Sunday, 27 May 2018 00:00

የዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣት አንደምታዎች

Written by  ታምራት መርጊያ
Rate this item
(11 votes)


    ካለፉት ሦስት ዓመታት አንስቶ፥ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ወደ ስልጣን እስከመጡበት ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያችን ክፉኛ ታማ ከርማለች። ሀገሪቱ ሙሉ ለሙሉ ህመሟ ሽሮ ከተጣባት ክፉ ደዌ ተፈውሳለች ባይባልም፤ እነሆ የጠ/ሚ አብይ ወደ ስልጣን መምጣት በጎ አጋጣሚ ሆኖላት፣ ቢያንስ ከህመሟ እያገገመች እንደምትገኝ ለማየት በቅተናል። እነኛን የከፉ ሦስት ዓመታት፣ ዛሬ ላይ ቆመን የኋሊት ስናስታውሳቸው፤ ሀገራዊ ስንክሳሮቻችን እጅግ የበዙባቸው፥ ሀገሪቱም የወላድ መካን የሆነች በሚመስል መልኩ ጣሯና ጭንቋ  በዝቶ፥ እንደ ሀገር የመቀጠሏ ነገር ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ገብቶ፥ አደገኛ አዝማሚያዎች በስፋት የተንሰራፋባቸው ጊዜያት ነበሩ ለማለት ያስደፍራል።   
በእነዚያ ሐገራዊ የመከራና የስጋት ጊዜያት በሐገሪቱ በቆዳ ስፋትም ይሁን በሕዝብ ቁጥር ትልቁ ብሄር ከሆነው የኦሮሚያ ክልል ተነስቶ፤ ወደ ሌላውና ሁለተኛ በርካታ የሕዝብ ቁጥር ወዳለው የአማራ ክልል፤ ብሎም ወደ ደቡብ (ጉራጌ) ክልል በተዛመተና በተደጋጋሚ (domino effect) በተካሔደ ሕዝባዊ የተቃውሞ ሱናሜ ማዕበላት ስንናጥ መክረማችን፣ በታሪካችን በጉልህ የሰፈረና ከቶውንም ሊዘነጋ የማይችል እውነት ነው፡፡ ይህንን እውነት መሪር የሚያደርገው ኩነት ደግሞ በዚህ አንዴ ጋብ ሌላ ጊዜ ደግሞ እንደ ሰደድ እሳት ሲቀጣጠል በቆየ ህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሳቢያ፣ በጸጥታ ሀይሎችና አንዳንዴም ምሬታቸው ጫፍ በወጣ የተቃውሞ እንቅስቃሴ አራማጅ ወገኖች አማካኝነት በተወሰደ ግብታዊና አሳዛኝ እርምጃ፣ ከህጻን እስከ አዋቂ፤ ከምሁር እስከ አርሶ አደር፤ ከሰራተኛ እስከ ነጋዴ ሳይለይ  የበርካታ ዜጎቻችን መተኪያ የሌለው ህይወት ላይመለስ በአሳዛኝ ሁኔታ አልፏል፤ የአያሌ ምስኪን ወገኖች አካል ለጉዳት ተዳርጓል፣ ዜጎች ለፍተው ጥረው ያፈሩት ንብረት ወድሞ ትቢያ ሆኗል፤ እንዲሁም በርካታ ወገኖቻችን ከቀያቸው ተፈናቅለው ለስደትና ለመከራ ህይወት ተዳርገዋል፡፡
የዚህ ሁሉ የፖለቲካና ማሕበራዊ ትራጀዲ ውጥንቅጥ ማክተሚያ ጊዜያዊም ይሁን ዘላቂ መፍትሄ፣ ቢያንስ ዶከተር አብይ ወደ ስልጣን እስከመጡበት ጊዜ ድረስ ሳይገኝም ቀርቷል፡፡ በርግጥ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራው የወቅቱ መንግስት፤ በመላው ሀገሪቱ የተከሠተው ችግር ያሳረፈበትን ከባድ የፖለቲካ ጫናና ግፊት ለማብረድና ለማለዘብ መፍትሄ ይሆኑኛል ያላቸውንና የመንግስቱ  ቀውስን የመፍቻ ዘዴዎች የማሰብ ልክ  በፈቀደለት መጠን ዘልቆ፤  ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትን ከስልጣን እስከ ማንሳትና በአዳዲስ ተሿሚዎች እስከ መቀየር፣ በሙስና ጠረጠርኳቸዉ ያለውን ባለስልጣናትም ወደ ወህኒ እንዲወርዱ እስከ ማድረግ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከአንዴም ሁለቴ እስከ ማወጅ፣ የችግሩ መንስኤ ነው ብሎ ያሰበውን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን እስከ መሰረዝ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት የማቋረጥ እርምጃ እስከ መውሰድ ድረስ ቢጓዝም፤ ችግሮቹ ከመቃለል ይልቅ እየተባባሱ ሄደው፣ ሐገሪቱ የመፍረስ መስቀለኛ መንገድ ላይ ደርሳ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
በመጨረሻ ላይ ግን፤ የሚመሩት መንግስት ከቶውንም መፍትሔ ለማምጣት የሚቻለው እንዳልሆነና ችግሩን ለመፍታት የግድ አዲስ አመራር እንደሚያስፈልግ የተገነዘቡ የሚመስሉት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ በመጨረሻዋ የባከነች ደቂቃ ላይ በስልጣን ዘመናቸው ከሰሯቸው በጎ ስራዎች ሁሉ በላቀ ደረጃ ጉልህ ሆኖ፣ በበጎ ጎኑ ሊታወሱ የሚችሉበትን ታላቅ ውሳኔ በማሳለፍ፣ “የመፍትሔው አካል ለመሆን--” በማለት ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው በመልቀቅ ወሳኝ ጎል አስቆጠሩ። ይህን ጊዜም ጥያቄዎቹ መልስ እስካገኙ ድረስ፤ ቂም መቋጠር የማያውቀውና የማይሆንለት የኢትዮጵያ ሕዝብ “ኃይለማሪያም ወንድ ወጣቸው” በማለት፥ በክብር ወደ መደበኛ ህይወታቸው ሸኛቸው።
በእርግጥ እነዚህን የታሪክ ጠባሳዎች ማንሳታችን የእለቱ አበይት ጉዳያችን ሆኖ ሳይሆን፤ የርዕሳችንን ሒደትና ዑደት በመመርመር፣ ለጠቅላላ ጉዳያችን ግብዐት ይሆን ዘንድና ከመጥፎ ታሪካችን በመማር፣ ለመጻኢ ሐገራዊ ዕጣ ፈንታችን ስንቅ ለመቋጠር ያስችለን እንደሆነ በማሰብ ነው። እናም ወደ ቀደመ ጉዳያችን ስንመለስ፤ በዚህ መልኩና በበርካታ የፖለቲካ ድራማዎች ታጅበው፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እነሆ ወደ ሐገሪቱ ቁጥር አንድ የስልጣ መንበር መጡ።
እንደሚታወቀው፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ከቀዳሚያቸው በበርካታ መንገድ የተለዩ ናቸው። ዶከተር አብይ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው አስቀድሞ የገነቡት የግል ሰብዕና፣ የፖለቲካ አካሔድና በሕዝብ የመታመን ሰብዕና እንዲሁም ድርጅታዊ ድጋፍና ወቅቱና መድረኩ የሚጠይቀውን የፖለቲካ ብቃት ለመመለስ የሚመጥን፤ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ ከፍተኛ ብቃት ባላቸው ፖለቲከኛ ግለሰቦች የተዋቀረውና “የለማ ቡድን” (Team Lemma) በመባል የሚታወቅ ቡድናዊ አደረጃጀት የኋላ ደጀን እገዛ፤ ከአቶ ኃይለማሪያም አንፃር ፍጹም የተለየ ነበር ማለት ይቻላል። ታዲያ እነዚህ ሁሉ አስቻይ ሁኔታዎች (Enabling Environment)  ያገዟቸው የሚመስሉት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመታየት የበቁ “ሁለት፥ሦስት” የሆኑ በጎ ውጤቶችን የተላበሱ አንደምታዎች ያሏቸው ሐገራዊ ለውጦችን ለማስመዝገብ ችለዋል፡፡
