Sunday, 03 June 2018 00:00

ዋለልኝ መኮንንና የብሔር ትግል በኢትዮጵያ

Written by  ዶ/ር ሁሴን አዳል መሐመድ
Rate this item
(1 Vote)

  በብሔር ትግል መዘዝ መማዘዝ
ዋለልኝ መኮንንን በሚመለከት ትችት፣ ከዚያም ከዚህም በፌስ ቡክ (ፌዝ ቡክ) የአጭር ርቀት ፈንጅ ይወነጨፋል፡፡ እያንዳንዱ “ፌዝ” በጥሞና ሲታይ፣ ተጻራሪ ወይም የተደበላለቀ ስሜት መስሎ ይታያል፡፡ ግን ሁሉም የሚሽከረከሩት ዋለልኝ መኮንን፣ የብሔር ትግል ተሳትፎ ዳራ ላይ ነው፡፡ ዋለልኝ መኮንን አሁን በሕይወት የለም፡፡ የብሔር ትግሉ ቋጠሮ ባለቤት የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (ቀ.ኃ.ሥ.ዩ.) ተማሪዎች ሕብረት በመሆኑ፣ የዋለልኝ መኮንን ስም ጎላ ብሎ ከሚነገር በስተቀር ትግሉ የአንድ ተማሪ ትግል ብቻ አልነበረም፡፡ የተቋጠረው የብሔር ትግል ንድፈ-ሓሳብ ከዋለልኝ መኮንን ሞት በኋላ ፈር በመሳቱ፣ ተማሪዎቹ የተለሙት መስመር ዳር ሳይዘልቅ በጅምር ተኮላሽቶ፣ እነሆ ዛሬ በአገሩ ፍቅር የነደደውን ዜጋ ሁሉ በሀዘን ረመጥ ውስጥ አስገብቶ ያርመጠምጣል፡፡ በሌላ ጽንፍ ደግሞ፤ ከፊሉን ዜጋ በጊዜያዊ የደስታ ስሜት ግርዶሽ ውስጥ አስገብቶ ያስቦርቃል፡፡ በሁለቱም ወገኖች ጩኸት፣ የዋለልኝ መኮንን ነፍስ ዕረፍት አጥታለች፡፡ ጩኸቱ የብሔር ትግሉ ውጤት አስደስቶናል/አስከፍቶናል የሚል የተለያየ የማህበረሰብ ክፍል ድምጽ ነው፡፡ በአገራችን ባህል በሕይወት በሌለ ሰው ላይ መረባረብ ውግዝ ቢሆንም ጩኸቱ ሊቋረጥ አልቻለም፡፡ ከዚህ በከፋ ደረጃ የሚያሳዝነው፣ የብሔረሰብ ፖለቲካ በአገራችን እንዳይቀጥል በሕግ እስካልተገደበ ድረስ መቼም ቢሆን መቋጫ የማይገኝለት መምሰሉ ነው፡፡
ዋለልኝ መኮንን ማን ነው? ዋለልኝ መኮንን የሚታወሰው ለግል ወይም ለቡድን ጥቅም በመታገሉ ሳይሆን ለሕዝብ በደል መወገድ ሲል ውድ ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠ፣ ከጊዜው በፊት ቀድሞ የተፈጠረ ዜጋ በመሆኑ ነው፡፡ ያልተዘመረለት፤ ሐውልት ያልቆመለት፣ ከአማራ አብራክ የወጣ ታጋይ ነው፡፡ ሕይወቱ በአረመኔዎች የተቀጠፈው፣ ለውድ አገሩ ኢትዮጵያና ሕዝቧ ዕድገት በነበረው ቀናዒነት ነው፡፡ ተማሪ ዋለልኝ መኮንን፤ ዛሬ ሁሉም ሰው የሚያውቀው፣ በብዕሩና በአንደበተ-ርቱዕነቱ፣ በቀድሞ ተማሪዎች የብሔር ትግል ንቅናቄ፣ አውደ ግንባር አትሞ ባለፈው አሻራ ግምገማ ነው፡፡
