Monday, 21 May 2018 00:00

ከሰዓሊ ታምራት ጋር ጥበባዊ ወግ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ሰዓሊ ታምራት ስልጣን ተወልዶ ያደገው እዚህ አዲስ አበባ ልደታ አካባቢ ነው፡፡ በልጅነቱ የእናቱን የስፌት ጥበብ እያየ ይመሰጥ እንደነበር የሚያስታውሰው ሰዓሊ ታምራት፤ ወደ ስዕል ሙያ እንዲገባ ያነሳሳውም የእናቱ የስፌት አሰራር እንደሆነ ይገልፃል፡፡  በ1988 ዓ.ም  በአዲስ አበባ ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ገብቶ፣ የ4 ዓመት ትምህርቱን ቢያጠናቅቅም የስዕል ሙያን የሙሉ ጊዜ ሥራው ያደረገው ግን ዘግይቶ ነው- ከዓመታት በኋላ፡፡ ሰዓሊው እስከ ዛሬ በቡድን 20፣ በግሉ ደግሞ 5 የስዕል አውደርዕዮችን በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ለእይታ አብቅቷል፡፡ በተለይ “አፈርሳታ የተሰኘው” አውደርዕዩ ከፍተኛ አድናቆትን እንዳስገኘለት ይናገራል፡፡
በዛሬው ዕለት ደግሞ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የኢትዮጵያ እናቶችና የመክተፊያ መስተጋብርን የሚያሳይ የስዕል አውደ ርዕይ ይከፍታል፡፡
 የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በሙያ ህይወቱ፣ በአውደርዕዮቹ፣ በስዕል ገበያና…  ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከሰዓሊ ታምራት ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

   የእናትህ ስፌት እንዴት ለስዕል ሙያ እንዳነሳሳህ አጫውተኝ ….
ሁሌም እናቴ ስፌት ስትሰፋ አያታለሁ፡፡፡ ከእናቴ ጋር ያለኝ ቅርበት በጣም የጠበቀ ነው፡፡  ስፌቶቹን ገና ስትጀምር የምትሰራውን ውጥን አይና፣ እያደገ ሄዶ የሚይዘው ቅርፅ ይገርመኝ ነበር፡፡ ከዚያ ቀለም የሚያቀልሙት ስንደዶና አክርማ (አለላ) በስፌቱ ላይ ቅርፅ እየያዘ ይመጣል፡፡ እርግጥ እናቶች ስፌት ሲሰፉ በቀላሉ ቆጥረው ነው ዲዛይኑን የሚሰሩት፡፡ ያ ነገር ቀልቤን ይስበዋል፡፡ አንዳንዴም እናቴ ውጥኑን ወጥና ስትሰጠኝ እሰፋ ነበር፡፡ ለቤቱ የመጀመሪያ ልጅ እንደመሆኔ የተሻለ ነፃነት ነበረኝ፡፡  ክረምት ላይ በተገዛልኝ ጥቁር ሰሌዳ ላይ ስዕል መሳል… በጠመኔ መሞነጫጨር ጀመርኩኝ፡፡ ለአዲስ ዓመት አበባ እያልን በየቤቱ የምናዞረውን ስዕልም እስል ነበር፡፡ መሳል ብቻ ሳይሆን ከመርካቶ ቀለም ገዝቼና ንድፍ ሰርቼ፣ በካርቦን ኮፒ እያደረግሁ ለሰፈር ልጆች እሸጥ ነበር፡፡ ለዚሁ ሁሉ ግን መነሻዬ እናቴ የምትሰፋው ስፌት ነው፡፡
ከስዕል ት/ቤት ተመርቀህ እንደወጣህ ወደ ስዕል ሙያ ገባህ?
ሙሉ ለሙሉ ወደ ስዕል ሙያ አልገባሁም ነበር። ግማሽ ጊዜዬን ለኑሮ ገቢ የሚያመጣ ስራ እየሰራሁ፣ በግማሹ ጊዜዬ ነበር የምስለው፡፡ ምክንያቱም የኑሮ ጥያቄዎችን ለመመለስ ሌላ ስራ መስራት ነበረብኝ። የመጀመሪዎቹን ሁለት ዓመታት ተቀጥሬ ሰራሁ። ከዚያም የራሴን የህትመት ቤት ከፍቼ መስራት ጀመርኩኝ፡፡ ቀስ በቀስ ነው፣ የሙሉ ጊዜ ሰዓሊ የሆንኩት፡፡
“አፈርሳታ” የተሰኘው አውደ ርዕይህ አድናቆት አትርፎልሃል፡፡ እስቲ ስለ እሱ ንገረኝ?
