Sunday, 03 June 2018 00:00

ማርክስ - መልካም ልደት!

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(2 votes)


           “--ካርል ማርክስ የሄግል ተማሪ ሆኖ አልቀረም፡፡ ሄግልን ተማረ፣ ብሩኖ ባወርን ተከተለ፡፡ ከዚያም በራሱ መንገድ ሄደ፡፡ ማርክስ፤ በተለያየ ዘዬና አውድ፣ ባናት-ባናቱ የሚጽፍ ትንታግ ፀሐፊ ሆነ፡፡ እናም ብዙዎቹ ሥራዎቹ የታተሙት ከዚህ ዓለም ከተሰናበተ በኋላ ነው፡፡ በርካታ ሥራዎቹ፤ ከእርሱ ዕረፍት በኋላ አንድ-አንድ እያሉ (በችርቻሮ መልክ) ለህትመት የበቁ ሥራዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ስራዎች መካከል አንዱ፤ ማርክስ ለአባቱ የጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡--”
           
    ጋሼ ስብሐት ካርል ማርክስን ‹‹የተቆጣ ኢየሱስ›› ይለው ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ስለ ካርል ማርክስ ለመነጋገር የሚገፋፉ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች አንዱ፤ ማርክስ በቅርቡ ሁለት መቶኛ ዓመት የልደት በዓሉን ‹‹ማክበሩ›› ነው፡፡ እኔ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ ስለ ማርክስ አጫውታችኋለሁ። ሆኖም የማጫውታችሁ የማላውቀውን የማርክስን ፍልስፍና አይደለም፡፡ ይልቅስ ከማርክሲዝም በፊት ስለነበረው ማርክስ ነው፡፡ ስለ ፈላስፋው ሳይሆን፤ ሰውዬው ማርክስ። ማርክስ ለአባቱ ከጻፋቸው ደብዳቤዎች አንዱን አለፍ አለፍ እያልኩ በመተርጎም፣ ከምታውቁት ማርክስ ጋር አስተዋውቃችኋለሁ፡፡
በአንድ ወቅት የአውሮፓ ሰዎች ጦረኛዋን ቱርክን በጣም ይፈሯት ነበር፡፡ እንደ አጼ ቴዎድሮስ ‹‹እኔ መዩ፣ ቱርክ ባይ፣ የምሸሽ ነኝ ወይ›› እያሉ ለመሸለል የሚያስችል ልብ አልነበራቸውም። ከቱርክ ቀጥሎ የሚፈሩት ካርል ማርክስን ይመስለኛል፡፡ ማርክስ የሚያቀርባቸውን ሐሳቦች፤ እንደ ቱርክ ጦር ይፈሩት ነበር፡፡ ብዕሩ ተናዳፊ ነው፡፡ ስለዚህ በርካታ የምዕራቡ ዓለም ምሁራን፣ ማርክስን በብዙ ይተቹታል። ሲናደዱ ‹‹የድህነት ፈላስፋ›› ይሉታል፡፡ እርሱም አይመልስላቸውም። ‹‹ስድባችሁ የፍልስፍና ድህነት ነው›› ይላቸዋል፡፡
ካርል ማርክስ የ19ኛው ክፍል ዘመን ፕሮሚቲየስ ነው፡፡ ‹‹ርኵስ ሰው የሚባለው፤ የህዝቡን አምላክ የሚያጠፋ ሳይሆን፤ የህዝቡን እምነትና አስተሳሰብ በአምላክ ሰንደቅ ላይ የሚሰቅል ሰው ነው›› (ሎቱ ስብሐት)፤ የሚለው ማርክስ፤ ‹‹…በዚህ ረገድ ፍልስፍና ምንም ምስጢር የምታደርገው ነገር የለም፡፡ የእርሷ መፈክር የፕሮሚቲየስ አዋጅ ነው›› ይላል፡፡ የፕሮሚቲየስ አዋጅ ‹‹ሁሉንም አማልክት እፀየፋቸዋለሁ›› የሚል ነው፡፡ እንደ ማርክስ ሐሳብ፤ የፍልስፍና ሙያ ‹‹ሁሉንም አማልክት መፀየፍ›› ነው። የፍልስፍና መፈክር፤ ‹‹የሰው ልጅ ‹ራስ አወቅ -ንቃተ ህሊና› (man’s self-consciousness)፤ የመጨረሻው ከፍተኛ የመለኮታዊነት ማዕረግ መሆኑን የማይቀበሉ ምድራዊና ሰማያዊ አማልክትን ሁሉ ማውገዝ ነው›› ይላል፡፡ ከሰው ልጅ ‹‹ራስ አወቅ -ንቃተ ህሊና›› (man’s self-consciousness) ወዲያ ምንም ነገር የለም ባይ ነው፡፡ ማርከስ ‹‹ሰው እግዚአብሔርን ፈጠረ›› ይላል እንጂ፤ እንደኔ ‹‹እግዚአብሔር ሰውን ፈጠረ›› አይልም፡፡
