Sunday, 03 June 2018 00:00

“መኝታ ቤት Show”

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(2 votes)


    ካሜራው “Close in” አድርጎ ሲቀርብ ትልቅ አልጋ ያሳያል፡፡ አልጋው እራስጌ ላይ “መኝታ ቤት Show” የሚል ፅሑፍ ላይ ያተኩራል፡፡ የአልጋውን የራስጌ ቅርፃ ቅርፅ የሰራው አናጢ የተጣመመ አክሱም ሐውልት፤ የገዘፈ የዋሊያ አይቤክስ ፍየል በሚያስፈራ መልክ አስቀምጧል፡፡ ይኼ የሚታየው መሀል ላይ ከተሰቀለው የጥያቄ ምልክቱ “መኝታ ቤት Show” መግለጫ ፅሑፍ በስተግራ ነው፡፡ በስተቀኝ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን በአንድ ጎን፣ከአጠገቡ ደግሞ አንድ ብር ላይ ያለው የባላገር ወጣት፣ፊቱን በቦታ እጥረት ምክኒያት፣ አብያተ ክርስቲያኑን አገጩ ስር ከቶታል፡፡
ካሜራው እነዚህን ያሉ ምስሎች እያሳየ አልጋው ላይ ብርድልብስ ለብሳ ወደ ራስጌው ተደግፋ ወደተቀመጠችው ወጣት ሴት እስኪወርድ ቀጭን በሆነ በስልክ የተከፈተ በሚመስል የጂጂ ሙዚቃ ታጅቦ ነው፡፡ ከዛ የልጅቱን ፊት እያሳየ ካሜራው ወደ ኋላ ቀስ እያለ ሙሉ ክፍሉን ወይም እስቱዲየውን ለማሳየት ሸሸት እያለ ይሄዳል፡፡ ሲሄድ የሆነ ነገር እንዳደናቀፈው ካሜራው ይንገጫገጭና ምስሉ ይናጋል፡፡ ከዛ ወዲያው ይስተካከላል፡፡ እስኪስተካከል ካሜራ ቀራጩ ሲራገም ይደመጣል፡፡
ምስሉ ሲስተካከል አልጋው ሙሉ ለሙሉ ይታያል፡፡ ወጣቷ ሴት ብርድልብስ ባለበሰችው እግሯ ላይ ያስቀመጠችውን ወረቀት እያስተካከለች፣ ስልኳን አንስታ ሙዚቃውን ታጠፋዋለች፡፡ ወደ ካሜራው እየተመለከተች፡-
“እንደምን ከርማችኋል ክቡራትና ክቡራን የፕሮግራማችን ተከታታዮች … ይሄ ዘወትር ከዚህ የኮንዶሚኒየም እስቱዲዮ የማስተላልፍላችሁ “መኝታ ቤት Show” የተባለው ተወዳጅ ፕሮግራም ነው። ፕሮግራሙን ይዤላችሁ የምቀርበው ሚጣ አስጨናቂ ነኝ፡፡” ብላ የሞባይል ስልኳን ትጫነዋለች። ዜና ከመነበቡ በፊት የሚሰማው አይነት ከበሮ የበዛበት፣ በጋጋታ የሙዚቃ አቀናባሪ የተቀመረ የሚመስል ሙዚቃ፣ በሚወጋ ድምፅ ክፍሉን ለመሙላት ይሞክራል፡፡ ትንሽ ከተሰማ በኋላ ሚጣ ስልኳን ታጠፋውና እሷ ላይ ለማተኮር በመሞከር የሚንቀጠቀጠው ካሜራ ላይ መልሳ ታተኩራለች፡፡
