Sunday, 10 June 2018 00:00

ከዋለልኝ መኮንን ወቀሳ በስተጀርባ ያለ እውነታ

Written by  ዶ/ር ሁሴን አዳል መሐመድ
Rate this item
(2 votes)

(ካለፈው ሳምንት የቀጠለ)
ዛሬ ዋለልኝ መኮንን ስሙ ለምን ይነሳል? በእነማን ይነሳል? ማንነታቸው እንዲታወቅ ቤዛ ከሆነላቸው ብሔረሰቦች ድርጅቶች መኻል ስንቱ ይዘክሩታል? ዛሬ የሌሎች ብሔረሰቦች ድርጅቶች ዋለልኝ መኮንን የወጣበትን የአማራ ብሔረሰብ ሕዝብ የሚያዩበት ዐይን፤ ዋለልኝ መኮንን የሌሎች ብሔረሰቦች ሕዝቦችን ባየበት ዐይኑ ልክ ነው ወይ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡
ዋለልኝ መኮንን ስሙ በበጎ የሚነሳው በመንግሥት የድል በዓል ንግግር ላይ ነው፡፡ ከብሔር ትግል ጥያቄው ጋር ተያይዞ፣ በአገራችንና በሕዝባችን ላይ በደረሰው ጥፋት ግዝፈት የተነሳ የዋለልኝ መኮንን ስም ጎላ ብሎ በክፉ ይነሳል፡፡ ነገር ግን የብሔር ትግል ውጤቱ በአመዛኙ አገሩን ለሚወድ ዜጋ ሁሉ የሚያስቆጭ ቢሆንም፣ ጥፋቱ የተፈጸመው ዋለልኝ መኮንን በሕይወት ባልኖረበት ዘመንና በሂደቱ ባልተሳተፈበት ወቅት ነው፡፡ ዋለልኝ መኮንን በጨቋኝ ስርዓቱ የተገደለው ገና የብሔር ትግል መጠንሰሻ ጋን ሲታጠን፤ ህዳር 29 ቀን 1965 ዓ.ም ነው፡፡ በአገራችን ሕዝቦች ላይ የደረሰው መከራ፤ ኤርትራ ከእናት አገሯ የተገነጠለችው፤ ሕዝቦች በቋንቋ ግድግዳ አጥር ተከልለው በጉርብትና እንዲተያዩ የተደረገው፤አገራችን የባህር በር ያጣችው ሁሉም ለወቀሳ የሚያጋልጥ የጥፋት ክስተት የተፈጸመው ከ1984 ዓ.ም ወዲህ ስለሆነ የዋለልኝ መኮንንን ስም በዚህ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ማንሳት “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ነው፡፡
ዋለልኝ መኮንን በብሔር ትግሉ መነሻ ወቅት በብዕሩ ጽፎ መሬት ባስያዘው “የብሔር ትግል ጥያቄ በኢትዮጵያ” ያልጠራ ጽንሰ-ሓሳብ የተነሳ በመጣብን መዓት ሊወቀስ ይገባዋል የሚባል ከሆነ ደግሞ በጽሁፉ ውስጥ የሰፈረው ንድፈ-ሓሳብ ሳይመዘን አይሆንም። ዋለልኝ መኮንን በብዕሩ ጽፎ “ታገል” መጽሔት ላይ ያወጣውን ጽሁፍ ስንመለከት፣ በውስጡ የያዘው ዋና ፍሬ ነገር፣ “ኢትዮጵያ የአንድ ብሔር/ብሔረሰብ አገር ብቻ አይደለችም፤ከሁለቱ ብሔሮች/ብሔረሰቦች (አማራ፤ ትግሬ) የወጣ ነፍጠኛ በሌሎች ላይ የባህልና ኢኮኖሚ የበላይነት ይዞ ይገኛል፤ ነገር ግን ይህ አባባል በከፍተኛ ድህነት የወደቁትን ብዙሐን የአማራውንና የትግሬውን ሰፊ ሕዝብ አይመለከትም” የሚል ነው። ይሁን! ይህ አባባሉ “የአማራ ወይም የትግሬ ብሔር፤ ጨቋኝ ነው” ለሚለው ድጋፍ አይሆንም፡፡ ሌላው ዋለልኝ መኮንን ያለው፤ “ብሔራዊ መንግሥት ዕውን እንዲሆን ሁሉም ብሔረሰቦች ባህልና ቋንቋቸው ሊከበርላቸው፤ በመንግሥት ጉዳዮች ዕኩል ተሳትፎ ሊኖራቸው ይገባል” የሚል ነው፡፡ ይህ አሁንም መሬት ላይ የሚገኝ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ነው፡፡
