Print this page
Sunday, 03 June 2018 00:00

ኦህዴድ እና ኦፌኮ ከሚወዳደሩ ቢደራደሩ!!

Written by  ከኬና ቀኖ
Rate this item
(4 votes)

      በኢትዮዽያ የፌደራልና የክልሎች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫ፣ ከሃያ አራት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ይካሄዳል፡፡ በምርጫው በኦሮሚያ ክልል፣ የእነ አቦ ለማ መገርሣና ዶ/ር አብይ አህመድ ፓርቲ ኦህዴድ፤ በኦፌኮ የመሸነፍ ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ኦፌኮ በቀጣዩ ምርጫ በኦሮሚያ ክልል በቀላሉ ማሸነፍ የሚችል ቢሆንም በሀገር አቀፍ ደረጃ ማሸነፍ የሚቀለው አይመስለኝም፡፡ ኦህዴድ በዚህ ጊዜ በኦሮሚያ መሸነፉ ለኦሮሚያ፤ ለአጠቃላይ የኢትዮዽያ ህዝብም የፖለቲካ ኪሣራ ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ ምርጫውን ለማካሄድ ዝግጅት ከመጀመራቸው በፊት ኦህዴድ እና ኦፌኮ፣ ለህዝብ የሚበጀውን አቅጣጫ ለመቀየስ፣ ወደ ድርድር መግባት አለባቸው፡፡
መግቢያ፡- ኢትዮጵያ  በአገር አቀፍ ደረጃና በክልሎች የህዝብ ተወካዮች ምርጫ ልታካሂድ ከሀያ አራት ወራት ያነሰ ጊዜ ይቀሩታል! በ2012 ዓ.ም እንደተለመደው ከሆነ፣ በግንቦት ወር ውስጥ ምርጫው ይካሄዳል ፡፡ይሄኛው ምርጫ ዙር እንደ 4ኛ ዙርና 5ኛ ዙር፡ ኢህአዴግ፣ እንደ ጎበዝና ሸምዳጅ የታሪክ ተማሪ የሚደፋፍነው አይነት ላይሆን ይችላል፡፡ ምክኒያቱም አሁን ብዙ ነገር ተለውጦአል፡፡ በዚህ አጭር ግዜ ውስጥ ይሆናሉ ተብሎ የማይገመቱ አያሌ ቁም ነገሮች ሆኗል፡፡ የዶላርም፤ የመሬትም፤የኮንዶሚኒየምም፤ የህዝብ ድምፅም- ስርቆት አይነቶች እየመነመኑ እንደሚሄዱ ታውቋል፡፡ ተመስገን ነው! ቀጣዩ ምርጫ አወዛጋቢና ብዙ የተነገረለት የ97ቱ ምርጫም ሊሻል ይችላል ተብሎ ይታሰባል፡፡ እኔ ያኔ ለአቅመ- መመረጥ ስላልደረስኩ፣ ፈረሰኛው የጎጤ ሰዎች የመረጡትን “ፈረስን” ሳልመርጥ ቀረሁ፡፡ ምናለበት ያኔ -18 በሞላኝ ኖሮ! ከ2012 ጋር በደንብ አወዳድረው ነበር፤ ስሜቱንና ሁኔታውን፡፡ ምርጫው ላይ ባልሳተፍም ግን አንዳንድ ትዝታዎች አሉኝና በመጠኑ አስታውሳለሁ፡፡ በተለይ የሰፈሬ ሰዎች ከምርጫ ጣቢያ በእርግጠኝነት “አባፈርዳን” በአጫሉኛ ”Araat kiiloodhaaf situ aanee ”ብለው ሲመለሱ፤ የሚጨፍሩትን “Garee kottee boottii፤ hammuma caamsaa torbaatti boontii” (ባለ ቦቲ ጫማው ገሬ፤ እስከ ግንቦት ሰባት ብቻ ትመካለች) ገሬ ማለት