Sunday, 03 June 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

 “ምክንያት ከሞተ፤ እውነት ሞተ!!”
              
     በደንብ የማላስታውሰው፤ በልጅነቴ ያነበበኩት የስለላ ታሪክ ነበር፡፡ መንፈሱ እንዲህ ይመስላል፡-
ሰውየው ባገሩ ጉዳይ ቀልድ አያውቅም። ይህን ያጠናው የአገሩ ደህንነት ቢሮ፣ ለሰላይነት መለመለው።… “ምነው በቀረብኝ” በሚያሰኝ ስልጠና ተፈትኖ አለፈ። የአገሩ ባላጋራ፣ ድብቅ ፕሮጄክት እየገነባ ይገኝበታል ተብሎ የሚጠረጠርበትን ጫካ እንዲፈትሽ አደራ (mission) ተሰጠው፡፡ …ከተባለው ቦታ ራቅ ብሎ በዣንጥላ ወረደ፡፡… አጋጣሚ ሆነና በጥቂት ቀናት ውስጥ ተያዘ፡፡
ማንነቱንና ለምን እዛ ቦታ እንደተገኘ ሲጠየቅ፣ ባጠናው ውሸት ለማታለል ሞከረ፡፡ በተለያየ መንገድ መረመሩት፡፡ ፍንክች አላለላቸውም፡፡ እንዳይሞት እንዳይድን አርገው ቢያሰቃዩትም ምንም አልወጣውም፡፡ በሰለጠነው መሰረት ራሱን ለማጥፋት አመቻቸ፡፡ ኮሌታው ውስጥ የደበቀውን መርዘኛ ኪኒን (ሲናይድ) ዋጠ፡፡…አልሞተም፡፡…አለመሞቱ አሳሰበው። ያልጠበቀው ነገር ነበር፡፡ ተናደደ፣ በሸቀ፣ አለቆቹን ተጠራጠረ፡፡ በምርመራና በሃይል ያልተነፈሰውን ምስጢር፣ በፍላጎቱና በነፃ ፍቃዱ አፍረጠረጠው፡፡ ባላጋራ ተብዬዎቹም ለውለታው ማካካሻ እንዲታከምና እንዲያገግም፣ በሁዋላም ወደ ጎረቤት አገር እንዲሰደድ ፈቀዱለት፡፡ የሚያስፈልገውን አሟልተው ድንበር ድረስ ሸኙት፡፡ ድንበር እንደተሻገረ የተቀበሉት ግን የሃገሩ የፀጥታ ሃይሎች ነበሩ፡፡… ምን ይጠብቀው ይሆን?
መልካምነትና ደግነት አሸንፎህ ሃሳብህን ትቀይራለህ፡፡ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ሲደጋገሙብህ ራስህን ትጠራጠራለህ፡፡ “ዕውነት የት ጋ ናት?” እያልክ መጠየቅ ትጀምራለህ…ይላል። “የሎጂክም ነገር እንዲሁ ነው” በማለት ይቀጥላል።…”ልክ ነው፤ ዕውነት ነው” ብለህ ያሰብከው ወይ የመሰለህ ነገር በጥልቅ ስትመረምረው የተሳሳተ ይሆንብሃል። ተሳስቷል ያልከው ደግሞ እውነትና ፍፁም ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡
…ሎጂክ ዕውነት የሚሆነው በሚንተራሳቸው አጋዥ ሃሳቦች ነው፡፡ አጋዥ ሃሳቦች ቢቀያየሩም… ዕውነት “ዕውነት” የሚሆንበት ውሃ ልክ አይሳነውም። አንተ አንቦጫርቀህ ያለፍከው ውሃ፣ ለሌላው የበረዶ ድንጋይ ሆኖ ይጠብቀዋል፡፡ ሶስተኛው ሲመጣ እንፋሎት፣ ለተመራማሪ ደግሞ የአየርና የጋስ ሞለኪዮል ሊሆን ይችላል፡፡
አይነ ስውራኑ፤ ዝሆንን የገለፁት የየራሳቸውን መንገድ ተከትለው ነው ተብሎ ይነገራል፡፡ እግሩን የነካ እንዲህ አለ፣ ጭራውን የነካ እንዲህ አለ፣ ኩምቢውን የነካ እንዲህ አለ፣ ጆሮውን የነካ እንዲህ አለ… እየተባለ። ዕውነቱ ግን አልተቀያየረም… በቦታው ነው፡፡ ውሃም ውሃ፣ ዝሆንም ዝሆን ነው፡፡ ልዩነቱ፣ ዋናው ጉዳይ ላይ አይደለም፡፡ የዕይታና የአተረጓጎም ነገር እንጂ!!