ሌላው ልብ ሊባል የሚገባው ቁም ነገር፣ የዋለልኝ መኮንን የአማራ ገዥ መደብ አተያይ፣ ከአማራ ብሔር አብራክ ከመውጣትና አለመውጣት ጋር የሚያያዝ አልነበረም፡፡ እርሱ “የአማራ ገዥ መደብ” ይለው የነበረው በአማርኛ ተናጋሪነትና የክርስትና እምነት ተከታይነት ድር ስለተሳሰረ ሕብረብሔራዊ ምንጭ ስለነበረው የተዋሃደ ስብስብ ነበር፡፡ በወቅቱ የኦርቶዶክስ ክርስትና ኃይማኖት፤በዋናነት የሁለቱ ብሔረሰቦች ህዝቦች ኃይማኖት ተደርጎ ይወሰድ ነበር። ግን ከአማራና ትግሬ ሕዝቦች መኻል የእስልምናና አይሁድ ኃይማኖቶች ተከታዮችም እንዳሉ የሚካድ አልነበረም፡፡
ዋለልኝ መኮንን ገዥ መደቡ ከጨቋኝ የአማራ ብሔር ሕዝብ አብራክ የወጣ ነው አላለም፡፡ ይህን የሚል ሰው የዋለልኝ መኮንንን ሀሳብ በመጥለፍ ለግል ፍላጎቱ ማሟያ የሚጠቀም ነው፡፡ ከሕዝብ መኻል ጨቋኝ ገዥ መደብ ሊወጣ ይችል ይሆናል እንጂ ሕዝብ ጨቋኝ ሊሆን እንደማይችል እንኳን ለዋለልኝ መኮንን በአሁኑ ጊዜ ላለ ማንም ፖለቲከኛ ቀላል የፖለቲካ ሀ…. ሁ…. ነው፡፡ ይልቁንም ዋለልኝ መኮንንና መላው የቀድሞ ተማሪዎች ይሉ የነበሩት “ኢትዮጵያ የአንድ ብሔር/ብሔረሰብ አገር አይደለችም” የሚል ሲሆን ከዚህ አባባል ሊቀሰም የሚገባው ትልቅ ቁም ነገር፣ለአገራችን ብሔረሰቦች ሕዝቦች አንድነት፣ዛሬ ተስፋ የሚጣልበት የዴሞክራሲዊ ብሔረተኝነት አስተሳሰብ የመሰረት ድንጋይ ዋለልኝ መኮንን መሆኑ ነው፡፡ የዴሞክራሲዊ ብሔረተኝነት አስፈላጊነትን የሚዘነጋ ብልህ ዜጋ ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡ በርካታ ብሔረሰቦች ሕዝቦች ላሏት አገር የዚህ ዕሴት አስፈላጊነት ዛሬም ቢሆን ለድርድር ሊቀርብ አይችልም፡፡
እርግጥ ዋለልኝ መኮንንን ጨምሮ በቀድሞ ተማሪዎች በኩል፣ በብሔር/ብሔረሰብ ጽንሰ-ሓሳብ ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ አለመያዙ ትልቅ ክፍተት ነበር። ትግሉ በአመዛኙ በተማሪዎች ይመራ ስለነበር ይህ ችግር ማጋጠሙ አያስደንቅም፡፡ ተማሪዎቹ “ብሔር”፤ “ብሔረሰብ” የሚባሉትን ሁለት ቃላት ላይና ታች እያፈራረቁ፣ ተመሳሳይ ሁኔታን ለመግለጽ ይጠቀሙ እንደነበር፣ ዋለልኝ መኮንን “ታገል” መጽሔት ላይ ባሰፈረው “የብሔር ትግል በኢትዮጵያ” የሚለው ጽሁፍ ላይ መመልከት ይቻላል፡፡ ተማሪዎቹ ቃላቱን በማፈራረቅ በመጠቀም፣ ጽንሰ-ሓሳቡን ጥርት ባለ ሁኔታ ያልተረዱ መሆኑን ቢያሳዩም፣ አንድ ነገር ላይ ግን ግልጽ ነበሩ፡፡ በወቅቱ ትግል የሚጠይቅ የሕዝቦች ዕኩልነት መጓደል በኢትዮጵያ ነበር፡፡ ሕዝቡ “ብሔር” ይባል “ብሔረሰብ”፤ ወደ ትግል እንቅስቃሴ የሚያመራ በደል ደርሶበታል፡፡ “ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው” እንዲሉ፤ ዛሬ ላይ ሆኖ የተማሪዎችን ትግል አቃቂር ከማውጣት ገድላቸውን አክብሮ ወቅቱ የሚጠይቀውን ትግል በማካሄድ የራስን ድርሻ ለአገር ሕልውና ማበርከት  ይሻላል፡፡
የቀድሞ ተማሪዎች የፖለቲካ ጥንስስ ሓሳብ፣ ዛሬ አገራችንን ለአጋጠማት ወቅታዊ ችግር መነሻ ሆኖ አገልግሏል ብለን ብንወቅሳቸው፣ አፈራቸውን አራግፈው ከመቃብራቸው አይነሱም፡፡ ከዚህ ይልቅ ከዋለልኝ መኮንን ወቀሳ በስተጀርባ ያለውን ዕውነታ መርምሮ መረዳትና የራስን አቋም ማስተካከል ይጠቅማል፡፡ ለአማራ ሕዝብ አያትና ቅድመ አያቶች ያልተገባ ስም በመስጠት ቀደምት ታሪኩ ረክሶ፣ አሁን ያለው የአማራ ትውልድ አያቶቹ በሠሩት አኩሪ ታሪክ እንዲሸማቀቅ፣ የፈጠራ ልብ ወለድ ተጽፎ ተሠራጭቷል፡፡ የአማራ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆነው የዋለልኝ መኮንን የብሔር ትግል ፖለቲካ ተሳትፎ፣ በዚሁ መሰሪ ተግባር ለኪራይ መሰብሰቢያ ውሏል፡፡