ከ1ለ5 የሚበልጥ፣ መለስተኛ ቡድን ነገር ነው) ጭፈራ ሲያማርራቸው የነበሩትን የሠፈር ንጉሶች ሲፎግሩ ትዝ ይለኛል፡፡ ያው ትዝታ ነው፤አለ አይደል- የማስታውሰው ነገር! ዛሬ ግን እንደ ሌሎቹ |የኢትዮዽያ ክፍሎች፣ የሠፈሬ ሰዎችንም የ97ቱን ነገር የሚያስረሳቸው፤ ያለፉት ሶስት አራት አመታት ውስጥ የተወሰነ፣ የእነ ደጀኔ ሰርቤሣ እናት እንባ ሊያብሱ የሚችሉትን፤ በእሳት ተፈትነው ወርቅ መሆናቸው የተረጋገጡ፤ቆራጦችና ከብቃትም በላይ ከፈጣሪ ሞገስና ፀጋን የታደሉ፤ በጠላትም በወዳጅም ዘንድ ተፈልጎ ተፈልጎ እንከን የማይገኝባቸው፣ እነ ክቡር ኦቦ ለማ መገርሣ ብቅ ብሎላቸዋል፡፡ ህዝቡም በእዚህ አንደበተ-ማር፤ ቆራጥና ሀሳበ-ረጅም ለማ መገርሣና ሩህሩው፤ገራገሩና ሆደ-ሠፊው ዶ/ር አብይ አህመድ ተስፋ ሰንቋል፡፡ ገና ሊያርሱት ያለውን ኮትቻውን የጤፍ ማሳቸውን ሲመለከቱ፣ የአይናቸው ውሃ ፀድቷል፡፡ ለቀጣዩ ወቅት በረካ (ልማትን )የተመለከቱ ይመስላል! ብዙዎች ፈጣሪን አመስግነዋል፡፡ ያው፤ ኢትዮዽያውያን መሪ፣ ከፈጣሪ እንደሚሰጥ ስለሚያምኑ መሠለኝ፣ ደግሞም ትክክልም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
የእነ ለማ ጮራና ቀጣዩ ምርጫ፣ እኔ ሃሳብ የሆነብኝ ይህ የተስፋ፤ አንድነት፤ እኩልነትና ዲሞክራሲ ጭላንጭል፣ በቀጣዩ የ2012 ዓ.ም ምርጫ ወደ ተሻለ የችቦ ብርሃን ይሸጋገራል ወይስ ጮራውም ጠፍቶ፣ ለውጡም ይቀለበሳል የሚል ነው፡፡ ይህንን የምለው፣ ከምርጫው በፊት ለውጡን ለማስተጓጎልና ወደ ኋላ ለመመለስ የሚተጉና የሚፍጨረጨሩ የፖለቲካ ”ቆሞ-ቀሮች” የሉም ማለቴ አይደለም፡፡ በእርግጠኝነት ምንም ቢያደርጉ ስለማይሳካላቸው ነው እንጂ፡፡ ስለዚህ እኔ በግሌ ለውጡ እንከን እንዳይገጥመው የምሰጋው፣ በቀጣዩ ምርጫ እንጂ በሌላ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ክቡር ኦቦ ለማ መገርሣ፣ በደንቢ ዶሎ የህዝብ ምክክር መድረክ ላይ የተናገሩትን መጥቀስ እፈልጋሁ፡- “ አሁን የደረስንበት የትግል ደረጃ ዳገት እየወጣ ያለ መኪና ይመስላል፡፡ ከተባበርን፣ አንድ ከሆንን፣ መኪናው ዳገቱን ጨርሶ ወጥቶ እንፈጽማለን፤ ካልሆነ መኪናው ተንሸራቶ ወደ ኋላ ሊመለስ ይችላል፡፡ ልንመልሰው የምንችል እኛው (ኦሮሞ ) ነን….. ” (ቃል በቃል አይደለም)
