Sunday, 03 June 2018 00:00

እኛና ዶክተር ዐብይ “የዜማ ጊዜ ደረሰ” እያልን ነው

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)


    ሌት ክዋክብቱ እንደፀደይ
አጥለቅልቆን በቀይ አደይ፣
ሰማዩ ስጋጃ አጥልቆ
ተሽለምልሞ አንፀባርቆ
ፈክቶ፣ አሸብርቆ ደምቆ
በአዝመራ በአጥቢያ አፀድ ሰፍኖ
በዓደይ አዝርዕት ተከሽኖ
በእንቁጣጣሽ ሰብል ታጥኖ
ኢዮሃ አበባዬ ሆይ፣
ጨረቃዋ ከቆባዋ፣ ከሸልምልሚት እምቡጧ
ጧ ብላ ከሰንኮፍዋ፣ ተንዠርግጎ የእንኮይ ቡጧ፣
ድንግል ጽጌረዳ ፈልቃ
ፍልቅልት ድምብል ቦቃ …
ተንሰራፍታ የአበባ ጮርቃ፣
ታዲያን ብሌኑ የጠጠረ
ባህረ ሀሳቡ የከረረ
የውበት ዐይኑን የታወረ
ልበ ሕሊናው የሰለለ
አይ፣ አበባ አይደለም አለ
አይ፣ እሳት አይደለም አለ
ያልታደለ፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት የስነ ጽሑፍ ሰው የሆነ የቅርብ ጓደኛዬ፣ በሀገራችን የፖለቲካ ጉዳዮችና የባለስልጣኖቻችንን እንከኖች በሚመለከት የተፃፈ መጽሐፍ አንብቦ ሲጨርስ፣ ተንሰቅስቆ አለቀሰ፡፡ እናም “ወይኔ ልጆቼ፡- ልጆቼን እዚህ ሀገርና እነዚህ ሰዎች እጅ ላይ ለመጣል በመውለዴ እፀፀታለሁ…” አለና በእጅጉ አዘነ፡፡
ለነገሩ ስሱ ስለሆነ ሁሉም ነገር ያምመዋል፡፡ በርግጥም የስነ ጽሁፍ ሰው ትክክለኛ ስሜት እንደዚያ ነው፡፡ ይህ ወዳጄ፤ የኦሮሚያ ወጣቶች ሲሞቱ፣ እናቱ እንደሞተችበት ልጅ አልቅሷል፡፡ ገበሬዎች መሬታቸው ተቀምቶ ተንከራተቱ ብሎ አንብቷል። እንባው ቅርብ፣ ነፍሱ የሁሉም ናት፡፡ በተለይ ወገኖቻችን በሊቢያ በታረዱበት ወቅት ስልክ ደውሎልኝ፣ ያለቀሰው ለቅሶ ፈፅሞ አይረሳኝም፡፡ ሰፈሩም ላይ ሲያለቅስ ያዩት፤ “ያንተ ዘመድ አለበት ወይ!” ብለውታል፡፡ ለእርሱ ግን ሁሉም ዘመዱ ነው። በዚህ መቆርቆሩም ወህኒ ገብቶ ወጥቷል፡፡
ታዲያ ይህን ወዳጄን ሰሞኑን አግንቼው ነበር፡፡ ለውጥ የተባለውንም ለመቀበል በእጅጉ ዘግይቷል። በኋላ ግን “በቃ አሁን ከልቤ አምኜ ተቀብያለሁ” አለኝ፡፡ ለነገሩ ውሸት አያውቅም፣ ማስመሰል አይወድድም፡፡ ይህ ወዳጄ በዚህ አላቆመም፡፡ እቤቱ ገብቶ ሁለት ልጆቹን “ልጆቼ! አሁን መልካም ጊዜ መጥቶላችኋል፤ አሁን የተስፋ ጊዜ ነው፤ እግዜር ዶክተር ዐቢይን አመጣላችሁ!” ብሎ ነገራቸው። ልጆቹ አላመኑትም፡፡ “አባዬ ስትቀልድ ነው አይደል?” … ሁለቱ ልጆቹ ተያዩ፡፡
“የእውነቴን ነው!” አለ፤ አላመኑትም፤ ምክንያቱም ጓደኛዬ መንግስትን ሲራገም እንጂ ሲያሞግስ ሰምተውት አያውቁም፡፡
ጓደኛዬም እውነቱን ነው፤ ልጆቹም አልተሳሳቱም፡፡ ምክንያቱም ብዙ ነገሮች ህልም በሚመስል ሁኔታ እየተቀየሩ ነው፡፡
የ“ካፒታል ጋዜጣ” አምደኛ የሆነው ወዳጄ ሰለሞን ከበደም ደጋግሞ፤ “በሕልሜ እየመሰለኝ እፈራለሁ፡፡ ስባንን ወደ ቀድሞው ቦታ የምንመለስ ይመስለኛል” ብሎኛል፡፡ የ “ጊዜ” መጽሔት አዘጋጅ፣ ወዳጄ ጋዜጠኛ አለማየሁ ባዘዘውም፣ ፌስቡክ ላይ ተመሳሳይ ሀሳብ ለጥፎ አይቻለሁ፡፡