ዋለልኝ መኮንንን “ዘመቻ ዋለልኝ” የሚል የጦር ግንባር በመክፈት፣ ወደ ደሴ ከተማ መግቢያና ለወሳኙ የአዲስ አበባ የማጠናቀቂያ ፍልሚያ መሰናጃ ከማድረግ ጀምሮ፣ የኪራይ መሰብሰቢያ መሳሪያ አድርገው ሲጠቀሙበት፣ በአንጻሩ አርአያነቱ በወጣቱ ትውልድ አእምሮ ውስጥ እንዲሰርጽ ለማድረግ ትክክለኛ የትግል ታሪክ ትረካና አንዳች የታሪክ ማስታወሻ እንዲዘጋጅለት አልተደረገም፡፡ ሐውልት የማቆም ልምድ ባላነሰበት አገር፣ ለብሔረሰቦች ዕኩልነት ሕይወቱን ለሰዋው ዋለልኝ መኮንን፤የመታሰቢያ ሐውልት የማቆም አስፈላጊነት ሊታይ አልቻለም፡፡ ይልቁንም ታሪኩ ተድበስብሶ መልካም ዝናው ሲጎድፍና ከኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ከአማራ ብሔረሰብ ሕዝብ ሊቸረው የሚገባው አድናቆት ሲያሽቆለቁል በቸልታ ታልፏል፡፡ ግን በዋለልኝ መኮንን ላይ ጣት መቀሰር እስከ መቼ ሊቀጥል ይገባዋል? አገራችን በአሁኑ ወቅት ለገጠማት ችግር ምን ፋይዳ አለው? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ለአገራችን አንድነትና ለሕዝቦች የቆየ ትስስር መቀጠል የሚጠቅመው ዋለልኝ መኮንን ላይ ተንጠልጥሎ፣ ሙትን እየወቀሱ መኖር ሳይሆን ለቀድሞ ተማሪዎች የብሔር ትግል ፈለግ ቀጣይነት፣ ቀሪ ፈተናዎችን በማጥናት ተገቢ የፖለቲካ መፍትሔ ለማፈላለግ በጽኑ መታገል ነው፡፡
ከአገር አንድነትና የብሔረሰብ ሕዝቦች የቆየ አብሮነት መዳከም አደጋ ጎን ለጎን የኤርትራ መገንጠልና የባህር በር ማጣት፣ የብሔር ትግሉ ውጤት፣ የጎን ጉዳት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በኢትዮጵያ አገራችን ላይ የደረሰውን ይህን አሳዛኝ ችግር፣ የብሔረሰብ ፖለቲካው ውጤት እንደሆነ አድርገው የሚያዩ ዜጎች፣ በትግሉ መነሻ ወቅት ላይ ጠንካራ ሚና የነበረውን ዋለልኝ መኮንን ጭምር ተጠያቂ ያደርጋሉ። እንደ ዕውነቱ ከሆነ፣ በብሔር ትግሉ ውጤት የደረሰውን አገራዊ ችግር በዋለልኝ መኮንን “የብሔር ትግል በኢትዮጵያ” ሥነጽሁፍ ሰነድ፣ ሒሳብ ማወራረድ በቂም ተገቢም አይደለም፡፡ ተቀባይነት ያለው የምክንያትና ውጤት ግንኙነት (cause and effect relationship) ትንተና አይሆንም፡፡
ዋለልኝ መኮንን የብሔር ትግል ሥነጽሑፍ ጽፎ ባያነብ፤ ጎላ ብሎ በመናገር ተማሪዎችን ቀስቅሶ ትግሉን ባያቀጣጥል፤ ይህ ችግር አይደርስም ነበር በማለት ዘመን ካለፈ በኋላ የወቀሳ ሂሳብ ስሌት ውስጥ መግባት ምክንያታዊነት ይጎድለዋል፡፡ እንደዚህ የሚያስብ ሰው ከአንድ የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍ ያነበብኩትንና ደስ የሚለኝን፣ በሁለት ስንኞች የተገነባ የማሟከሻ ግጥም ያስታውሰኛል፡፡
ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፤
ግብሩ ዕንቁላል ነበር ይሄን ጊዜ አበሻ፡፡
