Sunday, 27 May 2018 00:00

ከ‘ጥቅሻ’ ወደ ‘ኢንቦክስ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)


    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አንድ የከተማችን ክፍል የሆነ ሬስቱራንት ውስጥ የሆነ ነው አሉ፡፡ እሱየው አራድነትን ‘አግቶ’ ለመያዝ የሚሞክር አይነት ነው፡፡ የምር ግን…‘አራድነት’ ምናምን የሚባል ነገር ቀርቶ የለም እንዴ! እናላችሁ… እሱዬው ሬስቱራንት ሲገባ ‘ቆንጅዬ’ የሚባሉ ወጣት ሴቶች ሰብሰብ ብለው ያወራሉ፡፡ እናማ…አንድዬዋ ቀልቡን ሳበችውና ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው…ጠቀሳት፡፡ (የሆነ ‘ከታሪክ ማህደር’ መሰለ!) እናላችሁ… በግሎባላይዜሽን ዘመን ቅንድቡ ሊረግፍ እስኪደርስ ድረስ ጠቀሳት አሉ። (ቂ…ቂ…ቂ…)
እናማ ቢሆን ጥሩ ነው… የሆነ ‘ሚስተር ቢን’ ምናምን ነገር ትርኢት ያሳይ ይመስል፣ ወጣቶቹ ቤቱን በሳቅ አናጉት አሉ፡፡ አዝነውለትም ሊሆን ይችላል። እንደዛ ጽድት ባለ ሬስቱራንት “ውይ ምስኪን! ዓይኑ ውስጥ አቧራ ገብቶበት ይሆናል!” የምርእኮ… ከጊዜ ጋር አብሮ መሄድ ችግር የሆነብን መአትነን፡፡
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…‘ስማርትፎን’ በመያዛችን ብቻ ‘ስማርትነት’ ከእነ ምናምኗ መጥታ የሰፈረችብን ይመስለናል፡፡ ኢንተርኔት ከፍተን ከዩቲዩብ የእንትናን ‘ሲንግል ክሊፕ’ ማውረድ በመቻላችን ብቻ እውቀት የሞላን ይመስለናል፡፡ በሆነ ነገር ላይ… “ለምሳሌ ጀርመኖች እንደሚያደርጉት…” ምናምን እያልን ከጉግል ‘ከት ኤንድ ፔስት’ ማድረግ የዘመናዊነት ጣራ ላይ የወጣን ይመስለናል፡፡
በነገራችን ላይ… ይሄ ፌስቲቫልና ኮሰርት እንደ ልብ የሆነው…‘ግሎባላይዜሽን’ የሚባለው ነገር መሆኑ ነው እንዴ! ነገርዬው ትንሽ እየበዛብን ስለመሰለን ነው… ነገሬ ብላችሁ እንደሁ እኛ ዘንድ አንድ ነገር ሲጀመር ወዲያው መቀባበል የተለመደ ነው፡፡ አለ አይደል…ልክ ፈጠን ካላልን የሚያልቅ ነገር ያለ ነው የሚመስለው፡፡ የምር ግን…ቀደም ሲል ፌስቲቫል ምናምን የሚባሉ ነገሮች እኮ እየሰነበቱ፣ እየከረሙ ነበር የሚደረጉት፡፡ ይሄን ሰሞን የፌስቲቫሉ ብዛት፣ የኮንሰርቱ ብዛት!
“የሆነ ፌስቲቫል ብናዘጋጅ ምን ይመስላችኋል…”
“ምን ምክንያት ሰጥተን ነው የምናዘጋጀው?”
“የሆነ ምክንያት እንፈልጋ! መፍጠን አለብን--”
“ቀስ ብለን አስበንበት ብናደርገው አይሻልም!”
“ያምሀል እንዴ! ቶሎ ካላዘጋጀን ድርጅቶቹ የስፖንሰርሺፕ ገንዘብ ቢጨርሱስ!” አይነት ነገር ያለ ይመስላል፡፡
እናላችሁ…የጥቅሻ  ዘመን ማለፉን ማወቁ አሪፍ ነው፡፡ በፊት እኮ የሞባይል መልእክት የለ፣ “ፌስቡክ ኢንቦክስሽን ተመልከቺ፣” ብሎ ነገር የለ፣ “ኢንስታግራም ላይ የላኩልሽን አየሽው?” ብሎ ነገር የለ፡፡ (እድሜ ለሉክ ወረቀትና ለሚላላክ ትንሽ ልጅ!) እናላችሁ…ጧት ተነስቶ ይጠብቅና ትምህርት ቤት ያደርሳል፡፡ መግባቷን ካረጋገጠ በኋላ ይመለሳል፡፡ አሥር፣ አሥራ አንድ ሰዓት ላይ ከትምህርት ቤት ተቀብሎ ቤት ያደርሳል፡፡ ነገም እንደዛው፣ ከነገም ወዲያ እንደዛው፤ እናላችሁ…የድሮ ‘ቦይፍሬንድ’ አገልግሎት የ‘ስኩልባስ’ አይነት ነበር!
