ26 ዓመት አገልግሎት በኢትዮጵያ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 · “ገንዘብ የለኝም ብሎ አገልግሎት ሳያገኝ የሚሄድ የለም”
          · “እዚህ የቆየሁት ኢትዮጵያውያን እናቶችን ለማገልገል ነው”

    ሜሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል መቀመጫውን በእንግሊዝ ለንደን ያደረገ፣ በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ የተቋቋመና በዋናነት በስነ ተዋልዶ ጤና፣ በህፃናትና እናቶች ላይ አተኩሮ የሚሰራ የጤና ድርጅት ነው፡፡ የድርጅቱ መስራች እንግሊዛዊቷ ሜሪስቶፕስ፤ በትዳሯና በወሊድ ጉዳይ እንከን ገጥሟት፣ የእናቶችን ችግር፣ በራሷ ህይወት የተረዳች ሴት እንደሆነች ይታወቃል፡፡ ድርጅቱ በዓለም ላይ በ37 አገራት ቅርንጫፎቹን ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡ ከነዚህም አገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡
ላለፉት 26 ዓመታት ድርጅቱ፣ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን እናቶች ወጣቶችና ህፃናት ሰፊ የጤና አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን የመጀመሪያውን ክሊኒክ (ሜሪስቶፕስ አራዳን) ፒያሳ ካቴድራል ት/ቤት አካባቢ ከፍቷል፡፡ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞችም ቅርንጫፎቹን በማስፋፋት አገልግሎቱን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ለመሆኑ ሜሪስቶፕስ እስከ አሁን ምን ስኬቶችን አስመዘገበ? ምንስ ፈተናዎች ገጠሙት? አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ክሊኒኩ ሲከፈት የመጀመሪያዋ ነርስ ከነበሩትና ላለፉት 26 ዓመታት በዳይሬክተርነት ከአገለገሉት፣ የአሁኗ  የላይዘን አማካሪ ሲስተር ሸዋዬ ዓለሙ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

     ሲስተር ሸዋዬ ዓለሙ እባላለሁ፡፡ በሜሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የላይዘን አማካሪ ሆኜ እያገለገልኩ ነው፡፡ እኔ ወደዚህ ድርጅት የመጣሁት፣ ክሊኒኩ ሲከፈት የመጀመሪያዋ የቤተሰብ ምጣኔ ነርስ በመሆን ነው - ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በዝውውር፡፡
በዝውውር ሲባል እንዴት ነው? ከመንግሥት ወደ ግል…?
ትክክል ነሽ፡፡ መጀመሪያ ክሊኒኩ ሲከፈት፣ ከአገራችን የጤና ጥበቃ ጋር በትብብር ነበር፡፡ ስለዚህ እኔም ከጥቁር አንበሳ ተመድቤ ነው የመጣሁት። ለሁለት ዓመታት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ደሞዝ እየከፈለኝ ነበር ሜሪስቶፕስን ያገለገልኩት፡፡ ጥቁር አንበሳም ሳለሁ፣ በቤተሰብ ምጣኔ ላይ ነበር የምሰራው። ከሁለት ዓመት በኋላ መንግሥት ሁለት ምርጫ ሰጠኝ፡- “ከፈለግሽ ተመልሰሽ ነይ፤ ካልሆነ በዚያው ቀጥይ” የሚል፡፡ እኔም በሁለት ዓመታት ውስጥ በሜሪስቶፕስ በርካታ የሴቶችን ችግሮች አይቼ ውስጤ ስለተነካ፣ እዚሁ እቀራለሁ ብዬ ወሰንኩኝ፡፡ ባለፉት 26 ዓመታት፣ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች  አገልግያለሁ፡፡
ሜሪስቶፕስ የሚሰጣቸው ዋናዎቹ አገልግሎቶች ምንድን ናቸው?
