Sunday, 03 June 2018 00:00

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ምን ይላሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

• ግድቡን ዳያስፖራው ብቻውን ሊገነባው ይችል ነበር
• በውጭ ያለው ዳያስፖራ ሃገሩን ከልቡ የሚወድ ነው
• እኛ የተቃዋሚነት ሱስ የለብንም

    የ”አርበኞች ግንቦት 7” ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ባለፈው ማክሰኞ ነው ከ4 ዓመት እስር በይቅርታ የተፈቱት፡፡ አቶ አንዳርጋቸውን ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ይዞ የመጣው ቶዮታ ላንድ ክሩዘር፣ ባለ ጥቁር መስታወት መኪና፣ ቦሌ የሚገኘው ቤተሰባቸው ቤት ሲደርሱ፣ ለአቀባበል የተሠለፈው ህዝብ፤ ከፍተኛ ጩኸትና ሆታ በማሠማት ነበር ተሽከርካሪዋን የከበቧት፡፡ ፎቶግራፍና “ላንቺ ነው ኢትዮጵያ” የሚል ፅሁፍ የታተመበት ቲ-ሸርት በለበሱ የቤተሰብ አባላትና ደጋፊዎቻቸው የደመቀው የአቀባበል ስነ ስርዓት፤ ከእሁድ ጀምሮ ከእስር እስከተፈቱበት ማክሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2010 ዓ.ም አመሻሽ ድረስ የዘለቀ ነበር። ለሦስት ተከታታይ ቀናት ያለ መታከት አቀባበል ለማድረግ ሲጠብቅ የነበረው ደጋፊያቸው፣ እፎይታ ያገኘው ማክሰኞ አመሻሽ 11፡00 ገደማ ነበር፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ይዛ የመጣችው ቶዮታ ላንድ ክሩዘር፣ ባለ ጥቁር መስታወት መኪና በአካባቢው ስትደርስ ለአቀባበል የተሠለፈው ህዝብ ከፍተኛ ጩኸትና ሆታ በማሠማት ነበር ወዲያው ተሸከርካሪዋን የከበቧት፡፡
ከብዙ ግፊያና ፍትጊያ በኋላ አቶ አንዳርጋቸውን የጫነችው ተሽከርካሪ ወደ ግቢው ዘለቀች፡፡ አቶ አንዳርጋቸውም የመኪናዋን የኋላ በር ከፍተው ወጡ። ወጣቱም በሸክም ተቀብሎ ከመኪናዋ አወረዳቸው። ተሸክሞም ወደ ተዘጋጀላቸው ማረፊያ ክፍል ወሠዳቸው፡፡ በዚህን ወቅት አካባቢው በሆታና በእልልታ ደምቆ ነበር፡፡ ለክብራቸውም ረዘም ያሉ ደቂቃዎች የወሠደ ርችት ተተኩሷል፡፡
በጉጉት ሲጠበቁ የነበሩት እንግዳ፣ የተወሠኑ ደቂቃዎች ካረፉ በኋላ፣ ለህዝቡ ንግግር ሊያደርጉ ወደ በረንዳው ብቅ አሉ፡፡ በግቢው ውስጥ ብቻ በግምት ከ1 ሺህ በላይ ደጋፊዎቻቸው ነበሩ፡፡ አቶ እንዳርጋዛው የቤታቸው ደጃፍ በረንዳ ላይ ወጡ፡፡ ንግግራቸውንም እንዲህ ሲሉ ጀመሩ፤ “ሁላችሁንም እወዳችኋለሁ፤ እኔ ተዘግቼ ስለነበረ ምን እየተካሄደ እንደነበር አላውቅም። እንዲህ ያለ አቀባበልና ዝግጅት የሚያደርግልኝ ሰው ይኖራል ብዬ አልገምትኩም፤ በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን ስለ እኔ እንደሚጨነቁ አውቃለሁ፤ ግን እናንተ ያልገመትኩትን ነገር ነው ያደረጋችሁት፤ እወዳችኋለሁ አከብራችኋለሁ፤ ለእናንተ ጥቅም ለእናንተ መብት፣ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ መብትና ጥቅም መከበር፣ የታሠርኩበት ጊዜ ያንስ እንደሆነ እንጂ አይበዛም” ብለዋል፡፡