ማርክስ በኖረበት ዘመን፤ ፍልስፍና በህብረተሰቡ ህይወት የነበራት ቦታ የተበላሸ መሆኑን ይናገራል። እናም ይህ የተበላሸ ቁመናዋ የሚያስደስታቸውን ሰዎች ይነቅፋል፡፡ አሳዛኝ ፈሪዎች ይላቸዋል፡፡ እናም ፕሮሚቲየስ ለአማልክቱ አሽከር ለሄርሜስ የተናገረውን በመድገም ፍልስፍና ‹‹ይህን ነገር ልብ አድርጉ፤ ይህን የገጠመኝን ክፉ መከራ ለእናንተ ባርያ በመሆን ልለውጠው አልፈልግም›› (Understand this well, I would not change my evil plight for your servility) ትላቸዋለች›› ይላል፡፡
በርግጥ እንዲህ ያለ አመጽ የተጀመረው፤ በዘመነ ማርክስ አይደለም፡፡ ነገሩ ከዘመነ አብርሆት (Enlightenment) የሚነሳ ነው፡፡ ዘመነ አብርሆት ሲብት፤ የምዕራብ አውሮፓ ሰዎች መፈክር፤ ‹‹ኩሉ አመክሩ›› (ሁሉን መርምሩ) ሆነ፡፡ ይህ መፈክር፤ በእኛ የዘመናዊ ከፍተኛ ትምህርት ቤት በራፍ ላይ ተጽፎ አንብበነዋል - በከፊል፡፡ የእኛ መፈክር ‹‹ኩሉ አመክሩ፤ ወዘሰናይ አጽንዑ›› ነበር - ‹‹ሁሉን መርምሩ፤ መልካሙን ያዙ›› እንደ ማለት፡፡
አውሮፓውያን ሁሉን መርምሩ አሉ እንጂ ‹‹መልካሙ ምንድነው?›› የሚል ጥያቄ ያነሱ አልመሰለኝም፡፡ ምናልባት፤ ‹‹መልካሙ ነገር ምንድነው?›› የሚል ጥያቄ ቢነሳ፤ መልሳቸው ‹‹መልካሙ ነገር፤ ሁሉን መመርመር ነው›› የሚሉ ይመስለኛል፡፡  በዘመነ አብርሆት (Enlightenment) የአውሮፓ ሰዎች አመለካከት በእጅጉ ተቀይሯል። ቀድሞ ሐይማኖተኞች ነበሩ፡፡ ስለዚህ የቀድሞ ጥያቄአቸው ‹‹ሰማያዊ ዕድሌ ምን ይሆን?›› (How can I be saved?) የሚል ነበር። በዘመነ አብርሆት ይህ ጥያቄ፤ ‹‹እንዴት ደስተኛ ህይወት ለመኖር እችላለሁ?›› (How can I be happy?) ወደሚል ተቀየረ፡፡ ሰዎች ምድራዊ ደስታን ብቻ  መሻት ጀመሩ፡፡ ለቤተክርስቲያንና ለማህበራዊ ደረጃ የተገባ ባህርይ መያዝ ሳይሆን፤ የራሳቸውን ግላዊ ደስታ የሚያረጋግጥ መንገድ ፈላጊዎች ሆኑ፡፡ በአጭሩ፤ ሐብት ማካበትና ጤናን መንከባከብ ትልቅ ግብ ሆነ፡፡
የዘመነ አብርሆት ሰዎች እንደ ቀኖና የተያዙ ነገሮችን ሁሉ ለመጣስ የማይፈሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከመሰላቸው የኑሮ ደንብን ሁሉ ይጥሱታል፡፡ ጀርመናዊው ፈላስፋ አማኑኤል ካንት የዘመነ አብርሆት መፈክር፤ ‹‹ለማወቅ ድፈር! የማሰብ ችሎታህን ለመጠቀም ወደ ኋላ አትበል - አትፍራ›› (Dare to know! Have the courage to use your own understanding) የሚል ነበር›› ይላል፡፡
