Sunday, 27 May 2018 00:00

የማትበላ ወፍ

Written by  ትዕግስት ታፈረ ሞላ
Rate this item
(10 votes)

የሰንበት ትምህርት ቤቱ ወጣቶች አንድ የሚያከብሩት ወጣት አለ፡፡ ዮሴፍ ይባላል፡፡ ልክ እንደ ትልቅ ካህን፣ እሱ የሚለው ለእነሱ ሁልጊዜ ትክክል ነው፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤቱ መርሐ ግብር እንዳለቀ ወንዶች ሴቶችን መሸኘት  ግዴታ ያለባቸው  ይመስል በየሴቶች መንደር ይታያሉ፡፡ ጨለም ካለ እና ደፈር ካሉ ሴቷ ትከሻ ላይ እጃቸውን ጣል ያደርጋሉ፡፡ ትንሽ ድፍረት ያላቸው ሴቶች ከሆኑም፣ የእነሱም እጅ ሸኚው ወገብ ላይ ያርፍና አጋርነቱን ያሳያል፡፡ የአንድ ክብሪት እሳት ብቻውን ቤት አቃጥሎ አያውቅም፡፡ ግን ለቃጠሎው ዋና መነሻ ከክብሪቱ በቀር ማን ሊሆን ይችላል? 
ብዙዎች ለዘላለም በእግዚአብሔር ፊት ለማገልገል ምኞት ነበራቸው፡፡ ግን በማወቅም ባለማወቅም ክብሪቱን ጫሩት፡፡ ቆይቶ ተስፋቸው ተቃጠለ፡፡ ሴቶቹም እንዲሁ በእግዚአብሔር ፊት በክብር ሊያገቡ ከራሳቸው ጋር ጥብቅ መሀላ ነበራቸው፡፡  መሀላው የፈረሰ ቤቱ የነደደ ቀን ይመስላቸዋል፡፡ እነሱ ክብሪት እንደጫሩና እንዳያያዙት አያውቁም፡፡
ዮሴፍ ከዚህ ነፃ ነው፡፡ ነፃነቱን ከክርስትናው ይልቅ ተፈጥሯዊው ትዕቢቱ ሰጥታዋለች፡፡ ወንዶቹ እንዳይስቱ ይመክራል፡፡ ሴቶቹ ከማይሆን ሰው ጋር እንዳይገጥሙ ይመክራል፡፡ ብዙ ሴቶች የፍቅር ደብዳቤ ይጽፉለታል፡፡ ግድም መልስም እንደሌለው ጓደኞቹ ሲያውቁ ግራ ይጋባሉ፡፡ በእነዚህ ሁሉ ሴቶች መሐል ሳይደናቀፍ የሚያልፍ እሱ ማነው? ሴቶች ዝጋታም ብለው የሚሸሿቸው አይነት ወንድ አይደለም፡፡ ተጫዋች ነው ብለው የሚደፍሩትም አይደለም፡፡ ይሄ ልዩ ባህሪው ነው፡፡ አንድ ቀን ይሄን ባህሪውን የሚያናውጽ ነገር ተከሰተ፡፡ ቀኑ ሚካኤል ነው፡፡ ከቅዳሴ ሲወጣ ከሚያውቃቸው ሴቶች ጋር አንዲት ጥቁር እንግዳ አብራ ቆማለች፡፡ ብዙ ሰዎች እንደሚሉት አይነት፣ ልቡ ክው ሲል ይታወቀዋል፡፡ ከተፃፉለት የፍቅር ደብዳቤዎች ውስጥ ቀይ እስክርቢቶ ያደማቸው፣ ብዙ የልብ ስዕሎች ትዝ አሉት፡፡ ለትርጉማቸው ከዚህ የተሻለ ቅፅበት የለም፡፡ጠይም ናት፣ ቀጭን፡፡ ውበት ማለት ጠይም….ቀጭን መሆን ነው ተብሎ ቢታወጅ እንኳን ከዚህ በፊት ብዙ ጠይም ቀጭን ሴቶች ያውቃል፡፡ አይ ሰይጣን ነው፡፡ ብሎ አሰበና “አሃ ሰይጣን ከዚህ በፊት የት ነበር?” ተዋወቁ፡፡ የልቡ ምት በእጁ ወደ እሷ እንዳያልፍ የሰጋ ይመስል ቶሎ እጁን ሰበሰበ፡፡ በቅርበት ሲያያት አገጯን ለሁለት የተከፈለ የሚያስመስል መስመር አለባት፡፡ ይሄ ልዩ ነገሯ ነው ቢባል እንኳን እሱን ቀርቦ ከማየቱ በፊት ነው፣ ልቡን አንዳች የሰነጠቀው፡፡ ልጆቹ እንግዳዋን ይዘው ወደ ቤታቸው ሲሄዱ እያያቸው፣ እሷ እሱ ውስጥ ቀርታ፣ ልቡን ስታንኳኳና በስንጥቁ ለመግባት ስትፍጨረጨር ይሰማው ነበር፡፡ያን ቀን ሌላ ዮሴፍ ሆነ፡፡ ኮስታራ፤ ዝምተኛ…….ሰንበት ተማሪው ሁሉ የበለጠ መጨመቱ ነው፣ ብሎ ችላ አለው፡፡ ቤቱ ሲገባም አዲሷ እንግዳ መኝታ ክፍሉ ውስጥ አይኑ በዞረበት ትዞራለች፡፡ ሊያባራት አቅም ያንሰዋል፡፡ የታየችው ግድግዳ ላይ አፍጥጦ ብዙ ሰዓት ከመቆየቱ የተነሳ የዐይኑ ኃይል ግድግዳውን አለመብሳቱ ግንበኛውን ያስመሰግናል፡፡ ማንበብ….መቀደስ….