Sunday, 27 May 2018 00:00

አንጋፋው ፕሮፌሰር አብርሃም (አብይ) ፎርድ ሲታሰቡ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ፕሮፌሰር አብርሃም (አብይ) ፎርድ የሚለው ስም፣ በሕይወት በነበሩበት ጊዜም ሆነ ከሞቱ በኋላ ሲነሳ፣ አንዳች የአድናቆትና የአክብሮት ስሜት በብዙዎች ልብና አእምሮ ውስጥ ይፈነጥቃል። ዳሩ ግን ኢትዮጵያዊው ተወላጅ አብይ ፎርድ፣ በምርምር ሥራዎች ግርጌ  የሚጠቀሱ ብቻ ሳይሆኑ በአገራቸውም ሆነ በዳያስፖራነታቸው በእውነተኛ መንፈስ የሚሠሩ ነበሩ። ፕሮፌሰር አብይ  የተውልን ምርጥ ሥራዎቻቸውንና በአርአያነት የተሞላ አገልግሎታቸውን ብቻ አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ምርጫውን ተከትሎ፣ በነጻነት እንዲያስብና ያሰበውንም በንግግር እንዲገልጽ አጥብቀው በማስረዳት ረገድ መልካም ውርስ ትተውልን ያለፉ በመሆናቸው ሲዘከሩ ይኖራሉ፡፡   
በትውልዳቸው ኢትዮጵያዊ የሆኑት ፕሮፌሰር አብርሃም (አብይ) ፎርድ የተወለዱት የካቲት 27 ቀን 1927 ዓ.ም  በአዲስ አበባ ውስጥ ሲሆን ወላጆቻቸው የተከበሩ የአፍሪካ ባርባዶስና የአፍሪካ አሜሪካ ተወላጆች ነበሩ፡፡ አባትና እናታቸው፣ ማርከስ ጋርቬይ (1887-1940) የፓን-አፍሪካኒዝም ንቅናቄን በመፍጠር፣ በልዩ ልዩ ምክንያቶች አያት ቅድመ አያቶቻቸው፣ ወደ ሰሜንና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም  ካሪቢያን ደሴቶች የሄዱ ሁሉ ወደ ጥንታዊት አህጉራቸው አፍሪካ ተመልሰው፣ የልማቷ አካል እንዲሆኑ ያቀረቡትን ጥሪ በመቀበል፣ ወደ ጥንታዊት ሀገራቸው ኢትዮጵያ የመጡ ናቸው፡፡ በመሠረቱ፣ ማርከስ ጋርቬይ በመላው ዓለም የሚገኙ አፍሪካውያን ወደ አህጉራቸው እንዲሄዱ ከፍ ያለ ቅስቀሳ ከማድረጋቸውም በላይ ‹‹ጥቁር ኮከብ የሰውና የዕቃ ማጓጓዣ የንግድ መርከብ›› የተሰኘ ኩባንያ አቋቁመው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ያኔም ኢትዮጵያ ከወራሪ ጠላት እራሷን ጠብቃ የኖረች፣ የሌሎችን መብት የምትጠብቅና የምታከብር፣ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በማንነታቸው ኮርተው የሚኖሩባት ሀገር መሆኗ በብዙዎች ዘንድ ይታወቅ ስለነበር፣ አፍሮ አሜሪካውያን ወደ አፍሪካ አህጉር ለመምጣት ሲንቀሳቀሱ፣ ተቀዳሚ ምርጫቸው ያደርጓት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከ14 ክፍለ ዘመናት በፊት በተለይም እስልምና በምድረ አረቢያ መስፋፋት በጀመረበት ጊዜ የእምነቱ ተከታዮች ጭቆና ሲደርስባቸው የተሰደዱት፣ያኔ አቢሲኒያ ዛሬ ደግሞ ኢትዮጵያ ወደተባለችው አገር እንደነበር ይታወሳል፡፡ በእርግጥም አገራቸውን መልቀቅ ሲገደዱ በሞትና በሕይወት መካከል ሆነው የተሰደዱት፣ ፍትህ ወደማይጎድልበት የኢትዮጵያ ንጉሥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ፣ አሁን ልናስታውሰው ከምንችለው ጊዜ በፊት ጀምሮ የህሊና ነጻነትና ሰብአዊ ክብር የሚከበርባት፣ በማንነታቸው ኮርተው የሚኖሩ ህዝቦች የሚገኙባት አገር እንደሆነች የተመሰከረላት ናት፡፡  
የፕሮፌሰር አብይ ህይወት፣ ነጻነት ያለው ህዝብ፣የተለያየ ዘርና ባህል ቢኖረውም እንዴት አብሮ መኖር እንደሚችል ያስታውሰናል፡፡ ለመሆኑ አብይ ፎርድ ማን ናቸው?
