Sunday, 27 May 2018 00:00

የክፉ ዘመን ትዝታ …

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

 የአገራችን ምድር እንደ እሳት በሚንቀለቀል ሃሩር የተጠቃችበት፣ ጠብታ ዝናብ ለወራት የተናፈቀበት ጊዜ ነበር፡፡ 1977 ዓ.ም፡፡ ድርቁ አብዛኛውን የአገሪቱ ክፍል በተለይም ሰሜናዊውን አካባቢ ክፉኛ አጥቅቷል። ቀድሞ የወሎ ክፍለ ሃገር እየተባለ የሚጠራው ስፍራ ይላስ ይቀመስ ከጠፋባቸውና ሰዎች በረሃብና ወረርሽኝ እንደ ቅጠል ይረግፉ ከነበሩባቸው አካባቢዎች ዋንኛው ነው፡፡
የመንዝና ግሼ አውራጃና ዙሪያው አጎራባች አውራጃዎች ውስጥ የሚኖሩት ህዝቦች፣ ለከፋ ረሃብና ወረርሽኝ ተዳርገው ያለቁበት ክፉ ዘመን ነበር፡፡ በመንዝና ግሼ አውራጃ ውስጥ የምትገኘው የአንፆኪያ ገምዛ ወረዳ መኮይ ከተማ፣ ከአጎራባቾቹ ወረዳዎች በተሻለ ሁኔታ ውስጥ ትገኝ ስለነበር ድርቅ ክፉኛ ባጠቃባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦች፣ ከመኖሪያ ቀዬአቸው እየተሰደዱ አንጾኪያን አጨናነቋት፡፡ ከ60 ሺ በላይ ህዝብ ይኖርባት የነበረችው ይህቺው ወረዳ፣ ረሃብና ድርቅ ጠንቶባቸው ከየአካባቢው እየፈለሱ የመጡትን የረሃብ ስደተኛ ወገኖችን ተቀብላ፣ ለጥቂት ቀናት ያላትን እያካፈለች አቆየቻቸው፡፡ የድርቁ ሁኔታ ወሰኑን እያሰፋና እየበረታ፣ የስደተኛው ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ሲሄድ ግን እሷ ራሷ ለረሃብ እጇን ሰጠች፡፡ ከ60ሺ በላይ የሚሆነው የአንፆኪያ ህዝብ፣ ከሰባት አጎራባች አውራጃዎች በስደት ከመጡበት ቁጥራቸው ከ36ሺ በላይ ከሚሆኑ ወገኖቹ ጋር በረሃብ ተናጠ፡፡   
ረሃብ ያጠወለገው ህዝብ የተቅማጥ ወረርሽኝ ተጨምሮበት እንደ ቅጠል መርገፍ ያዘ፡፡ ከአንድ ቤት ውስጥ አምስትና ስድስት ሰዎችን እያወጡ መቅበር ተለመደ፡፡ በየዕለቱም ከ30 በላይ ሰዎች እየሞቱ አፈር የማልበሱ ተግባር ቀሪዎቹን እየፈተነ ሄደ፡፡ ይህ ሁኔታ በወቅቱ የወረዳው አስተዳዳሪ የነበሩትን አቶ ግርማ ወንዳፍራሽን አሳዘናቸው፡፡ ወገኖቻቸው በረሃብ ሲያልቁ … ወረርሽኙ እንደ ቅጠል ሲያረግፋቸው ማየቱ ስቃያቸውን አበዛው፡፡ ሁኔታውን ለአውራጃው ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ሪፖርት አደረጉ፡፡ ሰሚ ግን አላገኙም፡፡
ድርቁ ወሰኑን እያሰፋ፣ ረሃቡ እየበረታ ሄደ። የመንግስት ኃላፊዎች ዝምታ ግራ አጋባቸው። ኃላፊዎችን በስልክ በተደጋጋሚ ተማፀኑ - ስልክ ፍለጋ ከሚሴ ድረስ እየተመላለሱ፡፡ የአውራጃው የስራ ኃላፊዎች ምላሽ አለመስጠት አስተዳዳሪውን በእጅጉ ቢያሳዝናቸውም ተስፋ ቆርጠው መተው ግን አልፈለጉም፤ ሁኔታውን የበላይ ለሚባሉት የክፍለ አገሩ ኃላፊዎች ለማሳወቅ ተነሱ፡፡ ይህንን በማድረጋቸው ሊደርስባቸው የሚችለውን ስቃይና መከራ፣ እስርና እንግልት ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ ነበሩ፡፡ እናም እሳቸው በሚያስተዳድሩት ወረዳና በአጎራባች አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦች በከፍተኛ ረሃብና ወረርሽኝ እያለቁ መሆኑንና ስለ ሁኔታው ለአውራጃው አስተዳዳሪዎች በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም ምላሽ መነፈጋቸውን ጭምር ገልፀው፣ እያለቀ ስላለው ህዝብ “ተጠያቂዎች