ቀጣዩን ምርጫ ተስፋ ማድረጌ፣ እንዲሁም መፍራቴ፣ እንዲሁ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው እነ ኦቦ ለማ ና ዶ/ር አብይ የወጡት ለዘመናት ከህዝብ ከተለየውና ህዝቡ ከተጠየፈው ከኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ነው፡፡ በጣም የሚገርመው ህዝቡ፤ እነ ለማን (ኦህዴዶች አይልም)፤ ዶ/ር አብይ የድርጅቱ ሀላፊ ሆኖ ሳለ፣ ህዝቡ “ቲም ለማ” ይላቸዋል እንጂ የኦህዴድ መሪዎች ሲል አይሰማም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም ሆነ ወደፊትም የሚላቸው አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ከእነ ዶ/ር አብይ እና አቦ ለማ ይልቅ በየቀኑ የሚያገኟቸው፤ በግቢያቸው ደጅ የሚገኙ፤ ተስፋ የሚያስቆርጡ፤ይቀየራሉ ብሎ መታገስ አይደለም ማሰብን የማያስደፈሩ፣ህዝብን  የሚያማርሩ፤ ቁጥራቸው የትየሌለ የሆኑ፣ የታችኛው እርከን አመራር ኦህዴዶች ስላሉ (ለህዝብ አህዴድ ማለት፣ እነዚህ ናቸው እንጂ እነ ዶ/ር አብይ እና ኦቦ ለማ አይደሉም)፡፡ ይህ እንግዲህ ሀቅና አሁን ያለው ስዕል ነው፡፡ በቅርቡ OBN ላይ መግለጫ የሰጡት የድርጅቱ ማዕከላዊ ጽ/ቤት ሀላፊ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፤ አህዴድ፤ይህንን ታችኛው እርከንን (በተለየ የወረዳ አመራሮችን) እንደገና ለማዋቀር ወስኗል፡፡  እኔ በግሌ፤ በዚህ ሁለት አመታት ውስጥ የሚሳካ አይመስለኝም! ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ‹‹ቲም ለማ›› ኢትዮጵያን የተሻለች ለማድረግ መንግስት በመሆን እየተንቀሳቀሱ ይገኛል፡፡ ከኦሮሞም አልፎ በአገር ደረጃ ተስፋ ተጥሎባቸው፤ በፍቅር ተቀባይነት አግኝቷል! በተቃራኒው የቆመውን የታችኛውን ካድሬ ተሸክሞ ነፃና ዲሞክራሲያዊ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ምርጫ ውስጥ ሊገቡም አጭር ጊዜ ይቀራል፡፡
 በኦሮሚያ ከሰሞኑ ብቅ ያሉት ኦቦ ሌንጮ ለታና የፓርቲያቸው ሁኔታ ስላልለየ፣ ለጊዜው ትተን፣ ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ የተባለውን የእነ ዶ/ር መረራ ጉዲና እና አቶ በቀላ ገርባ ስብስብ እንመልከት፡፡ መቼም ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ተካሂዶ፣ ያ አስቸጋሪ የቀበሌ ሊቀ-መንበርን ያጠቃለለው ፓርቲ - አህዴድ፤ ለዘመናት በህዝቡ ልብ ውስጥ ከገባው ኦፌኮ አስበልጦ ይመርጣል ማለት እውነታን አለመገንዘብ ነው፡፡ እነዚህ እንቁ ግለሰቦችን ከሆነ ህዝቡ፤ ኦቦ ለማን፤ ዶ/ር አብይን፤ ዶ/ር መረራንና ኦቦ በቀለን፤ በተመጣጠነ ደረጃ ይቀበላቸዋል፤ ይወዳቸዋል፡፡ በኦሮሚያ ኦህዴድ ተሸንፎ ኦፌኮ ቢያሽንፍ ምን ችግር አለው? በቀጣይ ምርጫ አዲስ ነገር ካልተፈጠረ በኦሮሚያ ኦፌኮ ኦህዴድን