Sunday, 03 June 2018 00:00

የመተርጐም ገጽታዎች፡- ንባብ፣ አንድምታ፣ ሒስ፣ አርትዖት

Written by  ደገፍ ግደይ
Rate this item
(3 votes)

 ጥበብን ያየህ ወዲህ በለኝ!
“አይቴ ብሔራ ለጥበብ ወአይቴ ማኅደራ? አይቴ ደወላ ወበአይቴ ተረክበ አሠረ ፍኖታ?” (የጥበብ አገርዋ ወዴት ነው?
ማደርያዋስ? ዓጸድዋ ወዴት፡ ዱካዋስ የት ተገኘ?) እንዲህ ይላል ቅዳሴው። “ጐንጅ ነው በለው” አሉ አሉ አንድ አርፋጅ አባት። ሊቅም ነበሩ፤ የታበዩ መሰለባቸው እንጂ። ቅዳሴው ግን፡- “ሟች (መዋቲ) ሰው ባሕሪዋን አይመረምራትም፡ በመመርመርም ከሰው ዘንድ አትገኝ…” እያለ ቀጠለ። ሔኖክም በበኩሉ፤ ‘ጥበብ ኢረከበት መካነ ኃበ ትኃድር’ ሲል መንከራተቷን አስተዋለ።
ያኔ፤ ከዚህ ከኛው ዘንድ እንዲህ ሲቀደስ፣ ሲወደስ፣ ትንሽ ራቅ ብሎ ካለው መንደር፣ ይባሌ ተነሣ። እኔ ባይ ባደባባይ፣ ከነባሩ ያገር ልማድ አፈነገጠ፤ ከተጨባጩ  ፈጠጤ የታሰበውና የታለመው በለጠበት፤ ከቁጥቡ ለስዱ አደላ። አንዴ ሲቆዝም፡ አንዴ የሆዱን እስካንቀሩ ሲዘፍን፣ ቃናና አኳዃኑ ፍንደቃና ድበታ ተፈራረቁበት። ዓለመኛው ሰው ለፍቅርና ለሥን ዓዲስ መዝሙር ይዞ ብቅ አለ። ስሜቱን የሰውነቱ አዛዥ ናዛዥ አድርጎ ሾመናም፣ ፈጣሪን ይመስል በፈጣሪኛ ይጣራል፡- “ግጥም ሆይ፤ ወዴት ነሽ? ከቤት ነሽን፣ ከዜማው ልክ? ወይስ ከተባለው ጉዳይ ትገኚ?” ታፋልገው ያጫትን ሴት ነቀርሳ  ነጠቀው፤ ሞተች። እሱም (‘ማሕሌታተ ሌሊት’ ሲል) ሙሾዉን ደርድሮ ዓረፈው።
“ቅኔ ሆይ፤ ወዴት ነሽ? ተለክቶ፣ ተመጥኖ ከሰመረው ዜማን? ተሳክቶ፣ ተሰናኝቶ ግጥም ካለው ቤት? ወይስ ከተጣቀሰው ታሪክና ከተመሰጠረው ፍሬ ነገር?” ተሜም ባንጃው! እንዲህ ባዛኚቷ እየተማጠነ ውዱን ሲፈላልጋት፣ እናቱ ልጇ ተምሮ መመለሱን ስትጠብቅ… እሱ ከማኸል ይሞታል። አሁን እዚህ ቁጭ ብለን፣ ለንዲያዉ፣ ለወዲያዉ፣ “ውዱን አግኝቷት በነበር!” እንላለን። ውስጥ ውስጡን ግን፣ በየቦታው፣ በየጊዜው በሚቀጨው ሻይ ሰበብ፣ ለሠቀቀን ሲሳይ መሆን ነው። ሰው መሆን ይቃኘናል፤ይነዝረናል። መኳተን፣ መማሰን-- እንዴት ነው ሰው መሆን?
[…] እስቲ እሱስ ለምን ነው
ለሞተ ሙጫ ዕድሜ
ጤና ለታመመ
ጢኖ እንኳ ላመሉ እስካይለመነን            
እዚህ እንዲህ አሁን  መኳተን፣ መማሰን?
ሰው አባት፡ ሰው ልጁ፡
እንዴት ነው ሰው መሆን? […]
አሁን በቀደም ለት የሆነስ ሆነና፣ የታጣው ታጣና፣ ይኸው ጽዋ ለንግዲሁም እንዳይቀር ሆዳችን ሲያውቅ፣ ዛሬም፣ ‘የግጥም ምንነቱ ምኑ ላይ ነው?’ እንደተባለ ይቀጥላል።  ድንቅ እንጂ ነው ‘ሻ’ ይሉት አማርኛ። ይሁነኝ ብሎ ለዚህ ዘዬ ዓድሮ የኖረ ሰው- ዘሩ ይብዛ!- ያሳዝናል፤ ያስቀናል። ዕዝራ ዓብደላም የዛ ሰው ነበርና - ነበር እንዲህ ቅርብ ኑሯል? አሉ፡፡ ፀሓይቱ የሰው እምር - አገሩ፣ ዘመኑ በፈቀደ ላይ፣ ታች ብሏል። ይመስገነው! አስታዋሽ የጥበብ ወዳጅ ያድለው፤ ያብዛለት።
ውሎው ካነሣሣናቸው ሰዎች ዘንድ፣ ቁጥሩም ከነሱው የነበረው ዕዝራ፣ “ግጥም ሆይ፤ ምትሃትህ ከምን?” ሲል ሰነበተ።
“ከጭብጥህ? ከስንኝህ አደራደር? ወይስ ከምርጡ ቋንቋህ?” ነገር ግን፣‘እቅጩን አገኘዅ፣ ወዲህ ነው!’ ብሎ ሲጮህ አልተሰማም፤ እዛም፣ እዚህም ባያጣው። ሕይወት ሞትን ትሽር ዘንድ መሰል ጥያቄዎችን ዓብሮን የሚጠይቅ ባለ ሳምንት ያስነሣልን-- ለኛ ለሰንባቾች ነን ባዮቹ!