ይህ ማለት እኮ፤ በወቅቱ ዋለልኝ ባይኖር ኖሮ፣ የብሔር ትግል ጥያቄ በኢትዮጵያ አይነሳም ነበር የማለት ያህል ነው። ቢነሳም ሊመራው የሚችል ሌላ ብቁ ሰው ኢትዮጵያ የላትም ነበር ማለት ይሆናል፡፡ ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ እንጂ የዕድል ጉዳይ አይደለም፡፡ ሕብረተሰብ በቅራኔ ስለመሞላቱና በማያቋርጥ የለውጥ ሂደት ውስጥ ስለመገኘቱ፣ የህብረተሰብ ቁስአካልነት ፍልስፍና አስተምህሮ ይገልጻል፡፡ ቅራኔ ለህብረተሰብ ዕድገት አስፈላጊ ስለመሆኑና ዋናው ጉዳይ የቅራኔው አያያዝ መሆኑን ምሁራኑ ይገልጻሉ፡፡ በወቅቱ በአገራችን ሰፍኖ የነበረውን የህብረተሰብ ችግር ለመፍታት የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ በተማሪዎች የተመራ፤ ኋላ ላይ ግን ሕዝቡ ቀስ በቀስ እየነቃ ሲሄድ የራሱ ያደረገው ትግል ተፈጠረ፡፡ ውሀ የማይቋጥረው ትችት የዋለልኝ መኮንንን ማንነት ከሚያገዝፍ በስተቀር መሬት ላይ ያለውን ሐቅ አይቀይርም፡፡ የተሻለ የሚሆነው ወደ ኋላ ዞሮ የዋለልኝ መኮንንን የብሔር ትግል ጥንስስ አገላብጦ ማየት ነው። ዕውነቱ ምን እንደሆነ ለማወቅና በምክንያታዊነት ላይ ተመስርቶ አቋም ለመያዝ የሚመከረው፣ ነገሮችን ሰከን ብሎ ማየት ነው፡፡ በምክንያታዊነት ላይ ሳይመሰረቱ የሚሰጥ የፖለቲካ አስተያየት፣ ዐይንን ጨፍኖ በጫካ ውስጥ የመጓዝ ያህል ነው፡፡ ዐይኑን ጨፍኖ በጫካ ውስጥ የሚጓዝ ሰው፣ ጉድጓድ ውስጥ የመውደቅ ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡
በዋለልኝ መኮንን ላይ የሚሰነዘረው ወቀሳ በማን ጀርባ ላይ ይጫን የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ይህ ጥያቄ ቆም ብሎ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ ማንኛውም ነገር የሚከናወነው በጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ የወቀሳው መነሻ ጊዜ መሆን ያለበት የቀድሞ ተማሪዎች የብሔር ትግል ጥያቄ የያዘ መፈክር አንግበው የተነሱበት ወቅት ሳይሆን የብሔር ትግሉ ሂደት፤ ሂደቱ ፈር የሳተበትና በአሳፋሪ የትግል ውጤት የተደመደመበት ወቅት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ዋለልኝ መኮንን የነበረው በብሔር ትግሉ መነሻ ላይ ነበር፡፡ ዋለልኝ ከተገደለ በኋላ መስከረም 1967 ዓ.ም በንጉሡ ዙፋን ላይ የተተካው ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ፣ በተማሪው የትግል ንቅናቄ የተጠነሰሰውን የብሔር ትግል በአዋጅ ዘጋው። በዚሁ ወቅት በደርግ አፋኝ እርምጃ ከተቆጡ የቀድሞ ተማሪዎች እንቅስቃሴ አባላት መኻል ጥቂቶች በብሔረሰብ አውድ በሚደረግ ትግል ልክፍት ተለክፈው፣ ወደ የጎጣቸው በመበተን የጋራ የነበረውን የተማሪዎች የትግል እንቅስቃሴ ወደ ጎን በማለት በየብሔራቸው ስም በሚቋቋም ድርጅት መታገልን መረጡ። ለኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ነጻ መውጣት በጋራ እንታገል በሚለው ምትክ፣ “ለብሔሬ ሕዝብ” ልታገል የሚል ጠባብ አስተሳሰብ መሬት ያዘ፡፡ ይህ ደግሞ ያለአገራችን ታሪካዊ ጠላቶችና ቀድሞ የተቋቋመው ሻዕቢያ ደጀንነት ሊታሰብ የሚችል አልነበረም፡፡ የሕብረብሔራዊ ትግል አማራጭን በመቀበል የቀድሞ ተማሪዎች የጀመሩትን የፖለቲካ ዓላማ ለማስቀጠል በርዕዮተ ዓለም ላይ  የተመሰረተ የፖለቲካ ድርጅት ያቋቋሙት ሁሉ  የወታደራዊ ደርግን ጡጫ  አልችል ብለው ተራ በተራ ከሰሙ፡፡ ይህ ዝቅጠት በአገራችን የነበረውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዕድገት ጅማሮ ወደ ኋላ መለሰው፡፡