የማሸነፍ ሰፊ እድል አለዉ፡፡ ያ ማለት ደግሞ እነ ዶ/ር አብይን የያዘ ኦህዴድ፣ በኦሮሚያ መንግስት አይመሠርትም፤ ከፌዴራልም ፅዋ አይቀምስም ማለት ነው፡፡ ይህ በነፃ የህዝብ ዉሣኔ የሚካሄድ ስለሆነ በመርህ ደረጃ የተባረከ ነው፡፡ መዘዙ ግን ወዲህ ነዉ! ኦፌኮ በኦሮሚያ በቀላሉ የሚያሸንፍ ቢሆንም በፌዴራል ደረጃ (በኢትዮዽያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ ጥላ ሥር) የማሸነፍ ዕድሉ ግን በጣም ጠባብ ነው፡፡ ምክንያቱም ኦፌኮ፤በአማራ ብአዴንን የሚገዳደሩለት፤ በደቡብ ደህዴንን የሚይዙለት፣ የትግራይን ረስተን ጠንካራ እህት ፓርቲዎች ስለሌለዉ ነዉ፡፡ ስለዚህ ኦፌኮ እንደ ቅንጅት 1997ቱ አዲስ አበባ፣ ኦሮሚያን  አስተዳድር ሊባል ይችላል፡፡ የፌዴራል ሥልጣንን በሚገባ ሳይቆጣጠሩ፣ ኦሮሚያን በነፃነት አስተዳድራለሁ ማለት ዳግሞ ከቀልድም ቀልድ ነው፡፡ ኦሮሚያን ማስተዳደር ያስቸግራል፤ ከፌዴራል ሥልጣን ማጣት ደግሞ፤ ለኦሮሞም ለኢትዮጵያም ጉዳትና ኪሣራ ነዉ፡፡ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትርነትና ሌሎች ከፍተኛ ቦታዎች፣በሌሎች እጅ ሊወድቁ ይችላሉና! ኢህአዴግ ኦሮሚያን አስረክቦ፣ ከሌሎች ክልሎች በጥምረትም ቢሆን አሰባስቦ፣ መንግስት የመሆን እድል አለው፡፡ ኢህአዴግን ያለ አብይና ለማ!!…… ታዲያ መፍትሔው ምን ሊሆን ይችላል?
 እንደሚመስለኝ፤ ቀጣዩ ምርጫ ለኦሮሚያ፣ ከፓርቲም በላይ ነው፡፡ የህዝብ ነው፡፡ ኦቦ ለማ እንዳሉት፤ መተባበርና ሀይልን መቀናጀት ያስፈልጋል፡፡ ኦህዴድ የኦፌኮን አቅምና የሰፊዉን ህዝብ የልብ ትርታ በደንብ አጥንቶ ማወቅ አለበት፡፡ ተወደደም ተጠላ፣ ኦፌኮ ከፍተኛ የህዝብ ተቀባይነት አለው፡፡ በነፃ ምርጫ ያሽንፋል! ይህ ሀቅ ነው፡፡ ይህንን እውነታ ከተረዱ ደግሞ በሰጥቶ መቀበል መርህ፣ ለድርድር መቀመጥ አለባቸው፤ ለውድድር መዘጋጀት ሳይሆን! ዋጋ ለተከፈለበት ሕዝባዊ ትግል፤ ለኦሮሞ ህዝብና ለአጠቃላይ ኢትዮጵያ ህዝቦች ጥቅም ሲባል፣ ኦህዴድ እና ኦፌኮ መደራደር አለባቸው!! በግል ሀሳቤ እንደሚከተለው፣ ሰጥቶ በመቀበል ድርድራቸውን ማካሄድ ይችላሉ፡፡
 1. ኦፌኮ፡- ያለ በቂ የፌደራል ሥልጣን፣ ኦሮሚያን በነፃ ማስተዳደር ስለማይሆንለት፣ ኦህዴድ የፌዴራሉን አሁን ያሉትን  ቦታዎች ይዞ መቀጠል እንዲችል፤ በኦሮሚያ ክልል አብላጫ ድምፅ ማግኘት የሚችልበትን ዕድል ለመፍጠር ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ ይህ የሚሆነው በውድድር ሳይሆን በድርድር ነው!! ሰጥቶ በመቀበል ደግሞ፤ ኦፌኮ ይህንን ከሰጠ የሚቀበለው ነገር ሊኖረዉ ይገባል!!