ጠብም ሲገጥም ነው!
አንድም-ትርጕም
ዕዝራ ዓብደላ ‘አንድም’ እያለ ሲያነብ ነበር። የአንድምታ ጥበብ ስሙ ሲነሣ ሃይማኖት ነክ መጻሕፍትን ያግተለትላል።
አንድምታ የሠለጠነበት አገር ቤተ እምነት ሁኖ፣ አገልጋዮቹ  ምሁራን፣ ዓይናማዎች፣ ጠንቃቆች ናቸው። እንዲያም ሁኖና ተብሎም፣ ቃሉ፣ ውሎውና ግዛቱ፣ ፈቃደ ሥልጣኑ ቢሰፋለት አይጐዳውም። አልጐዳውምም፣ ባለማዊው ዓብደላ አፍ መዋሉ፣ ያንድምታ ነገሩ፣ ሥረ ነገሩ መተርጐም ነውና።
መተርጐም ካንዱ ልሳን ወደ ሌላው መመለስ ብቻም አይደለም፤ የዜማ ይትበሃልም፣ የጭፈራም፣ የትወናም እንዲሁ
ነውና። ሰው በጁ የያዘውን፣ መዋያዉን በተገነዘበው መጠን ፍቺ ሲያገኝለት፣ ሲያወጣለት ማለት ነው። ነገሩን ክፉኛ ተርትረነው ድፍን ሓቅ ሁኖ እንዳይቀር፣ ሄደን ሄደንም፣ መመለሻውም የሱን ያህል ይርቃልና በከንቱ እንዳንደክም እንጂ፡፡ራሱ መኖርም’ኮ ከዚሁ ከመተርጐም በገባ።  እርግጥ፣ እዚህ በያዝነው ውይይት፣ ጉዳዩ በቋንቋዎች ይከናወናል። እነሱም ቢበልጡ እንጂ ከሦስት አያንሱም፡-  ምንባቡ የተገኘበት እናት ቋንቋ፣ የመረዳት የአእምሮም የልብም ልዩ ቋንቋ  እና የገባንን የምናሰፍርበቱ።

ሰዋስው፡ አገባብ፡ ቃላት
ይኸው ቋንቋ፡ ባመዛኙ ቃላትን እየመረጡ ማሰናሰል ነው፤ በዚያም ሓሳብን ማደራጀት። እዚህ ላይ መግቢያም፡ መሰናዘሪያም የምትሆነንን ስለ ቃላቱ ትንሽ ልበል። ጭብጥ ቅጽሎችን (የስም ምትኮቹ ይህ፡ ይኸ፡ እሊህ፡ እለዚህ፡ ያ) ለጊዜው ላቈይና፡  አገባቦችን (ወደ፡ በ፡ ለ፡ እስከ፡ እና፡ እንደ፡  ወቦ ዘ…) ላውሣ። ከቋንቋ ቃላት በቍጥር የሚታወቁና በጣም ጥቂቶቹ  እነሱው ናቸው፤ ከዚህ  ከማያያዝ (ማሳካት) ሙያቸው ባሻገር ምስጢር አያቍሩ፡ አያቍቱ፤ ከራሳቸው መጠራት ዓልፈው  ምንም ነገር አይሉም። ማለትን አስቻዮቹ ግን እነሱ ናቸው።
የተቀሩት ቃላት በስምና በግብር ረገድ ቢወገኑም፡ በጥቅል ሲታሰቡ መጠሪያ ናቸው፤ ግዙፉንና ረቂቁን ነገር፡ ድርጊቱንና
አደራረጉን፡ ዓይነቱ፡ ሁነቱን፡ ኑረቱና ንብረቱን ወዘተ፡ እንጠራባቸዋለን። አንድ ላንድ ቢሆንማ የተጸውዖ ስም ብቻ በኖረን። በዚሁና በወዲያኛው ዓለም ያሉት ነገሮች መብዛታቸው፡ የሌለን ነገር ለመፍጠር ከመትጋታችን ተባብሮ፡ በጥቂት ቃላት እልፍ ነገር ማለት ተቻለ፤ ከይህ በፊት የነበሩ፡ ዛሬ ያሉ፡ ለንግዲሁ የሚፈጠሩ ስፍር ቍጥር የሌላቸው ቃላትን በጥቂት ፊደላት (በ30ሳ ገደማ ብቻ) መጻፍ እንዲቻል… ምስጋናው ለጠቢባን፡ በረከቱ ለኛ!

