Monday, 21 May 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

 “እናትነት ባለበት ህይወት አለ!”
               
   ሰለሞን ሜሮንን ከወላጆቹ ጋር ለማስተዋወቅ ቤት ወሰዳት፡፡ እናቱ ሜሮንን እንዳየች ክው፣ ድርቅ አለች። በደመነፍስ እቅፍ አደረገቻት… ትንፋሽ እስከምታጣ። ሜሮንም አናቷን የሰለሞን እናት ጡት ስር ወሽቃ፣ ወገቧን በሁለት እጇ እንደጨመቀች፣ የሆነ ስሜት ሲነዝራት ታወቃት፡፡ ሁለቱም ውስጥ ምቾት ነበር፡፡
ሜሮን አሜሪካን አገር ነው የኖረችው፡፡… ከልጅነቷ ጀምሮ፡፡ ከሰለሞን ጋር የተዋወቁት ከአራት ቀን በፊት አውሮፕላን ውስጥ ነው - ወደ አገራቸው ሲመጡ። ለእናቱ ይሄን ሲነግራት ከፍተኛ ሸክም ከላይዋ ላይ ተራገፈ፡፡…ለምን እንደሆነ አልገባትም፡፡
* * *
ባለፈው ዕሁድ ግንቦት 5 ቀን 2010 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የእናቶች ቀን ተከብሯል፡፡ ለነገሩ ሁሉም ቀን የእናቶች ነው፡፡ እናትነት የሌለበት ጊዜ፣ እናትነት የሌለበት ቦታ፣ እናትነት የሌለበት ጥበብ፣ እናትነት የሌለበት ጦርነት የለም፡፡… እናትነት ባለበት ህይወት አለ!!
እስራኤላውያን የዘር ግንዳቸውን የሚቆጥሩት በእናት ወገን ነው ይባላል - ማንነት ዕውነት የሚሆነው በእናትነት ነው በማለት፡፡ አባትነትን ቸል ለማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን አባት አባትነቱን የማያውቅበት አጋጣሚ ስለሚኖር፣ አባት አባትነቱን ካልፈለገ ሽምጥጥ አድርጎ ሊክድ ስለሚችል፣ አባት አባትነት እያማረው፣ እየጓጓ አባት አይደለህም የሚባልበት ሁኔታም ስላለ ነው፡፡ ከ DNA ዘመን በፊት ኳስ ዘጠናውን ደቂቃ በእናት ሜዳ ላይ ነበረች፡፡
እናትነት፤ እንደኛ ባለ አገር ለአንዳንዶች ክብርና ወግ፣ ለአንዳንዶች ሀብትና ንብረት፣ ለአንዳንዶች ድህነትና ጉስቁልና፣ ለአንዳንዶች ጌጥና ውበት፣ ለአንዳንዶች የቁሻሻና የዝንብ ምንቸት ቢሆንም የእናት ትንሽ የለም፡፡… “ጎሽ እንኳን ለልጇ…” እንደሚባለው!!