አቶ አንዳርጋቸው በዚህ አላበቁም፡፡ “በአቀባበሉ ላይ በተገኙ ወጣቶች ተደጋግሞ ስለ ሚዜመው ‹ላንቺ ነው ኢትዮጵያ› ስለሚለው ግጥም ጥቂት እንዳብራራ ይፈቀድልኝ፤ ግጥሙ ውስጥ ‹በባርነት ሸክም/ ጀርባሽ ለጎበጠው› የሚል አለ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ወደ አረብ ሃገራት ስሄድ የማያቸው ኢትዮጵያውያን አሉ፤ እህቶቼን በየኤርፖቱ አገኝ ነበር፡፡ በአንድ አጋጣሚ ግን እድሜዋ 18 ቢሆን ነው፤ ዱባይ ኤርፖርት ውስጥ ቁጭ ብላ ታለቅሣለች፡፡ እኔ ወደ ሌላ ቦታ ነው የምሄደው። አጠገቧ ተጠግቼ ላናግራት ብሞክር፣ ልታናግረኝ አልቻለችም፡፡ አባባልኳት፡፡ በእውነት ፊቷ ላይ ያለውን መከራና ስቃይ ለተመለከተ፣ መፈጠሩን ነበር የሚጠላው፡፡ በስንት ማባበል አንድትናገር አደረግኋት። ልጅቷ ከሀገር ቤት ወደ ዱባይ የተላከችው በቤተ ዘመድ መዋጮ ነው፡፡ መጨረሻ ላይ ይህን አለችኝ፤ ‹በተቀጠርኩበት ቤት አንድ ሽማግሌና አራት ለአቅመ አዳም የደረሡ ወንድ ልጆች፣ ደስ ባላቸው ሰዓት፣ ተራ በተራ እየተፈራረቁ ይደፍሩኛል› አለች፡፡ ይሄ ግጥም የመጣው በዚህ መነሻ ነው፡፡ “በባለጌ መዳፍ በጎደፈው / በባርነት ሸክም ጀርባሽ ለጎበጠው”…ያልኩት በዚህ መነሻ ነው፡፡
በአረብ ሃገር ውስጥ በኢትዮጵያን እህቶቻችን፣ ልጆቻችን ላይ የሚደርሰውን ግፍ ለተመለከተ፣ የህሊና እረፍት ይነሣል፡፡ በእውነት በዚህ ምክንያት ይህን መረዳት ያቃታቸው መሪዎቻችንን አውግዣለሁ። ደህንነትም ደጋግሞ የጠየቀኝ፤ ‹እንዴት እንዲህ ያለ ቃላት ትጠቀማለህ?› በሚል ነው፡፡ … እውነቱን ልንገራችሁ… እንዲህ ያለ ስቃይ እየደረሠባቸው ያሉ ልጆቹ፣ እንዲህ ሲዋረዱ ለክብሩ ሲል ‹የምበላውን ትበላላችሁ፣ ጠቅልላችሁ ኑ› ብሎ ሰብስቦ ያመጣቸው ነበር፡፡ እንዴት ከሴት የተወለደ ልጅ ያለው፣ ሚስት ያለው --- መሪ፤ በእነዚህ ኢትዮጵያውያን ላይ እንዲህ ያለ አስከፊ ግፍ ሲፈፅም ዝም ብሎ ያያል? በዚህ የተነሣ የቀድሞውን መሪ አውግዣለሁ፡፡ አሁን ተስፋ አለኝ፤ በየአረቡ ሃገር በተመደቡ አምባሳደሮች፣ የእነዚህን ልጆች ነገር እንደሚከታተሉ፡፡ እኔ ለዚህ አራት አመት አይደለም፤ አስር አመት ብታሠር ምንም አይደለም፡፡ ገና ብዙ መስዋዕትነት የሚያስከፍል ሃገር እንደሆነም ይገባኛል” ሲሉ አስረድተዋል - አቶ አንዳርጋቸው፡፡
የአቀባበል ሥነ ስርዓቱን ያዘጋጁት የአዲስ አበባ ወጣቶችም፤ “ላንቺ ነው ኢትዮጵያ” የሚል ፅሁፍ ያለበት፣ 17 ግራም የሚመዝን የወርቅ ሜዳልያ ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አበርክተውላቸዋል፡፡
 በሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኘው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ አቶ አንዳርጋቸውን አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-


    የመን ላይ የተያዙበት  አጋጣሚ እንዴት ነበር?