በተቃራኒው፤ የእኛ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መሪ ቃል ‹‹ኩሉ አመክሩ›› የሚል ብቻ አልነበረም፡፡ ‹‹ኩሉ አመክሩ ወዘሰናይ አጽንዑ›› ነው፡፡ ድንቅ መሪ ቃል ነበር፡፡ ሁሉን መመርመር ብቻ ሳይሆን፤ መርምሮ መልካሙን መያዝ ያስፈልጋል፡፡ አውሮፓውያን አሁንም ‹‹መልካም ነገር ምንድነው?›› የሚል ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋቸዋል፡፡ አለዚያ ሰው በምርምር ራሱን ሊያጠፋ የሚችል መሆኑን እያየን ነው፡፡ አንድ የአውሮፓ ሥልጣኔ ጎደሎ ይህ ይመስለኛል፡፡ የእኛ ጎደሎ ደግሞ ሁሉን አለመመርመር እና መልካሙንም መለየት እና መያዝ አለመቻል ነው፡፡
የዘመነ አብርሆት አውሮፓውያን ጥሩ ተማሪዎች ሆኑ፡፡ በሁሉም የህይወት መስክ መመሪያው ‹‹ኩሉ አመክሩ›› ነበር፡፡ ለምሣሌ ነገሩን በጤናው መስክ ያየነው እንደሆነ፤ አንድ ጥሩ አስረጂ ማንሳት ይቻላል። ‹‹ኩሉ አመክሩ›› ብለው፤ በጤናው መስክ በተደረገው ምርመራ የተገኘው አንድ ትሩፋት Variolation ነበር። Variolation ከክትባት ይለያል፡፡ ክትባት የኤድዋርድ ጄነር (Edward Jenner) ግኝት ነው - በ1799 ዓ.ም (እኤአ)፡፡ አውሮፓውያን የVariolationን ጥበብን ከየሐገሩ ተማሩ፡፡ ቫሪዮሌሽን በህንድና በቻይና እንዲሁም በአፍሪካ የታወቀ የህክምና ዘዴ ነበር፡፡
ለምሣሌ፤ በህንድና በቻይና፣ በፈንጣጣ በሽታ ከተያዘ ሰው መግሉን በመውሰድ፣ በበሽታው እንዳይጠቃ በሚፈለገው ሰው ክንድ ውስጥ እንዲቀበር ይደረግ ነበር፡፡ Variolation እንዲህ ያለ ህክምና ነው። በአፍሪካ ደግሞ ከደረቀው ቁስል ፍቅፋቂ ተወስዶ፣ ህክምና በሚሰጠው ሰው አፍንጫ እንዲነፋ የማድረግ ህክምና ነበር፡፡ ይህ ህክምና በኢትዮጵያም ይታወቃል። አባት-አያቶቻችንን ብንጠይቅ ይነግሩናል፡፡
ቫሪዮሌሽን ወደ እንግሊዝ የገባው በቱርክ የእንግሊዝ አምሳደር በነበረው ሰው ሚስት አማካይነት ነበር፡፡ እመቤት ሜሪ ወርትሌ ሞንታኝ (Lady Mary Wortley Montague) ያመጣችውን ይህን ህክምና፣ በመጀመሪያ የተቀበሉት፣ በመሳፍንቱ አካባቢ ያሉት ሰዎች ነበሩ፡፡ በ1721 ዓ.ም የእንግሊዝ ንጉሳዊ ቤተሰቦች ቫሪዮሌትድ ሆነው ነበር፡፡ ግን አስቀድሞ ህክምናው በጎዳና ተዳዳሪ ህጻናትና በእስረኞች ተሞክሮ ነው፤ ወደ መሳፍንቱ የሄደው፡፡ አውሮፓውያን በዚህ ምርምር ገፍተው ሄዱ፡፡ በ19ኛው ክፍል ዘመን መጨረሻ የበሽታ መንስዔ ጀርሞች መሆናቸውን የሚገልጽ ትወራ ደነገጉ። የቫሪዮሌሽን ጥበብን ከብራዚል፣ ከቻይና፣ ከህንድና ከአፍሪካ ወዘተ እየቃረሙ ራሳቸውን ብቁ አደረጉ፡፡ ግን ተማሪ ሆነው አልቀሩም፡፡ በአጭር ጊዜ አስተማሪ ለመሆን ቻሉ። አስተማሪ የነበርነው እኛ ግን፤ አሁን ጥሩ ተማሪ መሆን እንኳን አልቻልንም፡፡ አያያዛችን ሁሉ ተማሪ አድርጎ የሚያስቀር ነው፡፡ ነገሮችን በራሳችን ዓይን ለማየት እንፈራለን፡፡ የአውሮፓውን መነጽር ከዓይናችን አውልቀን፣ የራሳችንን አካባቢ፣ በራሳችን ዓይን የማየት ድፍረት የለንም፡፡  ራሳችንን ከአውሮፓ ጠቢባን ጋር  እያነጻጸርን ‹‹ተሳስቻለሁ - አልተሳሳትኩም›› የምንል ፈሪዎች ሆነናል፡፡ የእነሱን ስያሜ በመሸምደድ ራሳችንን እናደክማለን፡፡ ምላስ የሚያስሩ የላቲን ቃላትንና የግሪክ ሀተታ - አማልክት ስሞችን በመሸምደድ እንደክማለን፡፡ ይህንም ከዕውቀት እንቆጥረዋለን፡፡ እነሱ ይሰይማሉ እኛ እናጠናለን፡፡ ከደጃችን የበቀለውን ዛፍ፤ በራሳችን ቋንቋ አናውቀውም፡፡ ዛፉ ላይ የምናያትን ወፍም የላቲንኛ ሥም እንጂ በገዛ ቋንቋችን ምን እንደምትባል አናውቀውም፡፡ ውሃ ሲጠማን የሚነግሩን አውሮፓውያን ናቸው፡፡     የምርምር ዘዴውን ሳይሆን፤ ምርምሩን የምንቀዳ ሰዎች ሆነናል፡፡ ከእኛ ተጨባጭ ህይወት ጋር ይጣጣም - አይጣጣም ዝም ብሎ መቅዳት ነው፡፡ የራሳችንን ጥበብ ይዘን ለመሄድ ድፍረት የሌለን ሆንን። ጥበብ መሸንሸንና መሰየም ነው፡፡ እነሱ ይሸነሽናሉ፡፡ ሸንሽነው ይሰይማሉ፡፡ የእነሱን ሽንሸና ወይም ክልሰፋ ለመሸምደድ መከራችንን እንበላለን፡፡ እኛ በራሳችን መንገድ ለመሄድ አልቻልንም፡፡
ፍራንሲስ ቤከን የአርስጣጣሊስን ኢንሳይክሎፒዲያ አንብቦ፤ ‹‹በእንግሊዝ የቴምዝ ወንዝ ያሉት ዓሣዎች በአርስጣጣሊስ ሐገር ባሉት ወንዞች ከምናገኛቸው ዓሣዎች ጋር ይመሳሰላሉ - አይመሳሰሉም›› ሲል የድፍረት ጥያቄ ጠየቀ፡፡ በዚህ ጊዜ  የእንግሊዝ ካህናት ‹‹ቤከን ለምን አታርፍም!!›› ብለውት ነበር፡፡ አውግዘውት ነበር፡፡ ቁጣቸውን ፈርቶ ቢቀመጥ ተማሪ ሆኖ ይቀር ነበር፡፡
ለምሣሌ፤ ካርል ማርክስ የሄግል ተማሪ ሆኖ አልቀረም፡፡ ሄግልን ተማረ፣ ብሩኖ ባወርን ተከተለ። ከዚያም በራሱ መንገድ ሄደ፡፡ ማርክስ፤ በተለያየ ዘዬና አውድ፣ ባናት-ባናቱ የሚጽፍ ትንታግ ፀሐፊ ሆነ። እናም ብዙዎቹ ሥራዎቹ የታተሙት ከዚህ ዓለም ከተሰናበተ በኋላ ነው፡፡ በርካታ ሥራዎቹ፤ ከእርሱ ዕረፍት በኋላ አንድ-አንድ እያሉ (በችርቻሮ መልክ) ለህትመት የበቁ ሥራዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ስራዎች መካከል አንዱ፤ ማርክስ ለአባቱ የጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡ ይህ ደብዳቤ ከማርክሲዝም በፊት የነበረውን ማርክስ የሚያሳይ ብቻ አይደለም፡፡ የሐሳቦቹን የዝግመተ ለውጥ ሂደትም ሊያሳይ የሚችል ነው፡፡
የካርል ማርክስ የቅርብ ጓደኛና አጋዥ የነበረው ፍሬድሪክ ኤንግልስ እንደሚለው፤ የማርክስ እሳቤ የቆመው፤ በጀርመን ሐሳባዊ ፍልስፍና፣ በፈረንሳይ የፖለቲካ ትወራና በእንግሊዝ ክላሲካል ኢኮኖሚክስ ውህድ ቅንብር (synthesis) ነው፡፡ የማርክስ የመጀመሪያዎቹ ምሁራዊ ዘመኖቹ፤ ከጀርመን ፍልስፍናዊ ትውፊት (በተለይም ከሄግል ፍልስፍና) ጋር ግብ ግብ የገጠመባቸው ዘመናት ነበሩ፡፡ ወደ ፈረንሳይ በሄደ ጊዜም፤ ከፈረንሳይ ልዩ የሶሻሊዝም አስተሳሰብ ጋር ተዋወቀ፡፡ ታዲያ ማርክስ የህይወት ጉዞውን የጀመረው፤ ማቴሪያሊስት ሆኖ አይደለም፤ ሐሳባዊ ሆኖ እንጂ፡፡ ይህንንም ነገር ማርክስ ለአባቱ በጻፈው ረጅም ደብዳቤ ውስጥ መመልከት እንችላለን፡፡ ይህን ደብዳቤ ሲጽፍ የ19 ዓመት ወጣት ነበር፡፡ ከትውልድ ሐገሩ ርቆ፤ በበርሊን ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሆኖ ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው እምነት ‹‹ሆኖ በተገኘው›› እና ‹‹ሊሆን በሚገባው›› ነገር መካከል ‹‹ሮማንቲክ›› የሆነ ተቃርኖ አለ የሚል ነበር፡፡ ሆኖም ብዙ ሳይቆይ፤ በወቅቱ በበርሊን ሰፊ ተቀባይነት በነበረው የሄግል ፍልስፍና ተሸነፈ፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም፤ አማልክት የሚኖሩት ከምድር በላይ ከሆነ፤ አሁን አማልክቱ የምድር ማዕከል ሆነዋል›› ይል የነበረው ሄግል ተማሪ ነበር፡፡ የወጣትነት ዘመን የጽሑፍ ሥራዎቹ፤ ከሄግል አስተሳሰቦች ጋር ራሱን ለማስታረቅ የሚታገልባቸው መድረኮች (ጽሑፎች) ነበሩ፡፡ ማርክስን በደንብ የሚያውቁት ምሁራን እንደሚሉት፤ ይህ ትግል እስከ ህይወት ዘመኑ ፍጻሜ የቀጠለ ጥረት ነው፡፡
ምንም እንኳን ካርል ማርክስ፣ ሄግልን አብዝቶ የሚተቸው፤ በሐሳባዊነት የሚከሰው፤ እንዲሁም ‹‹በጭንቅላቱ ያቆመውን ዳይሌክቲክስን እኔ በእግሩ አቆምኩት›› እያለ የሚሸልልበት ቢሆንም፤ የጥናት ዘዴው በቀጥታ ከሄግል የመነጨ መሆኑን ለመናገር ከማርክስ የሚቀድም ሰው አልነበረም፡፡
ሄግል የእዕምሮን ወይም የመንፈስን ዕድገት ለመረዳት ባደረገው ጥረት፤ የሰው አዕምሮ ፍጹም ዕውቀትን ለማግኘት የሚችል መሆኑን ከመቀበል እምነት ደርሷል፡፡ የሰውን ልጅ የንቃተ ህሊና ዕድገት ሲተነትን፤ ሰዋዊ ንቃተ ህሊና፣ እዚህ እና አሁን ያለውን ነገር በስሜት ህዋሳት አማካኝነት ከመረዳት አንስቶ፤ ከራስ አወቅ ንቃተ ህሊና ደረጃ የሚደርስ የዕድገት ጎዳና እንደሚከተል አትቷል፡፡ ራስ አወቅ ንቃተ ህሊና፤ ሰዎች ዓለምን ለመተንተንና በዚያ ላይ ተመስርተው፣ ተግባራቸውን ለመወሰን የሚችሉበትን አቅም እንደሚሰጣቸው ይገልጻል፡፡
ሄግል፤ አሁን ባለው እና ወደፊት ለመሆን በሚገሰግሰው ነገር መካከል ሁልጊዜም ቅራኔ ይኖራል ባይ ነው፡፡ ምክንያቱም፤ አሁን ሆኖ የሚገኘው ነገር ሁሉ፤ ዘወትር ከአንድ ነገር ጋር በተቃርኖ የሚቆም በመሆኑ ትግል ይኖራል፡፡ በዚህ የቅራኔ ትግል ‹‹አሮጌው ነገር›› ወደ አንድ አዲስ ነገር እንዲለወጥ የሚያደርግ ሂደት ውስጥ ይገባል፡፡ አንድ ነገር ሲሆን ወይም ሲደነገግ፤ በሄግል ቋንቋ Thesis ነው፡፡ ይህ የሆነ ነገር፤ አንድ ተቃራኒ ይገጥመዋል፤ ይህ አሁንም በሄግል ቋንቋ Anti-thesis ነው፡፡ የሁለቱ ቅራኔ እልባት አግኝቶ፤ ከሁለቱ የተለየ አንድ አዲስ ነገር ይፈጠራል፡፡ ይህም Synthesis ይባላል፡፡ ሄግል ይህን የThesis፣ የAnti-thesis እና የSynthesis ሂደት፤ ‹‹ዲያሌክቲክስ›› ይለዋል፡፡
ታዲያ በሄግል የዲያሌክቲክስ ፍልስፍና ልዩ ትኩረት በማድረግ፣ ምሁራዊ ምርምር የሚያደርጉ ቡድኖች፣ ‹‹ያንግ ሄግሊያን›› ይባላሉ፡፡ የዚህ ቡድን ማዕከላዊ ሰው ብሩኖ ባውር ይባላል፡፡ ባውር የዩኒቨርስቲ መምህር ነው፡፡ ይህ ሰው በኋላ የማርክስ ምሁራዊ ሞግዚት (Mentor) ሆኗል፡፡ ብሩኖ ባውር በጸረ-ሐይማኖት አቋሙ ተጠልቶ፤ ከዩኒቨርስቲ ሥራው ሲባረር፤ ማርክስ በዩኒቨርስቲ ተቀጥሮ ለመሥራት የነበረውን ህልም እርግፍ አድርጎ ተወው፡፡
ማርክስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲጨርስ ለአንድ ዓመት በቦን ዩኒቨርስቲ ከቆየ በኋላ ወደ በርሊን አመራ፡፡ በዚህ ጊዜ አባቱ የጻፉለት 17 ደብዳቤዎች አሉ። ሆኖም ማርክስ አባቱ ለጻፉለት በርካታ ደብዳቤዎች ምላሽ የሰጠው በአንድ ደብዳቤ ነው፡፡ ይህ ደብዳቤ የተጻፈው ኖቬምበር 10 1837 ዓ.ም (እኤአ) ነበር፡፡ ለወትሮው ለአባቱ የሚጽፈው ደብዳቤ አጭር ቢሆንም፤ ከአንድ ዓመት በላይ በበርሊን የህግ ፋካልቲ ከቆየ በኋላ ለአባቱ የጻፈው ከታች የምታነቡት ደብዳቤ ግን ረጅም ነው፡፡ ርዝመቱም ለደብዳቤው ትልቅ ግምት እንድንሰጠው የሚያደርግ ነው፡፡ ደብዳቤው በበርሊን በቆየበት አንድ ዓመት የተፈጠረውን የሐሳብ ለውጥ የሚያመለክትና የቀድሞ ሮማንቲካዊ ዘዬ ያለውን የራሱን ሐሳብ የሚተችበት ነው፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ለካንት (Kant) እና ፊች (Fichte) ሐሳባዊ ፍልስፍናዎች የነበረውን ፍቅር መተዉን ያሳየበት ደብዳቤ ነው፡፡ ደብዳቤው እንደሚከተለው ይነበባል፡፡
ውድ አባቴ፤
በአንድ ሰው ህይወት ውስጥ አንድ የጊዜ ምዕራፍ መዘጋቱን፤ እንዲሁም አንድ አዲስ ጎዳና መከፈቱን የሚያመለክቱ ቅጽበቶች መኖራቸው አይቀርም፡፡ በእንዲህ ያሉ የሽግግር ጊዜያቶች፤ በወቅቱ የምንገኝበትን ትክክለኛ ሁኔታ ለመረዳት፤ ያለፈውንና የአሁኑን ጊዜ በሐሳብ የንስር ዓይን ለመመርመር የሚያስገድድ ውስጣዊ ስሜት ይፈጠርብናል፡፡ አዎ፤ ራሷ ታሪክ እንዲህ ያለ ‹‹የንብረት ቆጠራ›› (stock-taking) እና የነፍስ ምርመራ ማድረግን ትወዳለች፡፡ ይህም ብዙ ጊዜ ታሪክ ወደ ኋላ እየተመለሰች ወይም ቀጥ ብላ የቆመች መስላ እንድትታይ ያደርጋታል፡፡ ሆኖም ታሪክ በእንዲህ ያሉ የሽግግር ጊዜያቶች የምታደርገው፤ ራሷን ለመረዳትና ምሁራዊ በሆነ አግባብ የራሷን የአዕምሮ ሂደት ለመገንዘብ ፋታ ለማግኘት ከሶፋ ላይ ዘፍ ብላ መቀመጥ ነው፡፡
በእንዲህ ያሉ የሽግግር ጊዜያት፤ ማንኛውም ሰው ስሜቱን በውብ ቋንቋ ለመግለጽ እንደሚሻ ገጣሚ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም፤ እያንዳንዱ ለውጥ፤ በከፊል የመጨረሻ ኪናዊ እንቅስቃሴ ሲሆን፤ በከፊል ደግሞ ገና መልኩ በግልጽ ባልተለየ ውብ ቀለም ራሱን ለመግለጽ ጥረት የሚያደርግበት አዲስ የኤፒክ ግጥም አዝማች ነው፡፡ ያም ሆኖ፤ ያላለፉ የህይወት ገጠመኞቻችን፤ በድርጊታችን ውስጥ ያጡትን ቦታ በስሜታችን ውስጥ ዳግም ያገኙ ዘንድ ለእነሱ ማስታወሻ እንዲሆን የመታሰቢያ ሐውልት ማቆም እንፈልጋለን። እናም መታሰቢያ ለማቆም ምቹ የሚሆነው ሥፍራ፤ በርኅራኄ የሚቀበል ገራም ዳኛ የሆነው፤ እጅግ ቅርብ የወዳጅነት ስሜት የሚያሳየውና የጥረታችንን ማዕከል በእሣቱ የሚያሞቅ፣ የፍቅር ፀሐይ ማደሪያ የሆነው፣ የወላጆቻችንን ልብ ነው፡፡ ከወላጆቻችንን ልብ የተሻለ ሌላ ቅዱስ ሥፍራ ከቶ ሊገኝ አይችልም፡፡