የብሔረሰብ ፓርቲ ያቋቋሙት ተማሪዎችና ልሂቃን በነበረባቸው የአቅም ውስንነት የተነሳ ያልጠራውን የብሔር/ብሔረሰብ ጽንሰ-ሓሳብ እንደመሰላቸው በመተርጎም፣ “የአማራ ገዥ መደብ” ሲባል የነበረውን “ጨቋኝ የአማራ ብሔር” በሚል በመተካት፣ ትግሉን በአማራ ሕዝብ፤ የኦርቶዶክስ ክርስትና ኃይማኖትና የአማርኛ ቋንቋ ላይ እንዲያነጣጥር በማድረግ፤ የኤርትራ ጥያቄም “በጨቋኟ የአማራ ብሔር” ተጽዕኖ ምክንያት የመጣ፣ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው ብለው ተነሱ፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ለሚታየው አስወቃሽ ነገር መነሻ ምንጩ ይህ ነው፡፡ የወቀሳው ምዕራፍ የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው ወቅት፣ የቀድሞ ተማሪዎች በህብረት ለሁሉም ጭቁን ብሔረሰቦች ሕዝቦች መብት ዕኩልነት የታገሉበት ስለነበር በወቀሳው ዘመን ውስጥ አይካተትም፡፡ ያ ወቅት እነ ዋለልኝ መኮንን ለሁሉም የኢትዮጵያ ጭቁን ብሔረሰቦች ሕዝቦች የታገሉበት ወቅት ነው፡፡ የወቀሳውን የጊዜ ሠሌዳ ወደ ኋላ በመጎተት፣ የመላው ኢትዮጵያ ተማሪ የተሳተፈበትን የትግል ወቅት እንዲሸፍን የሚደረገው ሙከራ፣ “ዐይናችሁን ጨፍኑና እናሙኛችሁ” የሚል የብልጣ ብልጦች መላ ይመስላል፡፡
“በኢትዮጵያ ለሰፈነው ብሔራዊ ጭቆና ተጠያቂዋ “ጨቋኟ የአማራ ብሔር” ናት፤ ገዥ መደቡ የወጣው ከአማራ ብሔር ነው፤ “ጨቋኟ የአማራ ብሔር” ቋንቋዋንና ባህሏን በሌሎች ብሔሮች/ብሔረሰቦች ሕዝቦች ላይ ጭናለች፤ በኢኮኖሚ በሌላው ብሔር ላይ በልጽጋለች፤ አማርኛ የነፍጠኛ ቋንቋና የገዥ መደብ መሳሪያ ነው፤ “ጨቋኟ የአማራ ብሔር ህብረተሰባዊ ዕረፍት አታገኝም” የሚል የማይረባ አስተሳሰብ፣ የመታገያ ንድፈ-ሓሳብ ሆኖ፣ የፖለቲካ ፕሮግራም ተደርጎ ተዘጋጀ፡፡
የማይረባው የፖለቲካ ንድፈ-ሓሳብ ከቀድሞ ተማሪዎች የብሔር ትግል ንድፈ-ሓሳብ ጋር በዓይነቱ ፈጽሞ ይቃረናል፡፡ የመላው ኢትዮጵያ ተማሪ የብሔር ትግል ጥያቄ የሚያወሳው፣ በየጠቅላይ ግዛቱ የሚኖሩት ብሔረሰቦች ሕዝቦች መብት ስለመከበር፤ በቋንቋቸው እንዲማሩ፤ እንዲዳኙ ስለማድረግና አስተዳዳሪዎቻቸውን እንዲመርጡ፤ ዕኩልነት በሰፈነበት ምህዳር ተከባብረው በአንድነት እንዲኖሩ ስለማስቻል ነበር። ኢብሳ ጉተማ “ኢትዮጵዊ ማን ነው?” በሚል ግጥም የጠየቀው፣ ለዚህ ምላሽ ለማስገኘት ፈልጎ ነበር፡፡ የቀድሞ ተማሪዎች የብሔር ትግል ጥያቄ ዓላማው በየጠቅላይ ግዛቱ የነበረው ታህታይ ሕብረብሔራዊነት፣ የሁሉም ብሔረሰቦች ህዝቦች ዕኩልነት በሰፈነበት ምህዳር ወደ ዕውነተኛ ላዕላይ ሕብረብሔራዊነት (ኢትዮጵያዊነት) የሚረማመድበት አስቻይ ሁኔታ መፍጠር እንጂ ማህበረሰቦች ከያሉበት ዘውግ ተነጣጥለው፣ በቋንቋ ግድግዳ አጥር ለየብቻቸው ተኮልኩለው እንዲኖሩ ስለማድረግ፤ በዳር ድንበር ተለያይተው በጉርብትና እየተናቆሩ የሚኖሩ ብሔረሰቦች ሕዝቦችን ስለማየትና ኢትዮጵያን ቀስ በቀስ  አዳክሞ ስለመበታተን አልነበረም። ከዋለልኝ መኮንን ሞት