ዝርዝሩ በጣም ቀላል ነው፡፡ ይሄን ያህል የተወሳሰበ፣ ስለላ የሚጠይቅ አልነበረም፡፡ በአደባባይ ነው የተያዝኩት፡፡ እዚያ ኤርፖርት ላይም ሆነ አደባባይ ላይ የእነሱ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አንዳርጋቸው በዚህ አውሮፕላን እየሄደ ነው ብለው መደወል ብቻ ነው የሚጠበቅባቸው፡፡ የሆነውም ይሄው ነው፡፡ የእነሱ የረቀቀ ስለላ ምናምን የለም፡፡ በቀላሉ ነው የተያዝኩት። የመን ካሉ  የደህንነት ሰዎች ጋር በገንዘብ ተደራድረው ያደረጉት ነገር ነው፡፡ በዚያ አየር መንገድ መሄድ አደጋ ነበረው፡፡ በተወሰነ ደረጃ ለዚያ አደጋ ሃላፊነት ወስጄ ነበር የሄድኩት፡፡ 400 ዶላር ተጨማሪ ከፍዬ፣ ደህንነቱ በተጠበቀ አየር መንገድ መሄድ እየቻልኩ፣ የድርጅት ገንዘብ አላባክንም በሚል ላለመክፈል ባደረግሁት ጥረት ነው የተያዝኩት፡፡ እኔ በርካሽ አየር መንገድ እሄዳለሁ፤ ለምን የድርጅት ብር አወጣለሁ ብዬ ነው፣ ደህንነቱ ባልተጠበቀ አየር መንገድ የተጓዝኩት፡፡
ወደዚህ የመጣሁበት ሁኔታ በጣም አሠቃቂ ነው፡፡ አይኔንም፣ አፌንም፣ አፍንጫዬንም--- በእቃ መጠቅለያ ሲልቨር ጠቅልለውኝ፣እንደገና ጭንቅላቴ ላይ ጆንያ ጭነውብኝ፣ እጄን ወደ ኋላ አስረውኝ ነው የመጣሁት። ለተወሰኑ ቀናት የቆየሁትም በዚህ ሁኔታ ነበር፡፡
ከዚያ በኋላ የት ነው የተወሰዱት?
ቪላ ቤት ነው፤ ግን ሶስተኛ ወይም ማዕከላዊ አይደለም፡፡ ለዚህ ተብሎ የተዘጋጀ ቤት ይመስለኛል፡፡ ከተማው ውስጥ ብዙ ቤቶች እንዳሏቸው ነው የገባኝ፡፡ ብዙ ቤቶች ወስደውኛል፡፡ መጨረሻ ላይ ግን በግምት፣ ገነት ሆቴል አካባቢ ተጨማሪ ቪላዎች ያሉበት ግቢ ያስገቡኝ ይመስለኛል፡፡ በትክክል አላውቀውም። ምክንያቱም ከቦታ ቦታ ሲያንቀሳቅሱኝ፣ ፊቴና ጭንቅላቴ ላይ ብርድልብስ ወይም ጆንያ እያደረጉ ነበር፡፡
ብዙዎቹ ከእስር የተፈቱ ፖለቲከኞች፤የተለያዩ ማሠቃየቶች እንደተፈጸሙባቸው ይናገራሉ፡፡ የእርስዎ ሁኔታ እንዲህ ነበር?
