Sunday, 03 June 2018 00:00

የቬኒሱ ነጋዴ (‘Shylock Is My Name’)

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

 ዊልያም ሼክስፒር በሕይወት ዘመኑ፤ የኑሮው ጠባይ፤ የአንድ ትርፍ አጋባሽ ካፒታሊስት ነጋዴ አይነት እንደነበር አሳማኝ ማስረጃ በማቅረብ በብርቱ የተቸው ታዋቂው ጋዜጠኛ ሀዋርድ ጃኮብሰን ፤ በመቀጠል ደግሞ በእንግሊዛዊው ጸሐፌ ተውኔት አንዱ ስራ ላይ በማጠንጠን፤ በተውኔቱ ውስጥ ክፉ ገጸ ባሕርይ ተደርጎ የተሳለውን የሻይሎክን ስም ለራሱ በመስጠት ‹‹ሻይሎክ የኔ ስም ነው›› - ‘Shylock Is My Name’  የሚል መጽሀፍ ለህትመት አብቅቷል፡፡ እናም ‹‹ባለ ቅኔው ሳይሆን ታዳሚያኑ ናቸው ተውኔቱን አንጋድደው በጸረ-ጽዮናዊነት anti-semitic የተረጎሙት›› የሚል መንደርደሪያ በማስቀደም፤ በተውኔቱና በእሱ መጽሀፍ ጭብጥ ዙሪያ ያሉትን ተመሳስሎና ልዩነቶች ባጭሩ የዳሰሰበትን Shylock and me - ሻይሎክ እና እኔ - የሚል አርእስት የሰጠውን፣ ሼክስፒርን በጽኑ የሞገተበትን ጽሑፉን አስነብቧል፡፡ እነሆ . . .
*        *        *
የቬኒሱ ነጋዴ The Merchant Of Venice ተውኔት በተደጋጋሚ በመድረክ ቀርቧል፡፡ ሻይሎክ፤ ናዚዎች አይሁድን ለማየት በሚፈልጉት መንገድ ነው የተቀረፀላቸው፡፡ ገጸ ባሕርይው የመጨረሻው የክፋት ማሳያ ተደርጎ ነው የተሳለው፡፡የሻይሎክ ገጸ ባሕርይ የተገለጠበት ሁናቴ ምን ያህል የአይሁዳዊያኑን ቅስም ሰባሪ ሆኖ በመዝለቁ ጉዳይ ላይ አንዳችም ተቃውሞ ለማቅረብ ይቻላል ብዬ አላስብም፡፡ተውኔቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለእይታ ከበቃበት 1595 ጀምሮ፤ ዓለምን ፍትሀዊ ባልሆነ ግንዛቤ ለሚረዱቱና ፀረ-አይሁድ የፍረጃ አመለካከት ላላቸው ሁሉ፤ የሻይሎክ ገጸ ባሕርይ እንደ ማረጋገጫ ሆኖላቸዋል፡፡
ያላግባብ ትርፍ ለማካበት ወለድ በገፍ እሚያግበሰብስ አራጣ አበዳሪ፤ የሴት ልጁን ሕይወት የቁም ሲዖል ያደረገባት ጨቋኝ አባት፤ ያበደረውን ለማስመለስ የክስ ማመልከቻ አቅርቦ፤ በተነፈገው ገንዘብ ምላሽ የሰው ደም ለማፍሰስ በሕግ ፊት በድፍረት የጠየቀ አንዲት ቅንጣትም የርህራሄ መንፈስ የሌለው ኮምጫጫ . . . ሻይሎክ፤ በየቬኒሱ ነጋዴ ተውኔት ውስጥ፤ ኢየሱስ እንዲሰቀል በጠየቁት ጥቂት አይሁዳዊያን ተመስሎና ምድር ከተፈጠረች ታይቶ እማይታወቅ ‹እርጉም› ሆኖ ነው የቀረበው፡፡(የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትና ሐዋርያቱ ሁሉ አይሁዳዊያን መሆናቸውን ግን ልብ ይሏል፡፡)
