Sunday, 03 June 2018 00:00

ብሔርተኝነት በኢትዮጵያውያን መሃከል አጥር እየሠራ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ሌላው ተወያይ ባለሃብቱ ኢ/ር ፀደቀ ይሁኔ በሰጡት አስተያየት፤ “ኢህአዴግ የሚከተለውን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ
አለም አሸናፊ ሃሳብ ለማድረግ ከፈለገ፣ ጠመንጃውን ወደ ድንበር ልኮ ሃሣቡን ብቻ ቢያቀርብ ጥሩ ነው” ብለዋል፡፡
      
   የብሄርተኝነት አመለካከት በኢትዮጵያውያን መካከል የልዩነት አጥር እየሠራ መሆኑ ምሁራንና ፖለቲከኞች ያሣሳቢ ሲሆን ይህን ለማረቅም አዲስ አይነት አማራጭ የፖለቲካ ቅኝት ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
“ፍሬድሪክ ኤበርት ስቲፍቱንግ” ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል ባዘጋጀውና በሃገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በመከረው በሃገሪቱ ያለው ፅንፍ የወጣ ብሄርተኝነት ከፍተኛ ስጋት እየፈጠረ ነው ተብሏል፡፡
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የቀድሞ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ፣ የአሁኑ የህወኃት ማዕከላዊ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳ፤ “በኢትዮጵያ የመንግስት አስተዳደር ውስጥ ያሉ ተግዳሮቶች እና ተስፋዎች” በሚል ርዕስ፣ ለውይይት መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በዋናነት የማስፈፀም አቅም ማነስና የኢህአዴግን አብዮታዊ ዲሞክራሲ መርህ ጠንቅቆ አውቆ ያለመስራት፣ በስርአቱ ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ የኢህአዴግ ትልቁ በሽታ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው ይላሉ፡፡ “ባለፉት 27 ዓመታት በአገሪቱ ሲተገበር የኖረው ዲቃላ ርዕዮተ አለም ነው፤ ኢህአዴግ ሲመቸው ካፒታሊዝም ሣይመቸው ኮሚኒዝምን እያጣቀሠ ሲሠራ ነበር” ብለዋል-ፖለቲከኛው፡፡
ኢህአዴግ በሚከተለው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ምክንያት በሃገሪቱ ነፃ የፍትህ፣ ነፃ ምርጫ ቦርድ፣ ነፃ የሠብአዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋማት እንዳይፈጠሩ ተደርጓል፤ ይህም ሃገሪቱን ለውስብስብ ፖለቲካዊ ችግሮች ዳርጓታል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
ባለፉት 27 አመታት የመንግስት ስርአት ውስጥ የፓርቲና የመንግስት ስራ ሆን ተብሎ እንዲቀላቀል ተደርጓል የሚል እምነት እንዳላቸው የተናገሩት ሌላኛዋ የመድረኩ ተወያይ ወ/ሮ ሠሎሜ ታደሰ፤ “ኢህአዴግ ችግር አለብኝ ይላል፣ በዚያው ልክ ለችግር መፍቻ የሚሆነውን ስልጣንም ይዟል፣ ታዲያ ማን ችግሩን ይፍታው?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና የወ/ሮ ሠሎሜን ሃሳብ እንዲህ ሲሉ አጠናክረውታል፡፡ “ኢህአዴግ በፈጠረው ዲቃላ ስርአት፣ መንግስትና  የመንግስት ተቋማትን፣ የፓርቲው የግል ሃብቶች ወይም የግል ጉዳይ አስፈፃሚ አድርጓቸዋል፡፡ ምርጫ ቦርድና ፍ/ቤቶችም የኢህአዴግ የጦር መሣሪያዎች ናቸው” ያሉ ዶ/ር መረራ፤ “እነዚህን መሣሪያዎቹን ይዞ ኢህአዴግ አውራ ፓርቲ ሣይሆን አውሬ ፓርቲ ነው የሆነው” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከፖለቲካ መድረክ የተገፋው ምሁር፤ ኢህአዴግ ውስጥ ካለው ስብሰብ በእጅጉ የበለጠ ነው ያሉት ዶ/ር መረራ፤ ሆን ተብሎ ምሁሩ ከሃገሩ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ውጪ እንዲሆን ተደርጎ ቆይቷል- ይህም ወደ ውስብስብ ፖለቲካዊ ችግር አምጥቶናል ብለዋል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎችም አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፡፡ የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሠይፉ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፤ መንግስት ራሱ ችግር አለብኝ ካለ፣ ተቃዋሚዎችም ችግር አለባቸው ከተባለ፣ ምሁሩም ሚናውን እየተወጣ አይደለም የሚባል ከሆነ፤ ታዲያ ለዚህች ሃገር ችግር መፍትሄ የሚያመጣ ማነው? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ግርማ አክለውም፤ የማይረባ ተቃዋሚ፣ የማይረባ ሚዲያ፣ የማይረቡ ሲቪክ ተቋማት የፈጠረው የኢህዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡
የህግ ባለሙያ አቶ ውብሸት በበኩላቸው፤ የመንግስታት አስተዳደር ሁኔታ አሁን ላይ ሆኖ ለወደፊት በሚመጣውን ለመገመት በሚያስችግር ሁኔታ ተበላሽቷል፤ ይህን ለማስተካከል መሠረታዊ የሆነ ለውጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የመድረክ ተወያይ ሆነው የቀረቡት የፖለቲካ ተንታኝ ዶ/ር ሚሊኬሣ ሚደጋ በበኩላቸው፤ ብሄርተኝነት የሚገነው ጭቆና ሲበዛ ነው፤ ዲሞክራሲ እየሠፈነ ሲሄድና ለጥያቄዎች ምላሽ ሲገኝ መስተካከል የሚችል ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ሃገር ሚዲያዎች፣ የሲቪክ ተቋማትና፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ህዝቡ እምነት እንዲያጣ ሲደረግ መቆየቱ ትልቅ ችግር እንዳስከተለም ጠቁመዋል፡፡
ሌላው ተወያይ ባለሃብቱ ኢ/ር ፀደቀ ይሁኔ በሰጡት አስተያየት፤ “ኢህአዴግ የሚከተለውን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ አለም አሸናፊ ሃሳብ ለማድረግ ከፈለገ፣ ጠመንጃውን ወደ ድንበር ልኮ ሃሣቡን ብቻ ቢያቀርብ ጥሩ ነው ብለዋል፡፡” ኢትዮጵያዊነትን ዘላለማዊ ለማድረግ ከስር መሠረቱ የተንሠራፋውን ብሄርተኝነት ጉዳይም መፈተሽ እንደሚገባ ኢ/ር ፀደቀ አሣስበዋል፡፡
የህገ መንግስት ኤክስፐርቱ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ደግሞ፤ ኢህአዴግ ከ1997 ምርጫ በኋላ በገፍ ያከናወነው የአባላት ምልመላ፣ የ“እበላ ባይነት” ፖለቲካን አስፋፍቷል ባይ ናቸው፡፡
በፖለቲካው ከስነ ምግባርና ከሠብአዊነት ይልቅ ኢ-ሠብአዊነት በየጊዜው እየገነነ መጥቷል ያሉት ዶ/ር ጌዲዮን፤ የዜጎችን የአስተሣሠብ አድማስ ማስፋት የቻለ የትምህርት አልፈጠርንም ብለዋል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ባለ በርካታ ብሄሮች ባሉባት ሃገር፣ ብሄርተኝነት ከልኩ አልፎ  እጅግ እየገነነ ሄዷል የሚሉት ምሁሩ፤ ብሄርተኝነቱ በህዝቦች መካከል ትልቅ ግድግዳ እየሠራ፣ የወደፊቱን የሃገሪቱን ሂደት አስጊ አድርጎታል ብለዋል፡፡
አዲሱ ትውልድ እየገነነ ለመጣው የብሄርተኝነት ችግር መፍትሄ የማምጣት አቅም ቢኖረውም ሃሣቡን አውጥቶ የሚወያይበት ነፃነት በመነፈጉ “አርፌ ኑሮዬን ልኑር” በሚል ብሂል እየተመራ ነው ይላሉ - ዶ/ር ጌዲዮን፡፡
በቀረቡ አስተያየቶች ላይ ሃሳባቸውን የሰነዘሩት አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፤ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ ትክክለኛ መስመር ነው፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲን የሚያስጠቁት በየሰፈሩ መፈክር ይዘው የሚዞሩ ካድሬዎች ናቸው” ብለዋል፡፡ ከህዝቡ ጋር ግንኙነት የሚደረግባቸው መንገዶችም ሰዎችን የሚያቀርቡ ሳይሆን የሚያርቁ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ መንግስት ያበላሸው በርካታ ነገር አለ ብለዋል፡፡
አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀሩ ድርጅቱ የሚመራበትን አብዮታዊ ዲሞክራሲ መተንተን ይቸግራቸዋል ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ኢህአዴግ በዚህ ርዕዮተ ዓለም የሚሊዮኖችን ህይወት የቀየረ ስራ ሰርቷል፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲ በራሱ ችግር የለበትም ሲሉ ሞግተዋል፡፡
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅና ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ ልሂቃን፣ ምሁራንና የማህበረሰብ ለውጥ አራማጆች ተሳትፈዋል፡፡


Read 1505 times