ሜሪስቶፕስ በ1991 ዓ.ም ነው በአገራችን የተቋቋመው፡፡ የመጀመሪያ ክሊኒካችን ፒያሳ ካቴድራል ዝቅ ብሎ የሚገኘው አራዳ ክሊኒክ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ስላገለገለና ስላረጀ፣ የስራችንን ጥራት ለመጠበቅ አሁን ወደ መገናኛ ተዘዋውሯል፡፡ በአገራችን የእናቶችን ሞት ለመቀነስ፣ ችግር ሲከሰት ብቻ ከመሯሯጥ፣ ቅድመ ጥንቃቄ ላይ መስራት ወሳኝ ነው፡፡ ለምሳሌ የወሊድ መቆጣጠሪያ አገልግሎት በመስጠት፣ እናቶችና ወጣት ሴቶችን ግንዛቤ በማስጨበጥና በማስተማር፣ …ካልተፈለገ እርግዝናና ከአባላዘር በሽታ መከላከል ይቻላል፡፡ ክሊኒካችንም የስነ-ተዋልዶ ጤናና እንክብካቤ አገልግሎትን በመስጠት፣ እናቶችና ህፃናትን ለመታደግ ነው፣ ከ26 ዓመት በፊት የተከፈተው። እንግዲህ በእነዚህ ዓመታት፣ የስነ - ተዋልዶ ጤና፣ የቤተሰተብ ምጣኔ አገልግሎት በመስጠት፣ ልጅ ሳይፈለግ እንዳይወለድና ተናፍቆ እንዲመጣ፣ “Children by choice note by chance” የተሰኘውን መፈክር አንግቦ፣ የመንግስት አጋር በመሆን፣ እናቶችና ወጣቶችን ያማከለ፣ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ አሁንም እየሰጠ ይገኛል፡፡
ሜሪስቶፕስ በግል ክሊኒኮች “Blue stars” በሚለው አሰራሩ የሚሰጠውን አገልግሎት ያብራሩልኝ--?
የግል ክሊኒኮች ሲከፈቱ በጤናው ዘርፍ ሊያበረክቱ የሚችሉትን አላማ ይዘው ነው፡፡ ሆኖም እኛ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በሰፊው እንዲዳረስ፣ ለግል ክሊኒኮች ስልጠናና አንዳንድ ድጋፎችን በመስጠት፣ “Blue Stars” በሚል፣ በ328 የግል ክሊኒኮች እየሰራን እንገኛለን፡፡ በዚህም በክሊኒኮቹ ላይ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ፣ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት በኩል ስኬታማ ሥራ አከናውኗል፤ እያከናወነም  ይገኛል፡፡
ባለፉት 26 ዓመታት በስነ - ተዋልዶ ጤና፣ በቤተሰብ ምጣኔ፣ በወሊድና ተያያዥ አገልግሎቶች እንዲሁም በግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ምን ያህል ስኬታማ ናችሁ? ስኬቱስ በምን ይገለፃል?
ክሊኒኮቹ በቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በኩል ሰፊ ተደራሽነትን በማቅረብ፣ ብዙ ስኬቶችን ተጎናፅፈዋል። ለምሳሌ አንዲት እናት፤ ወደ ክሊኒካችን መጥታ የፈለገችውን አይነት የወሊድ መከላከያ ማግኘት ትችላለች፡፡ ይህን አገልግሎት ከእኛ ክሊኒኮች ውጭም በብሉ ስታርስ እንዲሁም፣ በተንቀሳቃሽ ቡድናችንም በኩል ማግኘት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ተደራሽነታችን ሰፊ ነው፡፡ ሁለተኛው በቤተሰብ ምጣኔ፣ በስነ - ተዋልዶ ጤናና በኤችአይቪ ኤድስ ምክርና ምርመራ በኩል ሰፊ ግንዛቤን ለማህበረሰቡ በማስጨበጥ የብዙዎችን ህይወት ቀይረናል፡፡ የአባላዘር በሽታ ምርመራና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራም እንዲሁ ከምናቀርባቸው አገልግሎቶች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል እንደ ኤክስቴንሽን የጤና ባለሙያዎች፤ “ፕሮሞተርስ” የምንላቸው ሰራተኞች፤ ቤት ለቤት እየሄዱ፣ ለማህበረሰቡ ከላይ በጠቀስናቸው የጤና አገልግሎት ዘርፎች ዙሪያ ትምህርት ይሰጣሉ፡፡ እነዚህ ሠራተኞች በየቀበሌውና በየክፍለ ከተማው የቡና ጠጡ ፕሮግራም በማዘጋጀት ጭምር፣ ከከተማው ሴት ማህበራት ጋር በማቀናጀት፣ እናቶችን ሰብስበው ትምህርት ይሰጣሉ፡፡
