Saturday, 26 May 2018 13:04

እንደ መግቢያ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

  እንደ መግቢያ
                   ነቢይ መኮንን

ምነው ዛሬ እንባዬ፣ ለሰው ሳይታይ ይወርዳል
ምነው ዛሬስ ልቅሶዬ ሰው - አይሰማው - ሙሾ ሆኗል
ምን ታላቅ ሰው ሙቶብኝ ነው
እንዲህ ድምፄ ድምፁን ያጣው?
ዋ! ጋሽ አብይ!
ጋሽ አብይኮ ሰው ነበር፣ ከሰውም ሰው የቅን ማማ
የረቂቅ ተምሳሌት በላይ፣ ዕፁብ ምስል የነብስ አርማ፡፡
እሱስ አዕምሮውን አዞ፣ ማወቅ ያለበትን አውቋል፡፡
ሳያውቅ ዱታው - ዘራፍ የሚል፣ ባገሬ ስንት ዐብይ ሞልቷል!
ከዚህ በላይ እርግማን አለ? በአገር ላይ አለመታደል?
ይህ ነው መሰል ያስለቀሰኝ
ድምፅ - አልባ እዬዬ ያስቃኘኝ?!
ነበር አይባልም እሱ!
ጋሽ ዐቢይ!
ሰፊ ነው የዕውቀት አትሮንሱ
ነበር አይባልም እሱ!
“አለ”ም ቢባል፣ ተራ “አለ” አደል
ፈልጉለት ሌላ ዕፁብ ቃል
ጥበብ ነው ጥሩሩ ልብሱ
ነበር አይባልም እሱ
ሌላ የነፃነት እኩል፣ ገድል - አከል ቃል አስሉ
ነበር አይባልም እሱ!
“አለ”ም ቢባል ተራ “አለ” አደል
ፈልጉ ሌላ ህያው ቃል!!
ከህይወት ከራሱ እሚሻል!!
እናም “ቢሞት ሞተ አትበሉ”
ለእሱ ሞተ አይደለም ቃሉ
ልዩ ኑሮ ኖሮ ኖሮ
ልዩ ጥበብ ፈጥሮ አፋጥሮ
አልፎ ሄደ በሉ እንግዲህ፣ እራሱን በዕውቀት አኑሮ
እንደአየር ኃይል ባየር በሮ
እንደጠቢብ ፊልም ፈጥሮ
እንደኮሙኒኬሽን ሰው፣ የየክህሎቱን ቸሮ
የልባም አዋቂን ገድል፣ ፈፅሞና አስከብሮ
እራሱን አውርሶን ሄዷል፣ የልካችንን ቀምሮ!
ዕውነት እንበል ካልን …
እንደማንም መሞትማ ለማንስ ምኑ ያቅታል
እንደምንም መኖርማ ለማንስ ምኑ ይሳናል፡፡
ሰው ሆነን ሰው ሆነን መሞት፣ የባጀን ለታ ነው ጭንቁ
እንደጋሽ ዐቢይ ሰው ፈጥሮ፣ ማለፍ ነው የልባም ሳቁ!!
ሞተ ካፋችን አይውጣ
ሞትማ ዕውቀት አይገልም
ምሥጥ ጥበብ አያኝክም
የዘለዓለም ነው ሥሪቱ
አትሮንስ አይቆረጠምም!
“From ashes to ashes”
Such a mind never allows!
ከትቢያ ወደ ትቢያማ፣ ብሎ ሐረግ ለሱ የለም
    እንደ ዐቢይ ላለው አይሰራም!
ሰፊ ነው የሊቅ አድማሱ
አየር ኃይል ህዋ ፈረሱ
ኪነ - ፊልም ጥበብ ግላሱ
የሐዋርድ አዋጅ መለከት፣ የጥቁር ድምፅ ምስል ቅርሱ
ነበር አይባልም እሱ፣ ነውም ያንሳል ቃለ - ግሡ
አይለካም ወርደ - አትሮንሱ!
ዩኒቨርስ በሰው ቢመሰል፣ ዐቢይ ነበር የምድር ዋሱ
ነቢብ - ገቢር ውቂያኖሱ!
ፒያኖ ማዕጠንት መቅደሱ
ኮንጋና ጀምቤ ከበሮ፣ የካሪቢያን ዳሱ
የፎርት ዋሺንግተን ጀማ፣ የሙዚቃ ደቦ ምሱ
የሰው ፍቅሩ፣ የሰው ሱሱ
ምን ቃል ይበቃዋል ለሱ?!
እልፍ ነውና መለኪያው
ስውር ነውና ሚዛኑ
ሳይለይ አበባ እሳቱ
አይሞላምና ቋቱ
ለዚህ ነው ታላቅ ሰው ሲሞት
ፀሐይ ዕንባዋ እሚያጥራት
ከምድር ምህዋሯን እምትስት
ፍጥረታት ጉዞ እሚገቱት
ላም መታለብ የምታቆም
ወፍም መዘመር እምትሰንፍ
ሲሰሙ ነው የሊቅ ማለፍ
ሲዘጋ ነው የዕውቀት ደጃፍ!!
ጋሽ አብዬ … የዘር ግንዱ የአገር ፍቅር
    የእናት ኢትዮጵያ አፈር መከር
የእሱም ጥሪ ሆኖ ይሄው
በእናቱ መሬት አየነው!
ያም ሆኖ ነበር አይባል፣ ኗሪም - ቢባል ነገ አይበቃው
የፓን - አፍሪካው ነጋሪት፣ ገና የመጪ ድምፅ ነው!!
ዋ! ጋሽ አቢይ! …
(ለፕሮፌሰር አቢይ ፎርድ፤
ግንቦት 8፣2010) 

Read 3886 times