“ለዛሬ የፕሮግራማችን ተከታታዮች ይመጥናሉ ብለን ያዘጋጀናቸውን መሰናዶዎች ወደናንተ ከማለታችን በፊት አንድ ምርጥ ሙዚቃ እናስደምጣችኋለን” ብላ እስማርት ስልኳን በድጋሚ አንስታ ትንሽ በጣቷ ወደ ላይ እና ወደ ታች ካንፏቀቀች በኋላ የማይክል ጃክሰንን “Beat it” ሙዚቃ ትከፍታለች፡፡ ድምፁን ከፍ ስታደርገው የካርቱን ፊልም ላይ አይጦች ሲዘፍኑ ዓይነት --ቅላፄ፣ የዘፋኙን ምርጥ ሙዚቃ የቀልድ ያደርገዋል፡፡ ስልኳን ከፍ አድርጋ ስትይዝለት ካሜራ ማኑ ጠጋ ብሎ ስልኳን ለመቅረፅ መሞከር ጀመረ፡፡ ካሜራ ማኑ እየቀረፀ ያለው በራሱ ስልክ መሆኑን እንዳይታወቅ ከፍተኛውን ጥንቃቄ እያደረገ በመሆኑ፣ በስልኩ የሚቀዳው ክሊፕ በደንብ ቀረፃው ላይ ባይገባለት አይገርምም፡፡ ሚጡ ከያዘችው ስልክ ዝቅ እያለ በለበሰችው ፒጃማ ወጣ ያሉትን ጡቶቿን ወይም ከፍ እያለ የተደፈጠጠ አፍንጫዋንና ያልተላጨ ቅንድቧን ማሳየቱ አልቀረም፡፡
ሙዚቃው ሲጠናቀቅ ካሜራ ማኑ ወደ ቀድሞ ቦታው ተመለሰ፡፡ እያነከሰ፡፡ ካሜራው ወደ ኋላ ሲመለስ ከሚጡ በስተግራ እስካሁን ተሸፋፍኖ የተኛ ሰው፣ ሽፍንፍኑን ገልጦ በአልጋው ተንጠልጥሎ ተኝቶ ማሳየት ጀመረ፡፡ የተኛው ወጣት እድሜው በሃያዎቹ የሚገመት ሲሆን የተገለጠው እጁ የፈረንጅ ሀገር ዱርዬዎች በሚያዘወትሩት ንቅሳት ተዥጎርጉራል፡፡ ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ መሆኑን አፉን ገርበብ አድርጎ በከፈተበት መንገድና በአተነፋፈሱ  ማወቅ ይቻላል፡፡
የተጋበዘው ሙዚቃ ሲያልቅ፣ ሚጡ ስልኳን አስቀምጣ፣ ወረቀቷን አነሳች፡፡ ወደ ካሜራው ፈገግታዋን ደመቅ አድርጋ አተኮረች፡፡
“እንግዲህ ተመልካቾቻችን --- ባዳመጣችሁት ሙዚቃ እንደተዝናናችሁ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡ ማይክል ጃክሰን ነበር ጊዜ በማይሽረው የጥበብ እጆቹ የዳሰሰን … Beat it! … እያለ፡፡ እንደሚታወቀው ማይክል ጃክሰን የፖፕ ሙዚቃ ስልትን በአለም ላይ ያስተዋወቀ፤ በቅርቡ ደግሞ በሞት በአፀደ ስጋ የተለየን የማይተካ የጥበብ አጎታችን ነበር፡፡ … በተከታይ የምናልፈው ወደ ሳምንታዊ የጭውውት ፕሮግራማችን ነው፡፡ በዛሬው ፕሮግራማችን እንግዳ አድርገን የጋበዝነው እውቁን ገጣሚ ኮከብ አጢስን ነው፡፡ ኮከብ አጢስ በዘመናችን ከተፈጠሩ፣ የትውልዳችንን እስትንፋስ በግጥም ካከሙ ወጣቶች አንዱ ነው፡፡ … ግን እንግዳችንን ወደ መድረክ ከመጋበዛችን በፊት በቀድሞዎቹ ዘመን ተወዳጅ ከነበረ አንድ የመድረክ ጭውውት ላይ ቀንጨብ አድርገን እናስደምጣችኋለን--” ብላ ወደ ስልኳ ሄደች፡፡ ስልኳ ላይ ጭውውቱን ፈልጋ  ስታገኘው፣ በእልህ ልክ የበላውን ቁንጫ ይዞ በጥፍሮቹ መሀል እንደሚጨፈልቅ ሰው፣ ከንፈሯን ነክሳ ስልኳን ተጫነችው፡፡ ካሜራ ማኑ ተጠግቶ መቅረፅ ሲኖርበት፣ በቆመበት ቀረ፡፡ ሚጡ ስልኩን ከፍ አድርጋ ይዛለት፣ በጭንቅላቷ እንዲጠጋ ምልክት ሰጠችው፡፡ አልታዘዝ አላት፡፡ የሆነ ነገር ሆኗል፤ ምን እንደሆነ ባይታወቅም፡፡ የሆነውን ነገር በምልክት እየገለፀላት እያስረዳት እንደነበር፣ ፊቷን ላለማኮሳተር በምታደርገው ጥረት መረዳት ይቻላል፡፡ ስልኩን በአየር ላይ ከፍ አድርጋ ይዛ ትንሽ ቆየች፡፡  …. ደግነቱ ጭውውቱም አጭር ስለነበር አለቀ፡፡
አልጋው ላይ ተጋድሞ በሀይል የሚተነፍሰውን ሰው ሚጡ ዞራ ላለመመልከት እየጣረች ትመስላለች፡፡ ልክ እርቃኑን የቆመ እብድን በመንገድ የሚያልፉ ሰዎች እያዩ እንዳላዩ ለመሆን እንደሚጥሩት፡፡
“…እነሆ በጉጉት ወደምትጠብቁት እንግዳ የምንሻገርበት ወቅት ደርሷል፡፡ እስቲ በጭብጨባ የሳምንቱን እንግዳችንን ወደ መድረኩ እንጋብዘው” ስልኳን እና ወረቀቱን በዘረጋችው እግሯ ላይ ጣል አድርጋ፣ ማጨብጨብ ጀመረች፡፡ ከእሷ ጭብጨባ ሌላ የሚያጅብ አልነበረም፡፡
ከጎኗ የተኛው ወጣት ግዙፍ ሰውነት ያለው መሆኑ ያስታውቃል፡፡ እግሮቹ ረዝመው የአልጋው ጥግ ደርሰዋል፡፡ የሚጡ እግሮች ግን አልጋው መሀል እንኳን ሳይደርሱ በአጭር ቀርተዋል፡፡ ምናልባት ያጠረችው ራስጌውን ስለተደገፈች ሊሆን ይችላል፡፡
ተጋባዥ እንግዳው ጭብጨባ እንደበዛበት ሰው፣ ከወገቡ ጎንበስ እያለ እጁንም በሰላምታ እያወዛወዘ ገባ። በተኛው ወጣት በኩል በሽተኛ ጠያቂ በሚቀመጥበት ወንበር ላይ ትሁት በሆነ መንገድ እጁን በእግሮቹ መሀል አቆላልፎ፣ አንገቱን ዝቅ አድርጎ፣ መሬት መሬት እየተመለከተ፣ የተቀመጠበት ወንበር ላይ የተኛው ሰው ያወለቃቸው ሸሚዝ፣ ሱሪ፣ ክራባትና ኮት ተሰቅለውበታል፡፡ … በተንጠለጠለው ሱሪ ኪስ፣ የመቶ ብር ኖት ወጣ ብሎ ይታያል፡፡ እንግዳው የተቀመጠበት ወንበር ስር ወድ በሱፍ ልብስ ብቻ የሚደረግ ጥንድ ጫማ ማሰሪያዎቻቸው ላልተው ጣል ተደርገዋል፡፡