እናንተ ናችሁ” ሲሉ መረር ያለ ደብዳቤ ፅፈው ላኩ። ኃላፊዎቹም፤ “ሰውየው ተይዞ መጥቶ እርምጃ ይወሰድበት” ሲሉ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ በዚህ መሰረት አንድ ቡድን ወደ ስፍራው መጣ፡፡ አቶ ግርማን አስጠርቶ “እንዴት እንዲህ አይነት ደብዳቤ ትፅፋለህ” ሲል ጠየቃቸው፡፡ እሳቸውም፤ “ወገኖቼ በረሃብና ወረርሽኝ እያለቁ ነው፤ በቀን ከ30 በላይ ሰዎች እየሞቱ፣ መቅበር እያቃተን ከነልብሳቸው ጉድጓድ እየጨመርናቸው ነው፡፡ ይህንንም በዓይናችሁ አይታችሁ ማረጋገጥ ትችላላችሁ፤ እኔ ላይ የፈለጋችሁን እርምጃ ውሰዱ፤ ለህዝቡ ግን ድረሱለት” ሲሉ ምላሽ ሰጡ፡፡ “አሳየን” አሉ ኃላፊዎቹ፡፡ እንግዶቹን ይዘው 5 ልጆች በረሃብና በወረርሽኝ ተይዘው ከሞት ጋር ትግል የገጠሙበት ቤት ገቡ፡፡ በዚህ ብቻ አላበቁም፡፡ 6 ሴቶች ልጆቹን ረሃብ የነጠቀው ክብረት ታፈሰ የተባለውን ገበሬ አግኝተው፣ መራራውን እውነት ሰሙት፡፡ ኃላፊዎቹ በሁኔታው ልባቸው ተነካ፡፡ ጉዳዩን ለበላይ ሪፖርት ለማድረግ የወረዳ አስተዳዳሪውን ይዘው ወደ አዲስ አበባ በመሄድ፣ የወቅቱ የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣን ለነበሩት ለጓድ ደበላ ዲንሳ ሁኔታውን አሳወቁ፡፡
ጉዳዩ አስቸኳይና ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ፤ ባለስልጣናቱ ተሰባስበው መምከር ያዙ፡፡ አቶ ግርማ በሚያስተዳድሩት ወረዳ ውስጥ ረሃብና ወረርሽኝ ህዝባቸውን እንደቅጠል እያረገፈ መሆኑን ለተሰብሳቢው ሲገልፁ፤ ተሰብሳቢዎቹ ስሜታቸው በእጅጉ ተነካ። እናም ጉዳዩ ለርዕሰ ብሔሩ ሊነገር ተወሰነ፡፡ ጓድ ደበላ ዲንሳ፣ የወረዳ አስተዳዳሪውን አስከትለው፣ ወደ ሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማሪያም ዘንድ ሄዱ። ሊቀ መንበሩ ሁኔታውን ሲሰሙ አዘኑ፡፡ የውጪ እርዳታ ለጋሾቹ ወደ ስፍራው ሄደው፣ አስቸኳይ የነፍስ አድን እርዳታ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ሁኔታውን የሚመለከት ሪፖርትም በአምስት ቀናት ውስጥ እንዲደርሳቸው አዘዙ፡፡ ጓድ ደበላ የአለቃቸውን ትዕዛዝ ለመፈፀምና በረሃብ እያለቁ ያሉትን ህዝቦች ለመታደግ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ገባቸው፡፡ “ምን ይሻለናል” ሲሉ ከእኚሁ ወረዳ አስተዳዳሪ ምክር ጠየቁ፡፡ አቶ ግርማ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ረሃብና ችግሮች ላይ ጥናት ለማድረግ የመጣ “ወርልድ ቪዥን” የተባለ ድርጅት መኖሩን ሰምተው ስለነበር ይህንኑ ለጓድ ደበላ ነገሯቸው፡፡ ቢሮውን አጠያይቀው፣ በሹፌር ወደ ስፍራው ሄዱ፡፡ ለድርጅቱ ኃላፊም በወረዳቸው ስለተከሰተው አስከፊ ድርቅና ወረርሽኝ በግልፅ አስረዷቸው፡፡ “እባካችሁ ድረሱልን” ሲሉም ተማፀኗቸው፡፡ ኃላፊውም፤ እኛ የምንረዳው ህጋዊ የሆነ፣ በመንግስት አካል የሚታወቅና ጥናት የተደረገበትን እንጂ በግለሰብ ደረጃ የሚመጡትን አይደለም” ሲሉ ምላሽ ሰጧቸው፡፡ አቶ ግርማ ረሃቡን የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ጭምር እንደሚያውቁት ተናገሩ። “እንግዲያውስ ህጋዊ ደብዳቤ ይዘህ ተመለስ” አሏቸው። ጓድ ደበላ ዲንሳ ቢሮ ተመልሰው፣ ደብዳቤ አፃፉ፡፡ ኃላፊው፤ “ምን