በሌላ በኩል በክልሎች በገበያ ቀናት፣ በገበያው ላይ ትምህርት ይሰጣል፡፡ የመንገድ ላይ ትርኢትም በማዘጋጀት፣ ሰው በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ትምህርትና ግንዛቤ ያስጨብጣል፡፡ ሌላው ወጣቶች በባህልም ሆነ በተለያዩ ነገሮች ተፅዕኖ፣ በስነ ተዋልዶ ጤና ጉዳይ ላይ በግልፅ ለመወያየት ይፈራሉ ተብሎ ስለሚታሰብ፣ ክሊኒካችን የራሱን “School health” ስትራቴጂ ነድፎ፣ በሁለተኛ ደረጃና በዩኒቨርሲቲ አካባቢዎች እየሄደ ያስተምራል፡፡ ተማሪዎች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶችም ለመቅረፍ ይሞከራል። ለምሳሌ የሃይማኖት፣ የቤተሰብና የባህል ተፅዕኖ ስላለ፣ ይሄንን ተፅዕኖ ለመቅረፍ. ከፍተኛ ስራ ይሰራል፡፡ የእኛን አገልግሎት ማግኘት ፈልገው. የገንዘብ ችግር ላለባቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ በ8044 ነፃ የስልክ መስመሮቻችን ተጠቅመው፣ ከእኛ ሰራተኞች ጋር ውይይትና ምክክር ማድረግ ይችላሉ፡፡
ወጣት ሴቶች ተሳስተውም ይሁን ተደፍረው ላልተፈለገ እርግዝና ቢጋለጡና ያንን ፅንስ ለማቋረጥ ፈልገው ገንዘብ ባይኖራቸው፣ ነፃ አገልግሎት የምትሰጡበት አሰራር አላችሁ? ምክንያቱም የፅንስ ማቋረጥ አገልግሎትም ትሰጣለችሁ ብዬ ነው …
ሜሪስቶፕስ ሲቋቋምም ዓላማው እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ነው፡፡ ድሮ አለቃዬ ምን ይላል መሰለሽ… “ካለው ትንሽ ወስደህ ለሌለው በነፃ ስጥ፡፡” ያንን መርህ ላለፉት 26 ዓመታት ተከትለን ስንተገብር ኖረናል። እንግዲህ በራችን ክፍት ነው፤ ማንም ሰው መጥቶ አገልግሎቱን ያገኛል፡፡ ገንዘብ የለኝም ብሎ አገልግሎት ሳያገኝ የሚሄድ የለም፡፡ “ቫውቸር ሲስተም” የሚባል አሰራር አለን፡፡ ገንዘብ የለንም ያሉትን በደንብ መረጃ እንወስድና በነፃ አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ ያልተፈለገ እርግዝና ገጥሟቸው ወይም አርግዘው አልባሌ ቦታ ሄደው ችግር ውስጥ ገብተው የሚመጡ አንዳንድ እናቶች አሉ፡፡ ወላድም ምጥ ይዟት ብትመጣና ገንዘብ ባይኖራት አንመልሳትም፡፡ ከመጀመሪያውም ምንም የለኝም ካለችና እሱን ካረጋገጥን፣ ከክትትል ጀምሮ እስከ ወሊድ በነጻ አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ ሌላው ቀርቶ የወለደችው ወንድ ልጅ ከሆነ፣ ለልጇ የግርዛት አገልግሎት ሰጥተን፣ እሷንም የወሊድ መቆጣጠሪያ እንድትጠቀም እናደርጋለን፡፡ በነገራችን ላይ የምንሰጠው አገልግሎት ከምናስከፍለው ክፍያ ጋር በፍፁም አይገናኝም፡፡ ከመንግስት ትንሽ ከፍ ያለ ቢሆንም ከግል ክሊኒኮች ጋር ግን ፈፅሞ የማይገናኝ ነው፡፡
እስካሁን ለምን ያህል ሴቶች ነፃ የወሊድና መሰል አገልግሎቶችን ሰጥታችኋል?
