Sunday, 10 June 2018 00:00

ሃይማኖት ተቋማት ሙስና መንግሥት እርምጃ ይወስዳል - ጠ/ሚኒስትሩ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

• “ሥራቸው የሞራል ልዕልና መፍጠር ነው፡፡ የሌብነት ምሽግ መኾን አይችሉም፤”
• “ሃይማኖት በመንግሥት፣ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም የሚለው ሚዛን ያስፈልገዋል፤”



    የሃይማኖት ተቋማት በውስጣቸው የተሰገሰገውን የሌብነት ድር በመበጣጠስ፣የሞራል አስተማሪነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከእንግዲህ መንግሥታቸው  በተቋማቱ ውስጥ የሚፈጸምን ዘረፋና ሌብነት በቸልታ እንደማያልፈው አስጠነቀቁ፡፡
“ሃይማኖት በመንግሥት፣ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም፤”የሚለው የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ትክክለኛ መርሕ ቢኾንም፣ የሃይማኖት ተቋማት የሚሰበስቡት መባ እና ዘካ የሕዝብ ሀብት እስከኾነ ድረስ መንግሥት አጠቃቀሙን የመቆጣጠር ርምጃ እንደሚወስድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ገንዘብ የሕዝብ ሀብት እንደኾነና በየትኛውም ዓለም ኦዲት እንደሚደረጉ የጠቀሱት ዶ/ር ዐቢይ፣ትንሽ የሌብነት ምልክት ካዩ ፈቃዳቸውን እስከመቀማት እንደሚደርሱ አስረድተዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ከመሬት ጀምሮ ለመንግሥት ለሚያቀርቡት ጥያቄ ባለሥልጣናቱ በእኩልነት ምላሽ መስጠት የሚገባቸውን ያህል፣ በአጸፌታው የመንግሥት ጥያቄ “ምከሩ፤ ገሥጹ፤ ሰላም አምጡ” በማለት ብቻ እንደማይወሰንና እንደማይቀጥል አስረድተዋል፡፡ “በዕለት ተዕለት የሃይማኖት ሥራ መንግሥት አይገባም፤ በመንግሥት የዕለት ተዕለት ሥራ ሃይማኖት አይገባም፤ ግን ደግሞ ቀይ መሥመርና ድንበራችን ሁሌ የቆመና የማይገናኝ አይደለም፤” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አጠቃላይ መርሑ ትክክል ቢኾንም ዘወትር እንደማይሠራና ሚዛን እንደሚያስፈልገው አስገንዝበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም፣“የሃይማኖት ተቋማት ዋነኛ ሥራቸው፣የሞራል ልዕልና መፍጠር ነው፤ የሌብነት ምሽግ መኾን አይችሉም፤ የለባቸውም፤ አላግባብ መባ እየሰበሰቡ ምን ላይ እንዳዋሉት የማይታወቅ ከኾነ ከእነርሱ የሚጠበቀው የሞራል ልዕልና ይጠፋና የሚያስተምሩትም ምእመን ሌባ ይኾናል፤”በማለት በውስጣቸው የተሰገሰገውን የሌብነት ድር በመበጣጠስ እንዲሁም ሃይማኖት በጥበብና በዕውቀት በባለሥልጣናት ላይ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ በመጠቀም፣ መንግሥትን በተግባር ለማስተማር ቀዳሚውን ድርሻ እንዲወስዱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ ባለፈው ረቡዕ፣ በሼራተን አዲስ የተካሔደውን 4ኛውን ሀገር አቀፍ የፀረ ሙስና ጥምረት ጠቅላላ ጉባኤ በንግግር የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣መንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማትን ከተደራጁ ሌቦች ለመከላከልና ለማጠናከር የሚደረገው ትግል፣ በመንግሥት ብቻ ከዳር የማይደርስ በመኾኑ፤ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ሲቪል ማኅበራት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች፣ ዘርፎ መክበርንና ሰርቆ አለማፈርን የሚያበረታታውን ባህልና አስተሳሰብ እያወገዙና እያጋለጡ በምሳሌነት በመዋጋት ለሕዝቡ ትምህርት እንዲኾኑ ጠይቀዋል - “እስኪ ምሳሌ ኾናችሁ ተገኙ፤ምሳሌ ኾናችሁም ታገሉ፤የሠራችሁትንም ለትምህርት እንዲኾን ለሕዝብ አሳዩ፡፡”

Read 5159 times