በኋላ ፈር የሳተው የብሔር ትግል መስመር፣ ባልነቃ ብሶተኛ ህዝብና በአገራችን ታሪካዊ ጠላቶች ድጋፍ ፈርጥሞ፣ ዘውዳዊውን ስርዓት የተካውን ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በተራዘመ የትጥቅ ትግል በማዳከም፣ ከመንበረ-ስልጣኑ ባስወገደ ማግስት የተዛባው ንድፈ-ሓሳብ ሕገመንግሥት ሆኖ በመጽደቁ፣ በአገራችን ላይ ክፉ በደል ደረሰ፡፡ በደሉም የትግሉ ዒላማ ለተደረገው የአማራ ህዝብ የግፍ ግፍ ሆነበት፡፡
የብሔር ትግሉን ቀድሞ ወደ ተነሳበት ፈር ለመመለስ፣ ውስንነት በማጋጠሙ፣ የአማራን ህዝብ እንደ ጠላት የሚመለከቱ ቡድኖች ረዥም የእፎይታ ጊዜ አገኙ፡፡ ከውስንነቶቹ መኻል የአማራነትና ኢትዮጵያዊነት ጠንካራ ቁርኝት መኖር፤ የአማራ ወጣቶች በደርግና ኢሕአፓ ጎራ መኻል ይበልጥ ማለቅ የፈጠረው ጠባሳ፤ “ትምክህተኛው” የአማራ ወጣት፣ የጠባብ ብሔረተኝነት ትግል ስልትን ተመራጭ አድርጎ ያለማየት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ድህረ-ደርግ በኢሕአዴግ የተመሰረተው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብ.አ.ዴ.ን.)፣ (የቀድሞው ኢ.ሕ.ዴ.ን.) እወክለዋለሁ ስለሚለው የአማራ ብሔረሰብ ሕዝብ መብት መከበር የሠራው ሥራ የሌሎች ብሔረሰቦች ድርጅቶች ካከናወኑት በጣም የሚያንስ መሆኑ ሊጠቀስ የሚገባው ተጨማሪ ውስንነት ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ብ.አ.ዴ.ን. የመንታ እናትነት ሚና እንዲጫወት ሁኔታዎች ስለሚያስገድዱት ነው፡፡ በአንድ በኩል አማራ ውስጥ ለዘመናት የዘለቀው የኢትዮጵያዊነት-አማራነት ቁርኝት፣ ድርጅቱንም ስለሚፈታተነው ሲሆን በሌላ በኩል፤ ወደ ኋላ በመመለስ ተረከዙን ከጠባብ ብሔረሰብ ድርጅቶች ጋር አስተካክሎ፣ መሮጥ ግድ ስለሆነበት ሊሆን ይችላል፡፡ ወርቃማ ስያሜው ከነበረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢ.ሕ.ዴ.ን.) ተንሸራቶ ወደ ብ.አ.ዴ.ን. እንዲገባ የተገደደበት ምክንያት ይኸው ሊሆን ይችላል፡፡ ምርጫው የድርጅቱ ቢሆንም ወደ ቀድሞ ወርቃማ ስሙ የመመለሻ የጉዞ ቲኬት እንዲቆርጥ የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እያመላከተው ይገኛል፡   
የሁሉም ብሔረሰቦች ሕዝቦች መብት በተከበረበት ምህዳር፤ ዴሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት እንዲሰፍን ለማድረግ በቀድሞ የኢትዮጵያ ተማሪዎች በግልጽ የተቀመጠው የብሔር ትግል ንድፈ-ሓሳብ፣ ከላይ በተጠቀሰው ውስንነት የተነሳ ከሸፈ፡፡ የብሔር ትግሉ የአማራ ብሔረሰብ ሕዝብን በጠላትነት የሚፈርጅ፤ ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ሕዝቦችን በአማራ ላይ የሚያስነሳ፤ የአማራ ሕዝብን ለበታችነትና ለከፍተኛ እንግልት የሚዳርግ፤ በኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ሕዝቦች መኻል ጸንቶ የቆየውን አንድነት የሚያዳክም አሳዛኝ አቅጣጫ ያዘ፡፡ ይህን አሳዛኝ ስህተት አርሞ የብሔር ትግሉን ፈር በማስያዝ ቀደም ሲል ወደ ተነሳበት ዓላማ ለመመለስ፣ የብ.አ.ዴ.ን. ንቁ ተሳታፊ አለመሆን በውስንነት ቢታይ የሚበዛበት አይመስልም፡፡