ስሙኝማ፣ አንዳንዱ ደግሞ አለላችሁ… የት እንድምትሄድ፣ ከእነማን ጋር እንደምትገጥም፣ ጓደኞቿ እነማን እንደሆኑ…አለ አይደል…ከሩቅ ሆኖ ሲከታተል ይውላል፡፡ ምን አለፋችሁ…የሆነ የሲ.ሲ.ቲቪ. አይነት ነገር ነው፡፡
እናላችሁ… “እኔ እኮ ዎክ እወዳለሁ፣ ለምን ቦሌ መንገድ ላይ ዎክ አናደርግም!” ብሎ ነገር ዘንድሮ አይሠራም፡፡ “አይ ዶንት ቢሊቭ ኢት! ዎክ ነው ያልከኝ? ዎክ ከፈለግህ ታላቁ ሩጫ ግባ!”
“ምን መሰለሽ… ዎክ ማድረግ ለጤንነትም እኮ ጥሩ ነው” ይሄ ሰውዬ አልገባውም ማለት ነው፡፡
“በኋላ እደውልልሃለሁ፤ አሁን ሳውና ባዝ ልገባ ነው” ሳውና ባዝ! እሱ ለራሱ እንኳን ሳውና ባዝ ገብቶ በእንፋሎት ሊታጠን፣ ኑሮ የሽቦ ጥብስ ሊያደርገው ምንም አልቀረው! የምር እኮ… የ‘ዘቢብ ኬክ በሻይ’ ዘመን እያለፈ ነው፡፡ ለነገሩ የዘቢብ ኬክና የቦምቦሊኖ ዋጋ ምን ያህል እንደወጣ፣ እግረ መንገዱንም የቦምቦሊኖ ‘ዳሌ’ ምን ያህል እንደሳሳ የሚያውቅ ሰው በቦምቦሊኖ አይቀልድም፡፡
በአንድ ቦምቦሊኖ “ቅዳሜ መሸትሸት ሲል ብንገናኝስ…” ብሎ ነገር ምንድ ነው! በቀኑ ሰዓት ለቦምቦሊኖ ሲከፍል ሊያቃስት ምንም የማይቀረው ሰው ማታ የሚቀጥራት… አለ አይደል… መስቀል አደባባይ መሀል አቁሞ… “ጨረቃዋ ደስ አትልም!” ምናምን ሊል ነው! እሷዬዋ እኮ… “ማታ፣ ማታ የሚለኝ ፌርማታ ላይ አስቀምጦ በበቆልቲ ሊወጥረኝ ነው እንዴ!” ልትል ትችላለች፡፡
እና የጨዋታው ህግ ተለውጧል፡፡ ስሙኝማ… አዲስ አበባ እኮ ከህንጻዎቿ ምናምን በስተቀር በባህሪይ እንደገና ከተማ ለመሆን እየሞከረች ያለች ትመስላላች፤ የምር! ‘የከተሜነት ምስጢር  ምናምን የሚል ማሰልጠኛ ተቋም ይቋቋምልንማ!
“ስሚ…የሆነ ቦታ አውቅሻለሁ መሰለኝ…” አይነት  መሰለህ፣ እውነት፤ እሷዬዋ እኮ በሆዷ “በዚህ ዘመን እንዲህ አይነት ፀሀይ ያልነካው እርጥብ ይምጣብኝ!” ምናምን ልትል ትችላለች፡፡ ድሮ “የሆነ ቦታ የማውቅሽ መሰለኝ…” ማለት…አለ አይደል…እንተዋወቅ ማለቱ እንደሆነ ‘የጋራ መግባቢያ’ አለ፡፡
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይቺን ስሙኝማ…
“ከእንግዲህ ከአንተ ጋር መሆን አልፈልግም፣ ቀለበትህን እንካ”
“ከማን ጋር ነው የምትሆኚው?”