መዘመር….. ከባድ ሆኑ፡፡ከባድ የጭንቅ ሳምንት አለፈ፡፡ ብዙ ሴቶች ፍቅር ያዘን ሲሉት በውስጡ ስቋል፡፡ ለእሷ እንዴት ብሎ ፍቅር ያዘኝ ይበላት? ክብሩን ከዚህ በላይ እሹሩሩ ማለት ግን አልቻለም። የት ያግኛት? ያመጧት ሴቶች አድራሻ ወዴት ነው? እያለ ሲጨነቅ ስልኩ ጠራ፡- “ሃሎ---ዮሴፍ?” ዝም፡፡ ከዚህ በፊት ድምፅዋን ሰምቶት ባያውቅም እሷ መሆኗን ወዲያው አወቀ፡፡ “ሄሎ” አለች ድጋሚ ፣መልስ ስታጣ “አቤት ማን ልበል?” ኩራቱ እየተናነቀው፡፡ “ማርታ ነኝ፣ ባለፈው ቤተ ክርስቲያን ተዋውቀን….” እስከ ህይወቷ ፍፃሜ የተሰጣትን ወኔ ያለ ይሉኝታ ዘረገፈችው፡፡ “እሽ እንዴት ነሽ?” ልቡ ደም እየረጨ ሳይሆን ደም እያፈሰሰ ድው…ድው…እያለ ምንም ያልመሰለው መስሎ መለሰ፡፡ እሷም የዘረገፈችውን ይሉኝታዋን “እ….አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄ….” በማለት ሰበሰበች፡፡ “ለምን ተገናኝተን አናወራም?” አለ እሱ እንደምንም። ትንሽ ብትዘገይ የትም ስልክ ቁጥሯን ፈልጎ እንደሚደውል እያሰበ፡፡ “እሽ” አለች፡፡ተገናኙ፡፡  ጥግ ይዘው ሲያወሩ ሰንበት ተማሪ ሁሉ እንደ ልማዱ እየመከረ ነው ብለው ልብ አላለቸውም፡፡ ሁለቱም ለምን እንደተገናኙ ያውቃሉ፤ ግን ሾላ በድፍን አውርተው ተለያዩ። በሚቀጥለው ቀን እሱ ሰበብ አዋጣ፡፡ “ትናንት ስላወራነው ነገር በደንብ የሚያብራራ መጽሐፍ አገኘሁ የት እንገናኝ ላውስሽ ነበር…” ተገናኙ፡፡ሾላው ዛሬም እንደተደፈነ ነው፡፡እንደገና በቀጣይ ቀን……..ሁለቱም ልብ ውስጥ ፍቅር ተተክሎ ስር እየሰደደ እየሰደደ….ሄደ፡፡ዮሴፍ እሷን አግብቶ ለመኖር ቆረጠ፡፡ ቀጥታ እንዴት ይጠይቃት? ተፈጥሯዊ ኩራቱ ይፈታተነዋል፡፡አንድ ቀን እንደተለመደው በድፍኑ ሲያወሩ ሲያወሩ…ማርታ ድንገተኛ ጥያቄ አመጣች፡፡“አንዲት ሴት ዲያቆን ለማግባት ምን መሆን አለባት?”“ማለት?” ልቡ ደም መርጨቷን ትታ ማፍሰሷን ተያያዘችው፡፡“ማለትማ ምን ማሟላት አለባት፡፡”“ክርስቲያን መሆን አለባት፡፡” የውሸት እየሳቀ፤ የጥያቄዋ አቅጣጫ እያስደነገጠው፡፡ “ሌላስ?” ድፍኑ ሾላ ሰልችቷታል፡፡ ጭንቅ እያለው “ሌላ ያው ልጃገረድ መሆን ይኖርባታል” አለ የሞት ሞቱን፡፡ የማርታ ፊት ልውጥውጥ አለ፡፡ የተከፈለው አገጯ ፊቷን ሙሉ ለሙሉ የከፈለው ይመስል፡፡ ስቃዩዋንና የተሰማትን ስሜት ለመደበቅ ስትጥር ባለ ሁለት መልክ ሆነች፡፡ዮሴፍ ገባው፡፡ በነፍሱ ሰይፍ አለፈ፡፡ ወሬ ቀየሩ፡፡ ሾላው መልሶ ተደፈነ፡፡ ነብሱ ሙግት ውስጥ ገባች፡፡ ስለ እሷ ማሰብ ማቆም አልቻለም፡፡ ልክ እንደ ወፍ በፊቱ ብር….ብር ትላለች፡፡ ግን ክህነቱስ? ያን ሁሉ ሰንበት ተማሪ የመከረበት ብርታቱ የት ሄደ? መጽሐፍ ቅዱስ  ሲገልጥ አንድ ቃል ብቻ ጎልቶ ይታየዋል፡፡ መፅሐፈ ኢዮብ ምዕራፍ ፬ “እነሆ አንተ ብዙዎችን ታስተምር ነበር፡፡ የደከሙትንም እጆች ታበረታ ነበር፡፡ ባንተ ሲደርስ ግን ደከምክ…፡፡  ወፊቱ አሁንም ውስጡ ክንፏን እያርገበገበች ልቡን ታደማለች፡፡ ደሙን ብቻውን ያብሳል፡፡ ሰው አብረው አያያቸውም፡፡ ግን ከእሱ ተለይታ አታውቅም፡፡ እሷ የልቡን በር በክንፏ ያለ ማቋረጥ ትደበድባለች፡፡ ቁልፉ ግን በጭካኔ ባህር ላይ ተጥሏል፡፡
(በአዲስ አድማስ ድረ-ገጽ በ Saturday, 13 October 2012 የወጣ)

Read 3635 times