2. ኦህዴድ፤ ደግሞ የታችኛውን የአመራር እርከን (በተለይ ወረዳን) ለኦፌኮ ቢያስረክብ የተሻለ ነው፡፡ ለመለወጥ ዝግጁነትም፤ ፍላጎትም ከሌላቸው አስቸጋሪ ወገኖች ጋር ከሚቸገር፣ የኦፌኮ ወጣቶችና ቄሮዎች፤ የለውጥ ሞተሮች፣ ለኢትዮጵያም አሪፍ ናቸው ብዬ እገምታለሁ፡፡ ይህ ኦህዴድ የሚሰጠው ነው!! ሁለቱም አሸናፊዎች፤ ኦሮሚያም፤ ኢትዮጵያም ያሸንፋሉ!! በዚህ አካሄድ፤ ኦህዴድ የጨፌና ፓርላማ ወንበር አብላጫ ካገኘ.፣ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጋር መንግስት መሥርቶ ይቀጥላል፡፡ እነ አብይ እና ለማ ተጨማሪ 5 ዓመታት ያገኛሉ!! እዚህ ላይ ኦፌኮዎች አብላጫ ወንበር ስለማይገባቸው አይደለም፡፡ በፌዴራል ደረጃ ማሸነፍ ስለሚከብዳቸዉ ነዉ፡፡ ቀጣዩ ምርጫ ከፓርቲም በላይ የህዝብ ነው ያልኩት ለዚያ ነው፡፡ ኦፌኮ የታችኛውን እርከን ተቆጣጥሮ በመያዝ፤ የክልልና የፌዴራል መቀመጫዎችን (አብላጫ ሳይሆን) ለ5 ዓመታት መቆየት የሚጎዳው ቢመስልም፣ ይቀጥላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለ5 ዓመታት የታችኛ ውን እርከን ተቆጣጥሮ ህዝብን በቅርበት እያደራጀና ራሱን እያጠናከረ፤ በሌሎች ክፍሎችም ጠንካራ የትግል ፓርቲዎች እንዲመሰረቱ፣ ድጋፍ አድርጎ፣ ኦህዴድን በሌላኛው ምርጫ በ36 ዓመቱ አካባቢ ጡረታ እንዲወጣ ማድረግ ይችላል!
ማጠቃለያ፡- ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም የፌደራልና ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫ ታካሂዳለች፡፡ ይህ ምርጫ ደግሞ እንደበፊቱ እንደማይሆን እሙን ነው፡፡ ዕድልም ሥጋትም ይዞ ይመጣል ፡፡ ምክኒያቱም ሀገሪቱ በሚያስደንቅ የለውጥ መንገድ ላይ ነች፡፡ ህዝቡ ተስፋ የጣለበት የእነ ዶ/ር አብይ አህመድ ቡድን፣ እየመራ ባለበት ጊዜ የሚካሄድ ምርጫ ነው፡፡ በተጨባጭ ሁኔታዎችና ባሳለፈው ታሪኮች ምክንያት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲ ኦህዴድ፣ በኦሮሚያ ውስጥ በኦፌኮ ሊሸነፍ ይችላል፡፡ ኦፌኮ ደግሞ  ኦሮሚያ ውስጥ አሸናፊ ሊሆን ቢችልም እንደ መድረክ በአገር አቀፍ ደረጃ ማሸነፍ ይከብደዋል፡፡ በዚህ ውስጥ የተጀመረውን የለውጥ እውነታ ካለመረዳት፤ ለፓርቲ ጥቅም ብቻ በመወዳደር፣ በማይሆኑ ሰዎች እጆች ውስጥ ሊወድቅ ይችላል፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ምርጫ፣ ከፓርቲ በላይ ዋጋ ለተከፈለበት ትግል፤ ለኦሮሞና ለኢትዮጵያ ህዝቦች የተሻለ ተጠቃሚነት፣ ኦፌኮ እና ኦህዴድ ለውድድሩ ከመዘጋጀት በፊት ለድርድር ቢቀመጡ ይሻላል፡፡ ሁለቱም በሰጥቶ መቀበል መርህ፣ ለሁሉም የሚበጀውን ማድረግ አለባቸው ብዬ ሃሳቤን አጠቃልላለሁ፡፡

Read 1787 times