Sunday, 27 May 2018 00:00

ህሊናን ማክበር ራስን ማክበር ነው!

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

 …. ሳድግ “እንትን” ወይንም “እንትናን” መሆን እንፈልጋለን ሲሉ እሰማለሁኝ፡፡ የሚገርመው ብዙውን ጊዜ እንደዚህ ሲሉ የምሰማቸው ሰዎች ቢያንስ በተፈጥሮ ከተሰጣቸው እድሜ አንፃር አድገው የጨረሱ ናቸው። መሆን የሚፈልጉትን ሰው ጫማ እየተለካኩ ነው፡፡ መሆን የሚፈልጉትን ሰው አንዳንዴ እግሩን ቆርጠው፣ ከራሳቸው እኩል ያደርጉታል፡፡ ወይም ከራሳቸውም አሳጥረው ቆርጠው ሳያድጉ ይበልጡታል፡፡
እኔ ግን ሳድግ ራሴን የማከብር ሰው መሆን ነው የምፈልገው፡፡ ከራሴ ጋር በራሴ ጓዳ ራሴን ማክበር ከቻልኩ፣ በሌላው መከበሬ አያሳስበኝም፡፡ ከራሴ ጋር በቅጡ ለመከባበር የውጭ አስተያየት አያስፈልገኝም፡፡ “አደግሁ” የምለው የውጭ አስተያቶች እንደማያስፈልግ ከማመን ባሻገር ያመንኩትን መኖር ስጀምር ነው፡፡  
“self respect” እና “egoism” በጣም የተራራቁ ነገሮች ናቸው፡፡ ኢጎይዝም በማህበረሰብ ውስጥ የሚፈጠር ነው፡፡ “self respect” ግን ግለሰቡ ውስጥ የሚመሰረት ውል ነው፡፡ ውሉ ከህሊና የተፈጥሮ ህግ (molarity) አንፃር ተመሳክሮ የሚፀድቅ ነው። ማህበረሰብ ጣልቃ አይገባበትም፡፡ … አንድ ግለሰብ ራሱን ለማክበር ማህበረሰብ የሚሰጠውን ማዕረግ ለማግኘት የሚጣጣር ከሆነ፣ ከህሊናው ጋር ፉክክር ውስጥ ገብቷል፡፡ ማህበረሰብ የግለሰቦች ህሊና ነፀብራቅ ነው፡፡ የማህበረሰብ ህሊና በተመክሮ (ባህል) የሚሰራ ወይም የሚዳብር ነው፡፡ ማዕረግ፣ ቆብና የዝና መሰላል በመሰጣጣት ወይም እድሜ ጠገብ በመሆን የሚገኝ ነው፡፡
የግለሰብ ህሊና በተመክሮ የሚገኝ አይደለም፡፡ ህሊና በልጦ በመገኘት የሚሰጥ ኒሻን አይደለም፡፡ ሰው ከህሊና ጋር ሲስማማ ከራሱ ጋር ተከባብሯል፡፡ ብዙውን ጊዜ ከራሱ ጋር መከባበሩን ራሱ ሰውየውም ላያውቀው ይችላል፡፡ የማይናወጥ ሰላም ውስጥ እንደሆነ ሊያውቅ አይችልም፡፡ ብዙውን ጊዜ ሰላሙ ሲናወጥ ነው፣ ቀደም ሲል የነበረበት ከፍታን የሚያነፃፅረው፡፡