ትርጕም፡ ንባብ፡ ሒስ
ብትን ቃላት ዓርፈውም፣ ተዛርፈውም፣ አረፍተ ነገር ፈጥረውም ከዓቅማቸው የሚትረፈረፍ ምስጢር አለ፤ ፍቺ/ ትርጉም ከቃሉ ይሞላል። የሚባለው ከሚነገረው (ተጽፎ ከሚነበበው) ይበዛልና፣ ይልቃልናም፣ ፍቺን ፈልፍሎ ማውጣት ይገባል። በመልካም ትርጉም/ትርጓሜ ይለቀማል፤ ይታፈሳል። ፊት ለፊት የሚታየው ገጸ ንባብ ወትሮም ጠቋሚ ነው፤ ስለ ሆነም፣ ወደ ተመራው መዝለቅ ያሻል። ያም ብልሓት አለው፤ ፍቺው ከምንባቡ ይወጣል፤ አስረጅ የሚገኝለት መሆንም አለበት። አለ ልኩ፡ አለ መልኩ ለምንባቡ ፍቺ አይሰጥም፤ ምስክር ቆጥሮ፣ መርቻ ጐዝጉዞ ነው። ተርጓሚ፤ አእምሮዉን መረን አይለቅም። ከቀለሙም ሳይጥሉ መንፈሱን መያዝ አለ። ቃል ከመንፈስ የሚያጣባ ሚዛን ባለቤት መሆን ግድ ነው።
ጥልቁ የትርጉም ሙያ፣ በቋንቋ ላይ ሌላም ችሎት ይጨምራል። ዋናው፣ ተዛማጅ ምንባቦችን ያቀፈ ሰፊ ዕውቀት ነው፤ በእጅ ያለውን ምንባብ ከነሱ (ከቅርብና ከሩቆቹ) ጋራ ያገናዝባል። የምስጢር ፍንጣቂ፣ ክፋይ፣ ሥንጣሪ እዛም እዛም ነውና፤ ማገናዘቡ ሞላ፣ ሰፋ ያለ ትርጉም ያስገኝ ዘንድ ተዟዙሮ መልቀም፣ አዙሮ አዟዙሮ መመልከት ከሙያው ባሕርይ ይቈጠራል።
ይህም ጥበብ  የደራ ውይይት እንዲካሄድ ያስቻለ ስምና መስም ወጥቶለት፣ መማሩ፣ መመራመሩ ተደራጅቷል፡- ሒስ (ምን ይላል? እንዴት ይለዋል? ምን ስሜትስ ያሠኛል?)፣ ዲበ ሒስ (የምን ምልክት ነው? ከምን ጋራ ተዛምዶ ምንን ይጠቁማል? ርባናና ፋይዳውስ?)፣ ምሁራዊ ምርምር (ምንባቡ በቦታው፣ በዘመኑ፣ በጥበባትና ሥልጣኔው ዓውድ አለና፣ ቃላቱና ሓረጋቱ በዛ በበቀለበት ዓለም/ ለምንባቡ አፋአዊ ከባቢ በሆነው/ ምን ያሰኙ ይሆን? ምንስ ያሰኙ ነበር? ሥራዎችን ከተአምር ይልቅ ከሚፈታ እንቆቅልሽ ቆጥሮ መመርመር፤ ብዙ ዕራፊ በባለሙያ ስውር ስፌት ዓርበ ወጥ ሸማ መስሎ ቢበጅም፣ እያንዳንዱ ያዋጣ ምንጭን ለማግኘት መጣር ወዘተ። ለሃይማኖት መጻሕፍት የሚጻፈው መቅድም ከዚህ ይገባል፣ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው)… ይህን ጉዳይ ዳኛቸው ወርቁ ደኅና አርጎ ያብራራዋል።  
እየበለቱ፣ እየተነተኑ  መማርና መመራመር እንዲህ ከደረጀ፣ የተበጀ፣ የተሰናዳ ሥራን ማጣጣሙስ? ምስጢር ከጣዕመ ነገር
መፋተቱስ? ያ ሌላ፣ ይህ ሌላ ከሆነ፣ ሒስ አጣማጁን ዓጥቶ ቀንጃውን ይቆማል ወይ? ይዘልቃልስ? ዝቅ ብዬ እመለስበታለዅ።
*   *   *
ትርጉምና ቅኔ
ማገናዘቡ፣ ማዟዟሩ፣ መፈልፈሉ፣ ማጠናቀሩ እንዲሰምር ቅጥና አቅጣጫ ከሚያስይዙት ሰዎች አንዱና ትልቁ  ደጋፊ ዓጅሬ ጠያቂ ነው፡-  አቶው በመተርጉሙ (በተርጓሚው) ኅሊና ተፈጥሮ፣ እሱኑ በዓይነ ኅሊና ይሞግተዋል። ይህ ጠያቂ፣ ጥያቄዎቹ ካመራመሩ፣ ሞገቱ ጥብቅ ከሆነ፣ ዳሰሳው ይሰፋል፣ ትርጉም ይበረክታል፤ እሱ በጠነከረ፣ በረቀቀ መጠንም የትርጉም ሥራው ውጤት ያምራል። ግልጹን መመልከት፤ ገራገር ጥያቄን ችላ አለማለት፤ ጠንቃቃ አእምሮ የሚፈነቅላቸውንም ጐርጉሮ ደርሶባቸው ለነሱም መልስ መስጠት፤ በተያዘው ጉዳይ ሌሎች ከሚሉት ሳይጠቅስ መለየቱን ማስተዋል (‘ሲለይ’ ይሏል)… እንዲህና መሰል ገጽታ አለው - የአንድምታ ጥበብ።
ለቅምሻ ያክል ከመዝሙረ ዳዊት ያንዲት ቁጥር ዓጭር ሓተታ  እዚህ ላቅርብና  የበለጠ ማሳያ ይሆን እንደዅ ደሞ  እስቲ
