Sunday, 10 June 2018 00:00

የስታዲየም ግንባታ ተነሺዎች ካሳና ምትክ ቦታ አልተሰጠንም ሲሉ አማረሩ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ለአራት ዓመት በፊት ቦሌ አካባቢ “የአደይ አበባ” በሚል ስያሜ ለሚገነባው ብሔራዊ ስታዲየም ከመኖሪያቸው የተነሱ 355 አባወራዎች እስካሁን ምትክ ቦታና ካሳ አልተሰጠንም ሲሉ አቤቱታ አቀረቡ፡፡ በግንባታ ላይ የሚገኘው ብሔራዊ ስታዲየም ሲጠናቀቅ 60ሺህ ተመልካቾችን ይይዛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አባወራዎቹ መሬቱ ለልማት ይፈለጋል ተብለው እንዲነሱ ሲደረግ አዲስ በሚዘጋጅ መመሪያ መሰረት፤ ምትክ ቦታና ካሳ ይሰጣችኋል፤ በሚል መሬቱን በኃይል እንዲለቁ ቢደረግም ላለፉት 4 ዓመታት ከ38 በላይ የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ቢመላለሱም ሰሚ ማጣታቸውን ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
ነዋሪቹ በአሁኑ ወቅት ከዘመድ ተጠግተውና አነስተኛ ቤቶችን በመከራየት ጎስቋላ ኑሮ እየመሩ መሆኑን በማስረዳት፣ መንግስት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ አቤቱታቸውንም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በደብዳቤ ያስገቡ ሲሆን በደብዳቤያቸው እንደገለፁት፤ በቦታው ላይ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ይኖሩ እንደነበር ጠቁመው፤፤ ቦታው ለልማት ይፈለጋል ሲባልም፣ የቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 3 አስተዳደር፣ ለእያንዳንዳቸው 75 ካሬ ሜትር የመኖሪያ ቤት መስሪያ ምትክ ቦታ ከእነካሳው እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸው ነበር፡፡
“ካሣና ምትክ ቦታ ይሰጣችኋል፤ ኮንዶሚኒየም ቤት እንዳትመዘገቡ ተብለን እድላችንን እንድናሳልፍም ተደርገናል” የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ በ2003 ዓ.ም የተነሳውን የአየር ካርታ ምስል በአቤቱታቸው ላይ በማያያዝ፣ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ጉዳዩን መርምረው መፍትሄ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል፡፡   

Read 1919 times