የፕሮግራሙ አዘጋጅ፣ ከአልጋዋ ሳትወርድ ተጋባዥ እንግዳውን ለማቀፍ ስትንጠራራ፣ ተንደርድሮ ታቀፈ፡፡ በተኛው ሰው ጉልበት ላይ ተመርኩዞ፡፡ ከዛ ወንበሩ ላይ ተቀምጦ መጠበቅ ያዘ - የሚቀርብለትን ጥያቄ፡፡ ካሜራ ማኑ ከተገተረበት ተንቀሳቅሶ የቀረፃ አንግሉን ቀየረ፡፡ ተጋባዡን እንግዳና ሚጡን በአንድ ላይ ለማግኘት የሚያስችለው የቀረፃ አንግል ላይ ተመቻቸ፡፡ ቀረፃውን ከመሬት ይጀምርና እንግዳው ላይ እንደ ጉንዳን፣ ቀስ እያለ፣ በሰውነቱ ላይ ወጥቶ ፊቱ ላይ ይቆማል፡፡ ከዛ ደግሞ ከእንግዳው ፊት ወርዶ፣ በአልጋው ላይ አድርጎ … በተኛው ሰው ፊት ላይ ትንሽ ቆም ብሎ ያተኩራል፡፡ ቆም ብሎ፣ የተኛው ሰው ጉንጭ ላይ ተቀምጣ፣እየመጠጠችው ያለችው ቢንቢ ላይ ከርሞ … ከዛ ደግሞ ይንቀሳቀሳል፡፡ ተንቀሳቅሶ በደብረብርሃን ብርድልብሱ ላይ ያሉትን የዳማ ካሬዎች ይዞ፣ በሲጋራ ትርኳሽ የተበሱ ቀዳዳዎችን እየተሻገረ … ሚጡ አካል ላይ ይወጣል፡፡ ወጥቶ ፊቷ ላይ ይቆማል። ቆሞ ይቀርና ትዝ ሲለው ወደ እንግዳው፣ እንደ አመጣጡ ይመለሳል፡፡
መሬቱ ላይ ሁለት ጥቁር ካልሲዎች በተለያየ አቅጣጫ ወድቀዋል፡፡ ለቃለ መጠይቅ የተጋበዘው እንግዳ በአይኑ የሆነ የሚፈልገው ነገር እንዳለ ዙሪያ ገባውን ይመለከታል፡፡ ሽንት የሞላውን ፖፖ ሲያጣው  አልቤርጎ አለመሆኑ ትዝ አለው፡፡ ጥሞናውን ሰብስቦ፣ ሚጡ የምትጠይቀው ጥያቄ ላይ አተኮረ፡፡
“የገጣሚነት ህይወት ከባድ ነው ይባላል፡፡ … ግጥምን እየፃፉ ብቻ መኖር እንዴት ነው? ያስቸግራል?”
“በጣም አስቸጋሪ ህይወት ነው፤ ለጥበብ ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈል የፈለገ ሰው ብቻ ነው ገጣሚ የሚሆን የሚመስለኝ፡፡ … በቃ መቅደስ ውስጥ የማይኖር፣ ደብር የሌለው መንፈሳዊ ሰው መሆን ማለት ነው ገጣሚነት፡፡ … በደብር ስም ብትለምኝ ሰው ይሰማሻል፤ በግጥም ስም የምታደርጊው መስዋዕትነት ግን እንደ ስራ ፈትነትም ሊቆጠርብሽ ይችላል፡፡ … እንዴት ብዬ ላስረዳሽ--” ብሎ በአይኑ የመግለጫ ቃላት ሲፈልግ፣ በተኛው ወጣት ጉንጭ ላይ ተቀምጣ የምትመጠው ቢንቢ፣ እንደ ሲሪንጅ ደሙን ስትስብና እየሞላች ስትመጣ ይታየዋል፡፡ … በጥፊ መትቶ ሊገድላትና ባለሀብቱንም በአንድ ላይ ለመቅጣት ፈለገ።
“እንዴት ላስረዳሽ …” ብሎ እንዳቋረጠ እንዲቀር ወይም እንዲቆይ ሚጡ ምልክት ሰጠችው፡፡ “ቆይ እሱን ሀሳብ እንደያዝክ ቆየንና፣ አንድ ማስታወቂያ ሰምተን እንመለስ” ብላ ከተጋደመችበት ተንጠራርታ፣ በተኛው ወጣት በኩል የተቀመጠ የቢራ ጠርሙስ አነሳች፡፡ ካሜራ ማኑ በእጇ የያዘችውን ጠርሙስ፣ ወደ ቀራጩ ካሜራ አስጠግታ  እያሽከረከረች፣ በሚስረቀረቅ ዜማ፣ ቢራው ላይ የተለጠፈውን ስያሜ እያሞጋገሰች ዘፈነች። ከዛ ወደ አልጋው ተመልሳ፣ ብርድልብሱን ለብሳ፣ ለቃለ መጠይቁ ተዘጋጀች፡፡