ማንነታቸውን በአጭሩ ለማስቀመጥ ይቻል እንደሆነ በአባታቸው የታላቁ ሙዚቀኛ፣ የሃይማኖት ፍልስፍና ሊቅ፣ ራባይ (ይሁዳዊ ጳጳስ)፣ የአስተማሪውና የስነ ልሳኑ ሊቅ የአርኖልድ ጆሲያህ ፎርድ እና በእናታቸው የታላቋ መምህር፣ የሙዚቀኛዋ፣ የመጋቢ ዕውቀቷ፣ የቴኒስ ጨዋታ አሰልጣኟ፣ በኢትዮጵያ ቀዳሚ የስካውት መሪዋ ሚኒዮን ሎራይን ኢኒስ ልጅ ናቸው፡፡ አብይ ፎርድና ወንድማቸው ዮሴፍ ፎርድ፣ በኢትዮጵያ በተቋቋመው ቦይስካውት ከግምባር ቀደምቱ ወጣቶች የሚሰለፉ ሲሆን በኋላም ‹‹ፈጣሪንና አገሬን፣ ሕጓን አክብሬ፣ በታማኝነት (ያለ ወገንተኝነት) ለማገልገል ቃል እገባለሁ›› ብለው በመሃላ ያረጋገጡ የስካውት መሪዎች ናቸው፡፡ ዛሬ እኔም እኒህን ታላቅ ሰው በመንፈስ የምሰናበተው፤ ለእናት አገሬ፣ ሕጓን አክብሬ፣ በመሃላ ባረጋገጥኩላትና ለብሸው በነበረው የስካውት አርማ ላይ ሦስት ጣቶቻቸውን በማውጣትና እስከ ትከሻዬ ከፍ በማድረግ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ሁሉ የፕሮፌሰር  አብይ እናት ወይዘሮ ሚኒዮን ሎራይን ኢኒስ፣ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረራ ይዞ በነበረበት ጊዜ፣ ያኔ ልዕልት ዘነበ ወርቅ ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት፣ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ከትምህርት እንዳይርቁ ያልተቆጠበ ጥረት ያደርጉ  ነበር፡፡ የቋንቋና የሙዚቃ አስተማሪ የነበሩት አባታቸው የሞቱት በ1935 ዓ.ም ሲሆን የተቀበሩትም አዲስ አበባ ውስጥ ነበር፡፡ እኒህ የጥንታዊ ዝርያዎቼ አገር ኢትዮጵያ ናት ብለው የመጡ ታላቅ ሰው (የፕሮፌሰር አብይ አባት) ዕድሜያቸው በአጭሩ ቢቀጭም፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ መዝሙር የደረሱ፣ እርሳቸው የደረሱት ብሔራዊ መዝሙርም ያኔ ‹‹Universal Negro Improvement Association [UNIA] in 1920›› ለተባለው ንቅናቄ፣ መዝሙር እንዲሆን ያበቁ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡  
ፕሮፌሰር አብይ፣ የአባትና የእናታቸውን ፈለግ በመከተል የመጀመሪያውን ዲግሪያቸውን ያገኙት ኒውዮርክ በሚገኘው በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን በአሜሪካ ውስጥም የአየር ኃይል አባል በመሆን በጦር አይሮፕላን አብራሪነት አገልግለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ባለ አንድ ኢንጅን የሆነች አይሮፕላን በመግዛት፣በሙያው መሠማራት ለሚፈልጉ አሰልጣኝ ሆነው ነበር፡፡ ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው ሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ፣ አንጋፋ ፕሮፌሰር ሆነው እየሠሩም፣ የተወለዱባት አገር ኢትዮጵያ፣ የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ እዳር ታደርሰው ዘንድ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከፍተኛ ዕውቀትና ልምዳቸውን ከ2007 ወዲህ በማካፈል፣ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ጥረት ያደረጉ ሰው ናቸው፡፡