ከሥርጌ  የአንድ ሁለት ገጸ ንባቦችን አንድምታ በከፊል ላኑር።
**[…] ወኮንኩ ከመ ዓድገ መረብ ዘገዳም[…]ዳዊት(101:6)
## በበረሃ እንዳለ  የበዳ አህያ ሆንኵ። ይህ የበዳ አህያ ቈርበተ ሥሥ ነው። አራዊት ዅሉ ይጣሉታል። ቀን ከቦታው አይወጣም፡ ሌሊት ከተራራ ላይ ወጥቶ  ፊቱን ወደ ነፋስ መልሶ  አፉን ክፍት ክድን፡ ክፍት ክድን ያደርገዋል፡ ‘ሓለስትዮታት ይቀውሙ ማእከለ አድባር ወያበቅዉ አንፎሙ መንገለ ነፋስ’  እንዲል። መልአኩ የሣር፡ የውኃ መዓዛ አምጥቶ ያሸተዋል። የሦስት ቀን መንገድ ሂዶ ሣሩን በልቶ፡ ውኃዉን ጠጥቶ ተሓዋስያን ከቦታቸው ሳይወጡ፡ ዕለቱን ከቦታው ገብቶ ያድራል።
ይህ የተመረጠው ሐተታ፣ የመላሽና የተርጓሚ (ያንድምተኛ) ሙያ እየቅል ቢሆኑ እንኳ፣ የጥልቁ ጥበብ ምስጢር ትርጓሜው  
ላይ  መገኘቱን እግረ መንገዱን ይጠቁመናል።                                               
ባለቅኔም (ግጥም ገጣሚም) ሲመስል ያንድምተኛው ቢጤ ነው፤ ያን ከይህ አገናኝቶ ግጥሙን ለማሰናዳት የዛው ያህል
ዕውቀት ያሻል።
 (ሀ)-- ዘምቶ የሞተ ሰው ያዝንለት አያጣ
አሞራ እንኳ ወርዶ ፊቱን ነጭቶ ወጣ።   
ከለቅሶ ያልዋለ፣ የቋንቋውን ሰዋስው ያልጠነቀቀ፣ የዘማች አሞራን ባሕርይ የማያውቅ እንዲህ አይቀኝም።
 (ሁ)-- እዃላ ቀሪ እንደ ሽሩባ
 ፊት ፊት ቀዳሚ እንዳዳል ዱባ
 እዃላ ሲሉት ይገኛል ከፊት
 በጐን ገቢ እንደ ሸረሪት…
ከሰው መልክ፣ ከተክል ጠባይ፣ ከረቂቋ ተሓዋሲት ባሕርይ አመሳስሎ፣ በ’እንደ’ አጣቃሽነት ሙያውን በሦስት ስንኝ ሣለው።
(ሂ) እዩልኝ፤ ስሙልኝ ይኸን ነገር መውደድ፡
ዓባይ ከጣና ዘንድ ይለምናል ምንገድ።
ዓይናማው፣ አስተዋዩ ገጣሚ፣ የሰውን ባሕርይ ከግኡዙ ወንዝም ላይ አገኘው፤ ይኸውም ባካልም ሆነ፣ በመንፈስም ሆነ በቅርቡ ከሚኖር።
(ሃ) ስጡኝ አንድ እንጀራ ውሻ የለከፈው፤
በምን ዓይኔ አይቼ እንዳልጠየፈው።
ከሰው በታች መሆንን የመሰለው፣ አገር ከርኩሰ ርኩስ የሚቆጥረውን ባለመጠየፍ ነው። ባለቅኔው ላንዱ ሕዝብ ነውሩ የሆነው ለሌላው ጌጡ ሊሆን መቻሉን ተገንዝቦ ተገቢውን ምሳሌ መምረጥ ያውቅበታል።
(ሄ)ሕይወት
[…]የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ
 ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ
ማን ያውቃል ?[…]
ይህ ስንኝ መንግሥቱ ለማ ሕይወትን እያስተዋሉ የተከዙበት ግጥም ላይ ይገኛል። ባሕረ ሓሳብ የክስተቶችን፡ የሁነተ ዓለምን ተባርዮ ለመገንዘብ የፈጠርነው መቁጠሪያ፣ መነጋገርያ ነው፤ ይህኑን የማይስቱት ገጣሚ፣ ዃኙ ግጥምጥሞሽ ላይ አተኰሩ። መልስ አግኝተንለት ሳይሆን፣ ባለመጠየቅ ተላምደን የምንኖረውን ነገር ልብ አስባሉን፤ ልባችን በለጸገ። ሁነት፣ እነት፣ ኡነት፣ ዕውቀት ምንና ምን ናቸው? ምስጢሩስ ምን?
(ህ)[…]ንፋሱን ጠይቂው ያስረዳሽ አብራርቶ
የልቤን አድምጧል ስተነፍስ ገብቶ[…]
ይላል አባት ዘፋኛ ማሕሙድ አሕመድ።
ጥራጥሬው፣ ረቂቁም አካሄዳቸው ጐን ለጐን ነው፤ ይደማመጣሉ። ‘ይዋሰኛ፡’ ሲል፣ ‘ሆድዬን ያማልደኝ ዘንድ የሆዴን፣ የልቤን የሚያውቅልኝን ነፋስን ልማጠን’ አላ! በሱው፣ ባንዱ መንገድ በሚመላለሰው ቃል።
(ሆ)በማጀትሽ ጸጋ፡ ችጋር ባንደበትሽ
አንቺ አገር ምናባሽ፡ የታባሽ፡
ግራ እንዳጋባሺኝ፡ አንቺም ግራ ገባሽ!
