Sunday, 27 May 2018 00:00

የቤኒሻንጉል ተፈናቃዮች መፍትሄ አላገኘንም ይላሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)


       

            “ወደ ተፈናቀልንበት መመለስ ራስን ለሞት መስጠት ነው”
              (ቄስ ምናለ አያሌው፤ ተፈናቃይ)

      ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማይ ዞን፣በለው ጅንጋፍወይ ወረዳ፣ ዴዴሳ ቀበሌ፣ ባለፈው ጥቅምት ወር በክልሉ ተወላጅ ወጣትና በአማራ ተወላጅ ወጣት መካከል በተፈጠረ ጠብ፣ የክልሉ ወጣት ህይወት ማለፉን ተከትሎ በተነሳ ግጭት 13 ሰው መሞታቸውን፣49 ከባድ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው፣ 149 ቤቶች መቃጠላቸውንና በርካታ ንብረቶች መውደማቸውን ተፈናቅለው በባህርዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ተጠልለው የሚገኙት የ517 አባወራዎች አስተባባሪ አቶ ዳንኤል ስመኝ ይናገራሉ፡፡
 ከቤኒሻንጉል ተፈናቅለው አሁን ተጥልለው ወደሚገኙበት የባህርዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል የመጡት ባለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ ቢሆንም እስካሁን የአማራ ክልላዊ መንግስት መፍትሄ እንዳልሰጣቸው ይናገራሉ፡፡ በርግጥ የክልሉ መንግስት ሃላፊዎች አነጋግረዋቸው፣ሁለት አማራጮች እንዳቀረቡላቸው ነገር ግን ሁለቱንም አማራጮች እንዳልተቀበሏቸውና የራሳቸውን አማራጮች ማቅረባቸውን ተፈናቃዮቹ ጠቁመዋል፡፡ እኒህ አማራጮች ምንድን ናቸው? ለምንስ አልተቀበሏቸውም? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ሦስት የቤኒሻንጉል ተፈናቃዮችን አነጋግራለች፡፡ ደረሰብን ከሚሉት አሰቃቂ ጥቃት አንስቶ አሁን እስካሉበት ሁኔታና ከመንግስት ምን እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ከአንደበታቸው እነሆ፡-