ዋለልኝ መኮንን፤ የስነጽሁፍ ችሎታና የአገር ፍቅር ነበረው፡፡ ከስነምግባር አኳያ ዋለልኝ መኮንን በግብረገብነት የታወቀ ወጣት ነበር፡፡ ገና የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ፣ የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስን ገጸ ባህርይ ተላብሶ መጫወቱ፤ በዕድሜ ከፍ እያለ ሲሄድ፣ የተቸገሩ ሰዎችን ይረዳ የነበረ መሆኑ፤ ውድ ሕይወቱን ጭቆናን ለማስወገድ ቤዛ ያደረገ መሆኑ፤ ከግል ሕይወት ታሪኩ ታውቋል፡፡ የስነጽሁፍ ችሎታውን በመጠቀም፣ የተማሪው የትግል ንቅናቄ፣ በዩኒቨርሲቲው  ግቢ ውስጥ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር፣ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶችና አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብ እንዲስፋፋ አድርጓል፡፡ የዋለልኝ መኮንን ሰብዓዊ ቁመና፣ አገራችን አሁን ለደረሰባት ውርደትና ሰብዓዊ ቀውስ የሚዳርግ ተግባር ውስጥ እንዲሳተፍ የማይፈቅድለት እንደነበረ ከዚህ መረዳት ይቻላል። አገር ሸጦ ለውጦ፤ ኪራይ ሰብስቦ ለመጠቀም የሚያፈደፍድ ሰው አልነበረም፡፡ በእርሱነቱ ላይ እንቶ ፈንቶ ትችት የሚረጩት፣ ያኔ ከተማሪ ትግል ጎራ ማዶ በርቀት ተደብቀው የቆዩ፤ የሆነውን ነገር በትክክል ለመዘገብ የተቸገሩ፣ “ኋላ ቀሪ፤ ወሬ ነጋሪ” ዕድሜ ጠገቦችና ከእነርሱ ተቀብለው፣ በየዋህነት የሚያስተጋቡ ወጣት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልሂቃን ናቸው፡፡ አለዚያም የቀድሞ ገዥ መደብ ግብረ በሎች፤ ወይም የአማራ ሕዝብን በመከፋፈል፣ አሁን በብሔረሰቡ እየታየ ያለውን የብሔረተኝነት ስሜት መነቃቃት በማዳከም፣ በህዝቡ ላይ እየጨፈሩ ለመኖር፣ የሌላ ዙር ትግል ጉዞ ትኬት የቆረጡ ኃይሎች ናቸው፡፡
የብሔር ትግል ፖለቲካ በኢትዮጵያ ያሳደረውን አሉታዊና አዎንታዊ ተጽዕኖ በመገምገም፣ ትክክለኛ አቋም መያዝ የሚቻለው፣ በትግሉ መነሻ ወቅት ላይ ስለ ብሔር ትግል ከዋለልኝ መኮንን አንደበት የወጣውን አስተያየት ወይም በብዕሩ ያስነበበውን ስነጽሁፍ፣ ሚዛን ላይ በማስቀመጥ ከመሆን ይልቅ በትግሉ ረዥም ሂደት በተደረገው ተጨባጭ እንቅስቃሴ፤ ትግሉን ለማሳካት በተነደፈው ተለዋዋጭ ስትራቴጂ፣ ፈር በሳተው የብሔር ትግልና በስተመጨረሻ ትግሉ ባስገኘው ፋይዳ ላይ በመመርኮዝ ሲሆን ነገሮችን በምሁራዊ መንገድ በተጨባጭ ለማየት፣ የተሻለ ዕድል ይሰጣል፡፡ ትችቱ ከዚህ በተለየ አግባብ ከሆነ፣ ከወፍ ጫጫታ አይዘልም፡፡
የብሔር ትግል መስመሩ ፈር መሳቱ፣ ባስከተለው የመጨረሻ ውጤት ምክንያት፣ ዋለልኝ መኮንን ባልኖረበት ዘመን ለተፈጸመ ስህተት እየተጠየቀ ነው። ለዋለልኝ መኮንን ወቀሳ፣ በዋናነት ሁለት መላምቶች ይቀርባሉ፡፡ አንዱ መላምት፤ ዋለልኝ መኮንን ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ለሚታገሉ ኤርትራዊያን አጋር ሆኗል የሚል ነው፡፡ ሌላው መላምት፤ በእርሱ ብዕር ተጽፎ የቀ.ኃ.ሥ.