“አፈርሳታ”ን ያሳሰበኝ ለተፈጥሮ ቅርብ መሆኔ ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ ተፈጥሮን የምንረዳበት መንገድ ቢለያይም ሁላችንም ለተፈጥሮ ቅርቦች ነን፡፡ አንድ ሰው መኖር ይፈልጋል፡፡ ለመኖር ደግሞ አካባቢውንና ተፈጥሮን መረዳት አለበት። ከተረዳን በኋላ የእኔ አበርክቶ ምንድነው የሚለው ሀሳብ ይመጣል፡፡ ለምሳሌ እኛ ቡድን አለን፤ ተራራ እንወጣለን፣ ጫካ ውስጥ እናድራለን፡፡ ይሄ ከተፈጥሮ ጋር ያለንን ግንኙነት ያጠናክረዋል፡፡ የሆነ ጫካ ቦታ ስትሄጂ፣ ዛፍ ስር ነው አረፍ የምትይው፤ ስለዚህ ዛፍ ማረፊያም ነው፡፡ አፈርሳታ በገጠር አካባቢ እቃ ሲጠፋ አውጫጭኝ የሚደረግበት ሥርዓት ነው፤ ዛፍ ስር ነው የሚደረገው፤ እንደ ፍርድ ቤትም ልታይው ትችያለሽ። ተፈጥሮና የሰው ልጅ ያላቸውን ቅርበት ተመልከቺ። በአፈርሳታ ሌባ ይለያል፤ ያጠፋ ይቀጣል፡፡ አካባቢያዊ ሥርዓትን ማክበርና ለዚያ መገዛት፣ የመኖር መሰረት ነው። በዚህ እሳቤ ተነስቼ ነው “አፈርሳታ”ን ያዘጋጅሁት፡፡ ጥሩ ተቀባይነት አስገኝቶልኛል፡፡
አንተ የመሃል ልደታ ልጅ ነህ፡፡ እንዴት ስለ አፈርሳታ በጥልቀት አወቅክ?
ትክክል ነው፤ የከተማ ልጅ ነኝ፤ ልደታ ነው የተወለድኩት፤ ነገር ግን በአገሪቱ ላይ የሚደረጉና የሚካሄዱ ባህላዊና ትውፊታዊ ነገሮችን ለማወቅ የግድ ገጠር መወለድ ላያስፈልግ ይችላል፡፡ አሁን ላይ ወቅቱና ሁኔታው አጠፋቸው እንጂ አሮጌው ኤርፖርት ወንዙ አካባቢ ትልቅ ጫካ ነበር፡፡ ጅብ ሁሉ ይጮህ ነበር፡፡ ልጅ ሆነን ዳክዬ ዋና የሚባል ቦታም እንዋኝ ነበር፡፡ በወቅቱ የገጠር ስሜትን የሚፈጥር ድባብ ነበረው፡፡ ማህበረሰቡም መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያለው፣ ግን ተቀራርቦና ተጋግዞ የሚኖርበት በመሆኑ፣ ሁሉን ነገር አውቀሽ የምታድሪበት ነው፡፡ እነዛ ስሜቶች የሚፈጥሩብሽ ነገር በውስጥሽ ይቀራል፡፡ ከዚያ ደግሞ የተለያዩ ታሪኮች ታነቢያለሽ፡፡ ድራማ ታያለሽ፡፡ ድራማውን ወይም ታሪኩን ከአካባቢሽ… ከአደግሽበት ዛፍ ጋር ታገናኚዋለሽ፡፡ አፈርሳታም የእነዚህ እሳቤዎች ውጤት ነው፡፡ አፈርሳታን ሳዘጋጅ ብሄረፅጌ መናፈሻ እየሄድኩ፣ ንድፍ እሰራ ነበር፤ የዛፎቹን ባህሪ አጠና ነበር፡፡ ከአንድ ዛፍ ብቻ ብዙ አይነት ባህሪን ታገኛለች፡፡ ዛፉ በክረምት፣ በበጋና በሌላ ወቅት ያለው ባህሪ ምንድን ነው? ቀለሙ ምን ይመስላል? ቅርንጫፎቹና ቅጠሎቹ እንዴት ይሆናሉ? በክረምት ውሃ አዝሎ ሲያብጥ፣ ከዚያ አልጌ ሲይዝ… የተለያየ አርት አለው፡፡ በሌላ አቅጣጫ ዞረሽ ያንኑ ዛፍ ብትመለከቺ፣ ሌላ አይነት ነው፡፡ ስለ መስመሮች ለምሳሌ፡- ስለ ቨርቲካል ሆሪዞንታል እናስብ ብንል፣ በዛፍ ላይ እነዛ መስመሮች በቅርንጫፍም በቅጠልም ምክንያት ይሰበራሉ ወይም ይቋረጣሉ እንጂ ቀጥ ብለው አይሄዱም። በዚህ ምክንያት “ተፈጥሮ ልክ ነው” የሚለውን ግንዛቤ ትወስጃለሽ፡፡ ቨርቲካልና ሆሪዞንታል መስመሮች የሌሉበት ተፈጥሮ ደግሞ ብዙ ጊዜ እረፍት አለው፡፡
“ጥላ” ስለተሰኘው አውደ ርዕይም ብዙ ሲነገር ሰምቻለሁ… እስቲ ስለሱ ንገረኝ?