አይነት አጣዳፊ ችግር ቢኖር ነው በዚህ ፍጥነት ደብዳቤ የተፃፈላቸው” ሲሉ ጠየቁና ሁኔታው እንዲጣራ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ በማግስቱ አቶ ግርማ “የወርልድ ቪዥን ኢንተርናሽናል” ባልደረባ የሆነ አንድ ሰው ይዘው ወደ ወረዳቸው ተመለሱ። ሁኔታውን በአይናቸው የተመለከቱት መልዕክተኛ፣ ስለ ጉዳዩ ለአለቃቸው ሪፖርት አደረጉ፡፡ በማግስቱ የነፍስ አድን እርዳታ የሚያደርግ ቡድን ወደ አካባቢው በመንቀሳቀስ፣ በረሃብና በወረርሺኝ እየረገፈ ላለው ህዝብ አስቸኳይ የምግብና የህክምና እርዳታ መስጠት ጀመረ፡፡ በአስገራሚ የሰብአዊነት ተግባር ላይ የዘመተው ወርልድ ቪዥን፤ ረሃብና ወረርሽኝ እንደ ቅጠል ያረግፈው የነበረው የአጎራባች አውራጃ ስደተኞችና የአንፆኪያ ወረዳ ህዝብን ከሞት ታደገው፡፡
በወቅቱ ረሃቡና ወረርሺኙ ከባድ ጉዳት ያደረሰበትን የአገራችንን ሰሜናዊ ክፍል ህዝብ ለመታደግና ከሞት ለማዳን የተመመው “ወርልድ ቪዥን ኢንተርናሽናል”፤ እርዳታና ድጋፉን ባሰበው መጠን ለመስጠት እንዳይችል ሁኔታዎች እንቅፋት ሆነበት፡፡ ስፍራው ለትራንስፖርት አመቺ አለመሆኑና አውሮፕላን ማሳረፊያ የሚሆን ቦታ አለመኖር ችግሩን ይበልጥ አባባሰው፡፡ የችግሩ ስፋትና የሚሰጠው እርዳታ የማይመጣጠን ሆነ፡፡ ይህንን ችግር የተረዱት አቶ ግርማ፤ በሁለት ቀናት ውስጥ አውሮፕላን ለማሳረፍ የሚያስችል ቦታ አዘጋጃለሁ ሲሉ ቃል ገቡ። ሁኔታው ለማመን የሚከብድ ቢሆንም የድርጅቱ የስራ ኃላፊዎች፤ “ከሆነልዎት ይሞክሩ” ሲሉ እድል ሰጧቸው፡፡ ረሃቡና በሽታውን ተቋቁሞ መንቀሳቀስ የቻለ፣ 3600 የህዝብ ኃይል ይዘው ቁፋሮውን ጀመሩ። በሁለተኛው ቀን መሬቱ ተደልድሎ፣ ነጭ ጨርቆች እንደ ባንዲራ ተንጠልጥለው፣ ለአውሮፕላን ማሳረፊያ ዝግጁ ሆኑ፡፡ ይህንንም አቶ ግርማ በስልክ አሳወቁ፡፡ በማግስቱ ወርልድ ቪዥን ኢንተርናሽናል የሚል ፅሁፍ ያለባት የነፍስ አድን ምግብና መድኃኒት የጫነች አውሮፕላን፣ በአንፆኪያ ሰማይ ላይ አንዣብባ፣ በረሃብና ወረርሺኝ ከሞት ጋር ትግል የገጠመውን የአንፆኪያ ህዝብ ልትታደግ በአዲሱ የአውሮፕላን ማረፊያ ላይ አረፈች፡፡ ይህ ሁኔታም በወርልድ ቪዥን የተጀመረው ወገንን ከሞት የመታደግ ተግባር በተሻለ ሁኔታ እንዲቀጥል አደረገ፡፡
የወረዳ አስተዳዳሪው አይበገሬ መንፈስና በህዝባቸው ያላቸው መተመማን በእጅጉ ያስገረመው የወርልድ ቪዥን የስራ ኃላፊም፣ “ለሰራኸው ታላቅ ተግባር ምን ልሸልምህ?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ “የቦርከና ወንዝ መንገድ አሳጥቶ፣ ህዝቤን በረሃብና በበሽታ እንዲያልቅ አድርጎብኛልና፣ እሱ ላይ ድልድይ ስራልኝ” አሉት፡፡ 1 ሚሊየን 500 ሺ ብር በጀት ተመድቦ፣ ከእንግሊዝ አገር ባለሙያ መጥቶ፣ ከአንድ ሺ በላይ የአንፆኪያ ህዝብ በጉልበቱ ተባብሮ፣ የቦርከና ወንዝ ላይ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ ድልድይ ተሰርቶ፣ የህዝብ ለህዝብ መገናኛ ሆነ፡፡ ድልድዩ ዛሬም ድረስ ለአንፆኪያና ለአካባቢው ህዝብ አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