ለ500 ያህል እናቶች ነፃ አገልግሎት ሰጥተናል፡፡ ወደፊትም ይህ አገልግሎታችን አይቋረጥም፡፡
የአገራችን ህግ አንዲት ሴት ፅንስ ብታቋርጥ በህግ የማትጠየቅባቸውን አራት ምክንያቶች አስቀምጧል፡፡ አንደኛው ተደፍራ ስታረግዝ፣ በአካልም በአዕምሮም ልጅ ወልዳ ለማሳደግ ዝግጁነት ከሌላት፣ ከቤተ - ዘመድ ካረገዘችና ያረገዘችው ፅንስ የማይድን የአካል ጉዳት ካለበት (Deformed ከሆነ) … ፅንስ ብታቋርጥ በወንጀል አትጠየቅም ይላል፡፡ ነገር ግን የትኛዋም ሴት ወደ ክሊኒካችሁ ስትመጣ ተቀብላችሁ አገልግሎቱን ከመስጠት በስተቀር የምትጠይቁት ጥያቄ እንደሌለ ያነጋገርናቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ነግረውናል። ለምንድን ነው?
እንግዲህ እ.ኤ.አ በ2015 ዓ.ም ገደማ ይመስለኛል … መንግሥት ይህንን ጉዳይ ሊበራላይዝድ አድርጎታል። ህጋዊ አይደለም ግን አንዲት ሴት እነዚህ ከላይ ያነሳሻቸውንና በህጉ የተቀመጡትን መስፈርቶች ይዛ ከመጣች ትስተናገዳለች፡፡ በየትኛው ጉዳይ አርግዛ እንደመጣች አትጠይቋትም ላልሽው፤ እንደየ ሰዉ ይለያያል፡፡ እኔ በነበርኩበት ጊዜ እንጠይቃለን፤ በደንብ እናወያያታለን፡፡ አሁን አሻሚ የሆነው 18 ዓመት ያልሞላት ከሆነች የሚለው ላይ ነው፡፡ እኛ አንዲት ሴት 30 ዓመት ቢሆናት፣ ከዛ በታች ነኝ - 18 አልሞላኝም ብትል፣ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ ማረጋገጫ አምጭም አንላትም፤ ያለችውን እንቀበላለን፡፡ ሌሎቹን ግን እንጠይቃለን፡፡ የምንመዘግብበት ካርድና መዝገብም ያንን እንድንከተል ያዘናል፡፡ አሰራራችን ስለሚያስገድድ ማለቴ ነው፡፡
ክሊኒኮቻችሁ በተለይ በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙት በየቀኑ ፅንስ በሚያቋርጡ ሴቶች የተሞሉ ናቸው፡፡ እርስዎ እንደነገሩን፤ በዩኒቨርሲቲዎችና በሌሎች ት/ቤቶች የግንዛቤና መሰል አገልግሎቶችን ትሰጣላችሁ፡፡ ታዲያ የግንዛቤ ትምህርቱ ላይ ክፍተት አለ ወይስ ምንድነው ችግሩ?
እርግጥ ነው ክሊኒኮቹ በሴቶች ይሞላሉ፤ ነገር ግን የሚሞሉት ፅንስ በሚያቋርጡ ሴቶች ብቻ አይደለም። ለምሳሌ ፅንስ አቋርጠው ሄደው፤ ለቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ለቼክአፕ፣ ለምክር አገልግሎትና ለተመሳሳይ አገልግሎቶች ተመልሰው ይመጣሉ። ስለዚህ በየክሊኒኩ ሞልተው የሚታዩት ሁሉ ፅንስ ለማቋረጥ የሚመጡ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ሌላው የእኛን አገልግሎት ተጠቅመው የሚሄዱ፤ በሁሉም ዘርፍ ማለት ነው፣ እኛን ቤተሰብ ነው የሚያደርጉን፡፡ አንድ ሴት እኔ ዘንድ ለአገልግሎት ስትመጣ፣ በፈገግታ ተቀብዬ፣ እንደ እህቴ፣ እንደ እናቴ፣ እንደ ልጄ አድርጌ አቅርቤ ስለምንከባከባቸው፣ ተመልሰው መጥተው፣ ቤተሰብ ያደርጉናል፤ ይጠይቁናል፤ ክሊኒካችንን ከሚሞሉት መካከል እነዚህ ቤተሰባዊ ግንኙነት ያላቸውም ቀላል አይደሉም፡፡ አገልግሎታችንም ሰፊ ነው፤ ለኤችአይቪ ምርመራ፣ ለአባላዘር በሽታ ምርመራና ህክምና፣ ለቤተሰብ ምጣኔና ለስነ ተዋልዶ ጤና ስለሚመጡ ብዙ ናቸው፡፡ እኔ በክሊኒኮቹ ለብዙ ዓመታት ሰርቻለሁ፡፡ ከዚህ ውጭም በቤተሰብ ግጭት ሲፈጠር፣ ሌላ የህይወት ፈተና ሲገጥማቸው፣ እንደ አማካሪ አድርገው ቀርበውን፣ ምክር ለመጠየቅ ይመጣሉ፡፡ በዚህ መልኩ ብዙዎችን ረድተናል፤ ተሳክቶልናል፡፡
ክሊኒኮቹ የሚሰሩበት በጀት የሚመጣው ከየት ነው? ለንደን ካለው ዋና መስሪያ ቤት ወይስ ክሊኒኩ እየሰራ በሚያገኘው ገንዘብ?