ጃንጥላ በእኛ ማህበረሰብ ውስጥም ሆነ በሌላው ዓለም ያለው ሚና በወቅት እንኳን የተገደበ አይደለም፡፡ በተለይ ከገጠር እስከ ከተማ ያለው አገልግሎት ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ እንደ መከላከያ የምንጠቀምበት እቃ ስም እስከመሆን ደርሶ፣ አንድ ለእኛ ጠቃሚ ደጋፊ የሆነን ሰው ጥላዬ ጥላሁን ብለን እንሰይማለን፡፡ ይህንን ለማንፀባረቅ ሞክሬያለሁ፡፡ ሌላው “ዩኒቲ” በተሰኘው ስራዬ በኢትዮጰያ ንግድ ባንክ ልደታ ቅርንጫፍ፣ አዲስ በተሰራው ህንፃ፣ ስራዬ አለ በዚህ  ህንፃ ላይ የሚታየው፣ ጥላው ዋና መጠለያ ሆኖ፣  የተለያየ ቁመትና ውፍረት ያላቸው ዛፎች በስሩ አሉ፡፡ ይሄ እንግዲህ የተለያየ አቅም እውቀትና ሃብት ቢኖረንም ከተባበርን መቆም እንችላለን የሚለውን ለማሳየት ነው፡፡
ቅዳሜ (ዛሬ ማለት ነው) በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የሚከፈት “መክተፏያ” የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ አዘጋጅተሃል?
ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ ከእናቴ ጋር ያለኝ ቁርኝትና ስሜት የጠበቀ ነው፡፡ እናቴ ደግሞ እቃ አረጀ አበቃለት ብላ አትጥልም፤ ያው ከድሮ ሰዎች አንዷ ናትና፡፡ እዚህ ፊት ለፊትሽ የምትመለከቻት መሃሏ ሳስቶ የተበሳችና የተሰነጠቀች መክተፊያ (ቃለ ምልልሱ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ውስጥ ነው የተደረገው) እኔ ሳድግ ከበላሁባቸው ወይም ከበላኋቸው አንዷ ናት፡፡
ከበላኋቸው ስትል ምን ማለትህ ነው?
ያው መክተፊያው የሚጎደጉደው፣ የሚሳሳውና የሚበሳው በቢላዋው አማካኝነት አብሮ እየተፋቀና ከምግብ ጋር እየተቀላቀለ ወደ ሆዳችን ስለሚገባ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ መክተፊያ በልቼበታለሁም፤ በልቼዋለሁም ማለት ነው፡፡ አንድ ቀን መክተፊያዋን ሳያት የሃሳብ መነሻዬ ሆነች፡፡ ከዚያ ማሰላሰል ጀመርኩኝ። እያሰብኩ ማስታወሻ እየያዝኩ ቆየሁና ሙሉ በሙሉ ማተኮር እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ ከመክተፊያው ጋር አብራ ያለችው ሴት ህይወትም ታሰበኝ፡፡ ከዛ በኋላ ከእናቴም ከሌሎችም መክተፊያዎችን ሰብስቤ፣ ስቱዲዮ አስቀምጬ ማየት፣ ማሰብና ከጓደኞቼ ጋር መወያየት ስጀምር፣ ሃሳቡ እያደገና እየዳበረ መጥቶ እዚህ ደረሰ፡፡
አሮጌና የጎደጎደ መክተፊያ እየዞርክ ስትሰበስብ… ችግር አልገጠመህም?