ህልም ይመስላል፣ ግን እውን ሆኗል፡፡ “The gloomy person lack hope, The fanatic lacks an understanding of the history” እንደሚባል ካልሆነ በቀር፡፡ ከላይ የጠቀስኩት የሎሬት ፀጋዬ ግጥምም የሚጠቅሰው የዚያ ዐይነቶቹን ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ግን የዜማ ጊዜ ነው፡፡ ተራሮች ፈርሰዋል፣ ፍርሀቶች ፈርተዋል፡፡
በተለይ የዚህ ለውጥ ፊት አውራሪ ወደሆኑት ወደ ዶክተር ዐቢይ አህመድ ስንመጣ፣ በእጅጉ እንድንደነቅ የሚያደርጉን ነገሮች ብዙ ናቸው። በተለይ ወደ ትውልድ መንደራቸው ዘልቄ ጎረቤቶቻቸውን፣ የዶክተሩን ጓደኞች እናቶች፣ እህቱን፣ ወደ ትግል ሲገባ አዛዡ የነበሩትን ኮማንደር፣ ደሀውን ሀብታሙን፣ ወጣቱን፣ ሽማግሌውን ስጠይቅ ቋንቋቸውና ሀሳባቸው አንድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በተለይ በሻሻ ስትሄድ እያንዳንዱ ሰው፣ ወጣት ሽማግሌ፣ ወንድ ሴት፣ ዐቢይን ብቻ ሳይሆን፣ የዐቢይን አላማና ቤተሰቦቹን ለመጠበቅ ዘብ ቆሟል፡፡ እኔም አንድ ቀን የታሰርኩት ጠቅላይ ሚኒስትሬን በሚጠብቁልን ሰዎች ነበርና ቅር አላለኝም፤ ይልቅስ በጥንካሬያቸው ደስ ብሎኛል፡፡
ጠቅላያችን የአስራ አራት ዓመት ወጣት ሆኖ ትልቅ ህልም ነበረው፡፡ ህልሙ ለድሆች ህይወት መለወጥ ነበር፡፡ ንግግሩና ሀሳቡ፣ ከዕድሜው ጋር አልሄድ ያላቸው ከማንደር ግዲ አብዶ፤ “ከአጠገቤ ዞር ሲል ይህ ልጅ እንዴት ነው የሚያስበው?” እያልኩ እደነቅ ነበር፡፡ “የሀገራችንን ችግር በምንድን ነው የምንቀይረው? እያለ” ይወተውተኛል፡፡ “ትግላችን ለውጥ ያመጣል” እለው ነበር፡፡” ሲሉ ብዙ ነገር አጫውተውኛል፡፡ ታዲያ ከልጅነት ታሪካቸው ጀምሮ ሳያቸው፣ ሰውየው ብዙ ሰው ናቸው፡፡ ብዙ ታላላቅ ሰዎችን ይመስላሉ፡፡”
ኮማንደሩ እንደነገሩኝ ድህና ችግረኛ ሲያዩ፣ ፊታቸው በርህራሄ ይገለባበጣል፡፡ ካደጉም በኋላ ሞባይላቸውን ከኪሳቸው መዥርጠው፣ ሲም ካርዳቸው ብቻ ሲቀር ለሰው የሰጡበት ለጋስነት አላቸው፡፡ ለጊዜው በዚህ ጉዳይ ላይ ለብቻ የምፅፋቸው እማኞች ስላሉኝ አልነካቸውም፡፡
ግን እዚህ ጋ ሌዎ ኤን ቶልስቶይን ይመስላሉ። ልብሱን አውልቆ፣ ለደሀ የሚሰጠው፣ የተራቡትን ሰብስቦ ያበላ የነበረው ቶልስቶይ፤ የዚህ ዓይነት ባህርይ ነበረው፡፡ በረሀብ ዘመን ብዙዎችን አብልቷል፣ የህፃናት ትምህርት ቤት ከፍቶ፣ ልጆች እንዲማሩ አድርጓል፡፡ ሀብት የነበረው ሰውዬ ያለ ሀብት ሞቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶክተር ዐቢይ፤ ርህራሄያቸው ከቶልስቶይ የሚለይ አይደለም። ኪሳቸውን ዘቅዝቀው ለቸገረው እንደሚሰጡ የቀደመው ታሪካቸው ይናገራል፡፡ ብዙዎቻችን እንደምናውቀው፤ የሁለት መጻሕፍት ደራሲም ናቸው፡፡ ስለዚህ ይህ ለሱነት ከየት መጣ? አንልም፡፡ ከብዕር ጋር የሚወለድ፣ የጥበበኛ መገለጫም ነውና!