መመታት መደብደብ፣ ያን ያህል አላጋጠመኝም፡፡ እግርና እጄ በሠንሠለትና በእግር ብረት ታስሬ ነበር፡፡ እጄን ለረጅም ጊዜ ወደ ኋላ ታስሬ ነበር፡፡ ይህ ሲሆን መተኛት አልችልም፡፡ በጣም ስቃይ ነበረው፡፡ መጨረሻ ላይ ብረቱ እጄን ሰርስሮ፣ ለማውጣት እንኳ በጣም ነው ያስቸገረው፡፡ ትንሽ ቆይቶ ቢሆን ኖሮ፣ እጄን ከጥቅም ውጪ ያደርገው ነበር፡፡
የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ “ላፕቶፕ ገብቶለት መፅሐፍ እየፃፈ ነው” ሲሉ  ተናግረው ነበር፡፡ ይሄ ነገር እውነት ነው?
አዎ፤ ላፕቶፕ ሠጥተውኝ ነበር፡፡ ይሄ እውነት ነው፡፡ ጠይቄያቸው ነው የሠጡኝ፡፡ ፖለቲካ ላይ ያተኮረ መፅሃፍ ስፅፍ ነበር፡፡ 850 ገፅ የሚሆን “እኛም እንናገር፣ ትውልድም አይደናገር” የሚል መፅሃፍ፤ እዚያው ኮምፒውተር ላይ ፅፌ ነበር፡፡ 185 ገፅ ያህል፣ ሌላ ፖለቲካውን የተመለከተ ፅሁፍ ነበረኝ። እዚያው ላፕቶፕ ላይ ነው የቀረው፡፡ በእጃቸው ነው ያለው። ትልቁ ይሄን ያደረጉበት ምክንያት፣ እነሡ የኔን አመለካከት ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ በ1997 ምርጫ፣ ዝዋይ በታሠርኩበት ወቅት መለስ ዜናዊ፤ “ምን ሆኖ ነው እንደዚህ የሆነው?” የሚል ጥያቄ ጠይቀው ብሎኝ ነው በሚል አንድ ደህንነት ጠይቆኛል፡፡ ስለዚህ አሁንም በሚፈጠሩ ነገሮች ላይ ያንን አስተያየት መስማት ይፈልጉ ነበር፡፡ እኔም ሌላ አማራጭ የለኝም፡፡ በዚሁ ወደ ማይቀርበት አለም መሄዴ ነው ብዬ በማያወላዳ ቋንቋ፣ በማያወላዳ መልኩ ምንም ነገር ሣይቀረኝ፣ በዝርዝር በእነዚህ ዶክመንቶች ገልጨላቸዋለሁ። ፅሁፉንም ሰጥቻቸዋለሁ፡፡ አሁን የት እንዳለ አላውቅም፡፡ መፅሃፍትም ለማጣቀሻ አምጥተውልኛል። ኮምፒውተሩም መፅሃፉም  በእነሡ እጅ ነው ያለው፡፡
ቃሊቲ የወረዱት መቼ ነው?
ከተያዝኩ ከ1 ዓመት ከ3 ወር በኋላ ነው፣ቃሊቲ ማረሚያ ቤት፣ አንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ የገባሁት፡፡
በእስር ወቅት መጥቶ ያናገርዎት የመንግስት ባለስልጣን ነበር?
ማንም አልነበረም፡፡ በእስር ወቅት የፈጠሩት ነገር ቢኖር፣ በተደጋጋሚ ነፍስ ግድያ የተፈረደባቸው ሁለት ሰዎችን አምጥተው ነው፣ አብረው ያሠሩኝ። እነዚህ ሰዎች ምንም አይነት ትምህርት፣ ምንም አይነት እውቀትና ግንዛቤ የሌላቸው፣ በምንም አይነት ልትግባባቸው የማትችላቸው አደገኛ ሰዎች ናቸው። እነሡ ናቸው የእስር ጊዜዬን ከባድ ያደረጉብኝ፣ ወደ ቡጢ ያመራ ፀብ ሁሉ አጋጥሞኛል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ ሰፊ ህዝባዊ ተቃውሞ ተደርጎ፣ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ተለቀዋል። አሁንም እየተለቀቁ ነው፡፡ እርስዎ በይቅርታ ልፈታ እችላለሁ ብለው ገምተው ነበር?