እነዚህ ውጤቶች ሁለት ሲሆኑ ሐገራዊ ሰላምና መረጋጋት ይሆናሉ፤ ሦስት ሲሆኑ ደግሞ ቀጣይ ሀገራዊ ተስፋን ያካትታሉ ከአንዳንድ አሉታዊ ኩነቶች በስተቀር፥ ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በመላው የሐገሪቱ ክፍሎች በሚባል ደረጃ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ጋብ ብለው፥ የሰላም አየር መንፈስ ጀምሯል። ይህንንም ተከትሎ በአሁኑ ጊዜ ሕዝቡ በተረጋጋ መንፈስ የእለት ተእለት ኑሮውን ቀጥሎ፥ ሰራተኛው ስራውን ተረጋግቶ በመስራት ላይ ሲገኝ፤ ነጋዴውም እንደ ቀድሞው ንግዱን እያከናወነ ነው፡፡ ተማሪውም ቢሆን ወደ ትምህርት ገበታው በመመለስ፣ ለነገ ህይወቱ ስንቅ የሚሆነውን እውቀት እየገበየ ይገኛል፡፡
ዶክተር አብይ በተለያዩ የሐገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወሩ ከሕዝቡ ጋር በመወያየት፣ የሕዝቡን ችግሮች ለማዳመጥ በሚያደርጉት ጥረትና ተስፋን በሚፈነጥቁ ንግግሮቻቸው ምክንያት ሕብረተሰቡ ሐገራዊ ተስፋን በልቡ ሰንቆ፣ መጻኢ ጊዜያትን ለማየት እንዲጓጓና እንዲነቃቃ የተዋጣለት ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመስራት ችለዋል። ሊፈቱ አይችሉም የተባሉና ከፍርግርግ የብረት አጥር ጀርባ ዘብጥያ ተወርውረው የነበሩ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ ማድረጋቸው ደግሞ ሐገራዊ ተስፋችንን ይበልጥ እንዲንር ያደረገ አዎንታዊ ተግባር ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በሐገሪቱ የመንግሥት ስርዓት ታይቶ በማያውቅ መልኩ፤ ሚኒስትሮቻቸውንና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን በጽህፈት ቤታቸው ሰብስበው፣ የመልካም አስተዳደር ስልጠና እራሳቸው አዘጋጅተው በመስጠት፤ ከመስከረም 2011 ጀምሮ ሁሉም ሚኒስትሮቻቸው ከተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ጋር የስራ አፈጻጸም ውል እንደሚፈፅሙ በማሳወቅ፥ ሚኒስትሮቹ በስልጣን መቆየት የሚችሉት ይህንን ውል መፈፀም ሲችሉና በየሴክተሮቻቸው በውሉ ላይ በቀጣይ ጊዜያት እናሳካዋለን ብለው  የሚያስቀምጧቸውን ግቦች ማሳካት ሲችሉ ብቻ መሆኑን ቁርጥ አድርገው ነግረዋቸዋል። በተጨማሪም ሚኒስትሮቹ እናሳካለን የሚሉት ግብ ከሕዝብ እይታ የተሠወረ እንዳይሆን በድረ ገጾች ላይ ተቀምጦ ሕዝብ እንደሚመለከተውም አስረግጠው ገልጸውላቸዋል። በዚህ መሰረትም ሁሉም ሚኒስትሮች በየሦስትና ስድስት ወሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት በቀጥታ በሚተላለፍ ስርጭትና ሕዝብ በሚሳተፍበት መድረክ ቀርበው፣ በሕዝብ እየተጠየቁ እንደሚገመገሙና፤ ይህን ማለፍ እስከቻሉ ድረስ ብቻ በስልጣን መቆየት እንደሚችሉ አብራርተውላቸዋል።
እንግዲህ የዚህ ሁሉ አንድምታ ከዚህ በኋላ ሚኒስትርነትና የመንግስት ኃላፊነት በፖለቲካ ታማኝነት ብቻ የሚገኝ ርስት መሆኑ ቀርቶ፤ ብቸኛና አውነተኛ የስልጣን ምንጭ ከሆነው ሕዝብ ተቆጥሮ፣ ተለክቶና ተሰፍሮ በሚሰጥ የስራ ክንውን እቅድና በኋላም ሕዝቡ ቆጥሮ በሚረከበው ሐገራዊ ውጤት መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ የተባለው ጉዳይ ወደ ተግባር ከተለወጠ፣ በእርግጥም ሕዝብ የስልጣን ባለቤት ይሆናል ማለት ነው።