የትም ቦታና ሁልጊዜ በማናቸው ጉዳይ ላይ የአመለካከትና የትርጉም ልዩነት ይኖራል፡፡ ይኼ ማለት ግን ሁሉም “የራሴ ዕውነት አለኝ” ብሎ እንዲከራከር አያበቃውም፡፡ ዕውነት ትርጉም ወይም አመለካከት ሳይሆን መዳረሻ ወይም ማጠቃለያ ነው፡፡ ዕውነት በትክክል ለሚፈልገው አጭርና ግልፅ መንገድ አለው - ጥበብና ምክንያት!!... ሶቅራጥስ “አደጋ ላይ እንዳይወድቅ እንጠብቀው” የሚለው ይህንኑ ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ የምክንያትና የውጤት ፅንሰ ሀሳብ፣ በህይወታችን ላይ ምን ያህል እንደሚሰራ አናስተውልም፡፡ ለምን እንደተዋደድን፣ እንደተፋቀርን ወይም ጓደኛማቾች እንደሆንን ምክንያቱን ላናስታውስ እንችላለን፡፡ ስንጣላ፣ ስንራራቅና ስንቀያየም ግን ምክንያቶቻችንን ነጥብ በነጥብ እንዘረዝራቸዋለን፡፡ በደላችንን በቀላሉ ስናስታውስ፣ ጥቅምና ትርፋችንን ግን እንዘነጋለን፡፡ ምክንያቱም “ጥቅም” ማለት መኖር ስለሆነ አይታወቀንም፡፡ መኖር ተፈጥሮ ነው፡፡ ካልተመቸን በስተቀር ስለ መኖር አናስብም፡፡ እጅ ለምን ተፈጠረ?... ፀጉር ለምን ተፈጠረ? እያልን አንጨነቅም። የምንጨነቀው  ሲጎድለን ነው፡፡ እንቅፋት ከሌለ፤ ድካም ከሌለ፣ ውሸት፣ ፍርሃት፣ ቅናት፣ ይሉኝታ፣ ሐዘን፣ ትካዜ፣ ህመም ከሌለ -- “እየኖርን” ነው ማለት ነው፡፡ እነሱ የሌሉበት ቦታ ደግሞ የለም፡፡ ምናልባት መንግሰተ ሰማያት ካልሆነ፡፡ ሁሌም በምቾታችን ውስጥ አለ፡፡ መመቸት፣ በኑሯችን ውስጥ አለመኖር ባንፈልገውም ተገደን እንቀበለዋለን፡፡ ከትርፋችንና ከጥቅማችን በላይ በደላችንንና ቅያሜያችንን፣ በቀላሉ የምናስታውሰው ለዚህ ነው፡፡
አንድ ነገር ልብ በልልኝ፡፡ ምክንያታዊነት ያስፈለገን እንደነዚህ ዓይነቶቹን የሰው ልጅ በግዴታ የተቀበላቸውን፣ ከቶም ሊያስወግዳቸው የማይቻላቸውን የመኖር “ህፀፆች” ማራቅ እንዲያስችለን ነው፡፡ ምክንያታዊነት ነገሮችን ከስራቸው የምንረዳበት፣ ወደ ዕርቅ፣ ወደ ሰላምና ፍቅር የሚመራን ብርሃን ነው። ምክንያታዊነት በትርጉምና በአመለካከት ልዩነት ከማይለወጠው ዋና ጉዳያችን የሚያደርሰን መንገድ ነው፡፡… ወደ ዕውነት!!