‘አይህ ላይ ነው ያለን!’ ስንል ነው። የወጉን አደረስን፤ አንድ ሙሉ ቤት ምሳሌ ይኸውና።
*   *   *
ትርጉም፡ ሒስ፡ ማገናዘብ --የእግረ መንገድ ረብ
አንድምተኛውና ባለቅኔው (ይኸዉ ተቺም) ያንድ ዓለም ሰዎች ከሆኑ፣ የሚቀዱበት ምንጭ ጐን ለጐን ይገኛል፤ የሚዝቁት ከተጣጋ ጐተራ (መዝገብ) ነው። ይህ ሁኔታ መናበብን ያስችላል፤ ይፈቅዳል።
ዓብደላ አንዱን ግጥም ሲመረምር፣ ለውብሸት ታደለ “የቀን ሠራተኛ” ማንጸሪያ፣ የኤፍሬም ሥዩምን ግጥም ምስክር ቢቆጥር፣ የዮሐንስ አድማሱን ‘የደንገጐዋ ቆቱ’ ቢጠራ፣ ሌላንም ቢጠቅስ፣ ቦታ ለመያዝ ማንፈራጠጥ አይደለም።  
ሐያሲው አንዱ ግጥም ካንድ ትልቅ የግጥም ጉባኤ (ገበታ) እንደ ወጣ ያውቃል፤ ነጠላ ግጥሞች ጥንትኑ አንድ ለሆነው መጽሓፍ ክፍሎቹ፣ ምዕራፎቹ ናቸው። የንባብ ሠረገላ ደንቡ ነው። የደራሲና ያንባቢም ጥበባቸው እምብዛም አይራራቅ፤ ለመድረሱም ለማንበቡም ሥንቅ ቋጥሮ ነዋ፤ እያስታወሱ ነው። ድንግልና የት ተገኝቶ!
ታዲያ.፣ የድርሰት መዛመድ መገለጫው ብዙ ነው። ብዛት፣ በጨዋ መንገድ ይከናወናል፤ ባይን ጥቅሻ፣ በከንፈር ንክሻ ያደገ ሰው ነጥቆ፣ ዘግኖ መሞጀርን አይከጅልም። የግዳስ፤ ጠቆም፣ ሰንዘር ተደርጎ በተተወው ሽንቁር የንባብ ሠረገላ ይሸጐጣል፤ ማስተጋባቱ ይሰማል። አንዳንዶች ግን ገልብጠው ይሰገስጉታል። የራሳቸው ችሎታ ኪገልጠው  የሌላው ደራሲ ችሎታ ቢገልጠው ይጐላል ይላሉና።
ይህ ከያ ይጣቀሳል ብሎ ማለትስ ፋይዳው ምንድር ነው? ተጠቃሹ ንባብ ማተራጐሚያ ሲሆን፤ እንዲያም ተጠቃሹን ተንተርሶ ወደ ሌላ ምርምር መዝለቂያ ሲያውሉት ይጠቅማል። ደሞም ዓወቅሁህ፣ ለየሁህ ብለው ሰውኛ ሲደሰቱበት፣ የሚያውቁትን ሰው ሆነ አገር፣ ነገርም አይተው እንዲደሰቱ። እስቲ ዓብደላ በመረጣቸው አንዳንድ ስንኞች(ሀ- ለ-ሐ-መ) የምለውን ልበል።
ሀ)- […]ወዲያ ከወደ ወሊሶ
 አንድ ዓራስ ድምፅ ተፀንሶ
 እናት ልጅ ወለድኩ ብላ
  አንቀልባ ሙሉ ድምፅ ዓዝላ[…]-----
ለ) - […]የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ
 ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ
 ማን ያውቃል ?[…]
ሐ)- ድንገት ዞር ስትዪ፡ ዞር ብል በድንገት፡
 በዐይን ንጥቀት ፍጥነት
 የቆጠርናቸውም፡ ያልቆጠርናቸውም፡
 ትንሹ... ትልቁ፡
 ከዋክብቱ ሁሉ ተደበላለቁ፤
 ከንፈሮቻችን ላይ እሳት አፈለቁ።
 ከዚያ የሆነውን፡
 እኛም አላወቅን፣ እነሱም አልነቁ።
መ)- ክፉ ሰው ሞተ አሉ፣ ኑ እናልቅስ እንቅበር
 ደሞ ከደጐቹ፣ ክፉ እንዳይፈጠር
*   *   *
 ደሞ፤ ከሌሎች ጋራ ላያይዛቸው እስቲ…
ሀ)- […]ወዲያ ከወደ ወሊሶ
 አንድ ዓራስ ድምፅ ተፀንሶ
 እናት ልጅ ወለድኩ ብላ
  አንቀልባ ሙሉ ድምፅ ዓዝላ[…]-----
(ቅጡ እንጂ ሰዋስዉ አይሰድም፡- ‘ዓራስ’ የተወለደ ጨቅላ ነው፤ አይፀነስም!)
 ሁ) - እዚያ ላይ ያለች  ሸክላ ሠሪ፡
 ድሃ ናት አሉ ጦም ዓዳሪ።
 ማን አስተማራት ጥበቡን
ገል ዓፈር መሆኑን?