   ከጎጃም ደጋ ዳሞት ወደ ቤኒሻንጉል ህይወቴን ለመቀየር የመጣሁት በ1997 ዓ.ም ነበር፡፡ በአካባቢው ማፈናቀል፣ ግድያና የንብረት ውድመት ሲፈጸም የመጀመርያው አይደለም፡፡ የዘንድሮው አርብ ቀን ነው ጉዳቱ የደረሰብኝ፡፡ በዕለቱ ት/ቤት ያሉ ልጆችን ሊፈጇቸው ነው ሲባል፣ በሬን ዘግቼ፣ ጎረቤቶቼን ሰብስቤ ወደ ት/ቤት በምሄድበት ሰዓት ነው፣ ገና ት/ቤት ሳልደርስ፣ በቀስት እጄ ላይ መትተው የጣሉኝ፡፡ ሁለተኛ ሲሰድዱ ቀስቱ ጉንጬ ላይ መታኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ደሜ እየፈሰሰ መሬት ላይ ወድቄ ዋልኩኝ፡፡ ልጆቼ ጋ ሳልደርስ፣ ከቤቴም ሳልሆን መሃል ላይ ቀረሁ፡፡ ልጆቼ እየሮጡ መጥተው የግቢውን በር ጥርቅም አድርገው ዘግተው ቁጭ አሉ፡፡ ጥቃት ፈፃሚዎቹ በሩን ከውጭ ሲደበድቡ አልከፈት አላቸው፡፡ በመጥረቢያ ፈልጠው ከፈቱት፡፡ ከቤቴ አካባቢ ባሉ ሌሎች ቤቶችና መጋዘኖች ላይ እሳት ለኩሰው አቃጠሉ፡፡ የእኔ በር ሲከፈት ልጆች በአንድ ላይ ሲጮሁ፣ እንዳይጨርሱኝ ብዬ ተደብቄ፣ ከወደቅኩበት ደሜን እያዘራሁ ተነሳሁ፡፡ ልጆቼ አንድ ነገር ሆነው እኔ እንዴት ቆሜ እሄዳለሁ ብዬ ስወጣ፣ በድጋሚ በቀስት መቱኝ፤ አቅም አጥቼ ወደቅኩኝ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ልዩ ኃይሎች አሉ፣ ፖሊስ አለ፣ የሚሊሺያ ፅ/ቤት ኃላፊና የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪዋም ቆማ ትመለከት ነበር፡፡ ይሄ የሆነው ጠዋት 2፡00 አካባቢ ነው፡፡ እኔ እዛው ወድቄ አቅም አጥቼ፣ አሻግሬ እያለሁ፤ ከቤቴ የተጠለሉትን ወንድሞቼን በተለይ በጣም የምወደውን ወንድሜን ምንይችል ሙሉን ሲያሯሩጡት፣ “አድኑኝ” እያለ እየጮኸ አረዱት፡፡ ሌሎች ወገኖቻችንም ጫካ ተወስደው ተገደሉ፡፡ ይህ ሁሉ ግፍና በደል መንግስት ባለበት አገር ሲፈፀም ማየት ራሴን እንድጠላ አድርጎኛል፡፡
እኔ በወደቅኩበት ሳር ውስጥ ደሜ ሲፈስ ውሎ፣ ጠዋት የወደቅኩኝ ማታ አንድ ሰዓት ነው የተነሳሁት፡፡ ሰው እየዞረ የወደቀ ሲያነሳ ነው አግኝቶ ያነሳኝ፡፡ በዕለቱ በጣም ራሴን የጠላሁት የሰባት ዓመት ሴት ልጄ ከት/ቤት ራሷን ለማዳን ወጥታ፣ ወደ ጫካ ስትሮጥ፣ ልብሷን ቆንጥር ሲይዝባት እያወለቀች እየጣለች ስትሮጥ፣ ራቁቷን ጫካ ውስጥ ውላ፣ ሰው እየዞረ ሬሳ ሲፈልግ ብቻዋን ተገኝታ መጣችልኝ፡፡ እስኪ ወላድ ይፍረደን … ይህንን ግፍ! አሁንም የወንድሜና የወገኖቼ ሀዘን፣ የልጄ ጫካ ውስጥ አዋዋል፣ ከአንዴም ሁለቴ በቀስት የተወጋሁት ህመም አለቀቀኝም፡፡ እየተሰቃየሁ አለሁ፡፡