“አሁን ወደ ጭውውታችን ተመልሰናል … ዛሬ በእስቱዲዮአችን ታዋቂው ገጣሚ ኮከብ አጢስን እንግዳ አድርገን ይዘን ቀርበናል፡፡ … ኦው! ስልክ እየጠራ ነው፣ አድናቂዎችህ አስተያየት ለመስጠት እየደወሉ መሆን አለበት፡፡ ሄሎ ማን ልበል? አዎ ይሰማል፣ ቀጥይ ስምሽን ማን ልበል? …እ አዛለች ከዚሁ አካባቢ--”
የስልኩን ድምፅ “Loud speaker” ላይ አደረገችው፡፡
“… አዛለች እባላለሁኝ፡፡ የተጋበዘው እንግዳ አድናቂ ነኝ፡፡” ድንገት የህፃን ልጅ ጩኸት እስቱዲዮውን አናወጠው፡፡ ጩኸቱ ከስልኩ ይሁን ከስቱዲዮው መናገር አይቻልም፡፡
“አዛለች! ሬዲዮኑን አጥፊው” ትላለች ሚጡ፡፡
“ሬዲዮ የለም፡፡ አቢ ነው፡፡ … እና እንግዳው ግጥሙን እንዲያነብልን ለመጠየቅ ነው፣ ደውይ እንዳልሽኝ የደወልኩት” ስልኩ ተዘጋ፡፡ ቀጥሎ ሚጡ እያጨበጨበች--- ገጣሚው ወረቀቱን ከካልሲው ለጣጥፎ ካስቀመጠበት፣ አውጥቶ ዘርግቶ ለማንበብ ተነስቶ ቆመ፡፡ ገጣሚው ወረቀቱን   ሲያነብ … ካሜራው ሙሉ ለሙሉ እሱ ላይ አተኮረ፡፡
ካሜራው በማይቀርፀው ጎን፣ ሚጡ በቀስታ ከአልጋው ወጥታ፣ አንዱ የክፍሉ ጥግ ህፃን እያጠባች እሹሩሩ የምትለዋን ሰራተኛዋን (አዛለችን)፤ የሌባ ጣቷን እያወዛወዘች እየተቆጣቻት ነው፡፡ “ደውይ እንዳልሽኝ ትያለሽ?! … ደሞዝሽን ባልቆርጥ እኔ አለሚቱ አይደለሁም …” እያለቻት ነው፡፡ ሚጡ ራሷን ስትጠራ በድሮ ስሟ ነው፡፡ እናቷ ባወጣችላት፡፡ ከተማ ስትገባ የለወጠችው ስም፣ “እኔ” ብላ ልትዝት ስትል አይመጣላትም፡፡
ገጣሚው ግጥሙን አንብቦ ከመጨረሱ በፊት ወደ አልጋዋ ገብታ ተስተካክላ ጠበቀች፡፡ ካሜራው ወደሷ ሲመጣ በጣም እያጨበጨበች ተፍነከነከች፡፡
“እንግዲህ ተመልካቾቻችን፤ በዛሬው ፕሮግራም እንደተዝናናችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት በተመሳሳይ ፕሮግራም እስክንገናኝ በፕሮግራሙ አዘጋጆች ስም የምሰናበታችሁ ሚጡ ነኝ፡፡” በተቀመጠችበት ጎንበስ ብላ እጅ እየነሳች፣ በሌላ እጇ የሂሩትን “ስምህን ጠርቼ” የሚለውን ዘፈን ከፈተች፡፡ አልጋው ላይ ወርወር አድርጋ የሙዚቃው ክሊፕ የሚታይበትን ስልክ አስቀመጠችው፡፡፡ ካሜራ ማኑ አልጋው ላይ የተወረወረውን ስልክ ተጠግቶ መቅረፅ ጀመረ፡፡
ካሜራው እያተኮረበት እንዳልሆነ ሲያውቅ ተጋባዥ እንግዳው አልጋው ላይ ሰክሮ ወደሚያንቀላፋው የፕሮግራሙ የዘወትር እስፖንሰር እየጠቆመ፣ ሚጡን ጠየቃት፤ “ኢናው ምን ሆኖ ነው?”