ገጥሞኛል፡፡ እንደውም ከመጥፎ አምልኮ ጋር ያገናኙትም ነበሩ፡፡ መክተፊያዎቹን በስጦታም በግዢም ነው የሰበሰብኳቸው፡፡ አንድ የታክሲ ሹፌርም ፍላጎቴን አይቶና ገርሞት መክተፊያ አምጥቶልኛል፡፡ በዚህ ኤግዚቢሽን ለማሳየት የምሞክረው ሁሌም ሰዎች ተሰናድቶና አልቆ የቀረበ ምግብ ላይ ደስተኞች ነን፡፡ ነገር ግን ከጀርባ ያለውን ለመስራት የሚያስፈልገውን ነገር ማሰብ አንፈልግም፡፡ ምግብ ከእናት ማህፀን እስከ ዕለተ ሞት ከኛ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የምንኖረው በምግብ ነው። መክተፊያና ምግብ በምሳሌነት አነሳሁ እንጂ በሁሉም የስራ መስክ አሰሪዎችም የላቀና የተጠናቀቀ ስራ ሲያዩ ደስ ይላቸዋል፡፡ ያ ሰው እንዴት አድርጎ  እንደሰራው፤ እንዴት እንደወጣና እንደወረደ ግን ማሰብ አይፈልጉም። መክተፊያና የኢትዮጵያ እናቶች… ምግብ ተሰርቶ  እስኪቀርብ የሚያዩትን ፈተና ማሰብ፣ ትኩረት መስጠት የተለመደ አይደለም፡፡
በሌላው አለም የስዕል ሙያ ከኑሮ መተዳደርያም አልፎ ያበለፅጋል፡፡ እኛ አገር አሁንም ድረስ “እንጀራ” መሆን አልቻለም፡፡ ለምንድ ነው ትላለህ?
ያነሳሽው ሃሳብ በጣም ሰፊ ነው፤ በአጭር ሰዓት ለመተንተንም ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን እኔ በገባኝ መጠን ለመመለስ ልሞክር፡፡ ስዕል በሌላው ዓለም ከታሪክም አኳያ ወደ ኋላ ርቀን ስንመለስ ብዙ ነገር አለው፡፡ ለምሳሌ በ14ኛ ክ/ዘመን (ዘመነ ትንሳኤ የሚባለውን) ብዙዎቹ ለአውሮፓ ስልጣኔ ፈር የቀደዱበት ዘመን ነበር፡፡ ከዛ ቀጥሎ ነው የኢንዱስትሪ አብዮት ሲመጣ፣ ከአርቲስቶቹ የመጡ ሃሳቦች ከስነ ህንፃ ጋርም የተያያዙ እሳቤዎች ናቸው ይሄንን ዘመን የገነቡልን፡፡ እንደውም አንድ ሃሳቤን የምትገልፅልኝን ጥቅስ ልንገርሽ፡፡ መድኃኒዓለም አጠቃላይ ሁለተኛ ት/ቤት ውስጥ በሚገኘው የስዕል ት/ቤት እማር ነበር፡፡  የስዕል ክፍል በር ላይ፡- “የፊዚክስና ኬምስትሪ ሳይንስ ባልነበሩበት ዘመን፣ ስነ -ጥበብና ዕደ ጥበብ ነበሩ” ትላለች፡፡ ስነ ጥበብና ዕደ ጥበብ ናቸው፣ ፊዚክስና ኬሚስትሪን ያመጡት፡፡ እኔ ሳይንስ አካዳሚ መጥቼ ይህንን አውደ ርዕይ ሳሳይ፣ በዚህ ማዕከል ብዙ ፕሮፌሰሮችና ዶክተሮች አሉ፡፡ ይህንን ሀሳብ ይዘሽ ስትመጪ፣ እነዚህ ሰዎች “ስዕል ውስጥም ለካ ሃሳብ አለ” የሚለውን ይገነዘባሉ፡፡ እኔ ወደነሱ ሄጄ ሀሳቤን እነሱ ላይ አጋባለሁ፤ ይሄን ኃላፊነቴን ተወጣሁ ማለት ነው፡፡ ሌሎችም በዚህ መልኩ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት፣ ወደ እነሱ የሚመጣን ነገር ከመጠበቅ እነሱ መሄድ አለባቸው ማለት ነው፡፡ በዚህ መልኩ ግንዛቤውን መፍጠር ካልቻልን፣ ስዕልን የሙሉ ሰዓት ስራ አድርገን ለመኖር መቸገራችን ይቀጥላል፡፡ እኔም የሙሉ ሰዓት ሰዓሊ ለመሆን የፈጀብኝን ጊዜ ቀደም ብዬ ነግሬሻለሁ። አመርቂ አይደለም፡፡ ገና ብዙ መሰራት አለበት። አሁንም ስዕልን ከግድግዳ ጌጥነትና ማድመቂያነት ባለፈ ውስጡ ሃሳብ እንዳለ የሚረዱ ጥቂቶች ናቸው፡፡
እኔ “አፈርሳታ”ን ከዛፍና ከማህበረሰብ ዕሴት ጋር አያይዤ ስሰራ፣ ቅጥ ያጣው የከተማው ግንባታ እያመጣ ያለውን ችግርም በማሰብ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለአገር ይጠቅማል ብለሽ ሀሳብ ይዘሽ የሆነ የሚመለከተው መስሪያ ቤት ስትሄጂ፣ “ሀሳቡ ምንድን ነው? ጠቀሜታው ምን ያህል ነው?” ብለው ማየት ቀርቶ፣ ሊያናግሩሽ አይፈልጉም፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች ለዚያ ቦታ አይመጥኑም፡፡ ለቦታው የሚመጥን ሰው ለማስቀመጥ ዞሮ ዞሮ ግንዛቤ ላይ መስራት ያስፈልጋል።
እስኪ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ሌሎች ተቋማት ስለስራሃቸው የጥበብ ውጤቶች ንገረኝ?
