Sunday, 10 June 2018 00:00

“መከላከያ ዘርና ብሄር የለውም… ሁላችንም የአንድ አገር ወታደሮች ነን” - ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)


    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሠሞኑን ባካሄዱት ሹም ሽር ላለፉት አስራ ሠባት ዓመታት የኢትዮጵያ ጦር ሃይሎች ኢታማዦር ሹም ሆነው ያገለገሉትን ጀነራል ሣሞራ የኑስ በጄነራል ሣአረ መኮንን የተተኩ ሲሆን የደህንነት ሃላፊው አቶ ጌታቸው አሠፋ፣ የአየር ሃይል ዋና አዛዥ በነበሩት ጀነራል አደም መሃመድ ተተክተዋል፡፡
የኦህዴድ መስራች፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሠ መስተዳደር፣ የሃገር መከላከያ ሚኒስትር፣ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ እንዲሁም ለሁለት ወራት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ በመሆን ያገለገሉት አቶ አባዱላ ገመዳና በንግድና ኢኮኖሚ ሚኒስትርነት እንዲሁም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አቶ ግርማ ብሩ በጠሩታ መሠናበታቸው ታውቋል፡፡
ላለፉት 42 አመታት ከተራ ወታደርነት እስከ የጦር ሃይሎች ኢታማዦር ሹምነት፣ በተዋጊና አዋጊነት ያገለገሉት ጀነራል ሣሞራ የኑስ፤ በተለይ በኢትዮጵያ ኤርትራ የድንበር ጦርነት ወቅት በሽሬ ግንባር ጀብዱ መፈፀማቸው ተነግሮላቸዋል፡፡
ጀነራል ሳሞራ የኑስ በጦር ሃይሎች ከ17 አመት በፊት በኢታማዦርነት የተሾሙት ከመከላከያ የተባረሩትን ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገብረ ትንሣኤን በመተካት መሆኑ ይታወሣል፡፡
ጀነራሉ ከትናት በስቲያ በብሄራዊ ቤተመንግስት አሸኛኘት በተደረገላቸው ወቅት ለሰጡት የረዥም ዘመን አገልግሎትና ለፈፀሙት ወታደራዊ ጀብዱ  ከፍተኛ የሜዳሊያ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡
ጄነራሉን ተክተው የጦር ሃይሎች ኢታማዦር ሹም በመሆን የተሾሙት ጀነራል ሣእረ መኮንን ደርግን ለመጣል በተደረገው የ17 አመት ጦርነት ወታደራዊ አዛዥ የነበሩ ናቸው፡፡ በቅርቡም የሙሉ ጀነራልነት ማዕረግ ከተሠጣቸው 3 ጀነራሎች አንዱ እንደሆኑም ይታወቃል፡፡ ላለፉት 17 አመታት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ደህንነት ሃላፊ ሆነው የቆዩትን አቶ ጌታቸው አሠፋን የተኩት ጀነራል አደም መሃመድ በበኩላቸው የአየር ሃይል ፓይለት የነበሩና በሱዳን አቢዬ ግዛት የተሠማራው የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ሃይል ምክትል አዛዥ እንዲሁም ከጥቅምት 2005 ጀምሮ ሜ/ጀነራል ሞላ ኃ/ማርያምን በመተካት የኢትዮጵያ አየር ሃይል አዛዥ የነበሩ ናቸው፡፡
በዚሁ ስነስርአት ላይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በማድረግ የሽብር ክስ ተፈርዶባቸው ከአመታት እስር በኋላ በቅርቡ የተለቀቁት ብርጋዴር ጀነራል አሣምነው ፅጌና የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ሃይል አዛዥ ሜ/ጀነራል አለምሸት ደግፌ የተነጠቁት ማዕረጋቸው ተመልሶላቸው፣ የጡረታ መብታቸው እንዲከብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወስነዋል፡፡
ብርጋዴዬር ጀነራል አሣምነው ፅጌ የግንቦት 7 ድርጅትን የሽብር አላማ በመቀበል፣ ከሌሎች የቀድሞ ጀነራሎችና ወታደራዊ መኮንኖች ጋር መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ሞክረዋል በሚል ተከሠው፣ የእድሜ ልክ ፍርደኛ እንደነበሩ ይታወሣል፡፡
ላለፉት ዘጠኝ አመታት ከታሠሩ በኋላ በቅርቡም እሣቸውን ጨምሮ አብረዋቸው የታሠሩ ወታደራዊ መኮንኖች በምህረት መለቀቃቸው ይታወቃል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ሰሞኑን በቤተመንግስት በተደረገው የሹም ሽር ሥነስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር “መከላከያ ዘር የለውም…መከላከያ ብሄር የለውም…ሁላችንም የአንድ አገር ወታደሮች ነን…” ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ።

Read 8417 times