“መጠጥ ጠጥቶ--” የሚለውን በእጇ እንቅስቃሴ፣ ብርጭቆ ይዛ መገልበጥን እያሳየች፣ መልስ ሰጠችው፡፡
“እከፍልሀለው ያልሽኝስ ገንዘብ?”
“እሱ ሲነቃ ጠይቀው!”  አሁንም በዱዳ ምልክት ጠቆመችው፡፡
“መቼ ነው የሚነቃው?” አላት ገጣሚው፤ ቅድም ቢንቢዋን ገድሎ በዛውም የፕሮግራሙን እስፖንሰርና ባለቤት ሊቀሰቅስ ይችል የነበረበት አጋጣሚ ማምለጡ  እየቆጨው፡፡
… “ምናልባት የአዲስ ዓመት ፕሮግራም ሲዘጋጅ ሌሎች እስፖንሰሮች ብርና ማስታወቂያ ይዘው በሚመጡ ሰዓት ተመለስ” አለችው፤ እግሯ ላይ ያለውን የተበታተነ ወረቀት ሰብስባ ወደ አንድ ሥርቻ እየወረወረችው፡፡  
ተጋባዡ እንግዳ፣መናጢው ገጣሚ፣ወንበሩ ላይ ከተሰቀለው የሱፍ ሱሪ ኪስ አምልጣ የወጣችውን መቶ ብር መላልሶ አያት፡፡ ቀስ ብሎ ሳያስነቃ መዝዞ፣ ከሩጫ ባልተናነሰ እርምጃ ተፈተለከ፡፡ ሚጡ ካሜራ ማኑ በስልኩ የእሷን ስልክ ሲቀርፅ እያየች፣ ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት  ከፍታ ግማሽ ያደረሰችውን ቢራ ጨረሰች፡፡ ቢራው፤ በማስታወቂያው ላይ አሞካሽታ የዘፈነችለት አይደለም፡፡ ብር የሚሰጣት ቢራ ጣዕሙን የማትወደው ነው፡፡ የፋብሪካው ባለቤት ራሱ አይወደውም፡፡
ከጎኗ ተኝቶ የሚያንኮራፋው የፕሮግራሙ እስፖንሰር ፕሮዲዩሰር …. ሌላ ያላመረተውን መጠጥ ጨልጦ ነው የሰከረው፡፡ የሰራተኛዋን ደሞዝ መቀነስ እንዳለባት ደግማ ዛተች፡፡ ደሞዝ ስትጨምርላት ሁሌ ታረግዛለች፡፡ አንዴ ወልዳ አሁንም ልትደግም ነው፡፡ ካሜራ ማኑ ዘበኛዋ ነው፡፡ ዘበኛዋን ካሜራ ማን …. ሰራተኛዋን ሴክረተሪ አድርጋ ልታሳድጋቸው ብትሞክር …. ደሞዝ ብትጨምርላቸው፣ እርስ በራስ ተጋብተው፣ ፕሮግራሟን የህፃን ልጅ ጩኸት አደረጉባት፡፡ ደግሞ ትዕቢታቸው፡፡ ዘበኛውም አልታዘዝም የማለት አዝማሚያ እያሳየ ነው፡፡ የሚቀጥለው ፕሮግራም ላይ አንዴ ይሰራላትና ከዛ ሌላ ምትክ ትፈልጋለች፡፡ ቢራዋን ጠጥታ ስትጨርስ ዘበኛው ወጥቶ፣ ሚስቱና ልጁ ወደሚላቀሱበት ጓዳ ገባ፡፡ ሚጡም  ያለ ፍላጎቷ ዞራ፣ እስፖንሰሯን አቀፈችው፡፡ ግን ሰውየው ከእንቅልፉ አልነቃም፡፡     


Read 3756 times