በእኚህ ታላቅ ሰው መነሻነት የተገኘው የወርልድ ቪዥን ኢንተርናሽናል ፈጣን የእርዳታ ደራሽነት ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ የአንፆኪያና የአካባቢው ወረዳና አውራጃ ነዋሪዎች፣ ከአስከፊው ረሃብና ወረርሽኝ እፎይታን አገኙ፡፡ የተጠፋፉ ቤተሰቦች መፈላለግ ጀመሩ፡፡ ቀስ በቀስም የአንፆኪያ ወረዳ ህዝብ ተስፋው እየለመለመ፣ ሰውነቱ እየተመለሰ ሄደ። ተፈጥሮም ፊቷን መለሰች፡፡ አይበገሬው የአንፆኪያ ገበሬ ወደቀደመው ስራው መመለስ ጀመረ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥም የወርልድ ቪዝን ድጋፍ ከፍተኛ ነበር። ጥማድ በሬዎችን፣ ምርጥ ዘርና የእርሻ መሳሪያዎችን በመስጠት፤ የበግ፣ የፍየልና የዶሮ እርባታ እንዲካሄድ ዝርያዎችን እያመጡ በመስጠትና የመስኖ እርሻ እንዲስፋፋ በማድረግ እንዲሁም የተራቆተው ደን መልሶ እንዲያገግም በማድረግ፣ ህብረተሰቡን መልሶ የማቋቋሙን ስራ ተያያዘው፡፡ ህይወት በአንፆኪያ በአዲስ ተስፋ ትለመልም ጀመር፡፡ ህፃናት በጤና ማደግ፣ ልጆች ት/ቤት መዋል ጀመሩ፡፡ ህዝቡ የጭንቅ ጊዜ ደራሼ ነው በሚለው ወርልድ ቪዥን ኢንተርናሽናል ድጋፍ፣ ኑሮ እንደ አዲስ ተጀመረ፡፡
ሰሞኑን በወርልድ ቪዥን ኢንተርናሽናል የተዘጋጀ አንድ የጉብኝት ፕሮግራም በዚሁ ወረዳ ላይ ተካሂዶ ነበር፡፡ የጉብኝቱ ዋነኛ ዓላማም ድርጅቱ ላለፉት 31 ዓመታት በአካባቢው ሲያከናውናቸው የቆየውንና ከ3 ዓመታት በፊት ለመንግስትና ለህብረተሰቡ ያስረከባቸውን የተለያዩ የልማት ስራዎች፣ የአካባቢው ማህበረሰብ እንዴት ቀጥሏቸዋል የሚለውን ማየት አንዱ ሲሆን የሚዲያ ባለሙያዎችም በአስከፊው የረሃብ ወቅት አካባቢው ላይ ስለነበረው ሁኔታ ከዋንኞቹ የችግሩ ገፈት ቀማሾች እንዲገነዘቡና አሁን አካባቢው ያለበትን ሁኔታ በአይናቸው በማየት በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡  
ድርጅቱ ሥራውን አጠናቆ ከስፍራው ቢለቅም በተለያዩ ጊዜያትና አጋጣሚዎች ወደ ስፍራው በማምራት ለህብረተሰቡ መደረግ የሚገባውን ድጋፍ ከማድረግ ወደ ኋላ ሳይል አሁንም ከአንፆኪያ ህዝብ ጋር አብሮ ይኖራል፡፡ ከዛች የጭንቅና የምጥ ጊዜ ጀምሮ ዛሬም ድረስ ባልተለያቸው በዚህ ድርጅት ላይ ያላቸው እምነት ከፍተኛ ነው፡፡ ድርጅቱ በአካባቢው ባደረገው የ31 ዓመት ቆይታ ከነፍስ አድን ምግብና መድኃኒት አቅርቦቱ ሌላ በመንገድ፣ በውሃ፣ በጤና እና በትምህርት ዘርፎች ላይ በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በወረዳው 3 የሁለተኛ ደረጃ፣ 8 መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃና በርካታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን፣ 5 ጤና ጣቢያዎችን አቋቁሟል፡፡ የመስኖ ልማት ስራዎችና የችግኝ ማፍሊያ ጣቢያዎች በድርጅቱ ከተሰሩ የልማት ስራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህን የልማት ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው በማድረጉ ረገድ የአካባቢው ህብረተሰብና መንግስት ከፍተኛ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ስፍራውንም ለተመለከተ ሰው በአንድ ወቅት በድርቅና ረሃብ የተመታና በሺዎች የሚቆጠሩ ህዝቦቹን በረሃብ ያጣ በፍፁም አይመስልም፡፡ በዚህ የበጋ ወቅት አካባቢው ለምለምና አረንጓዴ ነው፡፡ ወርልድ ቪዥን ኢንተርናሽናል በዓለማችን ከሚሰራባቸው 100 አገራት መካከል ይህ በአንፆኪያ ወረዳ ላይ ያስመዘገበው