“ከማንስ ቢሆን ምን ቸገረህ!”
“እንድታስተዋውቂኝ እፈልጋለሁ”
“ለምንድን ነው የማስተዋወቅህ?”
“ቀለበቴን እሸጥለታለሁ”
እውነቱን ነው… እሷ ከሌለች ቀለበቱ ምን ያደርግለታል፡፡
እናላችሁ…የሆነ አራድነትን ወይ ቋጥኝ በተራራ ሽቅብ ሊያስገፋ በሚችል ጉልበተኝነት ወይንም በ‘ትራያል ኤንድ ኤረር’ እየሞከረ ያለ ሰው…ለ‘ለከፋ’ ብሎ… “ይቅርታ…ዘነበች አይደለሽም!” አለቀ፡፡ በእንዲሀ አይነት ሎካል ስም ‘ለከፋ’ ቀርቷላ! “የእኔ እህት፣ ልክ ሳይሽ ማንን እንደመሰልሽኝ ልንገርሽ!...ሪሃናን፡፡ አታምኚኝም፣ ሪሀና መቼ ነው ኢትዮዽያ የመጣችው” ብቃት ማረጋገጫውን አልፏል ማለት ነው፡፡ ሎካል ስም ከፈለገ ደግሞ ለማቆላመጥ የሚመች መሆን አለበት፡፡
እናማ… “ሶሪ፣ ሜሊ ነሽ አይደል!” ከተባለም… አለ አይደል… የሪሃናን ያህል ባይሆንም ‘ግሪን ካርድ’ ያሰጣል፡፡ “ቤቲ መሰልሽኝ…” ነው እንጂ “ካልተሳሳትኩ ወርቅ ያንጥፉ ነሽ…” ብሎ ነገር ቀሺም ነው፡፡
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ምን የመሳሰሉ ትርጕም ያላቸው፣ ሳንቲም ወርውሮ “ዘውድ ከሆነ እገሊት፣ አንበሳ ከሆነ እገሊት” ተብሎ ሳይሆን በምክንያት የሚወጡ ስሞች እንደ ልብ በሆኑበት አገር… በየቦታው የፈረንጅ ስሞች መብዛት የሚገርም ነው፡፡
“ከተገናኛችሁ ስንት ጊዜያችሁ ነው?”
“ሁለት ወራችን”
“ትዳር ከያዛችሁስ?”
“አንድ ወር ተኩል”
ከፈጠኑ አይቀር እንዲህ ነው፡፡ እናማ… ‘ፋስት ፉድ’ እንደሚባለው ‘ፋስት ትዳር’ በሽ፣ በሽ ነው፡፡ በፊት እኮ ነገርዬው ‘ፕሮጀክት ፕሮፖዛል’ ማዘጋጀት በሉት፡፡ እናማ…ስለ ብዙ ‘ፋስት’ ትዳሮች ከሶስት ወር በኋላ ብትጠይቁ “ውይ በ‘ፋስት ዳይቮርስ’ ተጠናቆ ይሏችሁዋል፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ትናንት ስናሾፍባቸው፣ ስንዘባበትባቸው የነበሩ ነገሮች ስማቸው በእንግሊዝኛ ሆኖ ተመልሰው ሲመጡ ‘ግሎባላይዜሽንን’ እየተቀላቀልንባቸው ነው አይደል! “ነገርኳችሁ እኮ፣ ቦላሌ መልበስ ያስተማርኩት እኔ ነኝ! ቁምጣውን እንደ ድንኳን ወጥሮ አልነበር እንዴ ከተማውን የሚዞረው!” አይነት ፉከራ ጊዜ አልፎበታል። አሀ… ቁምጣ ‘ፋሺን’ ሆናለቻ! አለ አይደል… ንቅሳት ‘ታቱ’ ስትባል ‘እንደ ዘመነች’ ሁሉ፣ ቁምጣም ‘ሆት ፓንትስ’ የተባለች ጊዜ ነው እኮ ‘የዘመነችው!’
እናማ…ወጣቶቹን ‘የጠቀስከው’ ወዳጃችን፣ ‘ኢንቦክስ’ የሚባል ነገር አለ፡፡ ‘ቅንድብህ ከሚረግፍ’ ቀርፋፋ ኢንተርኔት ፍራንክህን ቢበላብህ ይሻላል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6620 times