ምንም አይነት ፈንድ የለንም፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደምታውቁት ኢትዮጵያ አድጋለች እየተባለ ለጋሾች እየወጡ ነው ያሉት፡፡ እኛ ግን ካለው ትንሽ ወስደን፣ ለሌለው እየሰጠን፣ በሚተርፈን ለሰራተኞቻችን ደሞዝና ሌሎች ሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን እንሸፍናለን። ክሊኒኩ ተጀምሮ 3 ዓመት እስኪሞላው ብቻ ነበር ከዋናው መስሪያ ቤት ፈንድ የነበረው፡፡ አሁን ራሱን በራሱ ነው የሚያስተዳድረው፡፡ በተለይ የማዋለጃ ክሊኒኩ ምንም ድጋፍ የለውም፡፡ ይህንን በመመልከት የበጎ አድራጎትና ማህበራት ኤጀንሲ፤ የገቢ ማስገኛ ሥራ ስሩ ብሎ ፈቃድ ሰጥቶን፣ ለሁለት ዓመት ያህል ስንሰራ ቆይተናል፡፡ ምክንያቱም ገቢው ለሰራተኛ ደሞዝ፣ ለመንግስት ታክስ ተከፍሎ፣ ትርፉ ለበጎ አድራጎት ስራ ማለትም በነፃ ለምንሰጠው አገልግሎት ይውላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የበጎ አድራጎትና ማህበራት ኤጀንሲን ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ በደንብ ይረዱናል፤ ይመከልሩናል፡፡ ደካማ ጎን ካለብንም እንድናስተካክል ያደርጋሉ፡፡ ጤና ጥበቃንም እናመሰግናለን፡፡
በስራችሁ ላይ እንደ ተግዳሮት የምትቆጥሩት ምንድን ነው?
አንዳንድ የመንግስት አካላት አሉ፤ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እንዘጋባችኋለን እያሉ የሚፎክሩ፡፡ አየሽ እኔ ከጀምሩ አንስቶ ስላለሁ አውቃለሁ፤ በሜሪስቶፕስ ብዙ የኢትዮጵያ እናቶችና ወጣቶች ተጠቅመዋል፡፡ ብዙ ችግሮችን ቀርፈናል፡ ይህን ተረድተውም ይሁን ችላ ብለው እንዘጋለን ይላሉ፡፡ እንዘጋለን ከማለት ይሄ ይሄ ጥፋት ነው ብለው ማስተካከል ሲችሉ፣ የስራችንን ጥቅም ክብደት ሳይሰጡት፣ እንዘጋለን ሲሉ ትንሽ ውስጤ ያዝናል፡፡
ለመሆኑ እንዘጋለን ሲሉ በምን ምክንያት ነው?