ሂ)--  ‘ዓይኔን ሰው ራበው፣ አረ ዓይኔን ሰው ራበው፡
የሰው ያለህ የሰው፣ የሰው ያለህ የሰው!’
ሃ)ቢጣራ አሉ ቀን ቢጨልም፡
ሰው በውኑ፣ ሰዉ በሕልም
እልፍ ራሱ ዘምቶ
አንድ ራሱን፡  አንዱው  ሙሉ፡
ራሱ መጣ፡ ራሱው ቅሉ!   
  (ሰው ጥራ ቢሉት ራሱ መጣ፣ ራሱ ቅሉ! ሰባት ራሱ ከተፍ አለ! እንዲል )  
ህ)-- <ጸደይ>  ------------(መስፍን ዓለማየዅ?)
ዕሰይ
ጸደይ ክረምቱን ሰብሮ ገባ
ትንፋሽ የዘመን ኬላን ዓለፈች
ተንፏቃ - አዝግማ - ጋልባ
ጠግባ ደግሞም ተርባ::
ዕሰይ
ጸደይ ክረምቱን ሰብሮ ሲገባ
የሕይወትም ዘሯ መልሶ ረባ፤
መቼም እርም ይሉ ነገር አያቅ
ተስፋም በየሰዉ ልብ ገባ::
(መስፍን ሀብተማርያም?)              
*   *   *
ለ) - […]የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ
 ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ
 ማን ያውቃል ?[…]
ሉ) - የለህም እንዳልል ይመሻል ይነጋል፤
 አለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል።
ያንተን ሥራ፡ ያንተን ግብር
ማን ይመራመር?
*   *   *
ሐ)- ድንገት ዞር ስትዪ፡ ዞር ብል በድንገት፡
 በዐይን ንጥቀት ፍጥነት
 የቆጠርናቸውም፡ ያልቆጠርናቸውም፡
 ትንሹ... ትልቁ፡
 ከዋክብቱ ሁሉ ተደበላለቁ፤
 ከንፈሮቻችን ላይ እሳት አፈለቁ።
 ከዚያ የሆነውን፡
 እኛም አላወቅን፡ እነሱም አልነቁ።
ሑ)- “በትንሽ ጐጆ
 ትንሽ ቈረንጮ ትነጠፍና…
እህ ዛዲያማ?—
እህ ዛዲያማ፡ ምን ልበላችዅ!
 ታውቁት የለም ወይ በየቤታችዅ?”
*   *   *
መ)- ክፉ ሰው ሞተ አሉ፣ ኑ እናልቅስ እንቅበር
 ደሞ ከደጐቹ፣ ክፉ እንዳይፈጠር
ሙ)- የገለባ ቤት ስሙ ደረባ
 ቀላምዴን በእሳት ዘሩ እንዳይረባ።
የወሊሶዋ ሴትዮ ሸክላ ሠሪዋን ብትጠራ፡ የዮፍታሔን እሪታ ብታሰማን ኖሮ ምን በጨመረልን? የመስፍንንስ  እንጆሃ! ዮሃና? ወፊትና አበባ የቀንና የሌሊት ተባርዮን፡ የጠፊና ያጥፊ ካንዱ ዓለም መገኘትን፡ ብስል ከጥሬነት ያስተባበረውን ሰውነት ቢያወሡልንስ ኖሮ? ያሁኑ ገጣሚ ‘ነገረ ፍትወትን ገላልጠው አይነግሩትም፣ የሆነውን ማን አስተውሎት?’ሲል፣ የቀደመውን ሌላው አዝማሪ፣ ‘ምን ተስኗችዅ’ ብሎ የተቀኘውን ቢያስታውሰንስ ኖሮ? ምን ባተረፍን? ‘በባህል ደምብ አፍን ጠመም አርጎ አንድ ጉንጭና ከንፈሮችን በመምጠጥ ያችን የምናቃትን ድምፅ’ አሰምቶ ዝም ይባል ኑሯል?
አይመስለኝም። ያለው  አገላለጻችን  ከየት ወዴት ደረሰ ባሰኘን እንጂ፤ ምናልባት መዲናን እንደ ገና ባሰብንበት፤ የጥሎ ማለፍ ጉዳይንም፤ ተባርዮ ባልንበት አፍ ያም፣ ያም የሚያስብል ዓብሮነትን፣ ገጸ ብዙነትንም እንደዚሁ። ደሞም መገረም ይሉትን  አማርኛ፣ በጥሬው፡ በደረቁ፤ ለምሳሌ፡- ሙሉውን ሰው አንዱን አካል ራስን (ቅሉን) ብቻ ባሳከልንበት ጥበብ (ከመስማት ብዛት ተላምደነው  ሓረጉ ኃይሉን ዓጥቶ እንጂ ባፍላ ዕድሜውማ ድንቅ ነበረ!)  ባለቅኔው ለጠቅ አርጎ ካካልም ባሕርዩን ብቻ (ድምፅን ብቻ) አሳክሎ ዓዲስ አብነት መፍጠሩ፤ ሦስት ቀን መንገድ፡ ሁለት ገበያ ሕዝብ፡ አንድ አገር ልጅ ብሎ በሰፈረው፣ ደሞም አንድ ቍና ውሸት፣ ስልቻ ሙሉ ተስፋ እንዲባል፣ ያሁኑ ገጣሚ ‘አንቀልባ ሙሉ ድምፅ…’ ብሎና የግዙፉን መስፈሪያ ለረቂቁ  ማዋሉ… (አዳራሽ ሙሉ ሣቅ-ትዕግሥት ማሞ)፤ የራስን አተያይ እንዲያ ኖሮ እንዲህ ሲሆን ማስተዋሉ፤ ሌላም፣ ሌላም። ከዅሉ፣ ከዅሉ ይልቅ ግን የራስን ጉዳይ በራስ ሰዋስው፣ እዝ ወዙን በምናውቀው፡ ማውጠንጠኑ!!!  