ዩ ተማሪዎች ሕብረት ልሳን በሆነው “ታገል” መጽሔት ታትሞ የወጣው የብሔር ትግል ጥያቄ ስነጽሁፍ፣ በአገራችን ብሔረሰቦች ሕዝቦች መኻል ለዘመናት ጸንቶ ለቆየው አንድነት መዳከም መነሻ ነው የሚል ነው፡፡ ዋለልኝ መኮንን ሁለት ስለት ባለው የወቀሳ ቢላዋ ይቆረጣል፡፡ በአንድ በኩል፤ የአማራ ሕዝብን ጨቋኝ ገዥ መደብ እንደሆነ አድርጎ አቀንቅኗል በሚል፣ ከራሱ ብሔረሰብ ከወጡ ምሁራን  በቂ ድጋፍ የለውም፡፡ በሌላ በኩል፤ “ብልጥ በልቶ አፉን በሞኝ ይጠርጋል” እንዲሉ፤ ከብሔረሰቦች መለያየት የሚያተርፉ ኃይሎች፣ የምክንያታዊ ድጋፍ ምንጭ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡
ዳሩ ግን ዋለልኝ መኮንንን የሚወቅሱ ዜጎች የመኖራቸውን ያህል የሚደግፉት ዜጎችም አሉ፡፡ ዋለልኝ መኮንን ለወቀሳ የተጋለጠበት አንዱ ምክንያት  በአመዛኙ፣ ለአገራቸው ከፍተኛ ፍቅር ያላቸው ዜጎች መኖር ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ግዛት አንዲትም ቅንጣት እንድትጎድል የማይፈልጉ፤ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ሕዝቦች አንድነት ለዘላለም እንዲኖር የሚፈልጉ ዜጎች መኖር፤ የአማራ ህዝብ ለጥቃት መጋለጥ የሚቆረቁራቸው ዜጎች መበራከትም ናቸው፡፡ በአማራ ብሔረሰብ ሕዝብ ስም የሚነግድ የገዥ መደብ አባላት የጥቅም ግጭት፤ የብሔር ትግል መስመሩን ፈር በማሳት፣ ለድብቅ ፍላጎት ማሳኪያ ያዋሉ ቡድኖች መኖር ጭምር በምክንያትነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡
የቀድሞ ተማሪዎችንም ሆነ ዋለልኝ መኮንንን ለመውቀስም ሆነ ለማመስገን፣ የብሔር  ጥያቄ የትግል አጀንዳ ሆኖ በቀረበበት ወቅት የነበረውን ዓለማቀፋዊና አገር አቀፋዊ ሁኔታ በአጭሩ መቃኘት ያስፈልጋል፡፡ ወቅቱ ዓለም በሁለት ተጻራሪ ጎራዎች የተከፈለችበት፤ ዘውዳዊ አገዛዙ ከምዕራቡ ጎራ ጋር የተወዳጀበት፤ የምስራቁ ጎራ በአፍሪካ አገሮች የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ለማስፋፋት በመሯሯጥ፣ በርካታ አገሮችን በእቅፉ ውስጥ ያስገባበት፤ ኢትዮጵያንም ለማቀፍ የሚሟሟትበት፤ አገራችን  ለሁለቱም ጎራዎች አማላይ  የነበረችበት፤ ፌደሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ ከእናት አገሯ ጋር በመቀላቀሏ፣ ጥቅማቸው የተነካባቸው ያኮረፉ የፌደሬሽኑ ባለስልጣናት ያሴሩበትና፣ ይኸውም ሴራ፣ ግብጽ በአገራችን ላይ ለሸረበችው ተንኮል፣ ለም መሬት የሆነበት፤ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ፈታኝ ወቅት ነበር፡፡
ግብጽ ጀብሀን በእጅ አዙር አቋቁማ፣ በሪፈረንደሙ ወቅት ያጣቻትን ኤርትራ ለመቆጣጠር፣ አለዚያም ቢያንስ ከእናት አገሯ ኢትዮጵያ ጋር እንዳትዋሃድ በማሰናከል፣ የረዥም ዘመን ህልሟን ለማሳካት የሚያስችል ሴራ በመጎንጎን ተጠምዳ ነበር። የሶቪዬት ሕብረት መንግሥት፣ የአዲስ አበባ ኤምባሲ ኮር ዲፕሎማቶች ቀ.ኃ.ሥ.ዩ ዘወትር እየገቡ፣ እየወጡ፣ ከዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ሕብረት አመራሮች ጋር እንደ ልባቸው እየተገናኙ፣ የተማሪውን ትግል የሚያነሳሱ ጽሁፎችን ሲያድሉና የሞራል ድጋፍ ሲሰጡ ማንም ከልካይ አልነበራቸውም፡፡