እንግዲህ በመንግስት ፈቃድ፣ ነፃና የገቢ ማስገኛ ብለን አሰራራችንን በሁለት ከፍለናል፡፡ ገቢ ማስገኛው የማዋለድ አገልግሎቱ ነው፡፡ ፈንድ ስለሌለና ስራው መቀጠል ስላለበት የማዋለድ አገልግሎት የምንሰጠው በክፍያ ነው፡፡ ለምሳሌ የጎተራ ማዋለጃችን ለጠጠር መጣያ ቦታ የለም፤ በሰው ይሞላል፡፡ አሁንም አራዳ ላይ ከፍተነል፡፡ ስራችን ጥራት ያለው በመሆኑ፣ ቤተሰባዊ አቀባበልም ስለምናደርግ፣ እናቶች ክትትል ጀምረው ይመጣሉ፡፡ አሁን በአዲስ አበባ ከማዋለጃዎቹ ጋር 7 ክሊኒኮች አሉ፡፡ እና የገቢ ማስገኛውን ለብቻ፣ የእርዳታ መስጫውን ለብቻ ተከራይታችሁ ስሩ፤ ያለበለዚያ እንዘጋዋለን ነው የሚሉት፡፡ እኛ ደግሞ ሌላ ስንከራይ፣ ሌላ ባለሙያ፣ ሌላ ፅዳት ሰራተኛ፣ ሌላ ኪራይ … ሌላ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ውስጥ ልንገባ ነው፡፡ ይህን ሊረዳልን አልቻሉም፡፡ እኛኮ የነፃውን ለብቻ፣ የገቢ ማስገኛውን ለብቻ አድርገን፣ እዛው ክሊኒኮቹ ባሉበት ቦታ እየሰራን ነው፡፡ ግን አልተቀበሉትም፡፡ ይሄ ደግሞ እኛን አስጨንቆናል፡፡ ለምሳሌ አንዱ የጎተራው ማዋለጃችን በወር 145 ሺህ ብር ነው ኪራዩ፡፡ የሃኪሞቹ ደሞዝ ትንሹ 60 ሺህ ብር ነው የምንከፍለው፡፡ ታዲያ ሌላ ቦታ ከተከራየን እንዴት ነው የምንቋቋመው፡፡ ትልቁ የማህፀን ሀኪም ደግሞ 80 ሺህ ብር ነው፡፡ ከ50 በላይ አዋላጅ ነርሶች አሉን፡፡ ለእነሱ ለእያንዳንዳቸው ከ10 ሺህ ብር በላይ እንከፍላለን፡፡ ብዙ ችግር ነው ያለብን፡፡
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል 13 ዓመት፣ በሜሪስቶፕስ 26 ዓመት፣ በአጠቃላይ ወደ 40 ዓመት ገደማ በጤና ዘርፍ አገልግለዋል፡፡ በስራዎ ደስተኛ ነዎት?
በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ኢትዮጵያውያን እናቶች ልዩ ናቸው፤ እነሱን ለማገልገል ነው እዚህ የቆየሁት፡፡ ለእኔ ከፍተኛ ክብርና ፍቅር አላቸው፡፡ እንደ ባለሙያም፤ አንድ እናት ተቸግራ መጥታ ተደስታ ስትሄድ እኔም እደሰታለሁ፡፡ በጥቁር አንበሳም እንደዛው ጥሩ ጊዜ ነበረኝ፡፡ የተማርኩትም ጎንደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ነው፤ በ1970 ነው የተመረቅሁት፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ በስራ ላይ ስሆን ደስተኛም ነኝ፡፡ በግል ህይወቴም ባለትዳርና የ3 ልጆች እናት ነኝ፡፡ ሶስት የልጅ ልጅ አይቻለሁ፡፡ አሁንም ሙያዬን ለማሻሻል በጤና መኮንንነት ትምህርቴን እየተከታተልኩ ነው፤ ልመረቅ ትንሽ ነው የቀረኝ፡፡ በሁሉም ነገር ደስተኛ ነኝ፤ አሁንም የኢትዮጵያን እናቶች ለማገልገል እስከምችለው ድረስ እተጋለሁ፡፡ አሁን “ሜሪስቶፕስን እንዘጋለን” የሚለው ፉከራ ቆሞ፣ ችግራችን ታይቶ፣ የእናቶች ተጠቃሚነት ግምት ውስጥ ገብቶ መፍትሄ እንዲበጅልን እጠይቃለሁ፡፡
ሜሪስቶፕስ በዓለም አቀፍ ደረጃ እስካሁን ለምን ያህል ሴቶች አገልግሎት ሰጥቷል ተብሎ ይገመታል?
በቅርቡ ለመቶ ሚሊዮን ገደማ ሴቶች አገልግሎት እንደሰጠ የሚጠቁም መረጃ ወጥቷል፡፡    

Read 834 times