የአማራ ሕዝብ በአንድነት ተነሳስቶ በሕልውናው ላይ የተደቀነበትን አደጋ ለመቀልበስ፤ በአገሪቱ የፖለቲካ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ በብቃት ለመሳተፍ፤ በአካባቢ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት  እንዳይችል ሆኖ አቅሙን ተቀምቷል፡፡ በብሔረሰብ ፖለቲካ ምሕዋር መንቀሳቀስ የማይቀር ከሆነ፤ ምንም እንኳ እንደ ኢትዮጵያ ላለ አገር የማይጠቅም፣ በሕግ መገደብ ያለበት ኋላ ቀር የፖለቲካ ስልት ቢሆንም፤ የአማራ ሕዝብ ከባድ ትግል የሚጠይቀው ፈተና ውስጥ መግባቱን በመረዳት፣ ተመጣጣኝ ተሳትፎ ለማድረግ መነሳሳት ግዴታው ይሆንበታል፡፡ ግዴታውንም ለማሳካት የአማራ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መድረስ፤ የአማራ ልሂቃን የአማራነትና ኢትዮጵዊነት ቁርኝት፤ በአለፉት ገዥ መደቦች ወቅት የነበረው የአማራነት ጭንብል የፈጠረው ለሰርጎ ገብ አታላይ ግለሰቦች በቀላሉ መጋለጥ፤ የአማራ ብሔረተኝነት ትግል በዴሞክራሲዊ ብሔረተኝነት አቋራጭ መታጠር፤ ለአማራ ብሔረተኝነት የሚተጋ ጠንካራ ወገንተኛ የፖለቲካ ፓርቲ አለመኖር የመሳሰሉ ፈተናዎችን ማለፍ አለበት፡፡  
በዚህ ከባድ ትግል አውድ ዙሪያ የአማራ ብሔረሰብ ሕዝብ እንዳይሰባሰብ የሚደረገው ተከላካይነት፣ በዋለልኝ መኮንን ምክንያት የአማራ ብሔረሰብ ሕዝብ እንዲሰነጠቅ ማድረግን ይጨምራል፡፡ የአማራ ሕዝብ ዳግም በሕይወትም በታሪክም እንዲሞት ይፈለጋል፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ያለቁትን ጥንታዊ አማራ ጀግኖች ለማጣጣል የሚደረገው ቀጣይነት ያለው ጥረት፤ የሚንኳሰሰው የጋራ ታሪክ፣ የሚቋቋም አንጀት ቆራጭ ሐውልት ወ.ዘ.ተ. አንደምታ ምን እንደሆነ በቅርብ ለማወቅ ሠፊ ዕድል ያላቸው ጥቂት የአማራ ሕዝብ ተወላጆች ነን ባዮች፤ እስከ አሁን ጉዳዩን በቸልታ በማየት፣ በተቃራኒው በአማራ ትውልዶች ላይ የሚደረግ ጥቃት አስፈጻሚ በመሆን ማገልገላቸው ያሳዝናል፡፡
የብሔር ትግል ታሪካዊ ዳራ በአገራችን ምን እንደሚመስልና ያስከተለው ጉዳት በዚህ መጠን ከተገለጸ፤ የሚቀረው ጉዳይ የብሔር ትግሉ ታሪክና ውጤቱ ለወጣቱ ትውልድ ሊሰጥ የሚችለውን ትምህርት ከትውልዱ ቀጣይ ኃላፊነት ጋር አያይዞ መመልከት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ወጣቱ ትውልድ ያለፈውን ታሪክ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ፣ በርካታ ነገሮችን በጥሞና ማስተዋል ስለቻለ፣ ለአገራችን ኢትዮጵያ አንድነት መልሶ መገንባት፣ ወደፊት መወሰድ የሚገባውን እርምጃ ለመወሰን የሚያስችለው ዕውቀትና መረጃ ባለቤት ሆኗል፡፡ አገራችን አሁንም በጂኦፖለቲካ መዘዝ ራዳር ክልል ውስጥ መሆኗን፤ ዛሬም ለግል ጥቅም የሚራወጡ የውስጥ ቦርቧሪና የውጭ ደመኛ ጠላቶች አለመገላገሏን መገንዘብ አለበት፡፡ ከዚህ አሳሳቢና አጣብቂኝ ከሆነ ችግር በመነሳት ለአገር ጥቅም ዘብ የሚቆም የብልህ፤ አስተዋይና አገር ወዳድ ወጣት ትልድ ዋስትና የሚያስፈልጋት መሆኑን  ማንም ሳያስተምረው በራሱ ጥረት አውቋል፡፡
