Sunday, 10 June 2018 00:00

ገዥው ፓርቲ የመንግስት ድርጅቶች ሽያጭ ላይ ማብራሪያ ሰጠ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

 ኤምቲኤን” እና “ቮዳፎን” ከቴሌ ድርሻ ለመግዛት አቅደዋል

    የመንግስት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ የማዛወሩ ሂደት በጥናት   በጥንቃቄና በጥብቅ ዲሲፒሊን እንደሚፈፀም ገዥው ፓርቲ ባወጣው የአፈፃፀም ዝርዝር ያስታወቀ ሲሆን የደቡብ አፍሪካዎቹ “ቮዳፎን” እና “ኤምቲ ኤን” “ኩባንያዎች በበኩላቸው፤ ከኢትዮ ቴሌኮም የአክሲዮን ድርሻ ለመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው ከወዲሁ መግለፃቸው ታውቋል፡፡
የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሜ ኮሚቴ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታነት የሚዛወሩበትን ዝርዝር በተመለከተ ባወጣው መመሪያ፤ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴልና የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ድርሻ ሊሸጥ የሚችለው ለሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ብቻ ነው ብሏል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርት ሎጅስቲክ ድርጅት ለሃገር ውስጥና ለውጪ ባለሃብት ገበያ የቀረቡ መሆኑን የጠቆመው ገዥው ፓርቲ፤ በእነዚሀ ኩባንያዎች ውስጥ የመንግስት አክሲዮን ድርሻ አብላጫ እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡
ከላይ በተጠቀሱት ሜጋ ፕሮጀክቶች እና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የባለሃብቱ አቅም እየተጠናከረ መሄዱን በማጤን ሙሉ ለሙሉ መንግስት የሚወጣበት ስትራቴጂ መቀመጡም ተጠቁሟል፡፡
ገዥው ፓርቲ እነዚህን የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ለማዞር ሶስት አበይት ሁኔታዎችን ታሣቢ በማድረግ መወሠኑንም አስታውቋል፡፡
የመጀመሪያ የውጪ ንግድን ለማሣደግ አጋዥ ይሆናል ከሚል እሣቤ ሲሆን ሁለተኛው ታሣቢ ዜጎችን አካታች የሆነ ሃገራዊ እድገት ማስመዝገብ መሆኑን ይገልፃል፡፡
ሦስተኛው ደግሞ የልማት ድርጅቶች በምርታማነት፣ በአገልግሎት አሠጣጥ ጥራታቸውና አቅማቸው ውጤታማ ሆነው ወደ አለማቀፋዊ ተወዳዳሪነት እንዲያድጉ አጋዥ ይሆናል ከሚል እሳቤ መሆኑን ፓርቲው አስታውቋል፡፡ በዚህ የአክሲዮን ሽያጭ የውጭ ምንዛሬና የካፒታል ገቢ እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡
የመንግስት ውሣኔን ተከትሎ በበርካታ የአፍሪካ ሃገራት በቴሌኮም ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙት “ኤምቲ ኤን” እና “ቮዳፎን” የተሠኙት ግዙፍ የደቡብ አፍሪካ የግል የቴሌኮም ኩባንያዎች፣ ከቴሌ አክሲዮን ለመግዛት ፍላጎት እንዳላቸውና በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እንደሚነጋገሩ አስታወቋል፡፡

Read 4741 times