እናም ይህንን ሻይሎክ ነበር ለረዥም ዘመናት በየትውልዱ ሁሉ የተፈራረቁ ተዋንያን ሲተውኑት የኖሩት፡፡ ልክ በሜዲቫል ድራማዎች ውስጥ በተደጋጋሚ ይታዩ እንደነበሩቱ - ገብጋባ እና ነጭናጫ፣ አፍንጫ ቆልማማ፣ ወገበ ጎባጣ . . .ወዘተ.  አሰልቺ ገጸ ባሕርያት አይነት፤ መሰሪ ‹ስጋ በላች› ይሁዲ - ላመል ታህል እንኳ አንዳችም የሰው ዘር ላህይ ያልፈጠረበት፡፡
ስለዚህ፤ ናዚዎች፤ በዚህ መልኩ የሚቀርብላቸውን ተውኔት አይተው ቢወዱት ምንም አይደንቅም፡፡
እኔም እንዲሁ፤ ምንም መሸፋፈን አልፈልግም፤ በየቬኒሱ ነጋዴ ላይ ተመርኩዤ ‹‹ሻይሎክ የኔ ስም ነው›› የተሰኘውን መጽሀፌን እጽፍ ዘንድ ግብዣ ሲቀርብልኝ፤ ላፍታ እንኳ አላቅማማሁም፡፡ ለምን ቢባል፤ ዛሬም ድረስ፤ የሼክስፒርን 400ኛ ሙት አመት እየዘከርን ባለንበት ጊዜ ላይ ሆነንም፤ ይህ በአይሁዳዊያን ሕዝቦች ላይ ጥላቻን ለማስፋፋት እሚያበረታታውና ከግምት ባለፈ አስፈሪ ቁመና የተመሰሉበት ለ400 አመታት ሲታይ የኖረ ትእይንት አሁንም እየቀረበ ነውና፡፡ እናስ፤ ከእንግዲህም ይህን ሼክስፒር ገጸ ባሕርይውን የሳለበትን የተሳሳተ መንገድ ተቀብለን መጪዎቹንም ዘመናት በድንቁርና ልንቀጥል ይቻለናልን?
ምናልባት የሻይሎክ ገጸ ባሕርይ የተጻፈበትን ዘመን የግንዛቤ መጠን ዛሬ እኛ ከምንኖርበት ‹በእውቀት የታነጸ› ጊዜ የአመለካከት ደረጃ ጋር በማነጻጸር ጉዳዩን ቀለል አድርገን ልናልፈው እንሞክር ይሆናል፤ ያም ሆኖ ግን ጥያቄው፤ የሻይሎክን ገጸ ባሕርይ ከራሱ ፈጣሪ/ደራሲ ነጻ የማውጣት ግዴታስ የለብንም ወይ ነው? ምህረት ልናደርግለት፡፡ ሼክስፒርንም እንዲሁ ይቅር ብለነው፡፡
መቸም ይቅር በማለት የሚመጣ ችግር የለም። በኔ አተያይ በሼክስፒር ድርሰት ውስጥ የጸረ-ጽዮናዊነት ጭብጥ የለምና፡፡ ምናልባት የረዥም ልቦለድ መጽሀፌ ‹ውሃ የሚያነሳ› ፍሬ ሀሳቡ ምንድነው ከተባለ፤  ሼክስፒር በየጥላቻ መገረንና ግድ የለሽነት የጻፈውን ወደ ጎን በመተው፤ ሻይሎክን በራሳቸው የክፋት መንገድ ለሚተርጉሙቱ የሚያነሳውና የሚያንሸረሽረው ጉዳይ ነው፡፡
በ‹ሻይሎክ የኔ ስም ነው› መጽሀፍ ውስጥ ያለው ሻይሎክም ታዲያ፤ፍጹም መልካም የሆነ፣ እንደው በምኑም ከምኑም እንከን የሌለበትና፤ ከምናውቀው በተለየ ሁኔታ የተቀባባም አይደለም፡፡ ያው የሼክስፒር ሻይሎክ ራሱ ‹ተብጠርጥሮ› ተጻፈ እንጂ፡፡
የምናነብበው ያንኑ የተጻፈውን ነው - ልክ እንደ አንድ ሰው ፤ ሙሉ ለሙሉ ራሱ እንዳለ ተወስዶ - ግን ‹ክፋቱን› ብቻ አካብደው ለሚያዩቱ ‹ማስተባበያ›ውን refutes ያቀርባል፡፡
እኔ ከሼክስፒር የተሻለ እድለኛ ነኝ፡፡ ብዙ ይሁዲዎችን ለመገናኘት በመቻሌ፡፡ በእርግጠኝነት ይህ አጋጣሚ ለእርሱ የተፈቀደ አልነበረም፡፡ እርሱ ከኖረበት የህይወት ዘመን መቶ አመታት አስቀድሞ የአይሁድ ሕዝብ ከኢንግላንድ ምድር ተባርረዋልና፤እንዲሁም የቬኒሱ ነጋዴ ከተጻፈ በኋላም ለቀጣዮቹ 150 ዓመታት ተመልሰው ለመግባት ገና አልተፈቀደላቸውም ነበር፡፡