ሰውየው ሊንከንን የመሰሉኝ በአረንጓዴ ቀለም ተነክራ፣ ደረቷ ላይ አረንጓዴ ቀለም ያፈሰሰችውን የትውልድ ሰፈራቸውን ሳይ ነው፡፡ ለምን እንደሆነ ሳላውቀው፣ እጅግ እጅግ ተወዳጁ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በዐይኔ መጣ፡፡ በዋዛ አልነበረም፡፡ ይልቅስ አርሶ አደር ቤተሰቦቹን አስቤ እንጂ፡፡
ሊንከን እናቱ በዘጠኝ ዓመት ብትሞትም፣ የእንጀራ እናቱ ግን ከእናት የማትተናነስ፣ ምናልባትም የምትልቅ ስለሆነች ፍቅሯ ልዩ ነበር። ሊንከንም ሲወዳት የዚያኑ ያህል ነው፡፡ ሊንከን እንደ ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ በሰፈሩ የተወደደ ታማኝ ነው፡፡ የሰው ሀብት አይፈልግም፡፡ ለድሆች ይራራል፡፡ እንዲያውም የጥብቅና ስራ በሰራባቸው ጊዜያት፣ ለብዙዎቹ ጥብቅና የቆመበትን ገንዘብ ሁሉ በምህረት ትቶላቸዋል፡፡ ያ ብቻ አይደለም፡፡ የራሱን ገንዘብ ሰጥቶ የተጣሉትን አስታርቋል፡፡
ይበልጥ የሚመሳሰለው የህይወታቸው ክፍል፣ ሊንከን ፕሬዚዳንት በነበረ ጊዜ ያደረገው ነው። ሊንከን ለምርጫ ሲወዳደር፣ ስታንተን ከፍ ዝቅ አድርጎ ሰድቦታል፡፡ ለፕሬዚዳንትነትም እንደማይበቃ፣ በአደባባይ፣ በዘለፋ አቃልሎታል። የሚገርመው ግን ሊንከን ስልጣን ሲይዝ፣ ያንን ሰው ስልጣን ሰጥቶታል፡፡ ብዙዎች “እንዴት ይህንን ታደርጋለህ?” ሲሉት፤ “ለአሜሪካ ያስፈልጋታል!” በማለት የይቅርታውን ልክ አሳይቷል፡፡
ዶክተር ዐቢይ አህመድም የዚህ ተመሳሳይ ዕጣ ደርሶበታል፡፡ የቀለም አብዮት ጠንሳሽ፣ አሳዳሚ፣ የስልጣን ጥመኛ አድርገው ከመመረጡ በፊት ጥቀርሻ የቀቡትን ሰዎች መልሶ ተቀብሎ አይተናል። ይህ የትልቅነትና የእውነተኛ መሪ ትልቁ ችሎታ ነው።
ሊንከን በይቅርታው ይታወቃል፡፡ ስለዚህም አምስት መቶ ሺህ ያህል ሕዝብ ባለቀበት ጦርነት አዛዥ የነበረውን ሮበርት ሊን ይቅር ብሎታል። ከእርሱ ጋር የነበሩትን አዛዦችና ተዋጊዎች “አንበቀልም፣ ዳግም በሀገራችን ደም መፍሰስ የለበትም” በማለት በይቅርታ እንዲታለፍ አድርጓል።
ህይወትን ቀለል በማድረግና ባለማካበድ ይመሳሰላሉ፡፡ ሊንከን አኗኗሩ ቀላል ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ሰው እኩል የማየት ጥሩ ጠባይ ነበረው። ለዚህም ማሳያው ከመሞቱ አንድ ቀን በፊት ናንሲ ቡኾሮድ የተባለች ባሪያ፣ የነፃነት ህጉ ነፃ ያወጣት፣ ቤተ መንግስቱ ድረስ መጥታ፣ በሚገባ አናግሯትና መክሯት ሸኝቷታል፡፡ የኛው ዶክተር ዐቢይም በወህኒ ቤት ተጥሎ፣ በሞት ጨለማ ውስጥ የነበረውን የፖለቲካ ታጋይ አንዳርጋቸው ፅጌን ቤተ መንግስት ድረስ አስገብቶ፣ እኩል አውግቶ፣ ሀሳቡን አድምጦ ሸኝቶታል፡፡
