Sunday, 27 May 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

 በጥንታዊት ቻይና የኖረ አንድ ጥበበኛ ተገዶ ከንጉሡ ፊት ቀረበ፡፡
“ጥበበኛ መሆንህን ሰምቻለሁ” አለው ንጉሡ፡፡
ዝም፡፡
“ብረት አቅልጠህ ወርቅ ታነጥራለህ አሉ?”
“አንዳንዴ ይቻላል፡፡”
“ሌላስ?”
ዝም፡፡
“የሞት መድሃኒት አታውቅም?”
ዝም፡፡
“መልስልኝ እንጂ”
ጥበበኛው የሆነ ተንኮል እንደታሰበ ገባው፡፡ በፍጥነት ማሰብ ጀመረ፡፡
“የጠየኩህን መልስልኝ” አለ ንጉሡ በድጋሚ፡፡
ጥበበኛውም… “ንጉሥ ሆይ፤ እንደዚህ ዓይነት ጥበብ በአደባባይ አይነገርም፤ ይረክሳል” በማለት መለሰለት።…ንጉሡም ባለሟሉንና ባካባቢው የነበሩትን ሁሉ ከሸንጎው እንዲወጡ አዘዘ፡፡…ብቻቸውን ሲሆኑም፤
“ንጉሥ ሆይ፤ የሞት መድሃኒት አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን መድሃኒቱ አሁን ተብሎ አሁን የሚዘጋጅ ነገር አይደለም፡፡…ጊዜ ይፈልጋል፡፡” አለ ጥበበኛው፡፡
“ምን ያህል ጊዜ?”
“በመጀመርያው ወር ከዕፀዋት ስር ይቀመጣል፤ ለሶስት ወራት እንዲብላላ ይደረጋል፡፡ ከዛ በሁዋላ ሌላ ግብዓት ተጨምሮበት ይቀበራል፡፡ ሶስት ዓመት አፈር ውስጥ ይቆይና ሲወጣ የመጨረሻው ቅመም ተጨምሮ ይጠናቀቃል” አለ ጥበበኛው፡፡
ንጉሡ የሞት መድሃኒት ሊገኝ በመሆኑ ደስ አለው። የሚያስፈልገውን ሁሉ እንዲጠይቀው ነግሮት አሰናበተው፡፡…
አራት ወር ሞላ፡፡ ሁለተኛው ግብዓት ቆዳው የነጣ (ሻሽ የሆነ)፣ የግራ እግሩ የሚያነክስ ሰው ጉበት መሆኑን ጠቢቡ ለንጉሡ አስታወቀ፡፡ ንጉሡም የተባለው ተፈልጎ እንዲዘጋጅና እንዲመጣ በሚስጢር አዘዘ፡፡ በግዛቱ ሁሉ ተፈልጎ ሊገኝ አልቻለም፤ ካለ አንድ ሰው በስተቀር፡፡ ሰውየው ደግሞ የንጉሡ አማካሪና ባለሟል ነው፡፡ አማራጭ የለምና ንጉሡ ባለሟሉን በድብቅ አስገድሎ፣ ጉበቱን ለጠቢቡ አስረከበ፡፡ የተዘጋጀው መድሃኒት በተቀበረ በሁለተኛው ዓመት፣ የንጉሡ ልጅ፣ አባቷ ለጥበበኛው እንዲድራት ወተወተችው። ይወዳት ነበርና እንቢ ማለት አልፈቀደም፡፡ ዳረለት፡፡… ከዚያስ?
* * *
ወዳጄ፤ ዕውቀት ጉልበት (energy) ነው። ፀጋና ሞገስም ያስገኛል፡፡ የማመን አለማመን ጉዳይን ወደ ጎን አቆይተን… ባይናቸው ጨረር ብረት የሚያጎብጡ፤ ከብረት ወርቅ የሚያነጥሩ (alchemy)፣ በግድግዳ ውስጥ አልፈው ማየት የሚችሉ፣ ሞትን የሚመለከቱ፤ አእምሮን ማንበብ የሚችሉ፣ ከብርሃን ፍጥነት በላይ መጓዝና ራሳቸውን በቀላሉ መሰወር የሚችሉ ሰዎች አሉ፤ ነበሩ ይባላል፡፡..