“Moral is what you feel good after” ይላል ሄሚንግዌይ፡፡ “Self respect” የሥነ ልቦና ቤተ ሙከራ አይደለም፡፡ አንድ ተግባር ከተከናወነ በኋላ አይደለም ልክና የተሳሳተ መሆኑ የሚረጋገጠው፡፡ ህሊና ቁማር የለውም፡፡ ትክክል የሆነውን ከመደረጉ በፊትም ሆነ በኋላ ያውቀዋል፡፡ መደረግ የነበረበት ነገር ችላ ሲባልም ሆነ መደረግ ያልነበረበት ሲከናወን አስቀድሞ በህሊና ሚዛን ውጤቱ ይታወቃል፡፡ ሚዛኑ አይዋዥቅም። የሚዛኑን ደረጃ መድቦ እንዳይጭበረበር በተፈጥሮ የሚሰጠው ፈጣሪ ነው፡፡ የፈጣሪን ሚዛን ለመደለል በሚደረግ ሙከራ ሁሉ ግለሰቡ ለራሱ ያለውን ክብር በተለያየ ደረጃ ያጣል፡፡
ሙሉ ለሙሉ የህሊናውን ኮምፓስ ሸፍኖ፣ በውጪያዊ የማህበረሰብ መለኪያ የሚገለገል ይኖራል። ግን በማህበረሰቡ ቢከበርም ከራሱ ጋር እንደተጋጨ ይቀጥላል፡፡ ትላንት የወሰነው ውሳኔ … ወይም ነገ የሚወስነው አቅጣጫ በእሱ እጅ አይሆንም፤ ልክ መሆኑንና አለመሆኑን ከሁኔታው በኋላ ነው የሚያረጋግጠው፡፡ “Moral is what you feel good after” ይላል ያኔ፤እንደ ሄሚንግዌይ፡፡ ከራስ ጋር እንደ መፎካከር ነው፡፡ … “ትላንት በተደሰትክበት ነገር ዛሬም በድጋሚ ለመደሰት ትላንት ያደረግከውን ጨምረህ ማድረግ አለብህ” ይልሃል …. የህሊና ቀመሩ የጠፋበት ማንነት፣ ከራስህ ጋር ሲያፎካክርህ፡፡
ከማህበረሰብ ቀመር ጋር ስትፎካከር፣ የፉክክሩ ደረጃ ማለቂያ እንደሌለው፣ ከራስ ጋር መፎካከርም ተመሳሳይ ነው፡፡ ከራስ ጋር መፎካከሩ ብዙውን ጊዜ ደስታን ለማግኘት ዘወትር የማይዘጋ የጨረታ ቤት ቅርፅ ለግለሰቡ ይሰጠዋል፡፡ ያሸክመዋል፡፡ የደስታ ሱሰኝነት ይፈጥራል፡፡ ከማህበረሰብ ልኬት ጋር መፎካከሩም ተመሳሳይ ነው፡፡ ስልጣን በስልጣን ላይ፣ ሀብትን በሀብት ላይ፣ ዝናን በዝና ላይ ቢያሸክምም እርካታ የለውም፡፡ “ኢጎኢዝም” እርካታ የለውም። ፉክክሩ ከራስ ጋርም ሆነ ከሌሎች ጋር … እርካታ አንፃራዊ ስለሆነ ቋሚ ልክ የለውም፡፡ … ሂደቱ ውጤቱ ይሆናል፡፡ “The means becomes the end” … የእርካታ ፍለጋውም እርካታ የሆነ ይመስላል፡፡ መነሻና መድረሻውን ያጭበረብራል፡፡ ያደናግራል፡፡  
ከራስ ጋር በመፎካከር ወይም ራስን በመፈለግ ራስ ጋ መድረስ አይቻልም፡፡ ህሊና በራስ ውስጥ ያለ ቅድመ ሁኔታ መጀመሪያም፣ ያለ ምክኒያት እንዳለ ያላወቀ ግለሰብ፣ በማህበረሰቡ ዘንድ … በማህበረሰቡ ደንብ ተረጋግጦ ይገኛል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ እኔም ሆነ እናንተ ሞኝነት ውስጥ ነን፡፡ ራስን ለማክበር በብዙ ፍለጋና ተሞክሮ ውስጥ እናልፋለን .. ከራሳችን ህሊና ጋር ብቻ ሳንከባበር እንተላለፋለን፡፡