እኔ ህዝቡ ዝም እንደማይል እገምት ነበር፡፡ ምንም መረጃ ስለማላገኝ ግን እንደዚህ አይነት ስፋት ያለው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ይኖራል የሚል ግምት አልነበረኝም። የህዝቡ ትግል የራሱ አስተዋፅኦ እንዳለው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በዚህ መሃል ደግሞ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ይዞ በመጣው ሃሣቦች፣ ብዙ እስረኞች እየተፈቱ ስለሆነ ወደ ብሄራዊ መግባባት የሚወስደውን መንገድ ለማሳለጥ በሚል የተወሰነ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ይሄ ሁሉ ድምር ሂደት፣ ዛሬ በዚህ መልክ እንድወጣ አድርጎኛል፡፡
ከልጆችዎ ጋር የሚገናኙበት አጋጣሚ ነበር? ልጆችዎና ቤተሠብዎ ያሉበትን ሁኔታ ያውቁ ነበር?
አንድም ደብዳቤም ሆነ መልዕክታቸው ደርሶኝ አያውቅም፡፡ ከየትም የሚመጣ ደብዳቤ አይገባልኝም ነበር፡፡ እንደውም ልጆቼ የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸውን አሰባስበው፣ 80 ህፃናት የሳሏቸው ስዕሎች ያሉበትን ካርዶች ልከውልኝ ነበር፡፡ እሱን ሁሉ አልሰጡኝም። የእንግሊዝ ማህበረሰብ የሚልካቸው የአጋርነት መግለጫ ካርዶች ነበሩ፡፡ እነሱ ሁሉ አይገቡልኝም ነበር፡፡ አንድ የደረሰኝ ፎቶ ልጆቼ፣ በአርሴናል ሜዳ፣ ከተጫዋቹ ቲዎ ዋልኮት ጋር የተነሱት ብቻ ነው፡፡
ከዚህ በኋላ እናንተ የምታደርጉት ትግል ወዴት ሊያመራ ይችላል?
ትግሉ ማቆሚያ የለውም፡፡ የምናደርገው የመብት ትግል ቢሣካ፣ ህዝብ መብት ብቻ በልቶ ጠጥቶ ማደር ስለማይችል፣ በኢኮኖሚ በኩል የሚደረገው ትግል አለ። ብዛት ያለው ወጣት ስራ አግኝቶ፣ በተስፋ በሃገሩ እንዲኖር ለማድረግ መታገል ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ዲያስፖራ ያለው እውቀትና ሃብት ቀላል አይደለም። እዚህ ካለው መንግስት ጋር ሠላማዊ ግንኙነት ቢኖረን እኮ በሌሎች መስኮች ዳያስፖራው ቀጥተኛ አስተዋፅኦ የማድረግ አቅም አለው፡፡ ሃገሪቱ ይሄን አቅም መጠቀም አልቻለችም፡፡ በተለያዩ መድረኮች ተናግሬያለሁ። በውጭ ያለው ዳያስፖራ ሃገሩን ከልቡ የሚወድ ነው። ከዚያም አልፎ በወጪ ያሉ ህዝቦችን አኗኗር እያየ፣ የሃገሬ ህዝቦች ለምን እንደዚህ አይኖርም እያለ፣ በቅናት የሚንገበገብና ይሄን ቅናቱን በአደባባይ የሚገልፅ ነው፡፡ ይህ ተቆርቋሪ ሃይል ነው ሃገሪቱ መጠቀም ያልቻለችው። የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአሜሪካ ባስተላለፈው አንድ ሪፖርት ላይ 95 በመቶ ዳያስፖራ፣ ከዚህ መንግስት ጋር ግንኙነት የለውም ይላል፡፡ ከመንግስት ጋር ግንኙነት ስለሌለው፣ በህዝቡ የእለት ተእለት ኑሮ ላይ አይሣተፍም ማለት ነው። ለአባይ ግድብ በአረብ ሃገር በስቃይ ውስጥ  ሆነው ከሚሠሩት ወገኖች ከሰበሰቡት ገንዘብ በቀር በሌሎች በአውሮፓ፣ በአሜሪካ ካሉ ዳያስፖራዎች ገንዘብ አልሰበሰቡም። ነገር ግን ግድቡን ዳያስፖራው ብቻውን ሊገነባው ይችል ነበር፡፡ ዳያስፖራውን በጠላትነት መፈረጅ ነው ይሄን ሁሉ ያመጣው፡፡ የሚሠራውን መቃወም፣ በጠላትነት ማስፈረጅ የለበትም፡፡ አሁን የመጣው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚናገራቸው ንግግሮች፣ ለዳያስፖራው ሠፊ ግምት የሠጠ ነው፡፡ ድሮ እንዳለ በጠላትነት ነበር የሚፈረጀው፡፡ አሁን ግን የተቀየረ ነገር አለ - በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር፡፡ አሁንም ይሄ መንግስት ይሄን በደንብ ሊያጤነው ይገባል፡፡
አሁን በተያዘው መንገድ በመንግስት በኩል ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት አለዎት?