በአጠቃላይ ስንመለከተው፣ ዶክተር አብይ በዚህች አጭር ጊዜ ውስጥ ያከናወኗቸው ተግባራትና የታየው ውጤት፤ እንደው ለጽሁፋችን ማጌጫ ያህል ካልሆነ በስተቀር ሁለት፥ሦስት ብቻ ተብሎ በቀላሉ የሚታይና የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም። በባዕድ ሃገር በእስር ሲማቅቁ የነበሩ እንጀራ ፈላጊ በርካታ ወገኖች እንዲፈቱ የየሀገራት መሪዎችን ከማሳመን ባለፈ፤ ሐገሪቱ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የነበራትን የፖለቲካ ተሰሚነትና ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም መልሶ እንዲያንሰራራ ለማስቻል ይረዳ ዘንድ ጅቡቲ፣ ሱዳንና ኬንያ በመጓዝ ያደረጉት ጥረትም ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነው። ብቻ ያዝልቅላቸው እንጂ “የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንዲሉ፥ ሰውየውስ አያያዛቸዉ ቀላል አይመስልም።
እኛ ኢትዮጵያውያን ሁላችንንም የሚያስማማ፣ በእኩል የሚያስተዳድር፤ ሁላችንም የምንስማማበትና የምናምነው መሪ ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ የሚያስፈልገንና የሚገባን ወቅት ላይ እንገኛለን። ምክንያቱም እንደ ግዮን ወንዝ ዘለግ ባለው ታሪካችን ውስጥ እንዲህ ያለውን መሪ ለመታደል አለመቻላችንን፣ በቀደሙት ጊዜያት በነበሩን መራዎቻችን ላይ ያለን ለየቅል የሆነ አቋምና አመለካከት  አመላካች ነው። አባ ታጠቅ ካሳ፣ ቴዎድሮስ ሲነሱ፤ የምንኮራባቸው ያለነውን ያህል፣ ከዚህ ተቃራኒ የሆነ አቋም የምናንጸባርቅም አለን። እምዬ ምኒልክ፣ ጃንሆይ፣ ኮሎኔል መንግስቱ፣ አቶ መለስና አቶ ኃይለማሪያምንም በተመለከተ እንዲሁ ፅንፍና ፅንፍ የያዙ አመለካከቶች እናራምዳለን።
ስለሆነም፥ ደቡብ አፍሪቃውያን በኔልሰን ማንዴላ፤ አሜሪካኖች በጆኔፍ ኬኔዲ፤ ፈረንሳዮች በቻርልስ ደጎል፤ እንግሊዞችም በማርጋሬት ታቸር፥ በአንድነትና በጋራ እንደሚኮሩባቸው ሁሉ፤ እኛም ወር ተራው ደርሶን ከቀደሙት መሪዎቻችን በተለየ መልኩ ቢያንስ  በዶክተር አብይ፣ በአንድነትና በጋራ ለመኩራት እንድንበቃ፣ ፈጣሪ ቅድስት ሐገራችንን ኢትዮጵያንንና ሕዝቦቿን እረድቶን፤ አዲሱን መሪያችንን የጠቢቡ ሰለሞንን ጥበብ፥ የማንዴላን የእርቅ ልቦናና የቶማስ ሳንካራን የሕዝብና የሐገር ፍቅር እንዲቸርልንና ፍጻሜያቸውም እንደ ጅማሯቸው ያማረ እንዲሆን ልባዊ ምኞታችንና የዘወትር ጸሎታችን ነው። ያለ ልዩነትና መከፋፈል መሆንም ያለበት ይህ ነው።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ከዘለቷ ታድሳ፤ ከህመሟ ሽራ፤ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ያድርግልን!!
ከአዘጋጁ፡- (ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው Feedback: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል)

Read 8329 times