…..እናም ውድ አባቴ፤ እዚህ በኖርኩበት የአንድ የዓመት ጊዜ በህይወቴ የተከሰቱትን ነገሮች፣ ወደ ኋላ ዘወር ብዬ በማየት፣ ዓይኔን ጣል በማድረግ፤ ከኤምስ ለላክልኝ እጅግ የከበረ ደብዳቤ ምላሽ እንድሰጥና በሁሉም መንገድ (በሳይንስ፣ በኪነጥበብና በግለሰባዊ ጉዳዮች ጭምር) መገለጫ ባገኘው ምሁራዊ እንቅስቃሴዬ የተነሳ፣ የተፈጠረውን የህይወት ሁኔታዬን እንቃኝ ዘንድ ፍቀድልኝ፡፡ አንተን ትቼ ወዲህ በመጣሁ ጊዜ፤ በራሱ የመሻትና ተስፋ የማጣት ስሜት የሰከረ አዲስ ዓለም፣ ከፊቴ መደቀን ጀምሮ ነበር፡፡ ለወትሮው በፍጹም ደስታ ያጥለቀልቀኝ የነበረው፤ በተፈጥሮ አድናቆት ቀልቤን ይነሳኝ የነበረው፤ በህይወት በመኖር ጥልቅ ስሜት ይለኩሰኝ የነበረው ወደ በርሊን የሚደረግ ጉዞዬ እንኳን፤ ስሜት የለሽና ባይገርምህ ድባቴ ውስጥ እንድዘፈቅ ያደረገኝ ጉዞ ነበር፡፡ ምክንያቱም፤ በመንገዴ የማያቸው አለቶች ሁሉ ከነፍሴ ጥልቅ ስሜቶች በበለጠ ያገጠጡና ያፈጠጡ አልነበሩም። ሰፋፊዎቹ ከተማዎች ከእኔ ደም በበለጠ በህይወት የተሞሉ አልነበሩም። የምግብ ቤቶቹም ጠረጴዛም፣ እኔ ከተሸከምኩት የህልም ዓለም የሐሳብ ጓዝ፣ በበለጠ ሊፈጭ በማይችል ምግብ የተዝበጠበጡ አልነበሩም፡፡ እንዲሁም፤ የትኛውም የስዕል ሥራ፣ ከጀኒ የበለጠ ውበት ያለው አልነበረም፡፡
በርሊን እንደገባሁ፣ እስከዛ ጊዜ ድረስ የነበሩኝን ግንኙነቶችን ሁሉ በጣጥሼ ጣልኩ፡፡ አልፎ አልፎ ብዙም ደስ ሳይለኝ አንዳንድ ሰዎችን ለመጎብኘት ከመውጣት በቀር፤ በሳይንስና በኪነ ጥበብ ውስጥ እስከ ጥልቀ ለመግባት ሞከርኩ፡፡ በወቅቱ ከነበረኝ ስሜት አንጻር፤ የግድ የመጀመሪያ ፕሮጀክቴ ላደርገው የሚገባኝ፤ በጣም የሚያስደስተኝና በቀላሉ ልሰራው የምችለው ነገር በስሜት የተሞላ ግጥም መጻፍ ነበር። ነገር ግን ዝንባሌዬና ያለፈ ዘመን ዕድገቴ ግጥምን ፍጹም ከእውነት የራቀ ነገር አድርጎ አሳየኝ፡፡ ፈጣሪዬና ኪነጥበብ፤ እንደ ፍቅር ስሜቴ ሁሉ ወዲያ ያሉ የሩቅ ነገሮች ሆኑ፡፡ እውን የነበሩ ነገሮች ሁሉ እንደ ጨው ሟሙ፡፡ ውሱን ፍጥረት የመሆን ባህርያቸውን አጡ። አሁንን ማጥቃት ያዝኩ፡፡ ስሜቶች ያለ ገደብና ቅርጽ መገለጽ ጀመሩ፡፡ ሁሉም ነገር ህልም ሆነ፡፡ ‹‹በሆነው›› (what is) እና ‹‹ሊሆን በሚገባው›› (what ought to be) ነገር መካከል ፍፁም ተቃርኖ መኖሩን አመንኩ። ምንም እንኳን የተወሰነ የስሜት ሙቀትና የጨዋታ ፍላጎት ቢኖርም፤ የመልካም ንግግር ሐሳቦች፤ የግጥማዊ ሐሳቦችን ቦታ ወሰዱት፡፡ ለጀኒ የላኩላት ሦስት ቅጽ የሚሆኑ ግጥሞች ባህርይ እንዲህ ያለ ባህርይ ነበራቸው፡፡ የገደብ የለሹ ናፍቆት ሰፊ ግዛት በተለያዩ መንገዶች ይገለጻል፡፡ በመጨረሻም ግጥምን ያፈራል፡፡ ሆኖም አሁን ትኩረቴ የህግ ፍልስፍና ነው። …የእውነተኛ ግጥም ቤተ መንግስት፤ ከእኔ ማዶ ሆኖ በሩቅ ሥፍራ ያለ፣ የተረት ቤተ መንግስት መስሎ ያንጸባርቃል፡፡ መላ ፍጥረቴ እንደ በረዶ ሟሙቶ ወደ ምንምነት ተቀይሯል፡፡