አገራዊ ሁኔታው ከዚህ ባልተናነሰ መልኩ ውጥረት የሰፈነበት ነበር፡፡ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ዜጋ ንጉሠ ነገሥቱን ለማገልገል ብቻ እንደተፈጠረ ያስብ የነበረው፤ “ስዩመ እግዚአብሔር፤ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ” ብሎ ራሱን የሚጠራው ዘውዳዊ መንግሥት የብሔረሰቦች ሕዝቦችን መብት ዕኩልነት ያላከበረ (ብሔረሰባዊ ጭቆና) ፤ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የረገጠ (መደባዊ ጭቆና) በመሆኑ በሕዝብ ላይ ይደርስ የነበረው የግፍ ዋንጫ ሞልቶ የፈሰሰበት ወቅት ነበር፡፡
በተጨማሪ በኤርትራ ላቆጠቆጠው ችግር አፈታት ንጉሡ የቀየሱት የየዋህ መንገድ ቀውሱን ለማባባስ ተጨማሪ ነዳጅ ነበር፡፡ ንጉሡ እሾህን በእሾህ በሚል ፈሊጥ በኤርትራ የተመሰረተውን ጀብሀ እንቅስቃሴ በእንጭጩ ለመቅጨት ኢሳያስ አፈወርቂን የመሳሰሉ ትኩስ ጉልበት የነበራቸው ወጣቶች፣ ከአዲስ አበባ በመመልመል ወደ አሥመራ በመላክ፣ የኤርትራ እንደ ራሴ ከሆኑት ልዑል ራስ አስራተ ካሳ ጋር በምስጢር እየተገናኙ እንዲሠሩ መላካቸው፣ ለወጣቶቹ የልብ ልብ ሰጥቷል፡፡ በሂደት ለንጉሡ ከምንሠራ ለምን እኛው አሥመራ ላይ ገዥ መደብ ለመሆን አንታገልም በማለት፣ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመመሳጠር፣ ሻዕቢያን በማቋቋም የፖለቲካውን ንፋስ ጠረን ቀየሩት።
ለተወሰነ ጊዜ በባዕድ አስተዳደር ስር በወደቀችው ኤርትራ የተገዙት ዜጎች፣ የኢትዮጵያዊነት ስነልቦናቸው እንዲመለስ በማሰብ፣ ንጉሡ የኤርትራ ወጣቶችን ወደ መኻል አገር በገፍ በማስመጣት፣ የስኮላርሽፕ ቅድሚያ በመስጠት፤ ነቄ የኤርትራ ልሂቃንን በከፍተኛ የሹመት ቦታና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ሥራ ላይ በመመደብ፤ ነጋዴዎችን የመሬትና የንግድ ሥራ ቅድሚያ በመስጠት በአንድ አገር ዜጎች መኻል የተፈጠረው አድልዖ ሌላው የትግል ጥያቄ መፍለቂያ ምንጭ ነበር። አንድ ምሳሌ ብቻ ለመጥቀስ፤ የአቶ ኢሳያስ አፈወርቅ አብርሐ አጎት የነበሩት ደጃዝማች ሠሎሞን አብርሐ በአገር አስተዳደር ሚኒስቴር ዳይሬክተርነት ከዚያም በኋላ የወሎ ጠቅላይ ግዛት የንጉሡ እንደራሴ በመሆን ሠርተዋል፡፡ በወሎ ጠቅላይ ግዛት የነበሩ ፋብሪካዎች፤ ንግድ ቤቶችና በመንገድ ዳር ያሉ ውሃ ገብ መሬቶች በአጠገብ ሌላው በጭሰኝነት እየኖረ በነማን የተያዙ እንደነበሩ በየቦታው በመሄድ ዕድሜ ጠገብ ሰዎችን ጠይቆ መረዳት ይቻላል፡፡ በመላው አገሪቱ የነበረው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡
ንጉሡ ከኤርትራ ህዝብ ያገኙትን ከልብ የመነጨ የሚመስል ድጋፍ የዝናብ ወቅት እየጠበቁ አሥመራ በሚሄዱበት ወቅት በሚጥለው የዝናብ ካፊያ ድባብ በሚደረግላቸው የኤርትራዊያን የሞቀ የአቀባበል ልክ በመገመት ሲታለሉ ሻዕቢያ ግብጽን ጨምሮ ከበርካታ አረብ አገሮች በሚሰጠው ድጋፍ የተነሳ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፈርጠም ቻለ፡፡ በጣሊያን አስተዳደር ጊዜ የተቋቋሙት ጥቂት ኢንዱስትሪወች በፈጠሩት የሥራ ዕድል ወጣቱ ከተቀረው ኢትዮጵያ ወደ አሥመራ ቀስበቀስ እየተሳበ መሄድ ሲጀምር በአንዳንድ የኤርትራ ነዋሪወች በንቀት ሲታይ፤ በአንጻሩ  እንደ ዕንቁላል በጥንቃቄ የተያዙት ኤርትራዊያኑ ስልጡን ነን ባይነታቸው ጋር ተደምሮ ለራሳቸው ከፍ ያለ ግምት በመስጠት መኩራራት ያዙ፡፡ አንዳንድ ኤርትራዊያን ጥጋባቸው ከልክ አልፎ “የሚበሉበትን ወጭት መስበር” ጀመሩ፡፡ ይህ የተዛባ ግንኙነት በአገር ውስጥ አንድ ሌላ ከባድ ፈተና እየሆነ መጣ፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የደረሰው ድርቅ ባስከተለው ረሐብ ያለቀው ሕዝብ ለተማሪው የትግል እንቅስቃሴ ተጨማሪ ጉልበት ሰጠ፡፡ ሲጠቃለል የአገሪቱ ስትራቴጂካዊ ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ፤ የተጻራሪ ዓለምአቀፍ ጎራወች ግፊት በተለይም የሶቪዬት ህብረት ጣልቃገብነት፤ ብሔረሰባዊና መደባዊ ጭቆና ከአድሎአዊ ንጉሣዊ አስተዳደር ጋር ተደምሮ የተማሪወች ትግል ጥያቄወች መፍለቂያ ምንጮች ነበሩ፡፡
ወቅቱ የአይቀሬ የፖለቲካ ትግል ወቅት ነበር። ከዚሁ ጎን ለጎን የተማሪውን ትግል በመጠምዘዝ ለስውር ዓላማቸው ማሳኪያ ለማዋል የሚጣጣሩ ኃይሎች መኖራቸው የሚጠበቅ አጋጣሚ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው ለቀድሞ ተማሪወች የመታገያ አጀንዳ የሆኑት ሦስቱ መሰረታዊ የፖለቲካ ትግል ጥያቄወች ነጥረው ለመውጣት የቻሉት፡፡ በእነዚህ ስር የሚካተቱ ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ይዘት ያላቸው የፖለቲካ ጥያቄወችም ነበሩ፡፡ የዋለልኝ መኮንንን የብሔር ትግል ተሳትፎና አስተዋጽዖ መመልከት የሚኖርብን ከዚህ ዳራ በመነሳት ነው፡፡
ዋለልኝ መኮንንን ጨምሮ የቀድሞ ተማሪወች ፊዳ ከሆኑላቸው ሦስት መሰረታዊ የፖለቲካ ጥያቄወች “የብሔር ትግል ጥያቄ” አንዱ ነው፡፡ “መሬት ላራሹ” እና “የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበሩ” የሚሉ ሁለቱ የፖለቲካ ጥያቄወች የገዥ መደቦቹ ባህርይ በፈቀደው ልክ ተስተናግደዋል፡፡ “መሬት ላራሹ” የሚለው ጥያቄ በደርግ ዘመን መሬት ለአርሶ አደሩ እንዲከፋፈል በመደረጉ ምላሽ አግኝቷል፡፡