ከራስ ወዳድነት ስሜት የራቁት ፕሮፌሰር አቢይ፤ ሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ የፊልም ጥበብ፣ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት እንዲሁም የስነጥበብ ዕውቀት ጮራ የሚፈነጥቅበት ትምህርት ቤት እንዲሆን ለአርባ ዓመታት ያልተቋረጠ ጥረት እንዳደረጉትና በርካታ አፍሪካውያንንና ትውልደ አሜሪካ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ለጋዜጠኝነት ሙያ እንዳበቁት ሁሉ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ነጻ የጋዜጠኝነት ሥራ ይስፋፋ ዘንድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡  
ፕሮፌሰር አብይ፣ በፈጠራ ጥበብ ላይ የተመሠረተ ሥርዓተ ትምህርት ያላቸው፣ ለሀገር እድገት ከፍተኛ ተስፋ የሚጣልባቸው የስነጥበብ ከፍተኛ ትምህርት ቤቶች በኢትዮጵያ እውን እንዲሆኑ የነበራቸውን የራዕይ ጥልቀት መለካት አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በተራ አገላለጽ ‹‹ከጥልቅ ስሜት፣ ከጥልቅ ማስተዋል፣ ከጥልቅ አመለካከት፣ መንፈስን ጨምድዶ ከሚያዝ ጥልቅ አስተሳሰብ የመነጨ ነው›› ለማለት ይቻል ይሆናል።  በ2006 ዓ.ም  በጡረታ ከመገለላቸው በፊትም በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ከሚገኙ ጥቂት የትምህርት ፋኩልቲዎች ጋር በመተባበር፣ በኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የስነጥበብ ዕውቀት እንዲሰጥ የሚያስችል ሥርዓተ ትምህርት ለመዘርጋት የተሳካ ሙከራ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡   
ፕሮፌሰር  አብይ ወጣት የፊልም ባለሙያ ኢትዮጵያውያን ስኮላርሺፕ አግኝተው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ፣ በሌሎች ለአፍሪካውያን ተብለው በተከፈቱ አካዳሚያዊ ዕድሎች እንዲጠቀሙም ያበረታቱ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከእህት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነት መስርቶ ለማየት ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው፡፡  
የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አንድርያስ እንደገለጹት፤ ‹‹አቢ ለፊልም ሙያ ትምህርት ቤት መቋቋም ከበስተጀርባ ሆኖ የሚገፋ ኃይል ነበር፡፡›› በእርግጥም ወዳጆቻቸውና የሙያ ባልደረቦቻቸው ስለ ወደፊቷ ኢትዮጵያ ፊልም እንዲያስቡ ይገፋፉና ዘወትር ሐሙስ በጁፒተር ሆቴል ፒያኖ እየተጫወቱ ያዝናኑ ነበር፡፡  እኔም ወደ አዲስ አበባ ስመጣና በግል ቤታቸው ብቻ ሳይሆን በዋሺንግተን ዲሲና በአዲስ አበባ በሚዘጋጁ የሙዚቃ ኮንሠርቶች ተጋባዥ ሆኜ የመመልከት ዕድል አጋጥሞኛል፡፡
ፕሮፌሰር  አብይ  ፎርድ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ  ታላቁ ሕልማቸው፣ ከእናታቸው ትምህርት ቤት አጠገብ፣ የአፍሪካ አሜሪካውያን ሙዚየም ተቋቁሞ ማየት ነበር፡፡ ከራስ ወዳድነት ስሜት የራቁና ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለሚያፈቅሯት ትውልድ ሀገራቸው የሚሠሩ መሆናቸውን የተገነዘቡ ወዳጆቻቸውም፣ ለኢትዮጵያውያን ቤተሰቦቻቸው፣ ለኢትዮጵያን አርበኞች አስፈላጊ ለነበሩት ለኩሩ አፍሮ ካሪቢያውያንና ለአፍሪካ አሜሪካውያን መታሰቢያ የሚሆን ሙዚየም እየገነቡላቸው ነው፡፡  
የሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት አመራር ቦርድም፤ እኒህ ታላቅ ታውልደ ኢትዮጵያዊ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ በክፍል ውስጥና ከዚያም ውጭ፣ በትርፍ ጊዜያቸው ሳይቀር ይሰጡት የነበረው በቅንነት ላይ የተመሠረተ አገልግሎት፣ ለትምህርት እድገት አስፈላጊ እንዲሁም ለተከታዮቻቸው፣ ለወዳጆቻቸውና ለአቻ የሥራ ባልደረቦቻቸው አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን በማመኑ፣ “ዝክረ አብይ ፎርድ” እንዲከበር ወስኗል፡፡ በዚህም አርአያነት የተሞላ ተግባራቸው በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡ እንደ አንድ አንጋፋ የሬዲዮ፣ የቴሌቪዥንና የፊልም ዲፓርትመንት ፋኩልቲ አባል፣ በዚህ የትምህርት መስክ ለተገኘው እድገት ባበረከቱት አስተዋጽኦ እንዲሁም በታወቁ ጆርናሎች ላይ ባወጡት የምርምር ሥራቸው የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል።
አንጋፋው ፕሮፌሰር  አብይ ፎርድ በሕይወት ዘመናቸው ያካበቱት ዕውቀት ወደ ኢትዮጵያ፣ ቡርኪና ፋሶና ወደ ሌሎችም አፍሪካ ሀገሮች ለሁለት ተከታታይ ዓመታት መጥተው እንዲሠሩ ያስቻላቸው ሲሆን በ2006 ዓ.ም  በጡረታ ከተገለሉ በኋላ እንኳን ሲመኙት የነበረውን ራዕይ ብቃት ያለው ምሁር ሆነው ለማሳካት የቻሉ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡
የሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ ባለአደራ ቦርድም፣ የብዙዎቻችንን ስሜት የሚጋራ ሲሆን  ለልጃቸው ለሚኒባ ፎርድና ለቤተሰቧም በአባቷ ሞት የተሰማውን ልባዊ ሐዘን ገልጧል፡፡   
ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ፤ ‹‹አብይ አፍሮ-ካሪቢያን፣ አፍሪካ አሜሪካውያንና ኢትዮጵያውያውያንን ያስተሳሰረ ሕያው ምስክር ነው›› በማለት ይገልጧቸዋል፡፡ እንደ ፕሮፌሰር አንድሪያስና ሌሎች ፕሮፌሰር አብይን ለሚያውቁ እንዲሁም ለተማሪዎቻቸው፣ ባልደረቦቻቸው፣ ጓደኞቻቸውና ሙዚቃቸውን ላዳመጡ ሁሉ፣ የእርሳቸው ማሸለብ ለሀገራቸውና ለፓን አፍሪካኒዝም ትልቅ ጉድለት ሆኖ እንደሚሰማቸው አያጠያይቅም፡፡   
ወዳጆቻቸውና ሌሎችም ምሁራን እርሳቸው ወደሚያገለግሉበት ዩኒቨርሲቲ ሲመጡ መልካም አቀባበል እንደሚደረግላቸው ይሰማቸው ነበር። አስተማሪያቸውና አማካሪያቸው ይሆኑ ዘንድም ይመርጧቸው ነበር፡፡ ከጥንታዊ የጥቁሮች ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ በሆነው ሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ታሪክ ሲያስተምሩ ለሚያውቋቸው፣ ሰዎችን የመረዳት፣ በጥንቃቄ የመቀበልና ጥልቀት ያለው ምሁራዊ አስተያየታቸውን፣ ፈገግታቸውንና የሚሰነዝሯቸውን ቃላት መርሳት ከቶ አስቸጋሪ ነው፡፡ እኔም ዓለም አቀፍ ጤናና ልማትን የሚመለከት ትምህርት በዩኒቨርሲቲው ሳስተምር፣ እንደ አንድ የዩኒቨርሰቲው አባል፣ ከእርሳቸው ብዙ የተጋራኋቸው ቁምነገሮች እንዳሉ እርግጥ ነው፡፡፡   
ፕሮፈሰር  አብይ ፎርድ፤ ስካውት ኮትኩቶ ያሳደጋቸው መሆኑን በሚያረጋግጥ መልኩ በመላ ህይወታቸው አዲስ መጭዎች፣ የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም  የሁለተኛና  ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች፤ ስለ ኢትዮጵያና ፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ እንዲማሩ፣ እንዲያውቁና በመላ ሕይወታቸውም ለዚህ የተቀደሰ ተግባር ጥብቅና እንዲቆሙ በትጋት የሰሩ ሲሆን ዳያስፖራዎችም አርአያ ሆነው እንዲገኙ አበክረው ይመክሩ ነበር፡፡ ግልጽነት እንደ ባህል፣ በምንሰጠው ህዝባዊ አገልግሎትና በምናካሂደው ውይይት ልዩነትን በማስወገድ፣ በሰላም አብሮ መኖርን የሚያስገኝ ጤናማ ዴሞክራሲያዊ ባህል በመሆኑ ከፍተኛ ግምት ይሰጡት ነበር፡፡  ምንም እንኳን ፓን አፍሪካኒዝምን በሚመለከት ያለው ክርክር በእርሳቸውና በወላጆቻቸው፣ በዳያስፖራ ወዳጆቻቸውና በጓደኞቻቸው ዘመን ሥር የሰደደ ቢሆንም፣ የሐሳብና ስሜትን የመግለጽ ነጻነት ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ለኢትዮጵያ የነበራቸው ፍቅር ጣልቃ እየገባ፣ እስከ ህይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ሲያስቸግራቸው ተስተውሏል፡፡  
ፕሮፌሰር  አብይ ፎርድ በብዙዎቹ ጓደኞቻቸው ዘንድ ሐሳባቸውን ከስሜታዊነት በራቀ መንገድ የሚያቀርቡ፣ ነገሮችን መዝነውና አስተንትነው በጥልቀት የሚያስቡ፣ ለማያምኑበት ነገር ቅን አስተያየታቸውን የሚሰጡ፣ የሚያደርጉትን ነገር ሁሉ መዝነው የሚሠሩ እንደነበሩ ይታወቃሉ፡፡ ሰባኪና አፈ ጉባኤ በመሆን ብዙ ሺህ ማይሎችን ተጉዘዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ የበለጠ ግን አፍቃሪ፣ ለሰው ልጅ እንክብካቤ የሚያደርጉ፣ ለቤተሰባቸው የተለየ መውደድ ያደላቸው፣ እንደ ጓደኛም የሚሰማቸውን ለማካፈል ዝግጁ የሆኑ ቅን ሰው ነበሩ፡፡ የሚያውቋቸው ሁሉ የሰለጠነ ባህላቸውን፣ የከተሜ ሰብእናቸውን በአድናቆት ከመግለጥ ተቆጥበው አያውቁም፡፡ ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩ ጊዜም ብዙዎች እንባቸውን ያፈሰሱት የሚፈጠረውን ትልቅ ክፍተት በመፍራት ነበር፡፡ እኔም ቤተሰባቸው፣ ጓደኞቻቸው፣ አድናቂዎቻቸው፣ ተማሪዎቻቸው፣ የዩኒቨርሲቲው ታላላቅ ምሁራንና የቦርድ አባላት በተገኙበት ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው በሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው “ዝክረ ፕሮፌሰር አቢይ ፎርድ” ላይ ተገኝቼ፣ ይህን እውነታ ለመመስከር ችያለሁ፡፡
የፕሮፌሰር አቢይ ፎርድ ሌጋሲ፣ የዘራቸው ሐረግ፣ ከቤተሰባቸው የወረሱት የአርበኝነት ስሜት በተቀበሩባት ኢትዮጵያ ምድር ሲታወስ ይኖራል። የተሰማንን ልባዊ ሐዘን ለልጃቸው ለሚኒያቢና ለልጅ ልጃቸው ፋሲል እየገለጽን፤ የፕሮፌሰሩን ችቦ ተቀብለው እንዲያበሩ፣ በትምህርቱ መስክ የጀመሩትን መልካም ሥራም ተክተው እንዲያከናውኑ ከልብ እንመኛለን፡፡
(ተጻፈ በፕሮፌሰር አሕመድ ዓብዱላሂ ሞኢን (DrPH, MPH, MHA) ሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ፣ ዋሺንግቶን ዲሲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ)

Read 1467 times