Saturday, 02 June 2018 11:45

1.2 ቢ. የአለማችን ህጻናት የድህነትና ግጭት ሰለባ ሆነዋል ተ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ለህጻናት ምቹ አገራት፡- ሲንጋፖር፣ ስሎቬኒያ፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን

   በመላው አለም ከሚገኙት ህጻናት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ወይም 1.2 ቢሊዮን ያህሉ የድህነት፣ ግጭት ወይም ጾታዊ መድልኦ ሰለባዎች መሆናቸውን አለማቀፉ የረድኤት ተቋም ሴቭ ዘ ችልድረን፤ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው አለማቀፍ ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በአለማችን አንድ ቢሊዮን ህጻናት በድህነት በተጠቁና 240 ሚሊዮን ህጻናት ግጭት ባለባቸው አገራት ይኖራሉ ያለው ሪፖርቱ፤ 575 ሴት ህጻናት ደግሞ ጾታዊ መድልኦ በተንሰራፋባቸው አገራት ውስጥ እንደሚኖሩ አመልክቷል፡፡
ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የአለማችን ህጻናት ድሃ በመሆናቸው፣ በጦርነት አካባቢዎች በመኖራቸውና ሴት በመሆናቸው ሳቢያ የከፋ ህይወት እየመሩ ይገኛሉ ያለው የተቋሙ ሪፖርት፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ የጉልበት ስራና የምግብ እጥረትም የአለማችንን ህጻናት ክፉኛ እየፈተኑ ከሚገኙ ተግዳሮቶች መካከል እንደሚገኙበት አመልክቷል፡፡
ሴቭ ዘ ችልድረን በ175 የአለማችን አገራት ላይ የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ባወጣው ሪፖርት፤ ምንም እንኳን ካለፈው የፈረንጆች አመት ጋር ሲነጻጸር ዘንድሮ በአብዛኞቹ የአለማችን አገራት፣ የህጻናት የችግር ተጋላጭነት ቢቀንስም፣ በ40 አገራት ግን ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉን አስታውቋል፡፡
ህጻናት በከፍተኛ ሁኔታ ለድህነት፣ ግጭትና ጾታዊ መድልኦ የተጋለጡባቸው ቀዳሚዎቹ የአለማችን አገራት ሁሉም ከአፍሪካ ናቸው ያለው ሪፖርቱ፤ ኒጀር፣ ማሊና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃን መያዛቸውን አመልክቷል፡፡ ለህጻናት ምቹ የተባሉት የአለማችን አገራት በአንጻሩ ሲንጋፖር፣ ስሎቬኒያ፣ ኖርዌይና ስዊድን ናቸው፡፡

Read 1362 times