የቀ.ኃ.ሥ.ዩ. ተማሪዎች ሕብረት የብሔር ትግል ፖለቲካ ንድፈ-ሓሳብ ዓላማ የግለሰብንና የብሔረሰብ መብትን በጣምራ እንዲከበር ለማድረግ ነበር፡፡ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሰያዊ መብት አያያዝ ከንጉሡ ወቅት ከነበረው ሁኔታ ቀስበቀስ እየተሻሻለ የመጣ ቢመስልም በአሁኑ ወቅት ከዜጋ መብት ይልቅ የብሔረሰብ መብት ቅድሚያ ትኩረት በማግኘቱ የዜጎች መብት በብሔረሰብ አጥር ውስጥ ገብቶ ተጨፍልቋል፡፡ በተጨማሪም በብሔረሰቦች ህዝቦች ልዩነት ላይ ትኩረት ሲደረግ የጋራ ለሆነው የኢትዮጵያዊነት ጸጋ የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ በመሆኑ በብሔረሰብ ሕዝቦች መኻል ለዘመናት ጸንቶ የቆየው አንድነት ተዳክሞ አገራችን ኢትዮጵያ ለከፍተኛ ጉዳት ተዳርጋለች፡፡ ይህ ማለት ብሔረሰብ ሲታወስ ዜጋና አገር ተረስቷል፡፡ ነገሩ ግራ የሚያጋባ ይመስላል፡፡
የብሔር/ብሔረሰብ ጽንሰ-ሓሳብ በቀድሞ ተማሪወች የብሔር ትግል ውስጥ ማዕከላዊ ቦታ አላቸው፡፡ከታሪካዊ ቁስአካልነት ፍልስፍና አተያይ በመነሳት ብሔር/ብሔረሰብ በአንድ የታሪክ ወቅት በመኖር የሚገለጽ ማህበረሰብ ነው፡፡ ብሔረሰብ፤ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ማለትም በፊውዳላዊ ወይም ቅድመካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ደረጃ ውስጥ የሚገኝ ማህበረሰብ ሲሆን፤ ብሔር፤ ከፊውዳሊዝም መክሰም በኋላ ከካፒታሊዝም ማደግ ጋር ተያይዞ የተዋሃደና በከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ያለ የጋራ ኢኮኖሚ ሕይወት ያለው ማህበረሰብ ነው፡፡ የጋራ ኢኮኖሚ ሕይዎት መፈጠር ዋናው ምክንያት የካፒታሊዝም ማደግ ነው፡፡
የካፒታሊዝም ማደግ የምርትን መዳበር ያስከትላል፤ የሥራ ክፍፍልን በሰዎችና በስፍራዎች መካከል ያከፋፍላል፤ የቴክኒዮሎጂ ዕድገት፤ የአንድን ሕዝብ ቋንቋና ባህል፤ የኢኮኖሚ ማደግና መስፋፋትን ያፋጥናል፡፡ በዚህም ምክንያት በሕዝቡ መካከል የበለጠ መቀራረብና መተሳሰር ይኖራል፡፡ በዚሁ የብሔረሰብ ወደ ብሔር መለወጥ ይሆናል፡፡ ከዚህ ተነስቶ ለሚያይ የተረጋጋ ሰው እንኳን የብሔር ትግል በተጀመረበት 1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ዛሬም ቢሆን በሁለተኛው የታሪክ ወቅት (ካፒታሊዝም) የሚኖር የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የለም፡፡ በእኔ እምነት ከታሪካዊ ቁስአካልነት ፍልስፍና ትንተና ጋር የሚጣረሰው “ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች አገር ናት” የሚለው እንጂ “ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔረሰቦች አገር ናት” መባሉ አይደለም፡፡ ዛሬ በየትኛውም የአገራችን ክፍል የሚገኝ አርሶ አደር የሚያርሰው ጠባብ ድግር የተገጠመለት ሞፈርና ቀንበር በበሬ ወይም በፈረስ እያስጎተተ በመሆኑ አንዱ ወይም ሌላው ብሔረሰብ ካፒታሊስት ኢኮኖሚ ሕይወት ውስጥ ፈጥኖ ሲገባ ሌላው ወደ ኋላ ቀርቶ በቅድመ ካፒታሊስት ኢኮኖሚ ሕይወት ውስጥ እየተንፏቀቀ ነው ለማለት የሚያስችል ቁመና የለም፡፡ ከየብሔረሰቡ ወጥተው በስሙ ኪራይ ሰብስበው ከባድ ኢንዱስትሪ ወይም ዘመናዊ ንግድ ሥራ የከፈቱትን ጥቂት ግለሰቦች የታሪክ ወቅት ሽግግር አድርገዋልና “የየብሔረሰባቸው ብሔር” ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉ አዋቂወች ካሉ ይሁንላቸው! ማለት መብት ስለሆነ! ወሬ አይከለከልም፡፡
ከዚህ ሁኔታ ተነስተን ስናይ ከላይ እንደተጠቀሰው “ብሔር”፤ “ብሔረሰብ” የጠራ ግንዛቤ ያልተያዘበት ጽንሰ-ሓሳብ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ ተማሪው ጨቋኙን ስርዓት ለመታገል የሚያስፈልገው ከጠራ ግንዛቤ መነሳት አልነበረም፤ በመሬት ላይ በግልጽ ከሚታይ በሕዝብ ላይ ከሚፈጸም ግፍ እንጂ። በአንዱም ሆነ በሌላው ጽንሰ-ሓሳብ ሊገለጽ የሚችል የኢትዮጵያ ሕዝብ በገዥ መደብ ጭቆና ስር ወድቆ ነበር፡፡ አገሩን እንደሚወድ፤ ለሕዝብ እንደሚቆረቆር ዜጋ፤ ዋለልኝ መኮንን በሕዝብ ላይ የደረሰውን ብሔረሰባዊና መደባዊ ጭቆና ተመሳሳይ ግንዛቤ ከነበራቸው ሌሎች ዜጎች ጋር አብሮ ወደፊት በማራመድ መፍትሔ ለማስገኘት የሚያስችል የፖለቲካ ትግል ስልት መርጧል፡፡ አስደናቂው ነገር የብሔር/ብሔረሰብ ጽንሰ-ሓሳብ ዋለልኝ መኮንን ከሞተ 45 ዓመታት በኋላም ሊጠራ አለመቻሉ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎትና የፖለቲከኞቹ አመለካከት ቅኝት ስለማይጣጣም የብሔር ፖለቲካው ከአሁን በኋላም እንደ ጓሸ የሚቀጥል ይመስላል፡፡ የብሔረሰብ ፖለቲካው ቢላዋ ከብሔረሰቦች አንድነት ይልቅ ልዩነትን ለማስፋትና ከአማራ ሕዝብ ለማቆራረጥ እንዲያስችል ተደርጎ ስለተሳለ በብሔረሰቦች ሕዝቦች መኻል የቆዬውን አንድነት ለማስቀጠል በሚያስችል መልኩ ሊቆርጥ አይችልም፡፡“ፈጣሪያችን የሰጠን ፖለቲከኞቻችን” የልቦና ውቅር ለውጥ እስካላመጡ ድረስ በአገራችን የብሔር ትግል መዘዝ  ጎራዴ እያማዘዘ መቀጠሉ አይቀርም፡፡
ከአዘጋጁ፡- (ጸሃፊው የቋንቋና ብሔርተኝነት መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ  ሁለተኛው  ክፍል “ከዋለልኝ መኮንን ወቀሳ በስተጀርባ ያለ ዕውነታ” በሚል ርዕስ በሚቀጥለው ሳምንት  ይቀርባል፡፡ ጸሃፊውን በአንባቢያንና በዝግጅት ክፍሉ ስም ልናመሰግናቸው እንወዳለን፡፡)

Read 7039 times