ንጉሥ ዳዊት የሚነገርለት ዳኝነት አለ፡- ሁለት ሴቶች በአንድ ህፃን እናትነት ተጣልተው ቀረቡ፡፡ “የኔ ነው፣ ያንቺ አይደለም” እየተባባሉ፡፡ ዳዊት ግራ ቀኙን አዳምጦና መርምሮ… ህፃኑ ሁለት ቦታ በሰይፍ ተሰንጥቆ እንዲካፈሉ አዘዘ፡፡ በዚህን ጊዜ አንደኛዋ ዝም ስትል፣ ሌላኛዋ ኡኡ! አለች፡፡…”ትውሰደው፣ ትውሰደው፤ እሷ ናት እናቱ!” ብላ ጮኸች፡፡ ንጉሡ ለሷ ፈረደ፡፡ … “አንቺ ነሽ እናቱ” ብሎ!!! … አልተሳሳተም፡፡
ወዳጄ፡- ተፈጥሯዊ እናትነት (መውለድ፣ ማጥባት) ከሞላ ጎደል፣ ሰውን ጨምሮ በሁሉም እንስሳት ላይ ተመሳሳይ ነው፡፡ ኑሯዊ እናትነት (ማሳደግ፣ አብሮ መኖር የመሳሰሉት) ግን ከእናት እናት ይለያያል። ሰው “ሰው” የሚሆንበት ውጫዊ ምክንያቶች (Enviromental factors) ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ምክንያቶች በተፈጥሮ ከምንወርሰው እኛነት (gens) በላይ “እኛነታችንን” ያደምቃሉ፡፡ በበዙና በጠነክሩ ቁጥር ተፈጥሯዊ እኛነታችን ይቀበራል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በስሜት ወይም በግልፍተኝነት የምንናገረው፤ ወይም የምናደርገው ነገርና በውስጣችን እንዲሆን የምንፈልገው ጉዳይ ይቃረንብናል፡፡… “የአፌን ሳይሆን የልቤን፣ የጠየቅሁህን ሳይሆን የሚያስፈልገኝን ስጠኝ” ብለን የምንማለደው ለዚህ ነው፡፡ እንደ ፍቅርና ደግነት፣ የመሆንና የመምስል ጉዳይ በ “ኑሮ” እናትነት ውስጥም አለ፡፡ እናትም ሰው ናትና!!
እናት መሬት፤ ትንሿን ፍሬ በማህፀኗ ዘርዝራ ቡቃያና ወርካን፣ አበባና እሾህን፣ ጣፋጭና መራራን፣ ለስላሳና ሻካራን፣ መርዘው የሚገድሉ፣ ፈውሰው የሚያድኑ ዕፀዋትን ታበቅላለች፡፡ እናትም እንዲሁ ናት።… ጎበዝና ደካማ፣ አጭርና ረዥም፣ ጥቁርና ነጭ፣ ደግና ክፉ፣ ደነዝና አስተዋይ፣ ብልህና ጅል ትወልዳለች፡፡ …የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ!!
እናትነትን ስናስታውስ፤ ታላላቅ እናቶችን እናስባለን። ከጥንታውያን ባለገድል እናቶች ድንግል ማርያምና የጦረኛው አኪላስ እናት ዋነኞች ናቸው፡፡ “ልጅሽን አማልጂኝ” እየተባሉ በአቤቱታ የተጨናነቁ። ወደዚህ ስንጠጋ ደግሞ፣ ከተረት ባለፈ፣ የምር እናቶች አሉ፡፡ ስምና ዝና የሌላቸው ምስኪኖች፡፡ አንጄላ ማካርት አንዷ ናት፡- ጉረኛ፣ ሰካራምና ዘላን የሆነ አባት ሊያስተዳድረው ያልቻለ፣ ደሃ የአየር ላንድ ቤተሰብ ያለፈበትን ፍዳና መከራ ተሸክማለች፡፡ የመጣችበት መንገድ ኮሮኮንችነት እንኳን ሊኖሩት ተፅፎ ሲያነቡት፣ አንጀት ያላውሳል፡፡ ልጆቿን ለማሳደግ የቁም ስቃይ ተቀብላለች፡፡ አንጄላ ቻይ፣ ታጋሽ፣--- ጠንካራ ከምንለው በላይ ቃል ቢኖር የሷ ነው፡፡ እናትነት በደል ነው የሚያሰኝ፡፡ ልጇ ፍራንክ ማካርት አድጎ ወደ አሜሪካ ከተሰደደ በሁዋላ የቤተሰቡን ሰቆቃ በዝርዝር ፅፎታል፡፡ በናቱ ስም የተሰየመው “Angela’s Ashes” የተሰኘው መፅሃፍ “ጉድ!” አለበት፡፡ ፍራንክ ከሞተ አራት ወይም አምስት ዓመታት ገደማ ቢሆነው ነው። ሲሞት ትልቅ ዜና ነበር፡፡ ኒውስ ዊክ መጽሄትም በሰፊው ዘግቦታል፡፡
ወዳጄ፡- ዘርዝረን የማንጨርሳቸው ሚሊዮን አንጀላዎች እኛም አሉን፡፡ ያልተፃፈላቸው፣ ማንም እማያውቃቸው፡፡ ቀን እንደ ስጦታ፣ ዕድሜ እንደ ማዕረግ የሚሸለም ቢሆን የናቶች ቀን ሁሌም ለነሱ ይሁን ያሰኛል፡፡
ወደ መጀመሪያው ታሪካችን እንመለስ፡- ከሃያ ሰባት ዓመታት በፊት ግንቦት 19 ቀን 1983 ዓ.ም ምሽት በአንድ የክፍለሃገር ሆስፒታል ውስጥ በከፍተኛ ምጥ የተያዙ ሁለት እናቶች ነበሩ፡፡ አንደኛዋ፤ አንድ ወንድና አንድ ሴት መንታ ልጆች ስትገላገል፣ አንደኛዋ ደግሞ አንዲት ሴት ልጅ ወለደች፡፡
እናቶች በምጥ ስለተዳከሙ ድብን ያለ ዕንቅልፍ ወሰዳቸው፡፡ መቀስ የሚያቀብለው ረዳት እንኳ ያልነበረው አንድ ቅን ሃኪም ብቻ ነበር በቦታው። ወዲያ ወዲህ እየተራወጠ ሁሉንም ህሙማን ይረዳል። መንግስት ባለመኖሩ ውጥረት ስለነበር የሆስፒታሉ ሰራተኞች አልነበሩም፡፡ ከተማው በጥይት በፍንዳታ ተቀውጧል። በዚህ ወከባ ጊዜ ነው፣ ሃኪሙ ጨቅላዎቹን ወደ ሙቀት መስጫ ክፍል ሲወስዳቸው፣ የሁለቱ ልጆች ቦታ የተቀያየረው፡፡ አንደኛዋ ህፃን በማህፀን ውስጥ ተጎድታ ስለነበር በጥቂት ቀናት ውስጥ አለፈች፡፡ የመንታዋ እናት ወደ ቤቷ ስትመለስ የተረፋትን አንድ ልጇን ይዛ ነበር፡፡ የዛሬው ሰለሞንን፡፡
ዛሬ ለሰለሞን ቤተሰብ አዲስ ቀን ነው፡፡ ሰለሞን አውሮፕላን ላይ የተዋወቃት ወጣት፤ እሱን እንደምትመስል አልጠረጠረም፡፡ እሷም ደግሞ እንደዚሁ። በእናት ጥርጣሬ ሳቢያ ፓስፖርታቸው፤ በሁዋላ ደግሞ የሆስፒታሉ ሪከርድ ሲታይ፣ የተወለዱበት ዓመት፣ ቀንና ሰዓት ተመሳሳይ ሆነ፡፡
“እህትህን ይዘህ መጣህ” አለችው እናቱ፤ ከመረጋጋት በሁዋላ፡፡
“ሳይሽ ፍርክስ ነበር ያልኩት” አለች ሜሮን
“ገና እንዳየሻት ደነገጥሽ” አለ ሰለሞን ለእናቱ - በDNA ምርመራ  ውጤት እየተገረመ፡፡ “እናትነት ሚስጢር ሳይኖረው አይቀርም” አለ በመቀጠል። ዕውነት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ኒውስዊክ The myth of motherhood ሲል አንድ የጥናት ሪፖርት አስነብቦ ነበር፡፡ እናትነት ምስጢር ሊኖረው ይችላል፡፡ ማን ያውቃል?
ወዳጄ፡-  blood recognizes blood በማለት የፃፈው ማን ነበር?.... ትስማማለህ?...በእኔ በኩል እንጃ!!
ሠላም!

Read 1034 times