ስኬት ግንባር ቀደሙ ነው፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ  ላለፉት 18 ዓመታት በኤፍራታ ግድም ወረዳ ሲያከናውቸው የቆየውን የልማት ስራዎች ለህብረተሰቡና ለመንግስት አስረክቦ የሚወጣበት ፕሮግራም የጉብኝቱ አካል ነበር፡፡ አጣዬ በሚባል ሌላ ስሟ በስፋት የምትታወቀው የኤፍራታ ግድም ወረዳ ነዋሪዎች በዚህ ድርጅት በጤና፣ በትምህርት በመንገድ ስራና በመስኖ ልማት የተሰሩላቸውን ስራዎች ተረክበው ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ የማንበቢያ ተቋማትና የህፃናት መዋያዎች በድርጅቱ ከተሰሩ ስራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አካል ጉዳተኞች መማር የሚችሉበትን መንገድ በማመቻቸት ከ165 በላይ አካል ጉዳተኞች የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ መደረጉ በዚሁ የፕሮግራም ማጠናቀቂያና የርክክብ ስነ ስርዓት ላይ ተገልጿል፡፡ የአጣዬ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አገኘሁ መርትሄ በዚሁ የርክክብ ስነ ስርዓት ላይ እንደገለፁት፤ ስፍራው በመንገድ፣ በትምህርትና በጤና ዘርፎች የነበሩበትን ችግር በመቅረፍ ላለፉት 18 ዓመታት ድርጅቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያበረክት ቆይቷል፡፡ በድርጅቱ የተጀመሩትን የልማት ስራዎችም ቀጣይነት እንዲኖረው የአካባቢው ማህበረሰብና መንግስት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል ብለዋል፡፡
የወርልድ ቪዥን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ናሽናል ዳይሬክተር የሆኑት ሚስተር ኤድዋርድ ብራውን እንደገለፁት፤በአካባቢው የተሰሩት የልማት ስራዎች በህብረተሰቡ ህይወት ላይ ያስገኟቸው ለውጦች እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም በድርጅቱ ብቻ ሳይሆን በህብረተሰቡም ርብርብ የተገኘ ትልቅ ድል ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም እጅግ አስከፊ ረሃብና ድርጅት የነበረባቸው አካባቢዎች እንዲህ ለምተውና አረንጓዴ ለብሰው ማየቱ እጅግ ስሜት የሚነካና የሚያስደስት ነገር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ህብረተሰቡ ለድርጅቱና ለተሰሩት የልማት ስራዎች ያለው ፍቅር ስሜታቸውን የነካ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ በቀጣይም በሌሎች አካባቢዎች የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና በስፍራው የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ቢወጡም ከህብረተሰቡ ጋር ያላቸው ግንኙነት እንደማይቋረጥ ተናግረዋል፡፡
ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ላለፉት 43 ዓመታት በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የልማት ስራዎችን በመስራት ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው።               

Read 2185 times