ስለዚህም፤ እነርሱ ባልነበሩበት ሁኔታ፤ ሼክስፒር የነበረው ግንዛቤ፤ ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣው፣ በኋላቀር ድንቁርና፣ ፍረጃና ማግለል ውስጥ ከተጸነሰው የተንጋደደ አመለካከት የሚቃርመው፤ ከእውነታው በእጅጉ ያፈነገጠ፤ የሜዲቫል / መካከለኛው ዘመን የተዘበራረቀ አስተሳሰብ ትቶት ካለፈው ፍርሀት፣ ጥላቻ፣ አሉባልታ የቀሰመው የተዛባ አሉታዊ እውቀትና በሰሚ ሰሚ የወረሰው ‹አጉል አምልኮ› ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡
ሻይሎክን እኔ ስጽፈው በውብ አልባሳት የሚሽቀረቀር ዘናጭ ሰው እና የዘመኑን እንግሊዝኛ እንዲናገር አድርጌዋለሁ፤ በተረፈ የቀረው ሁለመናው ተጽፎ እንዳገኘሁት/‹እንደወረደ› ነው፡፡ ያም ሆኖ በከፍተኛ ደረጃ ከአሾክሻኪዎቹ ቀንበር ነጻ አውጥቼዋለሁ፤ እነርሱም በሚወሻክቱት የፍረጃ ሀሜታቸው የወጣላቸው ወሬ ፈትፋች አሽሙረኞች እንደነበሩ አሳይቻለሁ፡፡ ቢሆንም በግልጽ በሚያስታውቅ ደረጃ፣ የበዛ ጨካኝነታቸውን እየነቀስኩ አድበስብሼ አልፌዋለሁ፡፡ ግን ደሞ የዚያኑ ያህል የፍርደ ገምድል ጥላቻቸውን በተለያየ አውድ እያብጠረጠርኩ ግልጥጥ አድርጌ አውጥቻለሁ፡፡
ሌላው መስህብ ያለው እሚመስለው/በጣም ነውም - ጥሩ አቀራረቡ፤ ለሰዎቹ መላወሻ ሆኖ የተሳለው አካባቢ ነው - ገጸ ባሕርያቱ የሚንከላወሱት በፖርቲያ አፀድ ዙሪያ በቤልሞንት መንደር ቪላዎች፤ በሰሜን ቼሻየር፣ አንዳንዴ ደቡብ ማንችስተር ይሉታል፤ በወርቃማና አንፀባራቂው የተሞላቀቀ ሰፈር ውስጥ  ነው - በርካታ የእግር ኳስ ተጫዋቾች በዚያ የመኖሪያ ቤቶች አሏቸው፡፡
በዚሁ የእግር ኳስ መቼት ውስጥም ነው፤ ዘመናዊ ሆና የተሳለችው ጄሲካ፤ እጅ ከሚነሳት ናዚ ጋር ብን ብላ ጠፍታ ለስህተት የምትዳረገው፡፡ ሼክስፒር፤ ስለ አይሁዳዊያን ፤ በእውን አይቶ የጨበጠው ትንሽ እንኳ ያልተበረዘ እውቀት የነበረው ቢሆን ኖሮ፤ ከጥላቻ ትርክቶች መሳ አብሮ ከመወሳት መተው የሌለበትን የርህራሄንም አንጓዎች የሚተነትነውን ምናባዊ ምልከታ ምጡቅ የፈጠራ ብቃትን በተጎናፀፈ ነበር፡፡
በተውኔቱ ከአንዱ ወደ አንዱ በተሸጋገርን ቁጥር፤በብዙኃኑ ዘንድ ዝና/ተወዳጅነትን ለማትረፍ ሲል በ‹አላባዊያኑ› በስልት እንደሚቆምርና ጉዳይ በመሳብና በማወሳሰብ እንዴት ‹እንደ እንዝርት› እንደሚሾር ነው እምናስተውለው፤ ጊዜ ያጋደለባቸውን የሰዎች መንጋ እያግተለተለ በሙሾ ሲያነፋርቅ፤ በክህደትና ውግዘት የተጥለቀለቁ የሰውን ልጅ የእለት ተእለት ህይወት በጭካኔ የታጨቁ ትእይንቶች ፤ ሰዎች የቅርብ ወዳጆቻቸውን ድክመት እያነፈነፉ፡ በደል እየቆጠሩ፡ ከስሰው በግፍ ሲያስፈርዱባቸው፤ እንዲሁም የእነርሱ ተከታይ ያልሆኑትን ክፉኛ ድባቅ ሲመቷቸው፡፡
እናም ይህን ፤ አይሁዳዊያን ሲፈረጁበት የነበረውን የዘልማዳዊ/ያረጀ ያፈጀ አጉል አተያይ ፤ እርሱም ያንኑ ከአያት ቅድማያቶቹ ወርሶ/ተውሶ ‹መዘገቡ› በሼክስፒር አያምርም፡፡