*  *  *
ወደ ትረካችን እንመለስ፡፡ ሰውየው ከጥቂት ወራት በኋላ ወደ አገሩ ተወሰደ፡፡ ከፍተኛ ድግስ ደግሰው፣ የጀግና ሜዳሊያ አዘጋጅተው ተቀበሉት፡፡ የጠበቀው እስር ወይም ከዛ በላይ የሆነ ቅጣት ነበር፡፡… ግራ ተጋባ። ቢቸግረው፡-  
“ሚስጢሩን እንደነገርኳቸው ታውቃላችሁ?…. አታውቁም?” ሲል አለቆቹን ጠየቀ፡፡
“በደንብ እናውቃለን” አሉት፡፡
“ያን ያደርግሁት በናንተ ተበሳጭቼ ነው”
“እናውቃለን”
“የሰጣችሁኝ መድሃኒት አይሰራም”
“እናውቃለን”
“እናውቃለን ማለት ምን ማለት ነው?...አልገባኝም!”
“ አሁን ይገባሃል” አሉ አለቃው፡፡ ለምን ብሔራዊ ጀግና እንደሆነም አስረዱ፡፡
“ሞተህ ቢሆን ኖሮ ድካማችን ሁሉ ከንቱ ይሆን ነበር፡፡… ተልዕኮው ይከሽፋል፡፡ ያንን ሁሉ ስቃይ ሳታልፍ፣ በመከራህ ውስጥ ሆነህ እንኳ ማንነትህን ብትነግራቸው አይሰሙህም ነበር፡፡ የሰጠኸውን ቃል ያመኑት ከልብህ ተበሳጭተህ፣ በገዛ ፍቃድህ የነገርካቸው መሆኑን በማረጋገጣቸው ነው፡፡ እኛም የፈለግነው እንደዛ እንዲሆን ነበር፡፡ ሆኖም እንድትሞት አልተፈለገም፡፡ በነገራችን ላይ አንድትያዝ ያመቻቸነውም እኛ ነን፡፡
“እንዴት?”
“አዎን፡፡ እንደሱ መሆን ነበረበት፡፡ አሁን ትልቅ መረጃ አገኘን ብለው ፕሮጀክቱን ዘግተው፣ ቦታውን ለቀዋል፡፡ በኛ ቁጥጥር ስር እየዋለ ነው፡፡ ይህ ድል የተገኘው ደግሞ ባንተ ፅናት ነው፡፡ ለአገርህ ባለውለታዋ ነህ፡፡… እንኳን ደስ ያለህ!!”
“ይሆናል ያልኩትና የሆነው ነገር ጨርሶ አይገናኝም!”
“ስለላ ጥንቃቄ፣ ፕሮፌሽናሊዝምና ቅንነትን ይጠይቃል፡፡ በፈቃደኝነት የሚሰራ በመሆኑ ደግሞ ከሁሉም በላይ ምክንያታዊ መሆን ያስፈልጋል፡፡ አንተ የተመረጥክበት ዋናው ምክንያት አገርህን በመውደድህ ነው፡፡ በጥቅም የሚደለሉ፣ ሃላፊነታቸውን የግል ቂም መወጣጫ የሚያደርጉ፤ በአገር ሃብት የሚዘባነኑ፤ ለባለስልጣናት የሚላላኩ ሰላዮችና ወሬ አመላላሾች አገራቸውን ይወዳሉ ማለት አይቻልም። መንግሥታቸውን የጠቀሙ እየመሰላቸው፣ የፈጠራ ወሬ እያመላለሱ ከህዝብ ጋር ያራርቁበታል፡፡..”
“ገባኝ” አለውና ነገሩ ተጠናቀቀ፡፡
ወዳጄ፡- ማንም የማያውቀውንና ያልሰለጠነበትን ስራ ለመስራት ከተዳፈረ፣ ከሚያለማው የሚያጠፋው ይበልጣል፡፡ የሚገርመው ታዲያ ከሁሉም ስራ በላይ አስቸጋሪ በሆነው፣ የመንግሥት አስተዳደር ላይ ለመሰማራት ሁሉም ራሱን ብቁ አድርጎ ማሰቡ ነው (No man undertakes a trade he has not learned, even the meanest, yet everyone thinks himself sufficiently qualified for the hardest of all trades that of government) የሚለን ሶቅራጥስ ነው፡፡ ለማንኛውም ወዳጄ፤ ምክንያታዊነት አደጋ ላይ መሆኑን እንዳትረሳ!! “ምክንያት ከሞተ፣ ዕውነት ሞተ!!” ነው ነገሩ!!
ሠላም!!

Read 794 times