ለውጥ መኖር አለበት፡፡ ይሄን ማድረግ ያለባቸው ለራሳቸው ሲሉ ነው፡፡ የምሠጣቸውን አስተያየቶች እነሡን የሚቃወምና የሚጠላ አድርገው ነው የሚያስቡት፡፡ የኔ እውነተኛ ስሜት፣ ቅርበት ባለው መንገድ፣ ከትግራይ ህዝብ ጋር በመኖር፣ በመከራና በጭንቀት ጊዜ ታምሜ ሣለ፣ ከልጆቹ ጉሮሮ እየነጠቀ፣ አንዴ በተስቦ፣ አንዴ በወባ በሽታ ስማቅቅ ያዳነኝ ህዝብ ነው፡፡ ያን ህዝብ ችግር ውስጥ የሚከቱ ነገሮች በማይበት ሠዓት መናገር አቁሜ አላውቅም፡፡ የምናደርጋቸው ለውጦች ሁሉ ለሁላችንም ጠቃሚ ነው፡፡ የዚህ ለውጥ በዋናነት ደጋፊ መሆን ያለባቸው ህወኃቶች ናቸው፡፡ አሁን በጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተነገሩ ያሉ ነገሮች፣ ህዝብን ለመድረስ የሚደረጉ ጥረቶች ቀደም ብለው ተደርገው ቢሆን ኖሮ እኮ፣ መመለስ የሚችሉ ሰዎች ይሆኑ ነበር፡፡ የቀድሞዎቹ ሲናገሩ እንኳ እንደ መሪ አልነበረም፡፡ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ግን እንደ መሪ ነው የሚናገሩት፡፡ የበፊቱ ግን እንዲህ አልነበሩም፡፡ አንዴ ጣት እንቆርጣለን፣ አንዴ ባንዲራ ጨርቅ ነው፣ ታሪክን በተመለከተም የተዛባ ንግግር ነበር የሚያደርጉት፡፡ የመሪነት ቁመና የነበረው ንግግር አልነበረም፡፡ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የመሪነት ቁመና አላቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጪ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችና ተቃዋሚዎች፣ ወደ ሃገር ቤት እንዲገቡና ፖለቲካዊ ውይይት እንዲደረግ ያቀረቡትን ጥሪ እንዴት ያዩታል? በሌላ በኩል የእርስዎ የትግል አጋር የሆኑት ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፤ ”አሁን ወደ ሃገር ቤት መምጣት፣ ሞኝነት ነው” ብለዋል፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
በተወሠነ ደረጃ አሁንም መነጋገር የሚገባን ነገር አለ፡፡ በአንድ ሃገር ላይ በግለሠቦች በጎ ፍቃድ ላይ የተመሠረተ ዲሞክራሲ አይደለም የሚያስፈልገው፤ በተቋማት ላይ የተመሠረተ ዲሞክራሲ ነው የሚያስፈልገው፡፡ በአንድ ሃገር ውስጥ እውነተኛ የሚሠራ ዲሞክራሲ አለ ብሎ ለመናገር፣ በዚያ ሃገር ውስጥ ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሁሉንም ህዝብ፣ ሁሉንም ዜጋ በገለልተኝነትና በነፃነት ሊያገለግሉ የሚችሉ ቁልፍ ተቋማት መኖር አለባቸው፡፡ እነዚህ ቁልፍ ተቋማት በሌሉበት ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሊጋብዝ ይችላል፤ ነገር ግን የማይቆጣጠረው ደህንነት ሊያስር