እነዚህን የተለያዩ ሥራዎች ይዤ በመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት የትምህርት ዘመን፣ ለበርካታ ምሽቶች እንዳፈጠጥኩ ለማንጋት ተገድጄ ነበር፡፡ በበርካታ ትግሎች ውስጥ በውጊያ ውስጥ የማለፍ፤ ከውስጥ እና ከውጭ ከሚነሱ በርካታ የስሜት ጫናዎችን ጋር የመጋፈጥ  ዕዳ ተሸክሜ ነበር፡፡ ከተፈጥሮ፣ ከኪነ ጥበብና ከዓለም ሁሉ ብፋታም፤ ከጓደኞቼ ብራራቅም፤ በትግሉ መጨረሻ ብዙ የማገኘው ነገር አልነበረም። እነዚህ ሐሳቦች በሙሉ በሰራ አካላቴ ተመዝግበው ነበር፡፡ እናም ዶክተሩ ወደ ገጠር አካባቢ እንድሄድ መከረኝ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ጠቅላላ ከተማውን ከእግር እስከ ራሱ አሰስኩት፡፡ እናም በከተማው በር ወደ ውጭ ወጣሁ፡፡ እንዲያ የዛለውና የተዳከመው ሰውነቴ መልሶ ኃይል አግኝቶ ይታደሳል የሚል ጥርጣሬ አልነበረኝም። …24 ገጽ የሚሆን ቃለ ምልልስ ጻፍኩ፡፡ … እዚህ ኪነጥበብና ሳይንስ ህብረት አገኙ፡፡ ቁጣ ነገሰብኝ፡፡ ቁጣዬ ለበርካታ ቀናት ማሰብን ከለከለኝ፡፡ ‹‹ነፍሳትን በሚያጥበውና የማያመረቃ ሻይ በሚያፈላው›› የመቅበዝበዝ ቆሻሻ ውሃ ከሚገኝበት ሥፍራ አጠገብ ባለው የአትክልት ቦታ እንደ አበደ ሰው ተሯሯጥኩ፡፡ ከቤት አከራዬ ጋር ለአደን ሄድኩ፡፡ ከዚያም በጥድፊያ ወደ በርሊን ተመለስኩ፡፡ እያንዳንዱን ሽማግሌ የጎዳና ተዳዳሪ እያቀፍኩ መሳም ፈለግኩ፡፡ …ውድ አባቴ ቀደም ሲል እንደጻፍኩልህ፤ በጀኒ መታመም፤ ፍሬ አልባና ከንቱ ድካም ሆኖ በቀረው ምሁራዊ ጥረቴና ሰውነትን በሚመዘምዘው የቁጣ ስሜቴ የተነሳ ታመምኩ። ከህመሜ ሳገግም፣ ሁሉንም ግጥሞቼንና ልቦለድ ለመጻፍ የሰራሁትን ቢጋር ወዘተ አቃጠልኩት፡፡ በዚህ የህመም ጊዜዬ፤ ሄግልን ከነደቀመዛሙርቱ፣ ከጫፍ እስከ ጫፍ ለመረዳት ጥረት ማድረግ ነበረብኝ፡፡ ከጓደኞቼ ጋር ስትራሎው ውስጥ በማደርገው ስብሰባ አማካኝነት በርካታ የዩኒቨርስቲ መምህራንና በጣም የቅርብ ወዳጄ የሆነው ዶ/ር ሩተንበርግ አባል በሆኑበት አንድ ክበብ ውስጥ ለመቀላቀል ቻልኩ፡፡ በዚህ ክበብ በሚደረጉ ውይይቶች በርካታ ተቃርኖ የሞላባቸው አስተያየቶች ይቀርባሉ፡፡ በዚህ መድረክ በጣም ልሸሸው ከምፈልገው የወቅቱ የፍልስፍና ዘዬ ጋር ይበልጥ ተጣበቅኩ፡፡
እናም በቤተሰባችን ላይ ያንዣበበው ደመና ቀስ በቀስ ገለል ይላል በሚል ተስፋ፤ ከአንተ ጋር የመሰቃየትና አብሬ የማልቀስ ዕድል አላጣም በሚል ተስፋ፤ ምናልባትም ብዙ ጊዜ በማይመች ሁኔታ በምገልጸው ለአንተ ያለኝ ወደር የሌለው ፍቅር፤ ጥልቅ እንዲሁም እውነተኛ ለሆነ ለአንተ ያለኝ መውደድ ተጨባጭ ማስረጃ ይሆናል በሚል ተስፋ፤ በተጨማሪም አንተ እጅግ አብዝቼ የምወድህ አባቴ፣ በጣም ብዙ ጊዜ ረብሻ የማያጣውን የህሊናዬን ሁኔታ ከግምት ታስገባልኛለህ በሚል እና በተዋጊ መንፈሴ ተሸንፎ ልቤ ለስህተት የተዳረገ መስሎ በሚታይበት አጋጣሚ ሁሉ ይቅርታን ታደርግልኛለህ በሚል ተስፋ፤ እንዲሁም ጤናህ በፍጥነት ሙሉ በሙሉ ተመልሶ ወደ ልቤ አስጠግቼ እቅፍ አድርጌህ፣ ሁሉን ነገር እነግርሃለሁ በሚል ተስፋ፣ ይህን ደብዳቤ ጽፌአለሁ፡፡
ዘላለም የሚወድህ ልጅህ ካርል  

Read 730 times