ዕውቀት እግዜርና ዲያብሎስን ያጣላ፣ አዳምን ከገነት ያባረረ፣ ሶቅራጥስን ያስገደለ፣ ጋሌሊዮን ያሳሰረ፣ ቮልቴርን ያሰደደ ምትሃት ነው፡፡…ማወቅ የጎዳቸው እንዳሉ ሁሉ አሸናፊ ያደረጋቸውም ብዙ ናቸው፡፡ “አንስታይን ባልሆን ኖሮ ጀርመኖች ጀርመናዊ ነው፤ አይሁዶች አይሁዳዊ ነው፤ አሜሪካኖችም የኛ ነው አይሉም ነበር” ብሏል አሉ…አልበርት አንስታይን። ቦልሼቪኮችና ሜንሼቪኮች “የኛ ነበር፣ የናንተ አይደለም” እያሉ በጎርኪ ተነታርከዋል፡፡ ጀርመኖችም በጉንተር ግራስ!!...  እዚህ ጋ እውቀት፤ ነፃነትና አለማዳላት ሊሆን ይችላል፡፡
መማር ወደ ማወቅ፣ ማወቅ ወደ ብፅዕና (wisdom) ይመራል ይላሉ፤ ሊቃውንት፡፡ ዓለም የምትመራው በዚሁ ስርዓትና በመፃህፍት ጥበብ መሆኑን በተደጋጋሚ ነግረውናል፡፡
ዕውቀት አጉል ምኞትና ጉጉትን ወደ ጥበብ በመቀየር፣ ህይወት ትርጉም እንዲኖረው ያደርጋል። ማህበራዊ ኑሯችንንና እምነታችንን ጨምሮ የፍትህ፣ የመብትና የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ተቋማት ብስለት ባላቸው ዜጎች ከተማሩ፤ በመርህ ከታነፁ የሚገፈታተር ሳይሆን የሚተጋገዝ፣ የሚናናቅ ሳይሆን የሚተሳሰብ፣ የሚሰጋ ሳይሆን ልበ ሙሉ፣ አንገት የሚደፋ ሳይሆን በራሱ የሚተማመን፣ በስሜት የሚነዳ ሳይሆን በምክንያት የሚያምን፣ በተሰጠው ሳይሆን በመፍጠር የሚኖር ቅንና ስልጡን ዜጋን በተራቸው ያንፃሉ፡፡ እንደነዚህ አይነት ዜጎች እስካልበዙ ድረስ ጥሩ ሃገርና ጥሩ መንግሥት ይኖራል ብሎ ማሰብ፤ “ማሰብ” ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡
መሪነት ጥበብም ሳይንስም መሆኑ ግልፅ ነው። መሪዎች ማሰብ ያለባቸው “ጥሩ መሪ” ስለመሆን ብቻ መሆን አለበት፡፡ ስለ ሃብትና ንብረት የሚያስብ፣ መሪ ሊሆን አይገባውም፡፡ ነጋዴውም ስለ ንግዱ፣ አምራችም ስለ ምርቱ፣ ወታደርም ስለ ውትድርናው፣ ሃኪምም ስለ ጤና ሲያስብ ሃገር ትቀናለች፡፡ ማንም መሪ ሊሆን አይችልም። መሪዎች ህይወታቸው፤ ትንፋሻቸው ህዝባቸው ነው፡፡ “ከናንተ መሃል ትልቅ የሚያስብ፣ እሱ አገልጋያችሁ ይሁን” የሚለን ፕሌቶ ነው፡፡ ከሱም በፊት ላኦፀ ተናግሮታል፡፡
ወዳጄ፡- ባህር በማዕበል እንደሚናወጥ፣ የተቸገረና ነፃነት የሌለው ህዝብም በወሬና በፕሮፓጋንዳ ይናወጣል፡፡ ጥሩ ነፋስ፣ ሲነፍስ ባህሩ እንደሚረጋጋ፣ ህዝብም በመልካምና ተስፋ ሰጭ ቃላት እፎይ ይላል። የተሻለ ሃሳብ ሲፈልቅ የህዝብ ሃሳብ ይሆናል፣ የተሻለ ራዕይ ሲታይ የህዝብ ራዕይ ይሆናል፡፡ ምኞት ከተደናቀፈ፣ ተስፋ ከጨለመ፣ ሃሳብ  ‹ሃሳብ› ሆኖ ከቀረ፣ የተጨበጨበለት ቃል በሥራ ካልተተረጎመ ዕዳ ማኖር ይሆናል፡፡ Promise is debt  እንዲሉ!!
* * *
ወደ ተረታችን ስንመለስ፡- የንጉሡ ባለሟል፤ ንጉሡ ልጁን ለልጁ እንዲድርለት፣ ዙፋኑን እንዲወርስ ምኞት ነበረው፡፡ ልዕልቲቱ ደግሞ ጥበበኛውን እንደምታፈቅርና በድብቅ እንደሚገናኙም ያውቃል፡፡ ባለሟሉ ጥበበኛውን በረቀቀ ዘዴ ሊያጠፋው ተነሳሳ። የሞት መድሃኒት ያውቃል ብሎ በርግጠኝነት ንጉሡን አሳመነው። “አላውቅም” ካለ “ውሸቱን ነው” ብሎ ሊያስገድለው፣ “አውቃለሁ” ብሎ መድሃኒቱን ከተናገረ ወይም ከሰጠ ደግሞ ሚስጢር ሳያወጣ እንዲሞት አመቻቸ፡፡ ጥበበኛው የንጉሡ ጥያቄ ተንኮል እንዳለበት በመረዳቱ ጠላቱን ለመለየት ጊዜ ያስፈልገው ነበር፡፡ ጊዜም የሴራው ጠንሳሽ ባለሟሉ መሆኑን አሳየው፡፡…እናም ጠቢቡ የባለሟሉን ጉበት ለ ‹መድሃኒቱ› ግብዓት አደረገው፡፡ ንጉሡ የባለሟሉን ሴራ፤ የጥበበኛውን ብልህነት፤ የልጁን ፍቅርና የሞት መድሃኒት ሊኖር እንደማይችል ያወቀው ዘግይቶ ነበር፡፡
ወዳጄ፡- “Knowledge is an advantage over the average man” ተብሎ መፃፉን ልብ በልልኝ፡፡
ሠላም!!

Read 830 times