ይችላል፡፡ ይሄ ሁኔታ በኢትዮጵያ እስካለ ድረስ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ሞኝነት ሊሆን ይችላል፡፡ ነፃነት የሌለው ፍ/ቤት ባለበት ሁኔታ መምጣት ሞኝነት ሊሆን ይችላል፡፡ ዶ/ር አብይ የጀመራቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነሡን በተግባር እየተረጎመ ከመጣ፣ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ሞኝነት ይሆናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ እኛኮ የተቋዋሚነት ሱስ የለብንም። መሠረታዊ የምንቃወማቸው ነገሮች ስላሉሉ እንጂ፡፡ እንደውም የፖለቲካ ችግሮች ተፈትተው፣የዚህ ህዝብ ህይወት እንዲቀየር ነው የምንሻው፡፡ ህዝቡ የሚበላው ነገር እንዲያገኝ፣ ልጆቹ ሲታመሙ የተሻለ ህክምና ማግኘት የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር ነው። እኛ የፖለቲካ ስልጣን፣ አምጡ አላልንም፡፡ የፖለቲካ ስልጣን ፍላጎትም የለንም፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ስልጣን የሚያዝበትን መንገድ ተገቢ እናድርገው፣ የዲሞክራሲ ተቋማት ይኑሩ ነው ትግላችን፡፡ ነፃ ምርጫ ቦርድ በሌለበት፣ ገለልተኛ ወታደራዊ ሃይል፣ ነፃና ገለልተኛ የደህንነት ሃይል፣ ፖሊስ፣ ሚዲያ ከሌለ፣ በአንድ ሃገር ላይ ከሌለ ዲሞክራሲ ሊኖር አይችልም፡፡ እነዚህ ነገሮች በሌሉበት በተስፋ ብቻ አምኖ፣ መመለስ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡
የአገሪቱ ፖለቲካ ምን ያህል ወደ ፊት የመራመድ ተስፋ አለው?
ተስፋ አለው፡፡ ግን ከፍተኛ ትግል የሚጠይቅ፣ ቀጣይ ትግልም አለው፡፡ ስር የሠደደ በጣም ከፍተኛ ችግር ያለበት ሃገር ነው፡፡ ቶሎ ብለን በፖለቲካ ያለው ችግር ተቀርፎ፣ ወደ ሌሎች መሄድ አስፈላጊ ነው፡፡ ግን ወደ ሌሎቹ ለመሄድ፣ ፖለቲካውን መልክ ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ በኔ አመለካከት፣ ይሄ ማነቆ ከተፈታ፣ ሌሎች ነገሮችን ማስተካከል ይከብዳል የሚል እምነት የለኝም፡፡
እርስዎ በሚመሩት አርበኞች ግንቦት 7 ምክንያት በርካቶች ታስረዋል፡፡ ስለ እነዚህ እስረኞች ከመንግስት ጋር የተነጋገራችሁት ጉዳይ ይኖር ይሆን?
ግንቦት 7 ሰው ለማሠሪያ ትልቅ ሰበብ ነው የሆነው፡፡ እኔ ደጋግሜ እነ አንዷለም አራጌ፤ እስክንድር ነጋ --- ከግንቦት 7 ጋር ቅንጣት ታህል እንኳ ግንኙነት እንደሌላቸው ለደህንነቶችም፣ ለእንግሊዝ ዲፕሎማቶችም ተናግሬያለሁ፡፡ ይሄ በሚገባ የማውቀው እውነታ ስለሆነ ደጋግሜ ተናግሬያለሁ፡፡ አሁን በተፈጠረው ሁኔታ፣ ይሄ ነገር ይቆማል ብዬ ነው የማስበው፡፡


Read 5796 times