አንድ ሌላ ነገር ልጨምር፤ ያልተለመደና ዶክተር ዐቢይ እያደረጉ ያሉት ነገር ነው፡፡ ይኼም የሊንከንን ይመስላል፡፡ ሳዑዲ አረቢያ ሄደው የአንዲት ተራ ኢትዮያዊት እናት ሀዘን ተጋርተውና ተሟግተው መጥተዋል፡፡ ውጤቱንም ሰምተነዋል። በባዕድ አገር በእስር ቤት የሚማቅቁ ወገኖችን ፍለጋ ባህር አቋርጠው፣ “ፍቱልን!” ብለው፣ የሙሴን ሥራ ሰርተዋል፡፡ እንደ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ላሉ፣ ለሀገር ውስጥ ደራሲያን ዕውቀት ሰጥተው፣ ጠቅሰው፣ አክብሮታቸውን አሳይተዋል፡፡ ሊንከንም፣ በጦርነቱ ልጆቻቸው ለሞቱት እንደ እነ ሚስ ቢክስባይን ለመሳሰሉ አሜሪካውያን፣ በግል ደብዳቤ ፅፎ፣ አድናቆት በመስጠትና አክብሮቱን በመግለፅ ወገንተኝነቱን አሳይቷል፡፡ አስቡት… የእኛ ዐቢይ ግን ይህንን ሁሉ ያደረገው ገና ሥልጣን በያዙ በሁለት ወራቸው ነው፡፡
ምናልባት የገጣሚአሌክስ አብረሃም ምኞት ሰምሮለት ይሆን? እላለሁ፡፡ ግጥሙን እዩልኝማ፡-
የሕፃናት ሳቅ በደጃችን ይድመቅ፣
ያዋቂዎች እረፍት በሰላም ይመረቅ፣
ከእስረኞች አንጓ ካቴናቸው ይውለቅ፣
የመለያየት ግንብ - በፍቅር መብረቅህ
ተንኮታኩቶ ይውደቅ!!
ጎዳናዎቻችን ሞት ሞት አይሽተቱ፣
ወጣቶች አሻግረው ነገን ይመልከቱ፣
ቤታችን ይጎዝጎዝ ተስፋ እንደቄጠማ፣
ለተራብን እህል ውሃ ለተጠማ …
በሰፊው ይከፈት የመሪዎች ጆሮ፣
ሕዝብ ድምፁ ይሰማ - ያመፃን መቃብር
የአመፃን ትቢያ በፅናት ቆፍሮ!
ብሶት ሰለቸና
ምሬት መረረና
በማያልቅ ውቅያኖስ የማያልቅ ዋና
መዳከር ይብቃና …
ግጥሙን ተመልክተን፣ አሁን ያለውን ሁኔታ ስናይ፣ ህልሙ እውን እየሆነ ነው፡፡ እንዳልሟዘዝ ብዬ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከማህተማ ጋንዲ ጋር የሚመሳሰሉበት ነገር እልፍ ነው፡፡ ከገጣሚው ፈላስፋውና ደራሲው ሄነሪ ዴቪድ ቶሮው ጋር ተመሳሳይነታቸው እጅግ ብዙ ነው-በተለይ ሀሳብ አመንጪነታቸው፣ ለውጥ ፈላጊነታቸው… ህይወትን ቀለል አድርገው ማየትና ለትውልድ መጨነቃቸው።
ናፖሊዮንን መምሰላቸውን በሌላ ሰፋ ባለ ጽሑፍ ላይ እመጣበታለሁ፡፡ ግን ደግሞ ገና በልጅነት ወታደራዊ ስልጠናና ህይወት ውስጥ ማለፋቸው ያመሳስላቸዋል፡፡ እንገነጠላለን ብለው ከሚዋጉ እናትና አባታቸው መሀል ወጥተው፣ የሀገር መሪ መሆናቸው በእጅጉ አንድ ያደርጋቸዋል- ከናፖሊዮን ጋር፡፡ የእኛው ዶክተር ዐቢይም “ኦሮሞ መገንጠል ይፈልጋል!” ሲባል፣ የኢትዮጵያዊነትን ድምፅ ከዚያው ህዝብ ይዘው ወጥተው፣ የኢትዮጵያችን መሪ የሆኑት እንደ መፅሐፉ፤ “ከናዝሬት መልካም ነገር!” ተብሎ ሲታሰብ ነው፡፡ ይኸው የዜማ ጊዜ ደርሶ የሚወድደንና የሚያስብልንን መሪ አገኘን፡፡ አድማሳት ዘምሩ፣ ተራሮች እልል በሉ!

Read 1797 times