… ስለዚህ እኔ ወደ ተፈጥሮ ግሳንግስና ኮተት አልባ ህሊናዬ መመለስ ነው ሳድግ የምፈልገው፡፡ ሳድግ መሆን የምፈልገው፣ በተወለድኩባት ቅፅበት፣ ከእናቴ ማህፀን ስወጣ እንደነበርኩት ነው፡፡ መደረግ ያለበትና የሌለበትን ከማህፀን ከወጣሁ በኋላ ማህበረሰቡ ቀጥቶ ሳያስተምረኝ በፊት ወደ ነበርኩበት የውሃ ልክ መመለስ ነው፣ለእኔ እድገት፡፡ ራሴን ማክበር ነው የምፈልገው፡፡ በሌሎች ለመከበር የኖርኩት ህይወት፣ ከራሴ ህሊና ጋር ሆድና ጀርባ አድርጎኛል፡፡
ራስን ለማክበር ሲሉ ብዙዎች የብትውትና ህይወትን መርጠዋል፡፡ ራስን ማክበር ማለት ህሊናን ማክበር ነው፡፡ ዋናው ነጥብ ግን የህሊና ምንጭ የሆነውን ፈጣሪ፣ መንገድ አክብሮ መከተል ነው፡፡ … ለራስ በሚል ባንዲራ ከሌሎች ጋር የሚያፎካክረውን ተለጣፊ የማህበረሰብ ህግ መተው ነው፡፡ ወደ መስመር መግባት ነው፡፡ ወደ ፈጣሪ መስመር፡፡
“egoism” ለራስ የሚደረግ ፉክክር ይመስላል እንጂ ፉክክሩ ለሌሎች ነው፡፡ ከሌሎች ጋር ነው። በሌሎች ተቀባይነትን ለማግኘት፣ ከሌሎች በላይ ለመጉላት፣ በሌሎች ላይ የራስን አሻራ ለማተም፡፡ ይኼ ሁሉ ለራስ፣ ስለ ራስ አይደለም፡፡ ስለ ራስ የሆነ ሁሉ፣ ስለ ህሊና ነው፡፡ ስለ ህሊና የሆነ ሁሉ፣ ስለ እውነት ነው፡፡ ስለ እውነት የሆነ ሁሉ፣ በእውነት ስለ ፈጣሪ ነው፡፡
“egoism” ካለ ፉክክር አለ፡፡ ፉክክር ካለ ንዴት ሀዘን፣ ተስፋ ማድረግና መቁረጥ፣ በፍላጎት መናጥና መሰልቸት፣ አልጠግብ ባይነትና ስሜታዊነት፣ ጭቅጭቅና እወደድ ባይነት፣ ደስታን ፍለጋ--- በአራቱም አቅጣጫ (በምላስ፣ በወሲብ፣ በአእምሮና በጡንቻ) አለ፡፡
የራስ መሀከለኛ ነጥብ ግን በእነዚህ ርቀቶች ውስጥ አይገኝም፡፡ መድረሻው አስቀድሞውንም መነሻው ላይ  ነበር፡፡ መሬትን ስተኸው መሬትን ፍለጋ ወደ ጎዳና ከወጣህ፣ የራስ ወዳድነት ሀይልን ተከትለህ የምትገጥማቸው ፌርማታዎች፣ ከላይ የገለፅኳቸው ናቸው፡፡ ፍለጋውን ውጤቱ አድርገህ እንደባከንክ መቀጠል ትችላለህ ወይም ወደ መነሻ መሬትህ መመለስ ትችላለህ፡፡