በዚሁ ዕለት 13 ሰው ህይወቱ አልፏል፡፡ 49 ሰዎች ከባድ የመቁሰል አደጋ ሲደርስባቸው፣ 139 ቤቶች በእሳት ጋይተዋል፡፡ ይገርማችኋል፤ እኛ ባህርዳር መጥተን ጊዮርጊስ ወድቀን፣ መጋቢት 8 ቀን የቀሩትን 10 ቤቶች አነደዷቸው፡፡ በቀደመው ጥፋት ሳይፀፀቱ ማለት ነው፡፡
በወቅቱ 49ኛችንም ጤና ጣቢያ ሄደናል፡፡ እኔን ጨምሮ በጣም የተጎዱትን ጤና ጣቢያው አልችልም ብሎ ወደ ነቀምት ሄድን፡፡ እኔ ነቀምት ተኛሁ፡፡ ከእኔ በላይ የተጎዱት ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተወሰዱ፡፡ እራሳቸው ገዳይ፣ እራሳቸው አዳኝ ለመሆን ማለት ነው፡፡ መጀመሪያ ቆመው አስፈጁን፡፡ በኋላም አሳከምን ለማለት ሲሯሯጡ አየን፡፡ ሌላው ግፋቸው የሞተውን ሰው ሬሳ ለመደበቅ ያደረጉት ጥረት ነው፡፡ በፓትሮል እየዞሩ፣ ሬሳ እየለቀሙ ጫካ መጣል ጀመሩ። አራት ወንድሞቻችን በዚህ ምክንያት ለመጠጥ ውሃ የቆፈርነው ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ገብተው ቀርተዋል። ህዝቡ ለማውጣት ቢታገልም አልተቻለም፤ እዚያው ቀሩ፡፡
በዚህ ላይ እያለን ቀይ መስቀል ለአንድ ወር ያህል ገብቶ፣ ቀለብ ለቤተሰባችን አምስት አምስት ኪሎ እህል ሲሰጠን ሰነበተ፡፡ እኛም መልሰው ሊያቋቁሙን ነው ብለን ተቀምጠን ስናበቃ፣ ከአንድ ወር በኋላ ቀይ መስቀል ገብቶ እንዳይረዳን ታገደ፡፡ እኛም እዛው ታፍነን ልንሞት ሆነ፡፡ ሲጨንቀኝ መሰሎቼን አሰባስቤ፣ 96 ሰዎች ሆነን ወደ ወረዳው አስተዳዳሪ አቤት ለማለት ሄድን፡፡ የምንኖረው ከማይ ዞን በለው ጅንጋፍወይ ወረዳ፣ ዴዴሳ ቀበሌ ነው፡፡ “ሁላችሁንም አንፈልግም፤ ሰው መርጣችሁ ወክሉ” ተባልን፡፡ አምስት ሰው ተመረጠ፡፡ እኔም አንዱ ሆኜ፣ የወረዳው አስተዳዳሪ ጋ ቀርበን፣ ችግራችንን አስረዳን፡፡ በዚህ ጊዜ አስተዳዳሪው ምናለ፤ “እናንተ መንግስት ጋር አትሂዱ፤ ብትሄዱም ምንም የምታገኙት ነገር የለም፡፡ ቆፍራችሁም የቀን ስራ ሰርታችሁም መብላት ትችላላችሁ” አለን፡፡ “መብላት መጠጣቱ ይቅርብን፣ እስከ ዛሬ የተፈፀመብን በደልና ግፍ በምን ይካሳል? የመብታችንስ ጉዳይ?” ብንለው፤ “እንደውም የደረሰባችሁ በጣም ቀላል ነው። አሁን እኮ ሰላም ነው፣ የሞቱባችሁ 13 ሰዎች ብቻ ናቸው… አይደለም? እነዚህ በጣም ትንሽ ናቸው፤ ዱሮ እንዲያውም ከዚህ ይብስ ነበር፡፡ ወረዳው በለው ጅንጋፍወይ ነው አይደል? ትርጉሙ የወንዶች … የጀግኖች አገር ማለት ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ባህል አንድ ሰው ሲሞትብን፣ ብዙ ሰው መግደል ባህላችን ነው፤ ይህን የኖረ ባህል በአንድ ጊዜ መቅረፍ አስቸጋሪ ነው” ሲለን፣ በቃ ተስፋ ቆረጥን፡፡
--ከዚህ በኋላ ወደዛ ቦታ ተመልሰን አንሄድም፡፡ ተመልሳችሁ ሂዱ የሚል አካል ካለ፣ ከሞት የተረፋችሁት ሙቱ ብሎ መፍረድ ነው እንጂ መፍትሄ አይሆንም። እኛ መንግስት እንዲያደርግልን የምንፈልገው ትልቁ ነገር፣ እዚሁ የትውልድ አካባቢያችን መቋቋሚያና መጠለያ ተሰጥቶን፣ ህይወታችንን እንድንቀጥል ነው፡፡ ነገር ግን አንደኛ ወደተፈናቀላችሁበት ተመለሱ፤ ሁለተኛ ወደየ ትውልድ አካባቢያችሁ ሄዳችሁ ተቀላቅላችሁ ኑሩ ነው ያሉን፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ ወደተፈናቀልንበት መመለስ ራስን ለሞት መስጠት ነው፡፡ ሁለተኛው አማራጭ፣ ወደ ትውልድ ቦታዬ ሄጄ ለመቀላቀል እኔ ብቻዬን አይደለሁም፤ 8 ቤተሰብ ሆኜ ነው የተመለስኩት፡፡ ምን መሬት አግኝቼ፣ የት ተጠግቼ ነው፣ ይህን ሁሉ ቤተሰብ የማስተዳድረው?
መንግስት ለሁላችንም መጠለያና መቋቋሚያ ሰጥቶን፣ ልጆቻችን ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉና ኑሯችንን እንድንገፋ እጠይቃለሁ፡፡ በመጨረሻም ለባህር ዳር ከተማ ህዝብ እጅግ በጣም የከበረ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ እርቦን ነበር፣ ታርዘን ነበር፣ ህዝቡ እያበላን እያላሰን ነው፡፡ ብቸኝነት ወርሶን ፍቅር አጥተን ነበር፣ ወገን እንዳለን አውቀናል፡፡ የባህር ዳር ፍኖተ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን ዋና አስተዳዳሪም እናመሰግናለን፡፡


---------------------------


                  “መጀመሪያም መሬት አጥተን ነው ከቀዬአችን የተሰደድነው”
                    (አቶ ጫኔ ታደሰ፤ ተፈናቃይ)


     ሚያዚያ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ገረመው ታደሰ የተባለው ታላቅ ወንድሜ ለማገዶ የሚሆን እንጨት ተሸክሞ ወደ ቤቱ ሲሄድ፣ “እንጨቱን ወዴት ነው የምትወስደው?” ብለው ልዩ ኃይሎች ጠየቁት፡፡ “ለማገዶ ነው የፈለግኩት፤ የምወስደውም ወደ ቤቴ ነው” ብሎ መልስ ይሰጣቸዋል፡፡ “መሬቱን ይሁን ግዴለም ኑርበት ብለን ስንፈቅድልህ ጭራሽ ማገዶ ምናምን እያልክ ትሰበስባለህ” ብለው በጠራራ ፀሐይ ሰባት ሆነው በዱላ፣ በእርግጫ፣ በቦክስ ሲደበድቡት ውለው ነው ጥለውት የሄዱት፡፡
እኛም ወድቆ እንዳገኘነው ቶሎ ወደ ነቀምት ሆስፒታል ወስደነው፣ ነቀምት ሆስፒታል ከአቅሜ በላይ ነው ብሎ ወደ ጥቁር አንበሳ ሪፈር ፅፎለት መጥቶ ነበር፤ ሆኖም ሁኔታው ተስፋ የሌለው ሲሆን ውሰዱት አሉን፡፡ በሞትና በህይወት መሃል እያለ ወደ ቤተሰብ ወስደነው እዚያው አረፈ፡፡ ወንድሜ ሰባት ልጆቹንና ሚስቱን እንደ ጥሬ በትኖ ነው የሞተው። አሁን ትልልቅ ልጆቹና ሚስቱ እዛው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሲሆኑ ትንንሾቹ በየዘመዱ ቤት ተበትነው፣ የሰው ፊትና ግንባር ሲያዩ ውለው ያድራሉ፡፡
ገዳዮቹ በጠራራ ፀሐይ ወንድሜን አሰቃይተው፣ በሞትና በህይወት መካከል ጥለውት ሲሄዱ ሰው አይቷቸዋል፤ ተጠቁመው ተይዘውም ነበር፡፡ ነገር ግን የወረዳው ሚሊሺያ ፅ/ቤት ኃላፊ፤ ለእነዚህ ሰዎች ስማቸውን ቀይሮ አዲስ መታወቂያ በመስጠት፤ “እነዚህ የምትሏቸው ሰዎች አይደሉም፤ ስማቸው ይሄ ነው፤ ሊጠየቁ አይገባም” በሚል ከእስር ፈትቶ ጫካ እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡ አሁን የታሰሩት በጉዳዩ ላይ የሌሉበት ወጣቶችና ህፃናት ናቸው፡፡ እኛም ታጥቀው ጫካ የገቡት ልዩ ኃይሎች ይገድሉናል በማለት ሸሽተን፣ ይሄው ለረሃብና ለእንግልት ተዳርገን ነበር፡፡ አሁን ህዝቡም ቤተ ክርስቲያኑም እያበሉን እያጠጡንና እያለበሱን ይገኛሉ፡፡ በጥሩ ሁኔታ ላይ አለን፤ ወገኖቻችን ደርሰውልናል፡፡
በአሁኑ ሰዓት የአማራ ክልል መንግስት ወይ ወደነበራችሁበት አለበለዚያ ወደተወለዳችሁበት ሂዱ እያለን ነው፡፡
እኛ እኮ መጀመሪያውኑም ለአንድ ራሳችን ጎመን መዝሪያ ቦታ አጥተን ነው የተሰደድነው። አሁን ደግሞ ሰባትና ስምንት ቤተሰብ አፍርተናል። መጀመሪያ ለራሳችን ቦታ አጥተን ቀያችንን የለቀቅን ሰዎች፤ እንዴት ነው ይህን ሁሉ ቤተሰብ ይዘን፣ ወደ እኛ ቤተሰብ የምንቀላቀለው? ምንስ ላይ ነው የምንወድቀው? ወደነበርንበት እንዳንመለስ ወረዳና ቀበሌው የገዳዮችን ስም ቀይሮ፣ መሳሪያ አስታጥቆ ጫካ ሰደደብን። ለህይወታችን ምን ዋስትና አለንና እንመለሳለን፡፡ አሁን በዚህ መሃል ግራ ገብቶን፣ እንደ ውሃ ላይ ኩበት እየዋለልን አለን፡፡
እኛ መንግስት እንዲያደርግልን የምንፈልገው አንደኛ፤ እንደ ማንኛውም ተፈናቃይ በዚሁ በአማራ ክልል ቦታ ይሰጠንና ሰርተን አርሰን እንብላ፤ ልጆቻችንን እናስተምር፡፡ አይ ይሄ አይሆንም ከተባለም በዚሁ በከተማ አካባቢ መጠለያና መቋቋሚያ ይሰጠንና ድንጋይም ቢሆን እየፈለጥን፣ የጉልበት ስራም እየሰራን እንኑር፡፡ እድሜያችንም ገና ነው፤ ጉልበትም አለን፡፡ ከዚህ ውጭ የሚታየን ነገር የለም፡፡