ሩቅ መንገድ አለሥንቅ ያውካዋል። በቅጡ ማጣቀስ ሥንቅን የማሰናዳት ያህል ነው። እንዲህ እንዲህ እያልንም ሐሳብ ባበጀን፣ ባደራጀን።  በዛ መንፈስ መጻፉ ይጠቅመናል።
ነገር ግን በብዙ ጽሑፎቻችን የሚስተዋለው ይህን አይመስልም። ግጥሙን  እንገነዘብበት፡ የቁም ነገሩ ማንጸሪያ ይሆኑን ዘንድ እንዲህ ዓይነቶቹ እሴቶች ከተፍ አይሉልንም፤ ከቅርብ አይገኙንልንም፣ ከልሳናችን አይውሉም። አላቅህ አታቀኝ፣ መች ቤተኛ ነን? ይሉን ይመስላል። ምሳሌ እሚፈለግ ለምንድር ነው?  ነገር የራስ ሁኖ ሳለ ጥጥር ካለ ያቀርብ፣ ያጐላልን፣ ይገልጽ፣ ያብራራልን እንደዅ ተብሎ ነው፡፡ የራስ ነገር  መጠጠሩ ላይ የማያውቁት ምሳሌ (የምሳሌው ምንጣፍ ትራስና የዳር ጉዝጓዝ ከተነሣበት አገር ነውና፣ አለና ) ታክሎበትማ…
ይህም ሲባል፡ ቢሱ ከደጉ ላይቃየጥ እንደ መጻሕፍት ቅዱሳን ተቆጥረው የተረከቧቸ፣ ተሰፍሮ  የተቋጠረ ሥንቅ አይምሰለን። ይልቅ፤ ያሹት የተለማመዱት ይትበሃል፣ እየታነጠ እየተነጠጠ የሚቀባበሉት ትውፊት፣ እየወቀሩ እያለዘቡ የሚያኖሩት ሥራት ነው፤ ሳፉ ፡ ንቡር ፡ ወግ፡  ወቦ ዘ  እያሉ ያቆዩታል።  እንግዲህ ልብ በሉ፤ ባናት ባናቱ ደሞ፣ የጣምና የምርጫ ነገር በየምናምኒቷ አፍታ ባገርም፣ በግልም ይካሄዳል። ያሬዶ፡ ኪዱ፡ መንጌ፡ ጸግሽ፡ ገብራይ፡ ሰይፉሻ፡  ሙሌ… ሲባል በስም በስሙ ለቤክ! ማለት አለ። አማናውን፣ ሓቁን ብድግ አርጎ መዝለቅ ነው። ያልተጠራነው እኛ ደሞ የፍቅራችን፣ የሰውነታችን ዓጀባና ዓንጀባ እናስከትል ይሆናል- ብቻ፣ ከመጣም ዘግይቶ ደራሽ አላህ ያርገው!
አንድምተኛ፡ ሓያሲ---ዓላማ
ታዲያ፤ አንድምተኛውም፣ ሓያሲውም አስፍተው ሲያስሱ ይመሳሰሉ እንጂ  የእምነት ነክ አንድምታና የዓለማዊው ሥነ ጥበብ ሒስ ዓላማው እየቅል ነው።  ያ በከፊሉ ሙሉዉን መረዳት ሲሻ (የአንድምታ ዓላማ አማኞችን ለመምከር፣ ለማጽናት አይደለም፤ ለምሳሌ፡- የፍጥረት ነገር ሲነሣ ፈጣሪን ያመሰጥራል)፡ ይህኛው ደሞ ሙሉውን ደጋፊ አርጎ በጁ የያዘው ከፊሉን በቅጡ ለመረዳት ይጥራል (አካል ብሎ ለመሆኛው፣ መከወኛው ቦታ፣ ለድርጊቱና ለሁኔታው ጊዜ ይፈልግለታል። አካሉን ታሪክ ብንለው፣ እያንዳንዱ ድርጊት  የሚገዝፍበት፣ የሚፈጸምበት ቦታ፣ ድርጊቶቹን የሚያያይዝ፣ የሚሰፋ ጊዜ ይሉት ረቂቅ ክር መመርመር ነው- መቼት። የምክንያትና የውጤት ጥምረት ሲባል መጎራበታቸው ሳይሆን አንዱ ቀድሞ ሌላዉን ወልዶ ማስከተሉ ነው)።
አንድምተኛ፡ ሓያሲ---ጥበብ
ያተረጓጐሙ ጥበብም አንዳንዴ ይለያያል። መነኩሴ ቆቡን ፈቶ መልሶ እንዲሰፋ፣ የእምነት ነክ አንድምታ ቀድሞ ያለውን ሽሮ በዓዲስ መንገድ ማስኬዱን አይፈራም። እንዲህ ሲመራመር፣ ውሉን ከሳተ፣ ከንቱነት ሃይማኖቱ ይታደገዋል፤ አረፍት ይሆነዋል።
ዓለማዊው የሥነ ጥበብ ሒስ በበኩሉ፣ እርግጡ ላይገኝ መፈጠም እስኪመስል፣ አፍርሶ መሥራቱን ሲደጋግም ይገኛል።  