መመለሻ መንገዱ አንድ ብቻ ነው፡፡ እሱም ከህሊናህ ጋር መልሰህ አንድ እና ያው መሆን ነው። የደስታ ቁማርና ጨረታ ቤቶችህን ለማህበረሰባዊ የፉክክር ሜዳው ጥለህ ወደ ቤትህ መግባት፡፡ ከራስህ ጋር በቅጡ መተዋወቅ፡፡ ህሊናህን ማወቅ፡፡ ከማወቅ በኋላ ማክበር፡፡ ህሊናን ማክበር ራስን ማክበር ነው፡፡
ራሱን ያከበረ ሰው የፍቅርን ትክክለኛ ትርጉም ያወቀ ነው፡፡ ንፋስ በነፈሰበት አቅጣጫ ሀሳቡም ሆነ ስሜቱ አይነፍስም፡፡ በግጥም ሆነ በዜማ ስሜቱን ማባበል አይፈልግም፡፡ ግጥምና ዜማ እሱ ራሱ ነውና፡፡ አእምሮው የ “አያዎ”፣ ተቃርኖ፣ አመክኒዮ፣ አስተፃምሮ፣ አንብሮ ወይም እንጉርጉሮ ቋት አይሆንም። በራሱ ውስጥ እሱ በተገቢው ስፍራ ሳይጋነንም ሆነ ሳይኮስስ ሰፍሯል፡፡ በማውራትም ሆነ በመናገር የሚሞላው ነገር አይኖርም፡፡ ውሃ ልኳ ነፍሱ “ከዐት” መሀሉ ላይ ሳትንጫገጭ፣ ሉቤሎ ጠብቆ፣ በቀስታ መጓዝ ነው ጨዋታው፡፡ … ማንም ተንኮለኛ መጥቶ ልኩን አንገጫግጮ፣ የህሊናህን ውሃ ልክ ሳታስበው አያስደፋህም፡፡ ያከበርከውን ራስህን፣ ከራስህ ፈቃድና ትብብር ውጭ ማንም ጣልቃ ገብቶ አያስንቅህም፡፡ ራስህን ነው መጠበቅ፣ ራስህን ነው አክብረህ መቀጠል።
አዎ ዓለሙ ሰፊ ነው.. ፈጣሪ የሰጠህም ጊዜ በቂ ነው፡፡ ጨብጠህ የተወለድከውን ተፈጥሮ ጥለህ፣ ዓለማዊ ማህበረሰባዊ ቁማር ለምደህ ተጉዘህ፣ በመንፈስ ከፍታ ዝዋዥዌ ተጫውተህ ስትጠግብ፣ “የአባቴ ቤት ካየሁት ሁሉ ይሻለኛል” ብለህ ለመመለስ፣ ፈጣሪ የሰጠህ የህይወት ቴአትር ፕሎት በቂ ነው፡፡ … ለሁሉም በቂ ጊዜ አለ፡፡ ጊዜህን ግን በአግባቡ መጠቀም አለብህ፡፡ … ወጥተህ ዞረህ ከመምሸቱ በፊት መመለስ አለብህ፡፡
… በጣም ከመሸ በኋላም ራሱን ሸንግሎ … የፉክክር ውሃ ቅዳ፣ ውሃ መልስ ጨዋታውን የቀጠለ … የመንቃት አጋጣሚ ባለማግኘት ሳይሆን ባለመፈለጉ ነፍሱን ጅብ እንዳስበላት ጨዋታው ከመጠናቀቁ በፊትም ይገነዘባል። ከመሸም በኋላ ጅቦቹ ሲከቡት የተጸጸተ፣ በቂ ጊዜ አለው፤ ከራሱ ጋር በድጋሚ ለመታረቅ፡፡ ከራሱ ጋር እንደ አዲስ ለመተዋወቅ፡፡ የደለዘውን የህሊናውን ፋና መልሶ ለመለኮስ፡፡ ራሱን መልሶ ለማክበር፡፡
እኔም ጊዜ አለኝ፡፡ አድጌአለሁ በአካል፡፡ በመንፈስ ለማደግ የሚያስችሉኝን ውጤት መስለው፣ አዙሪት ውስጥ የሚያመላልሱኝን ሂደቶች መቁረጥ ብችል አድጋለሁኝ፡፡ ሳድግ መሆን የምፈልገው፣ ራሴን በሚገባው መንገድ ማክበር ነው፡፡ ከራስ ክብር በድጋሚ ላለመውደቅም እስከ ፍፃሜው መጠንቀቅ፡፡ ይህ ነው ምኞቴ!!

Read 1349 times