በተቋም ደረጃ እንግዲህ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተጠቃሽ ነው፡፡ ስራዎቼን በ“አፈርሳታ” ምክንያት አይተውት ነበር፡፡ አፈላልገው አገኙኝና አወሩኝ። ከሳይንስና ቴክኖሎጂ አንፃርም ሆነ በሌላ ጥሩ ሀሳብ ይዘዋል የሚሏቸውን ሥራዎቼን ወሰዱና ቦታ መርጠው ሰቀሉ። የሰው ልጆች አዕምሮ እንዴት ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተሸጋገረ የሚል ሀሳብ ያላቸው ሲምቦሊክ ስራዎችንም ሰርቼላቸዋለሁ። ለምሳሌ ጃካራንዳ የተባለውን ዛፍ ልብ ብለሽ ብትመለከቺ፣ ብዙ የተጠላለፉ እርስ በእርስ የተቆራኙና የተወሳሰቡ መስመሮችና ቅርንጫፎች አሉት፡፡ በተለይ ቅጠሉ ሲረግፍ ደግሞ አንዷን መስመር ብትይዢ ተጠላልፎ ውሉ ይጠፋል ይሄ ደግሞ የቴክኖሎጂውን የተጠላለፈውን ኬብል ይወክላል፡፡  በወቅቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ነበሩ መጀመሪያ ስራዬን ያዩትና ያናገሩኝ። ከዚያም የተቋቋመው ኮሚቴ አማካኝነት ሰርቼ፣ ሥራዬ በብዛት እዚያ ይገኛል፡፡ እንደ ተቋም የማመሰግነው ሳይንስና ቴክኖሎጂን እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ነው፡፡ ስዕል ያለውን ሀሳብ አምነውበት፣ ብዙ በጀት መደበው፣ በፕሮጀክት መልክ ነው የተሰራው።
ከአገራችን ሰዓሊያን ማንን ታደንቅሃል? ከአንጋፎቹም ከወጣት ሰዓሊያንም ሊሆን ይችላል…
እኔ ትልቅም ይሁን ትንሽ ስራውንና ሙያውን አክብሮ የሚሰራ ሰው አደንቃለሁ፡ እስከ ሰራ ድረስ አበርክቶው አይናቅም፡፡ አሁንም ድረስ ስቱዲዮአቸው እየሄድኩ፣ ሀሳብ የምካፈላቸው አስተማሪዎቼ የነበሩ አሉ፡፡ በህይወት ከሌሉት መካከል አርቲስት ታደሰ ግዛው በጣም የማከብረው ትልቅ ባለሙያ ነው። ማስተማሩንም ስራውንም ወድዶ የኖረ ትልቅ ሰው ነው፡፡ አሁን ካሉት ሰዓሊ ዘሪሁን የትምጌታ እና ረዳት ፕሮፌሰር ጌታቸው ዮሴፍ ለእኔ ልዩ ናቸው፡፡ እነዚህ ትልልቅ ሰዎች ከትንንሾቹ ጋር ሁሉ ሲመክሩ፣ ወጣቶችን ሲኮተኩቱ ነው የሚውሉት፡፡ እነሱ እውቀት ብቻ ሳይሆን ከኪሳቸው ሁሉ የማይሰስቱ አባቶች ናቸው፡፡ አርአያዎቻችንም ናቸው፡፡

Read 2318 times