በወጣት አጥፊ ፖለቲከኝነት በውድ አገራቸው ላይ በፈጸሙት ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት ተጸጽተው ላለፈ ክረምት ቤት ለመሥራት እየሞከሩ ካሉ አንዳንድ አረጋዊያን ታጋዮች፤ ወጣቱ የሚማረው በርካታ ቁም ነገር አለ፡፡ ነገሮችን የሚዘበራርቁትንም ታዝቧቸዋል፡፡ ወጣቱ ትውልድ በወጣትነት ወቅት ከሚከሰት፤ አገርን ከሚጎዳ የኋላ ኋላ ከባድ የእግር እሳት ከሚሆን ግብታዊ የፖለቲካ ተሳትፎ መታቀብ አለበት፡፡
በምክንያት የሚቃወም፤ በምክንያት የሚደግፍ በሳል ትውልድ ሊሆን ይገባል፡፡ አገራችን አሁን ከምትገኝበት መስቀለኛ መንገድ እንድትወጣ ጊዜው የሚጠይቀውን ዓይነት ትግል ማድረግ፤ ለአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የሚስማማ ፌዴራላዊ ስርዓት እንዲዘረጋ፤ የዴሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት ባህል እንዲዳብር፣ በውጤቱም አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ተገንብቶ፣ አገራችንን ወደ ቀደምት ገናናነቷ ለመመለስ የሚደረግ ጉዞ እንዲጀመር፣ በውጤት የሚለካ ጥረት ለማድረግ የሚባክን ጊዜ የለውም፡፡
ከላይ የተጠቀሰውን የትውልድ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት የሚያስፈልገው ዋለልኝ መኮንንን ወቅሰው በሚያስወቅሱ፣ የራሳቸው የሆነ ዓላማ ባላቸው ቡድኖች አጉል ትችት መፍዘዝና መፋዘዝ ሳይሆን፣ ፈር የሳተውን የዋለልኝ መኮንን የብሔር ትግል መስመር አቃንቶ፣ ወደ ፈሩ በመመለስ፣ በአዲስ መንፈስ ለትግል ለመሰለፍ ዳግም “ፋኖ ተሰማራ፤ እንደ ሆችሚን እንደ ቼጉቬራ፤” ማለት መጀመር አለበት፡፡ ድህረ ዋለልኝ የብሔረሰብ ትግል የተመራበት ስልት በኋላ ቀር አመለካከት የታጀለ ነበር፡፡ አገራት ወደ አገራት ሕብረት ሲገሰግሱ፤ ዓለም ወደ ሉላዊነት ስትገሰግስ በብሔረሰብ ፖለቲካ አንቀልባ በመታዘል፣ ከምቾት ማማ ላለመውረድ፣ የአንዲት አገር ብሔረሰቦች ሕዝቦችን ለዘላለም በቋንቋ ግድግዳ አጥር ለያይቶ ለመኖር፣ በተቃራኒ አቅጣጫ ለሚገሰግሱ አረጋዊያን ፖለቲከኞችና ግብረ በላ ደቀመዝሙሮቻቸው፤ እንደዚሁም የብሔረሰብ ፖለቲካ ፓርቲ ልምድ በመኮረጅ፣ ይኽንኑ ኋላ ቀር የፖለቲካ ጉልት ለማስቀጠል ለሚያቆበቁቡ ደራሽ ፖለቲከኞች ጋሻ አጃግሬ በመሆን፣ በብሔረሰብ ፖለቲካ አዙሪት ውስጥ ገብቶ፣ መንቀዋለልን ወጣቱ ትውልድ ሊጠየፍ ይገባል፡፡ በብሔረሰብ ፖለቲካ ተጠምዶ ትልቅ የነበረችውን አገር፣ እንደ አሞሌ ጨው ለማቅለል ዋጋ በመክፈል፣ ከሙት ጋር መሞት፣ የጤና አለመሆኑን በአንድነት ማውገዝ አለበት፡፡ በአገራችን የሰፈነው ድህረ ዋለልኝ የፖለቲካ አስተሳሰብ፤ አሮጌ አስተሳሰብ መሆኑን በማያወላውል ሁኔታ መረዳት አለበት። የቀድሞ ተማሪዎች ትግል ሊያሟላው የነበረውን የንጉሡ ዘመን የፖለቲካ ክፍተት በመሙላት፣ ታህታይ ህብረብሔራዊነትን ወደ ላዕላይ ሕብረብሔራዊነት (ኢትየጵያዊነት) መተኮስ የአገር ህልውና ጥያቄ ነው፡፡ አገራችን ወደ ቀድሞ ገናናነቷ ልትመለስ የምትችለው በብሔረሰቦች ፓርቲዎች የአስማት ስጋጃ አለመሆኑን ተገንዝቦ፣ ለሁሉን አሳታፊ ርዕዮተ ዓለማዊ (ሕብረብሔራዊ) የፖለቲካ ትግል መነሳሳትና ከጎረቤት አገሮች ጋር ትብብር መፍጠር፣ ነገ ዛሬ የማይባል የትውልድ አደራ ነው፡፡

Read 2069 times