ሻይሎክ ስለ ስብዕናው ክብር (ስጋዊ ሰውነቱ) ሙግት የሚያንጎራጉረው - በእውኑ እኛስ እንደናንተ ‹ብትወጉን ደም አይወጣንምን፤ ብትኮረኩሩንስ አንስቅምን› - አባባልም ቢሆን፤ ብዙውን ጊዜ ልክ እንደ አንድ የተለመደ በቃ የማንኛውም ቅር የተሰኘ ሰው ንግግር ተደርጎ በቀላሉ ሲታለፍ ይስተዋላል፡፡
የምንሰማው ግን ፤ የአንድ ለብቻው የተነጠለ ፣ በዙሪያው ከከበቡት ቬኒሲያዊያን ሁሉ በተለየ የግራ መጋባት ዓይኑ ዓለምን የሚታዘብና ውጣ ውረዷን የሚጋፈጥ ባይተዋር ግለሰብን ድምጽ ነው፡፡
በዚህና በሌሎች መሰል ኩነቶች ውስጥም እንዲሁ፣ ሻይሎክን ከሌሎች ነጥሎ በባይተዋርነት ብቻውን በሚያቆምበት ጽንፎች በሙሉ ስንታደም፤ የሻይሎክን ህመም ታምመን፣ ስቃዩ ተሰምቶን፣ ሀዘኑን እንድንጋራና ሆዳችን ለእርሱ እንዲንቦጫቦጭለት ሳይሆን፤ ይልቅስ በገጸ ባሕርይው እንድንዝናና (‹ሙድ እንይዝ›) ነው የሚያደርገን ሼክስፒር ፡፡
እርሱው ራሱም  ከቬኒሲያዊያኑ የባሰ የሰላ ስላቅ ይፈጥርበታል፤ እናም ለከበቡት ቬኒሲያዊያን በጠፋው ቀለበት ዙሪያ የሚያክላሉበትን የ‹አሽኮለሌ› ድባብ ይፈጥርላቸዋል፡፡ሻይሎክ፤ ስለተለየችው ሴት ልጁ በመሪር ሀዘን ሲብከነከን፤ እንዲሁም ጄሲካ የሰረቀችውን ቀለበት በስጦታ ያበረከተችለትን በሞት የተለየችው ሚስቱን እያስታወሰ ሲብሰለሰል፤ ልባችን ይነካል፡፡
ሼክስፒር እንድንወደው ያደርገናል አላልኩም፡፡ ግን እንድናውቀው ያደርገናል፤ የሰው ዘርን ሁሉ እንጉርጉሮ መነሻ ምንጭ፡፡ በተውኔቱ ውስጥ ካሉት ቬኒሲያዊያን ነጥለን የአንዱን የእርሱን ብቻ ስጋና ደም የተላበሰ ሰብእነት በብርቱው በማውጠነጥን እንጠመዳለን፡፡
በዙሪያው የከበቡት ቬኒሲያዊያን ፍቅር የነጠፈባቸው መንጋዎች ናቸው - የቁስ ምኞት ያነሆለላቸው፤ ከእነርሱ በቀር ማንም መልካም ሰው እንደሌለና እነርሱን ራሳቸውን ብቻ ፍጹምና ጻድቅ አድርገው እሚቆጥሩ ፤ መረን የወጡ ስድ አደጎች፡፡
እነርሱውም ሻይሎክን ይነቅፉታል፤ ጢቅ ይሉበታል፤ ሴት ልጁንና ንብረቱን ይዘርፉታል፤ ከዚህ ሁሉ በኋላም እምነቱን ክዶ በእነርሱ እምነት ይጠመቅ ዘንድ ግዳጅ ይጥሉበታል፡፡ ሼክስፒር እርሱ የፈጠረውን የሻይሎክ ገጸ ባሕርይ ከሳለበት የተገለለ መልኩ ይልቅ፤ ከዚህኛው ሻይሎክ ጋር በወዳጅነት አብረነው ቆመን፤ ሲቃና ሰቆቃዎቹን፡ እንጉርጉሮና መትከንከኖቹን ለማጣጣም ይቻለናል፤ ስለ አይሁዳዊያን ያለን አመለካከት የቱንም አይነት ቢሆንም እንኳ፡፡
እነሆ፤ የሻይሎክ እና የጨቋኞቹ ሁለንተና ይህን ነው እሚመስለው፤እኔ በጻፍኩት ጭፍግ-ፍግ  tragi-comic ረዥም ልቦለድ ውስጥ፡፡ ‘Shylock Is My Name’ by  Howard Jacobson is published by Vintage, priced at £16.99

Read 813 times