--------------------------



               “መንግሥት ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠን እንጠይቃለን”
                  (አቶ ፈንታ ብርሃን፤ ተፈናቃይ)


    ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም ለእኛ ጥሩ ጊዜ አልነበረም። በዕለቱ አንድ የአማራና አንድ የጉሙዝ ወጣቶች ባልታወቀ ምክንያት ይጋጫሉ፡፡ ሁለት ሆነው የአማራውን ወጣት ሲመቱት አባት “ምን አደረጋችሁ? ተዉት” ብሎ ወደነሱ ሲሄድ፤ አባትም ተመታ፡፡ በዚህ መሃል ግርግር ይነሳና የጉሙዙ ወጣት ይወድቃል፡፡ ያን ጊዜ ፖሊስ መጥቶ የወደቀውንም አሁን በእስር ላይ የሚገኘውንም ተጠርጣሪ የአማራ ተወላጅ ጭኖ ሲሄድ፣ የጉሙዝ ወጣቶች “አማራውን ወጣት ትታችሁት ሂዱ፤ እንግደለው” ብለው መኪና ሲደበድቡ፣ ፓትሮሏ በፍጥነት ተፈትልካ ሁለቱንም ይዛ ሄደች፡፡ በነጋታው ጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ.ም የጉሙዙ ልጅ ሞቶ ሬሳ ሲመጣ፣ ወጣትም ሽማግሌም ንቅል ብለው ወጡ፡፡ በደንብ ተደራጅተዋል፡፡
ወጣቱ ፊት ፊት፣ ሽማግሌዎች ከኋላ፣ ልዩ ኃይሉና ፖሊስ ጎን ለጎን ሆነው፣ በዕለቱ በየጫካው የተገደለው ሳይቆጠር፣ 13 ሰው ህይወቱ ሲጠፋ፣ 140 ቤትና ሌላ ንብረት ሲወድም፣ እንዴት መንግስት ባለበት አገር አንድ የማረጋጊያ ጥይት እንኳን ወደ ሰማይ አይተኮስም፡፡ እኔ አገሩን የጠላሁትና ተስፋ የቆረጥኩት ያን ጊዜ ነው፡፡
ከዚያ ብዙ መንከራተት፣ ብዙ ጉዳት ደርሶብን ወደ ባህርዳር መጣን፡፡ የክልሉ መንግስት የምግብ ዋስትና ብሎ አንድ አራት ቀን አባይ ማዶ ወሰደን፡፡ ጧት አንድ ዳቦ ይሰጡናል፡፡ ምሳ ላይ አንድ እንጀራ ለሶስት እንበላ ነበር፡፡ ይህንን አንክድም፤ አገራችንንም አናማም፡፡
ከዚህ ውጭ የክልላችን መንግስት ያደረገልን ነገር የለም፡፡ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከመጣን በኋላ ነው ነፍስ የዘራነው፡፡ አሁን ግራ የገባን አንድም ወደተወለዳችሁበት አካባቢ ሂዱ፤ አለበለዚያ ወደነበራችሁበት ተመለሱ የሚል ሁለት አማራጭ ቀረበልን፡፡
እኔ ወደ ስደት ስሄድ ብቻዬን ነበርኩ፤ አሁን አራት ሆኛለሁ፡፡ 8 እና 9 ቤተሰብ ያለው አለ። እንዴት በዚህ የ50 ዓመት ጉልምስናዬ፣ ቤተሰቤን ሸክፌ እንደገና ቤተሰብ ላይ እወድቃለሁ፡፡ ሁለተኛው፣ ወደ ነበራችሁበት ሂዱ ይሉናል፡፡ እኔ በበኩሌ፤ ወደነበራችሁበት ሂዱ ሲሉኝ፣ ወደ ተሳለ ሰይፍ ቅረብ እንደማለት ነው የምቆጥረው፡፡ ይህን ስቃይና እንግልት ያዩ ልጆቼ፤ ወደዛ ተመልሰው እንዴት ነው ተረጋግተውና ሰላም ተሰምቷቸው መማር የሚችሉት። እኔስ ብሆን አገሬ ብዬ እንደ ልቤ ቀና ብዬ ገብቼ እወጣለሁ ወይ? ብዬ ውስጤን ስጠይቅ፣ ለራሴ መልስ አላገኝም፡፡ ይህ እንዴት ይሆናል፡፡ ከደረሰብኝ ስቃይና እንግልት አኳያ እንኳን እዛ ሄዶ መኖር፣ ቦታውን ለማሰብና የአካባቢውን ስም ለመጥራት ይከብደኛል። ከዚህ በኋላ ጎዳና ተዳዳሪ ሆኜ፣ ሰው ካልመፀወተኝ በስተቀር ወደዚያ ቦታ አልመለስም፡፡
የቀረቡልን ሁለት አማራጮች አልተስማሙንም። እኛ በአማራ ክልልም ሆነ በድንበርተኛ ሌላ ክልል ላይ መሬት ተፈልጎ ይሰጠንና አርሰን እንብላ፤ ጉልበትና አቅም አለን፡፡ እንደምታዩን ንብረታችን ወድሞ ልብሳችን ተቃጥሎ፣ ባዶ እጃችንን ቀርተን ነበር፡፡ ፋሲል ከነማ ታርዘን ሲያየን ወገንተኛነቱን ለመግለፅ መለያ ልብሱን አልብሶን፣ የባህርዳር ህዝብና ቤተ ክርስቲያን እያበላች እያጠጣች ነው ያለነው። እግዚአብሔር ብድራቱን ይክፈላቸው፡፡ መንግስት ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈልግልን እንጠይቃለን፡፡


  

Read 3538 times Last modified on Wednesday, 30 May 2018 09:58