ቅድም  የምርምሩ፣ የሙግቱ፣ የዳሰሳው ዓይነት ጠቅሰን፣ ያሞካሸነው የትርጉም መበራከትና ማማር፣ የናዳ ካብ ሁኖ እንዳይቀር ያሠጋል። ምንስ፣ ማንስ ይድረስለት? ደሞም፣ ገጣሚው እም ኃበ አልቦ እንዳይፈጥርና የሚዝቅበት የቃላት፣ የሓሳብ ጐተራ (ያገር፣ የጋራ መዝገብ) እንዳለው ቢታወቅም፣ ቁም ነገሩ ከኪነ ጥበቡ ነው፤ ከውጤቱ። የዛቀውን ዝቆ ምን አበጀበት? እንዴት እንዴት አርጎስ ነው ያበጀው? አንባቢው (ሓያሲው) ወደ ተዛቀበት ጐተራ (ያገር፣ የጋራ መዝገብ) ከዘለቀም፣ መመለሻው ቀልጣፋ ሁኖ፣ ይዞት የመጣውም ጓዝ ኪነ ጥበቡን፣ ስልቱን ይበልጥ የሚገልጽ፣ የሚያብራራ ሊሆን ይገባል፤ ‘ቤት አመታቱን፣ የስንኙን አሰካክ፣ የቃላቱን አመራረጥ፣ የግጥሙን አወራረድ፣ የስሜቱን አፈላለቅ፣ የሓሳቡን ርቀትና ጥልቀት አንድ ባንድ፣ ደሞም አንድነት አስተውሎ ያመዛዝን ዘንድ የሚረዳው’።
*   *   *
አንድም፡ አራትም--- መተርጎም፡ ባለቅኔ፡ ሒስ፡ አርትዖት
[በውጥን ወደተውነው  ንጽጽር  እንመለስና፣  አንድም ባዩ መተርጕም ከባለቅኔው ጋራ በቅርብ ይዛመዳሉ ብለናል።
ዳግመኛም፣ አንድም ሒስ ነው፣ ወዲህም አርትዖት። ከዚህ ላይ አንድም፣ አራትም  በሚያሰኝ ቅኝት ስለ አርትዖት ትንሽ  ጣልቃ እናስገባ። መተርጕማን አንድም ሲሉ፣ ሳት ብሎ ንባብ ይጐረብጣቸዋልና ነው። እንዲህ ሲገጥም፣ ቀድመው ይደለድላሉ፡- መጽሓፍ ምስጢርን እንጂ ሰዋስውን፣ አገባብን አይጠነቀቅም ብለው ያውጁና ንባብ ያቀናሉ። ካገባብ መጐርበጥ ልቆ ጠነን ያለ ንባብ ሲገጥምም የሚያለዝቡበትን፣ የተጣላ ገጸ ንባብ የሚያስታርቁበትን፣ ከምስጢር የሚያደርሳቸውን መንገድ ከሰፊው ዕውቀታቸው ያወጡታል።  ባለማዊው የሥነ ጽሑፍ ስምሪት፣ ደራሲ በፈጣሪ አምሳል፣ ድርሰቱ በፍጥረት፣ በሊቃውንቱ ንባብ የማቅናት ተግባር ደግሞ የአርትዖት ሙያ ተሰይመዋል። የኋለኞቹ ልዩነት፣ ያ በቅዱስ መንፈስ ተቃኝቶ ንባብን አቅንቶ መረዳት ሲሆን፣ ይህ የደራሲን ጥልቅ ሓሳብ ተገንዝቦ፣ በደራሲው መንፈስ እየተመሩ፣ አንድን ልቦለድ ድርሰት አቃንቶ ዳር ለማድረስ መትጋት ነው።
የድርሰት አርትዖት መርሕ በየመማርያው መጽሓፍ የምናገኘው ነው፡- የታሪኩን ጠገጎችና አንጓዎች የሚያሰናስለው ጭብጥን ምንነት፣ የገጸ ባሕርይን አሣሣልና አኳኳል፣ የሴራን አወቃቀር (ርብርብ ድርድሩን)፤ የዝርዝሮችን አመጣጠን፣ ያተራረክን ስልት፣ ያገላለጽን ጥበብ፣ ወቦ ዘ ያያል፤  አርትዖቱ ዓልፎ ዓልፎ በሚታይ እንከን ይከናወናል። ቢሆንም፣  የጐደለውን መምላት፣ ጠማማውን ማረቅ ብቻውን አይበቃም፤ አርትዖቱ የታሪኩን ፈትለ ሓሳብ፣ ወጥነቱን ከተፈታተነው፣ ጽሑፉ ጥቅምቃምና ጥርቅምቃም ሁኖ መነበብ ይሳነዋልና በደራሲው መንፈስ መቃኘት ያሻል።  ቡጫቂና ድሪቶ ዓይነቱን ጽሑፍ  ከደረሰ ግን፣  መንገዱ ተገቢ ይሆናል፤ ለጥበባዊ ፋይዳው ይሁነኝ ብሎ የፈጠረው ነውና፤ የደራሲው መንፈስ እሱው ነው።]    (ይቀጥላል)

Read 2125 times